Saturday, 10 October 2020 12:14

አየር መንገድ ለደንበኞቹ የኮቪድ 19 ኢንሹራንስ መስጠት ጀመረ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(2 votes)

 የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለ6 ወራት የሚቆይና የኮቪድ 19 የኢንሹራንስ ሽፋን መስጠት መጀመሩን አስታወቀ፡፡
የኢንሹራንስ ሽፋኑ በአየር መንገዱ ለሚጓዙ ዓለምአቀፍ መንገደኞች በሙሉ ሲሆን መንገደኞቹን መመለስና ለይቶ ማቆያና ሌሎችም የህክምና ወጪዎችን መሸፈን የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡
ኢንሹራንሱ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ተሳፍረው በጉዟቸው ወቅት በኮቪድ - 19 ለሚያዙ ደንበኞች እስከ አንድ መቶ ሺ ዩሮ ድረስ የሚሸፍን ይሆናል ተብሏል፡፡ በበሽታው ተይዘው ለይቶ ማቆያ ለሚገቡ መንገደኞችም በየቀኑ 150 ዩሮ ለአስር ቀናት እንደሚከፍል ታውቋል፡፡
“ሼባ ኮምፎርት ኢንሹራንስ” ከአክስፓርትነርና አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ ጋር በመጣመር ሽፋኑን የሚሰጥ ሲሆን ኢንሹራንሱም ለደርሶ መልስ ትኬት ለ92 ቀናት፣ ለአንድ ጉዞ ትኬት ደግሞ ለ31 ቀናት የሚሸፍን ነው ተብሏል፡፡
ባለፈው መስከረም 21 ቀን 2013 ዓ.ም የተጀመረው የኢንሹራንስ ሽፋን እስከ መጋቢት ለ6 ወራት የሚዘልቅ ይሆናል ተብሏል፡፡
በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአየር ትራንስፖርቱ ዘርፍ 84 ቢሊዮን ዶላር ይከስራል ተብሎ የተገመተ ሲሆን ባለፉት አምስት ወራት  በኮሮና  ምክንያት በአየር ትራንስፖርት ዘርፉ ላይ በተጣለው ገደብ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አንድ ቢሊየን ዶላር ማጣቱንና ከ90 በመቶ በላይ የመንገደኞች አውሮፕላኖች ስራ ማቆማቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡  


Read 3791 times