Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 28 July 2012 11:52

ምስራቅ እና ምዕራብ ያልተገናኙት ስለሞቱ ነው!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ኤግዚዝቴንሻሊዝም የውድቀት ወይንም ዝቅጠት ፍልስፍና ተብሎ ነው በቅፅል ስሙ የሚጠራው፡፡ የሀሳብ ባህል ሞት ውስጥ የተወለደ “የመሆን (being)” ምንምነትን የሚያስረዳ የፍልስፍና አይነት ነው፡፡ … ምንምነትን የሚገልፀው ግን መግለፅ የሚችለውን ብቸኛውን ፍጡር፣ ሰውን ሆኖ ነው፡፡ በህልውና መገኘት ለህልውና ትርጉም ከመስጠት ይቀድማል፡፡ “የምንምነትን አንዳች ነገርነት (ምንምነት ባዶነት አለመሆኑን) መጀመሪያ የተነተነው ሀይደርጋር (Heidgger) ቢሆንም፤ “ምንምነትን ወደ አለም ያመጣው የሰው ልጅ ነው” ያለው ግን ዣን ፖል ሳርተር ነው፡፡ …ለዚህ ግኝቱ የኖቤል ሽልማት ተበርክቶለት … ለመጀመሪያ ጊዜ አልቀበልም ያለውም ይኸው ፈረንሳዊ ፈላስፋ ነበር፡፡ ምናልባት ምንምነት ስለሆነበት ሊሆን ይችላል፡፡

ለማንኛውም የምንምነት ፍልስፍናው የሚያነጣጥረው የሰው አእምሮ (ራሱን በራሱ የማወቅ ብቃቱ) ላይ ነው፡፡ Consciousness ነው ምንምነት፡፡ የሰው ልጅ በአእምሮው አማካኝነት የማወቅ ብቃቱ እንደ ፈጣሪ (እግዜር) ማንነት … አለ ወይንም የለም ተብሎ ሊመረመር አይችልም፡፡ ኒቼ “እግዚአብሔር ሞቷል” ሲል እንኳን አእምሮውን ተጠቅሞ ስለሆነ … ለፍልስፍናው ህጋዊነት ችግር አልፈጠረበትም፡፡ … የአእምሮ ብቃቱን ግን በአእምሮው አማካኝነት ከገደለ፤ ከዛ በኋላ … ለምንም አይነት ነገር ምንም አይነት ትርጉም ሊኖር አይችልም፡፡

እንደ ሳርተር፤ ሰው እንደ ራሱ ብቁ ባለመሆኑ፤ ከራሱ ውጭ ካለው አለም በእውቀትም ሆነ በጥቅም ረገድ የማይፈታ ቁርኝት አለው፡፡ ይህም ቁርኝት ሁልጊዜ እንዲፈልግ እና እንዲለውጥ እንጂ እንደራሱ ሆኖ ረክቶ እንዲቀመጥ አይፈቀድለትም፡፡ … እንስሳት እና ሌሎች ግዑዝ የተፈጥሮ አካላት ግን ይህ የለውጥ ፍላጐት የለባቸውም፡፡ በዚህም ምክንያት እንደራሳቸው ሙሉ ናቸው፤ ባይ ነው፡፡

አባባሉን ወደ ጥንታዊዉ የአዳም እና ሄዋን ሀጢአት ታሪክ ወስደን ልናስተውለው እንችላለን፡፡ አዳም እና ሄዋን ምንም ተጨማሪ እውቀትም ሆነ ለውጥ በማያሻው አለም ውስጥ ነበር የሚኖሩት፡፡ ምርጫ የሚባል ነገር አያውቁም፡፡ ምኞትም ሆነ ህልም፣ ስቃይም ሆነ ደስታ ጉድለት ስላልነበረባቸው አያስፈልጋቸውም፡፡ እንደ እንስሳ ነበሩ፡፡ ሀጢአት የመስራት አቅም ግን ነበራቸው፡፡ …እውቀትን ለማወቅ የሚያስችል አእምሮ፤ ወሲባዊ ተራክቦን መፈፀሚያ ደግሞ የመራቢያ አካላት ከሀጢአቱ በኋላ ሳይሆን ከመጀመሪያው እነዚህ አቅሞች በተፈጥሮ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ሀጢአት እንዳይሰሩ የሚፈልገው ፈጣሪያቸው ሀጢአትን መስሪያ ግን ከመጀመሪያው ፈጥሮ ሰጥቷቸዋል፡፡

እንግዲህ የመጀመሪያው እውቀት ፍሬዋን ከመብላት ጋር ተያይዞ የመጣ ነው፤ እንደ አፈታሪኩ፡፡ … በፊት የማያስፈልገውን ነገር ለመፈለግ … የምርጫ ብቃቱን ተጠቀመ፡፡ እንደ ራሱ መሆን ከዛ በኋላ ሳይችል ቀረ፡፡ እውቀት ራስን በራስ ሳይሆን ራስን ከውጫዊው ተፈጥሮ ጋር በማስተሳሰር የሚገኝ ነው፡፡ ይህም ነው ለሳርተር “ኮንሽስነስ” ማለት፡፡

ይህም እውቀት ነው ባዶነት፡፡

ይህ የኤግዚዝቴንሻሊዝም ፍልስፍና … በውድቅት ዘመን የወጣ በመሆኑ ከነበረበት ዘመን ጋር ብዙ ትስስር ይኖረዋል፡፡ የዘመንን መንፈስ ገላጭ ነው፡፡ ሞቶ እየሰራ ወይንም እየኖረ የሚመስለውን የሳይንስ፣ የሀይማኖት፣ የስነ ምግባር … ባህል ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡

ለባህል መነሳትም ሆነ መውደቅ  አስተዋፅኦ የሚያደርገው ሰው ነው፡፡ ምክንያቱም ባህል ራሱ ከእውነታ ውስጥ የሚገልፀው ስለ ሰው እውነት ብቻ ነው፡፡ የፍልስፍና ሞት አልያም የሞት ፍልስፍና … ስለ ባህል ህይወት የሚገልፅ ግለ-ታሪክ ነው፡፡

ኤግዚዝቴንሻሊዝም ስለ እውቀት ሞት ባህል የሚያስረዳ የፍልስፍና አይነት ነው፤ የመጨረሻው የፍልስፍና እንቅስቃሴ አይነት ነው፡፡

በዚሁ በኤግዚዝቴንሻሊስት እይታ ሳይንስም ሞቷል፡፡ ሀይደርጋር ስለ ሳይንስ ሞት ምክንያት የሚከተለውን ይላል፡- በሳይንስ… ጥናት የመጀመሪያው ስፍራ የሚሰጣቸው “ነገራት” objects ናቸው፡፡  Science is humble before objects and facts, so  that “what-is” in the world may reveal itself. But what this means in practice is that one entity or object in the world (man) pursues science in the hope of persuading what is to make itself plain.

በአጭሩ፡- ሰው የሚባል አንድ ፍጥረት ወደ መጠን የለሽ እውነታው በረብሻ መልክ ገንፍሎ ገብቶ… በአንድ ጊዜ ስለሆነው ነገር ሁሉ … ሆኖ የተገኘለትን ውስን መጠን እንደ ሙሉ እውነት አድርጐ መቀበል ነው ሳይንሳዊ ስህተት እንደማለት ነው፡፡ መለካት በቻለው መጠን መለካት ያልቻለውን ማረጋገጥ አይችልም፤ ነው፡፡ (ምናልባት ለዚህ ዘመነኛው ምሳሌ … በአንስታይን የንፅፅር ሀሊዮት (theory of the big) እና በኳንተም ሜካኒክስ (theory of the small) መሀል ያለው የመጣጣም ችግር ምሳሌ ሊሆን ይችላል፡፡…)

በአስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን የነበሩ ሳይንቲስቶች አለም ለሰው ልጅ እውቀት ክፍት ናት ብለው ያምኑ ነበር፡፡ የግዜ ጉዳይ ነው እንጂ በህዋ ውስጥ ምንም ሊገለፅ የማይችል ነገር እንደማይኖር እርግጠኛ ነበሩ፡፡ በአስትሮኖሚ ረገድ፣ በዝግመተ ለውጥ ረገድ፣ በሜካኒካል እና በኤሌክትሮኒክ ዘርፈ ጥናቶች ላይ የተገኙ ውጤቶች ለእርግጠኝነታቸው ምክንያት ናቸው፡፡ ይህ በውጫዊ ነገሮች (objects) ላይ የተደረሱ እመርታዎች … በስተመጨረሻ “ሰውን” ሙሉ በሙሉ ወደ ማወቅ ይደርሳሉ፤ ተብለው ተስፋ ተጥሎባቸው ነበር፡፡

ለዚህ አይነቱ የዋህ አስተሳሰብ ሶረን ኪርከርጋርድ በዘመኑ “ስህተት! ቂልነት!” ብሎ ጮሆ ነበር፡፡ የሚያደምጠው ባያገኝም፡፡ ስህተት ሲል ምን ማለቱ ነው? … ያልን እንደሆነ … ሰው ነገሮችን (Objects) የሚያጠና እንጂ ራሱ ግን “ነገር” አይደለም፡፡ ሰውን ከእንስሳ ጋር በማነፃፀር ባህሪውን በሳይንስ እያጠናን እንመረምራለን እንጂ፤ ሰው ግን እንስሳ አይደለም … ሀሳብን (ነብስን) አንጐል (አካል) እንደሆነ አድርጐ ማሰቡ ላይ ነው ስህተቱ፡፡

… The whole world became a collection of objects to be analyzed and explained on the analogy of the treatment science would give to a piece of rock handed to a laboratory to be assayed.

… የኢቮሉሽን ሀልዮት አራማጆች (ቻርለስ ዳርዊን፣ ጁሊየን ሀክስሌ፣ ቴርላንድ ደ ቻርዲን) የዘነጉትም ነገር በእንስሳት አለም ቅሪት ላይ ያደረጉት ጥናት የእንስሳውን ህይወት አልነገራቸውም፡፡ በተለይ ደግሞ እንስሳው “ሰው” ሲሆን፤ ከባዮሎጂያዊ ዝግመተ ለውጡ ባልተናነሰ … የሀሳብ እና የባህል ዝግመተ ለውጡ ስለ ማንነቱ ለመናገር መሰረታዊ እዉቀቶች በመሆናቸው ምክንያት ነበር፡፡

ኤግዚዝቴንሻሊዝም፤ ከፍልስፍናዎች ሁሉ ትንተናን አብዝቶ የማይወድ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ምክንያቱም፤ ትንተና ብዙውን ጊዜ ነገርየውን በህይወቱ እና በተሞክሮ ላይ እያለ ሳይሆን በሌለበት በሩቁ ለማጠቃለል እና ለመግለፅ ሙከራ ስለሚያደርግ ነው፡፡ ቁጥሮች በስሌት ውጣ ውረድ ተቆንነው የሚሰጡት መልስ፤ እንደ ህይወት እውነታ ተቀያያሪ ሳይሆን ቁልጭ ያለ ነው፡፡ ቁልጭ ያለ ስሌት… ቁልጭ ያለ እውነት ላይሆን ይችላል፡፡

Man is not to be explained. Dissection and abstraction are techniques in post - mortems which may “explain” why the living are dead but why the living are living.

ሳይንሳዊ ባህሉ የሞተው የነብስን ጥያቄ በቁሳዊ ነገሮች ጥናት እና ልኬት ውስጥ በማንበብ ነው ከተባለ … በሳይንሱ ፋንታ የጥንቱ እምነት (old time religion) ተመልሶ መንገስ ነበረበት፡፡ ግን እንደዛ አልሆነም፡፡ እምነትም ከጥንቱ የሳይንስ ሀይማኖት ባልተናነሰ ሞቷል፡፡ ኒቼ “እግዜር ሞቷል” ባለበት ጊዜ ገዳዩ እሱ ራሱ ሆኖ አይደለም፡፡ እሱ፤ መርዶ ነጋሪ ሆኖ ነው ብቅ ያለው፡፡

… የድሮው ፈጣሪ ላይ የነበራችሁ እምነት … በአሁኑ ህይወታችሁ ላይ በማስመሰል ባህል አድርጋችሁ ትኖሩታላችሁ እንጂ፤ በእርግጥ ግን አብሯችሁ የለም፡፡ ስለ ሌለ… ሞቷል ማለት ነው፡፡ ከሞተ ደግሞ፤ አዲስ መፍጠር አለብን፤ ነው የኒቼ ስብከት፡፡ እሱ ፈጣሪን በልዕለ ሰብ ለመተካት ተፈላሰፈ … ሌሎቹ የሞተውን ፈጣሪ በሀይል ለማስነሳት፡፡ የሞተ ባህል ግን ተመልሶ አይነሳም፡፡ ታሪክም ራሱን አይደግምም፡፡ መልሶ የተነሳው ክርስቶስ እንኳን ሙሉ አምላክ ሆኖ ነው፡፡ ዳግም በድሮው ስጋና መንፈስ ከሞት የሚነሳ ባህል የለም፡፡

… ለሳይንሳዊ ባህል ሞት ኤግዚዝቴንሻሊስቶች ያቀረቡትን ምክንያት በተገላቢጦሽ አድርገን ካየነው፤ ለእምነቱ መሞት ምክንያቱ ምን እንደነበር እንደርስበታለን፡፡ … ሳይንስ “ከነገሮች” (በኦብጀክት) ጥናት ላይ የተጠመደ ከሆነ፤ እምነት ደግም ከግል ጥናት (Subject) ውጭ ማየት አይችልም፡፡

ነብስን እና ፈጣሪን እንጂ ከተጨባጩ አለም ጋር ፍቺ ውስጥ ገብቷል፡፡ ….እምነት የሰውን ልጅ የሚገልፅበት መንገድ ለምድር የሚያመች ስላልሆነ … እምነቱን በሙሉ ማንነቱ ይዞ ለመቀጠል ይከብደዋል፡፡ ቁሳዊ ህይወት ያምረዋል፣ ፍትህን በምድራዊ መንገድ ለመመለስ ወደ ማህበረሰቡ ይቀላቀላል፡፡ ጥቅም በተገኘበት ሁሉ ሲስት እና ሲያሳስት ይገኛል፡፡ … እንደ ክርስትና ጠንካራ ለሆነ እና ብዙ መቶ አመቶች በእውነተኛ ቅንነት በጨለማው ዘመናት ለነገሰ ሀይማኖት እንኳን … ትንሽ የትንሣኤ ዘመን ብቅ ሲል በፍጥነት ለውጥ ሞትን ተመስሎ አነቀው፡፡ … በዶክትሪን የሚሰበከውን ማከናወን ማቃት የሚያሳየው… መሆን መፈለግን ግን ከተጨባጩ የዘንድሮ እውነታ አንፃር መሆን አለመቻልን ነው፡፡ እምነቱ ሞቶ ግን በቀደምት የጉብዝናው ዘመናት የፈጠራቸው ከኑሮ ጋር የተገናኙ ባህላዊ ስነ ስርዓቶች የተግባር ውጤት ሆነው ለረጅም ጊዜ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም፤ የድሮ ሀይሉን ያሟጠጠ የእምነት ውጤት ለቀሪ ለዘመናት ሀይማኖት ሆኖ እየሰራ ሊዘልቅ ይችላል፡፡

***

ሥነ-ልቦና (ሳይኮሎጂ) እንደኔ አተያይ እነዚህን ሁለት አለሞች (እምነት/ሳይንስ) መልሶ ከሞቱበት በሀያኛው ክፍለ ዘመን ለማምጣት ብቅ ያለ ወይንም ሁለቱን አጣምሮ የሰውን ነብስ ለመፍታት የሞከረ ዘርፍ ነው፡፡ ሙሉ ሳይንስነቱ አሊያም ሙሉ እምነትነቱ ያጠራጥራል፡፡ ለማጥናት የሚሞክረው ስለ ሰው ነብስ ነው፡፡ ግን ለማጥናት የሚሞክረው በተጨባጩ የልኬት ቋንቋ ማለትም በሳይንስ ነው፡፡

በዚህም ድብልቅ ባህሪው ምክንያት ሳይኮሎጂ (ሶሲዮሎጂን ጨምሮ) ከሳይንስ ዘርፎች ጋር የሚመደብ አይደለም፡፡ እስካሁን በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች ሁሉን የሚያስማማ እርግጠኝነትን አልታደሉም፡፡ (Psychology when its scientific basis is disputed it shows all the touchiness at a lady whose virtue is questioned)

እንግዲህ በዚህ አጠራጣሪ ሳይንስ ውስጥ ባለመስማማት በአንድ ዘርፍ ውስጥ የተጠቃለሉ ት/ቤቶች አሉ፡፡ የዋትሰን ት/ቤት ለምሳሌ ቢሄቪየራሊዝም (ሰው የአካባቢው ውጤት ነው) በሚል ስርዓት የሰውን ማንነት የሚያጠና ነው፡፡ የፍሮይድ ት/ቤት ደግሞ … በአልነቃው አእምሮ እና በነቃው መሀል ያለውን ግንኙነት በህልም አማካኝነት የሚፈታው ነው፡፡

የጁንጊያን ትምህርት ቤት ደግሞ ከወላጆቻችን በዘረ መል ስለምንወርሳቸው ስነ ልቦናዎች የሚተነትን ነው፡፡ … ሁሉም ግን ተጨባጭ ነገር ላይ አልደረሱም … ወደ እምነት ወይንም ወደ ሳይንስ ከመቅረብ በስተቀር፡፡ … የእርግጠኝነት ማጣት አይደል ታዲያ ምንምነት? … ወደፊት እና ወደኋላ በተመሳሳይ ፍጥነት በተመሳሳይ ጊዜ የሚሄድ መኪና … ወደየትም ባለመንቀሳቀሱ የእንቅስቃሴ ሞት ላይ ነው ይባላል “ምንምነት ”እስካሁን ያልሆንነውን ግን በመሆን ሂደት ላይ ያለ የማይታወቅ አቅጣጫችን ነው፡፡ ስለማናየው መጠኑን መገመት ያቅተናል እንጂ… ከሞቱት የሰው ልጅ ባህሎች ውስጥ አዲስ መወለዱ አይቀርም፡፡ ህልውና እስካለ ባህል እየሞተ እና እየተፈጠረ መኖሩን ይቀጥላል፡፡ በአሉታዊ እና በአዎንታዊ መመዘኛ ባህልን የሚመዝነው ሰው እንጂ ባህል እንደራሱማ ግኡዝ ነው፡፡

 

 

Read 3050 times Last modified on Saturday, 28 July 2012 11:57