Saturday, 03 October 2020 00:00

በአለማችን በ6 ወራት 15 ሚ. ሰዎች ተፈናቅለዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  እስከ ሰኔ በነበሩት ስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ በመላው አለም 15 ሚሊዮን ያህል ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውንና የተፈናቃዮች ቁጥር በመጪዎቹ ወራት በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ባለፈው ረቡዕ ይፋ የተደረገን አንድ አለማቀፍ ጥናት ጠቅሶ ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
ተቀማጭነቱ በስዊዘርላንድ የሆነው ኢንተርናል ዲስፕሌስመንት ሞኒተሪንግ ሴንተር የተባለ ተቋም ያወጣውን የጥናት ሪፖርት ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፤ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ከ120 በላይ በሚሆኑ የአለም አገራት የእርስ በእርስ ግጭት፣ ብጥብጥና የተፈጥሮ አደጋዎችን ጨምሮ በተለያዩ አስገዳጅ ምክንያቶች ከ15 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የአገር ውስጥ ተፈናቃይ ለመሆን ተዳርገዋል፡፡ በተለያዩ የአለማችን አገራት ከተፈጥሮ አደጋዎችና የእርስ በእርስ ግጭቶች መባባስ ጋር ተያይዞ በመጪዎቹ ወራት የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር በእጅጉ ይጨምራል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተቋሙ ባወጣው መግለጫ አስጠንቅቋል፡፡
ከአጠቃላዩ የተፈናቃዮች ቁጥር ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የሚይዙት ጎርፍ፣ ሃይለኛ ንፋስ፣ የደን ቃጠሎና የአንበጣ ወረራን ጨምሮ በተለያዩ የተፈጥሮ አደጋ ለተፈናቃይነት የተዳረጉት ሲሆኑ፣ 4.8 ሚሊዮን ያህሉ ደግሞ በእርስ በእርስ ግጭትና ብጥብጥ የተፈናቀሉ እንደሆኑም ዘገባው አመልክቷል፡፡
እስካለፈው የፈረንጆች አመት 2019 መጨረሻ በመላው አለም በአገር ውስጥ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከ50.8 ሚሊዮን በላይ መድረሱንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡


Read 2150 times