Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 28 July 2012 10:08

የድንዛዜና የግርግር ጎዳናዎች

Written by 
Rate this item
(2 votes)

የብሄረሰብና የሃይማኖት ፖለቲካ - (የአክራሪነት ፖለቲካ)

የስራ አጥነትና የኑሮ ውድነት ኢኮኖሚ - (የኮብልስቶን ኢኮኖሚ)

መረጃ የመደበቅና የውስጥ ለውስጥ አስተዳደር - (የበረሃ መንግስት)

መፍዘዝም ሆነ ማድፈጥ መፍትሄ አይሆንም። የጠ/ሚ መለስ ዜናዊን መታመም ለወር ያህል ደብቆ በማቆየትና አድፍጦ በመጠበቅ ምን ትርፍ ተገኘ? ምንም። አንገትን ጭድ ውስጥ አስገብተው ቢሸሸጉ፤ እውነታውን ሊያጠፋ አይችልም። መፍትሄ እንደማያስገኝ ግልፅ ቢሆንም፤ እንዲህ አይነቱ ባህርይ፤ ነባር የአገራችን ባህል ነው (የመፍዘዝ ባህርይ፤ የማድፈጥ ባህል፤ የድንዛዜ ጎዳና ልትሉት ትችላላችሁ)። ግን ብቸኛ ባህል፤ ብቸኛ ጎዳና አይደለም - መንትያ አለው።

ከኢህአዴግ ድብቅነትና ድንዛዜ ጋር አብሮ ምን እንደተፈጠረ ታውቁት የለ? አገር ምድሩን ያተራመሰ የወሬ ማዕበል፤ በኢንተርኔትና በፌስቡክ፤ በየቢሮውና በየጓዳው፤ በየመጠጥ ቤቱና በየካፍቴሪያው... ለወሬ ግርግር መቅበዝበዝ በርክቷል። ለነገሩ፤ ለወር ያህል አድፍጦ የነበረው ኢህአዴግ፤ ወሬው ከቁጥጥሩ ውጭ ከሆነበት በኋላ፤ ከድንዛዜ ለመውጣት ማርሽ ቀይሮ እንዴት መንፈራገጥና መደናበር እንደጀመረ ሳትታዘቡ አትቀሩም። ግን ምን ዋጋ አለው? ይሄም መፍትሄ አይደለም። የሚገርመው ምን መሰላችሁ? መንፈራገጥም ሆነ መደናበር መፍትሄ እንደማያመጣ ግልፅ ቢሆንም፤ ነባር የአገራችን ባህል ነው -  የመቅበዝበዝ ባህርይ፤ የመደናበር ባህል፤ የግርግር ጎዳና ልትሉት ትችላላችሁ)።

የአገራችን የሺ አመት ታሪክ፤ በእነዚሁ መንታ ባህሎች የተቃኘ ነው - የማድፈጥና የመደናበር ባህሎች፤ የመፍዘዝና የመቅበዝበዝ ባህሎች እየተፈራረቁ የሚፈጥሩት አዙሪት ነው የአገራችን የረዥም ጊዜ ታሪክ። በድንዛዜ ጎዳና ይጓዝና በግርግር ጎዳ በኩል ዞሮ ወደ ድንዛዜ ጎዳና ይመለሳል - እንደገና ወደ ግርግር ጎዳና ሊያመራ። ከአገራችን የመንግስታት የስልጣን ዘመንና የስልጣን ለውጥ ላይ ሲፈራረቁ የሚታዩ የድንዛዜና የግርግር ወቅቶችን ማየት ትችላላችሁ። ዛሬ በዘመናችን፤ ከሃይማኖት አክራሪነት ጋር ተያይዘው የሚታየውን ድንዛዜና ግርግር እንደ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል። ከዚያ በፊት ግን፤ የስራ አጥነትና የስደት ጎርፍ በሚመለከት የተፈጠሩትን አዝማሚያዎች ተመልከቱ።

ባለፉት አስር አመታት በተለይም ከአምስት አመት ወዲህ፤ የስራ አጥነት ችግር እየተባባሰ፤ የስደት ጎርፍ እየጨመረ መምጣቱ ሚስጥር አይደለም። ግን፤ በሰከነ አእምሮ መፍትሄ ለማበጀት የመትጋት አዝማሚያ አልተፈጠረም - እንዲህ አይነት ባህል ለአገራችን እንግዳ ነው - (የማስተዋል ባህርይ፤ የመስከን ባህል፤ የትጋት ጎዳና ልትሉት ትችላላችሁ)።  ይህን ጎዳና ከመሞከር ይልቅ፤ ነባሮቹን ድንዛዜና የግርግር ጎዳናዎች ናቸው ጎልተው የሚታዩት።

ከአመት አመት የስራ አጥነትና የስደት ችግሮች ሲባባሱ፤ ምንም አልተደረገም። መፍዘዝና መደንዘዝ ብቻ! እጅን አጣጥፎና አድፍጦ መጠበቅ ብቻ! ግን በድንዛዜ ስንጠብቅ ውለን፤ ስንጠብቅ ብናድር መፍትሄ ጠብ አይልም፤ ጠብ አላለም። ይሄ የድንዛዜ ጎዳና አላዋጣ ስላለ፤ ችግሩ አብጦ ሊፈነዳ ስለደረሰ፤ አሁን ማርሽ ቀይረን ወደሌላኛው የተለመደ ጎዳና ገብተናል። ቢዝነስ እንዲስፋፋና የስራ እድሎች በስፋት እንዲፈጠሩ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚን ለማስፋፋት ከመጣርና ከመትጋት ይልቅ፤ በከንቱ መንፈራገጥ ተጀምሯል። ስደትን በደፈናው ለማጣጣል መቅበዝበዝ፤ በክልከላና በእገዳ ስደትን ለማስቆም መደናበር በርክቷል። ከዚሁ ጋር አብሮ፤ መንግስት ለህዝብ የስራ እድል የመፍጠር ምትሃታዊ ችሎታ ያለው ይመስል፤ የፕሮፓጋንዳው ግርግር ተነስቶበታል። አገር በኮብልስቶን የምትበለፅግ ይመስል፤ ነጋ ጠባ ስለ ድንጋይ ጠረባ በፕሮፓጋንዳ ግርግር ህዝቡን መተግተግ የት ያደርሳል? የትም። ሲደናበሩ ውለው ሲወራጩ ቢያድሩ፤ የስራ አጥነትን ችግር የሚያቃልል መፍትሄ የግርግር ጎዳና ውስጥ አይገኝም።

እንግዲህ፤ የትም መቼም ቢሆን፤ ችግር የማይገጥመው ሰው ወይም ቤተሰብ፤ ድርጅት ወይም አገር፤ ፓርቲ ወይም መንግስት የለም። በመጠንና በአይነት ይለያያል እንጂ፤ ሁሉም ሰው ላይ ችግር ይፈጠራል። በዚህ በዚህ ሁላችንም እንመሳሰላለን። ልዩነት የሚመጣው ከዚያ በኋላ ነው። ችግር ሲደርስብን ወይም በራሳችን ላይ ችግር ስናደርስ ምን እናደርጋለን? ይኸኔ መንገዳችን ይለያያል፤ የአስተሳሰብና የምርጫ ጉዳይ ነዋ።

በግለሰብም ሆነ በቤተሰብ ደረጃ፤ በፓርቲም ሆነ በመንግስት ደረጃ፤ ለተለያየ ችግር የምንሰጠው የሃሳብና የተግባር ምላሽ፤ እንደየምርጫችን ይለያያል። የምናገኘው ውጤትም የዚያኑ ያህል ይራራቃል። እንደየምርጫችን ስኬትን እንጎናፀፋለን፣ አልያም ውድቀትን እንከናነባለን። በሌላ አነጋገር፤ ለክፉም ሆነ ለበጎ፤ “ስራው ያውጣው” እንደሚባለው አይነት ነው። “የስራውን አገኘ፤ የእጁን አገኘ” ይባል የለ? “የምርጫውን አገኘ” ብለን ልንጨምርበት እንችላለን።

ችግር ሲያጋጥማቸው፤ የሚባንኑና የሚነቁ አሉ - ችግር መከሰቱን ሲያዩ፣ ከእውነታው ለመሸሽ በድንዛዜ አይናቸውን አይጨፍኑም፤ እውነታውን ለመደበቅ አንገታቸውን አሸዋ ውስጥ ቀብረው አያደፍጡም። አልያም በአሉባልታና በፕሮፓጋንዳ ግርግር እውነታውን ሰርዘው ደልዘው ለማጥፋት አይደናበሩም። መፍትሄ ፍለጋ በሰከነ አእምሮ በአስተዋይነት ያስባሉ፤ በተግባርም ተግተው ይጥራሉ። የእነዚህን ሰዎች ምርጫ ነው፤ “የትጋት ጎዳና” ብለን የሰየምነው። ግን ምን ዋጋ አለው? የአገራች ዜጎችና ምሁራን፤ ፓርቲዎችና መንግስት፣ በአብዛኛው በዚህ ትክክለኛ ጎዳና ሲጓዙ አይታዩም።

ሁለተኛው ጎዳና፤ የግርግር ጎዳና ነው - ብዙዎች የሚመርጡት ጎዳና። ችግር ሲያጋጥማቸው፤ እየቃዡ ይቅበዘበዛሉ። ለምሳሌ፤ የመንግስት መሪ መታመምና መጥቀስ ይቻላል። የብሄረሰብና የሃይማኖት ፖለቲካ መስፋፋቱም ከፍተኛ ችግር ነው - የአክራሪነት ፈተና። ስራ አጥነትና ስደትም ቀላል ችግሮች አይደሉም። የፖለቲካ ነፃነት መጥበብ ወይም የመንግስት መግነንም እጅጉን የባሰ ችግር ነው። እንግዲህ፤ አንዱ ወይም ሌላኛው ችግር ተከስቶ የለ? ችግር መከሰቱ እውነት አይደል? በወሬና በፕሮፓጋንዳ እውነታውን መሰረዝ የሚችሉ እየመሰላቸው ማምታታትና ማደናበር፤ ወይም በዘፈቀደ መንጫጫትና ቀውጢ መፍጠር የት ያደርሳል? የትም አያደርስም - ችግሮቹን ያባብስ እንደሆነ እንጂ።

ሶስተኛው ጎዳና የድንዛዜ ጎዳና ነው - ብዙዎች የሚርመሰመሱበት ጎዳና። ችግር ሲያጋጥማቸው፤ መፍዘዝንና መደንዘዝን ይመርጣሉ። የተከሰተውን ችግር ላለማየት፤ አይተው ከሆነም እንዳላዩ ለማለፍ፤ ማለፍ ካልቻሉም መፍትሄ እንደሌለው “እርግማን” አድርገው በመቁጠር እጅ አጣጥፈው የሚተክዙና የሚቆዝሙ ናቸው።

በአገራችን፤ ብዙ ዜጎችና ፖለቲከኞች፤ ፓርቲዎችና መንግስታት በአመዛኙ የትኞቹን ጎዳናዎች እንደሚያዘወትሩ ተመልከቱ። የሰከነ የትጋት ጎዳናን ሳይሆን፤ የመደናበር አልያም የመደንዘዝ ጎዳናን ነው የሚያዘወትሩት። ለዚህም ነው፤ የአገሪቱ የወደፊት እጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል ተብለው የተጠየቁ በርካታ ምሁራን፤ “ስርዓት አልበኝት ወይም የጭካኔ አምባገነንነት” በማለት ስጋታቸውን የገለፁት። (በዊኪሊክስ ይፋ የተደረጉ የአሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ደብዳቤዎች ላይ የቀረበውን ዳሰሳ መመልከት ትችላላችሁ። AddisAbaba1357 በሚል መለያ ቁጥር የተፃፈውን ደብዳቤ ጨምሮ ዳሰሳው በአምስት ክፍል የቀረበ ነው)። በአዲስ አበባ በተለያዩ ተቋማት ውስጥ ከሚሰሩ አስር ምሁራን አስተያየት ከተሰበሰበ በኋላ ዳሰሳውን ያቀረቡት የወቅቱ የአሜሪካ አምባሳደር ዶናልድ ያማማቶ፤ እነዚህ ምሁራን አስተሳሰብ በአጠቃላይ የአገሪቱን ምሁራን መንፈስ ያንፀባርቃል ብለዋል።)

በዳሰሳው ውስጥ እንደተጠቀሰው፤ የአስሩም ምሁራን ስጋት ተመሳሳይ ነው - አገሪቱ ወደ ስርዓት አልበኝነት አልያም ወደ ጭካኔ አምባገነንነት እንዳታመራ ይሰጋሉ። የስጋታቸው ተመሳሳይነት በአጋጣሚ የተፈጠረ አይመስለኝም። የምሁራኑ ስጋት፤ በአገራችን እየተፈራረቁ የሚዘወተሩ ሁለት ጎዳናዎችን ያመላክታል። በአንድ በኩል፤ መደናበር የበዛበት የግርግር ጎዳና አለ። በሌላ በኩል ደግሞ፤ አምባገነንን አሜን ብሎ የመቀበልና ሁሉንም ሸክም ችሎ የማደር ዝምታ የሰፈነበት የድንዛዜ ጎዳና አለ። የግርግር ጎዳና አልያም የድንዛዜ ጎዳና ናቸው አማራጮቹ። የምሁራኑ ስጋት የአገሪቱን ባህል ያንፀባርቃል ማለት ይቻላል - “በስርዓት አልበኝነት የተቀጣጠለ ግርግር ወይም በጨካኝ አምባገነን የተቀጠቀጠ ድንዛዜ”። የአገሪቱ ታሪክ፤ የሁለቱ ጎዳናዎች አዙሪት ነው።

አንዳንዴ፤ የመደናበር ጎዳናው እየተጥለቀለቀ፤ አገሩ ሁሉ በጭፍን ስሜት ይፍለቀለቃል፤ በወሬና በስብሰባ ይናጣል። በመግለጫና በፕሮፓጋንዳ ይንተከተካል። በጩኸትና በመፈክር ይበጠበጣል፤ በዛቻ ይንቀጠቀጣል፤ በአመፅ ይቃወሳል፤ በተኩስ ይርበደበዳል። ሌላ ጊዜ ደግሞ፤ አዳሜ የመደንዘዝ ጎዳና ውስጥ ይገባና አገር ምድሩ ጭር ይላል፤ አንገት መድፋትና አንገት መቅበር፤ ማድፈጥና ማድባት፤ መተከዝና መቆዘም ይበዛል።

እውነትም፤ ኋላቀርነት ክፉ ነው። እንዲህ በመደናበርና በመፍዘዝ መሃል እያላጋ፤ ነፃነትንና ብልፅግናን አሳጥቶ፤ በውርደትና በድህነት ያዳፋናል። ችግሮቹ መፍትሄ ሳያገኙ፤ ትውልድ አልፎ ትውልድ ይተካል።

በአንድ በኩል፤ ችግር ራሱ መፍትሄን የሚወልድ ይመስል፤ በዝምታ መቀበልና እጅን አጣጥፎ መቀመጥ፤ አንገትን ቀብሮና አድፍጦ መጠበቅ፤ መተከዝና መቆዘም እናበዛለን። እኮ ለምን? ችግር እየበዛና እየመረረ ሲመጣ፤ ራሱ የመፍትሄ ሃሳብ እንዲሰጠን እንጠብቃለን እንዴ? “... መከራ ይምከረው” ይባል የለ። ችግር ሲደራረብብህ ዝም ብለህ ተሸከም፤ እጅህን አጣጥፈህ በድንዛዜ ጠብቅ፤ አንድ ቀን መከራህ ይመክርሃል...። ችግር ሲለበልበንና ሲገርፈን ቆይቶ፤ በመጨረሻ መፍትሄ ብልጭ ያደርግልናል? አያደርግልንም። “መከራ ይምከረው” የሚለው አባባል አይሰራም። ሌላው ቢቀር ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳልሰራ እርግጠኛ መሆን ይቻላል። ከስልጣኔ መንገድ ጋር የተለያዩት ኢትዮጵያውያን፤ ቢያንስ ለሺህ አመታት መከራ አይተዋል። በችጋር ብዛት፤ ብልህ አልሆኑም። የድህነት ክምር፤ እውቀት አልሆናቸውም።

ምናልባት፤ ያንን የድንዛዜ ጎዳና የምናዘወትረው፤ ችግርን እንደእርግማን ስለምንቆጥር ይሆን እንዴ? “ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም” ብለን እንተርት የለ! “የጊዜ እንጂ የሰው ዠግና የለውም” ብለን ስንተርትም ትርጉሙ ግልፅ ነው። “ችግር ቢገጥምህ እድልህ ነው... ምንም ብታደርግ የትም አትደርስም፤ እጅህን አጣጥፈህ ተቀመጥ፤ ከመፍዘዝና ከመደንዘዝ፤ ከመተከዝና ከመቆዘም ውጭ ሌላ አማራጭ የለህም...” እንደማለት ነው። የድንዛዜ ጎዳናው በባህላዊ አባባሎች የበለፀገ ባህላዊ ጎዳናችን ነው።

ይህንን እያሰብኩ እያለ ነው፤ የአንዱን ምሁር አስተያየት ያስታወስኩት። ያማማቶ ያዘጋጁት ዲፕሎማሲያዊ ደብዳቤ ውስጥ የተጠቀሱ አንድ ኢትዮጵያዊ ምሁር፤ አገሪቱ በዝምታና በፍርሃት ድባብ እንደተዋጠች ይገልፃሉ። አንድ ሺ የሚሆኑ የኢህአዴግ ካድሬዎች የአገሪቱን ፖለቲካና የአገሪቱን ህዝብ በቁጥጥራቸው ስር አስገብተው እንዳሻቸው ያደርጉታል ሲሉም ምሁሩ ይናገራሉ።

አሁን ይህ አስተያየት ትክክለኛ ሊሆን ይችላል? እንዴት ነው አንድ ሺ ሰዎች ሰማኒያ ሚሊዮን ህዝብን መቆጣጠርና መንዳት የሚችሉት? ጨርሶ እውነት አይመስልም። ግን... ምናልባት ህዝቡ በድንዛዜ ጎዳና አንገቱን እየቀበረ አድፍጦ የሚጠብቅ ከሆነስ? ያኔ አንድ ሺ ሰዎች ሚሊዮኖችን ማገትና መቆጣጠር ላያቅታቸው ይችላል። መጀመሪያ ግን፤ ህዝቡን ወደ ድንዛዜ ጎዳና ማስገባት የግድ ነው።

ኢህአዴግ ይህን አስተያየት እንደማይቀበልና እንደሚያስተባብል ግልፅ ነው። ነገር ግን፤ ሰሞኑን በሌላ ርዕሰ ጉዳይ ተመሳሳይ አስተያየት ከኢህአዴግ በኩል ሳትሰሙ እንዳልቀራችሁ እገምታለሁ። በመንግስት ሚዲያ በተደጋጋሚ ሲነገር ሰምታችሁ ከሆነ፤ በአዲስ አባባ ታላቁ አንዋር መስጊድ ውስጥ “ጥቂት አክራሪዎች ህዝበ ሙስሊሙን መስጊድ ውስጥ አግተው እንዳይወጣ ከልክለዋል” ተብሏል። ይሄ እንዴት ሊሆን ይችላል?

ጥቂት ሰዎች እንዴት እንዴት በሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን ማገትና መንገድ መከልከል ይችላሉ? በቲቪ በተሰራጨው ምስል፤ እጅ ለእጅ ተያይዘው መንገድ ሲዘጉ የሚታዩት ደርዘን የሚሆኑ ወጣቶች  ነው - መንገድ የተዘጋባቸው ደግሞ በጣም ብዙ ናቸው፤ መንገድ ሲዘጋባቸው እንዴት ዝም ይላሉ? አሁን ይሄ እውነት ሊሆን ይችላል? አስቸጋሪ ጥያቄ ነው። ነገር ግን፤ በአንድ ሺ ካድሬዎች አማካኝነት አገሬውን ለመቆጣጠር ከፈለግን፤ ህዝቡም በዝምታ ወይም አሜን ብሎ ታዛዥነትን እንዲቀበል ከተመኘን፤ ህዝቡን ወደ ድንዛዜ ማስገባት የግድ ይሆናል። ነገር ግን፤ ህዝቡ በዝምታ ለኔ ታዛዥ እንዲሆን ካደረግኩት በኋላ፤ አዛዥ ልሁን ብሎ ለሚመጣ ሌላ ሰውም ታዛዥ እንዲሆን አዘጋጅቼዋለሁ ማለት ነው። የእንቆቅልሹ ፍቺም ይሄው ነው። ኢትዮጵያዊያን፤ ሁሉን ቻይ መሆን ይችሉበታል። ባህላችን ነው።

የተነሳብን እለት ግን ጉድ ይፈላል። እንደ ድንዛዜ ጎዳና ሁሉ፤ የግርግር ጎዳናም ባህላችን ነው። በድንዛዜ ጎዳና ችግራችንን መፍታት ሲያቅተን፤ ድንገት አንድ ቀን ይነሳብናል - በእርግጥ ያኔ የምንመርጠው የመደናበርና የግርግር ጎዳናም ችግራችንን የሚፈታ አይደለም። ቢሆንም ግን፤ ራሳችንን እንደጥፋተኛ አንቆጥረውም ... “ቢቸግረን ነው የተደናበርነው” በማለት ለባህላዊ የግርግር ጎዳና ተከራካሪ ጠበቃ እንሆንለታለን። “የጨነቀው እርጉዝ ያገባል” የሚለውን አባባል ተመልከቱ። “ችግር በቅቤ ያስበላል” ሲባልስ አልሰማችሁም? “የተቸገረ ሰው እየተደናበረ በግርግር ጎዳና ውስጥ እየተደናበረ ቢጓዝ አይፈረድበትም” እንደማለት ነው። የግርግር ጎዳናም በባህላዊ አባባሎች የበለፀገ ጎዳና ነው።

በእነዚህ ሁለት ባህላዊ ጎዳናዎች ምክንያት ነው፤ አገራችን በዡዋዥዌ ታሪክ የተሞላችው። የአፄ ሃይለስላሴን ዘመን መመልከት ይቻላል። በአንድ በኩል ሁሉን ነገር ችሎ የማደር፤ የመፍዘዝ፣ የመደንዘዝ፣ የመቆዘምና የመተከዝ መንፈስ ለበርካታ አመታት ዘልቋል በሃይለስላሴ ዘመን። በሌላ በኩል ደግሞ በ60ዎቹ ዓ.ም. አገሪቱን ያጥለቀለቃት የፀበኝነት መንፈስ አስታውሱ - ቅዠታምና ግርግራም፣ ቀዥቃዣና ደንባራ ዘመን። ብዙ ኢትዮጵያዊ አንዴ ድምፁን ያጠፋል፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ “ሆ” ብሎ ይጮሃል።

አንዴ ራሱን እንደሳተ ሰው አንገቱን ቀብሮ ጥቅልል ብሎ ይተኛል - (ሰዎች የበላይና የበታች እንደሆኑ አምኖ፤ በፈጣሪ ለተሰየሙ ምርጦች እየተገዛ፣ የባሰ አታምጣ እያለ በድንዛዜ ይቀመጣል - ለምሳሌ ለአፄ ሃይለስላሴ እየተገዛ)

ሌላ ጊዜ ደግሞ፤ የሰው አጥር እያፈረሰ እንደ እብድ ይወራጫል (ሰዎች ሁሉ ምንም ሳይበላለጡ በሃብት እኩል መሆን አለባቸው እያለ የሰው ንብረት እየወረሰ፤ ሰዎችን በአደባባይ እየረሸነ - ለምሳሌ በአፄ ሃይለስላሴ ላይ እያመፀ)።

ከሁለቱ ጎዳናዎች አዙሪት መውጣት ካልቻልን፤ የአገራችን ታሪክ የድንዛዜና የግርግር ዡዋዥዌ እንደሆነ መቀጠሉ ነው።

 

 

 

Read 3512 times Last modified on Saturday, 28 July 2012 10:20

Follow us on twitter

Due to an error, potentially a timed-out connection to Twitter, this user's tweets are unable to be displayed.