Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 21 July 2012 13:59

የእግር-መንገዱን መረጥኩኝ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

የእግር-መንገዱን መረጥኩኝ

ጐማ ከበዛበት አስፋልት፣ የእግር-መንገዱን መረጥኩኝ

ከማህል ጐዳናው ይልቅ፣ ዳር ዳሩን መሄድ ተሻለኝ

መጨናነቅን ለመሸሽ፣ ከነፃው ሰው ተሰለፍኩኝ

ነፃ የሆነ እግር መንገድ፣ ነፃነት ነው የሚመስለኝ!

ከአውራ-መንገዱ ጥርጊያ፣ ሣር ያለበት ቀጭን መሬት

ልዩ ስሜት ይሰጠኛል፣ ለቅን አዕምሮዬ ፅናት

ቀጭን መንገድ፤ የዕምነት ዓይነት

እንደልብ የሚሄዱበት!

ደሞም የእግር መንገድኮ፣ ብዙ እግረኛ ያገናኛል

ለምለም ሰው እንደለምለም ሣር፣ ነፃ ግጥም ይመስለኛል

ራሱ በነፃነት በቅሎ፣ ነፃነቴን ይሰጠኛል

ማንም ስላልከረከመው፣ ራሱ ሲያድግ ይታየኛል!

ይሄ ሥልጣኔ ያልነው፣ ክንፍ ያወጣ ሥይጣኔ

ሲፈጠር ቅንነት ያጣ፣ አድሮም የፈጠራ ጠኔ

እንደቆርቆሮ በሚሥማር፣ የግጥምን ቤት እየመታ

ካሳብ ርሃብ ሳይላቀቅ፣ ያለጣዕም በቃል ሆታ

የቴያትር የፌዝ እሩምታ፣ አድሮ ለገበያው ጌታ

ጥበብ እንደፍሬን ሸራ፣ ሟልጦ ቁልቁል ሲያንደረድር

በዘመናዊነት ሽፋን፣ ድንቁርናችን ሲሞሸር

ይሄ ሆኗል ዕድገት ማለት

ይሄ ሆኗል ሥልጣኔ

ያዲያቆነ ሠይጣን መቼም፣ ሳያቀስ አይተውም መጥኔ

ያለ ስብዕና ቅኔ

ያለልቡና ያለሰው

በአቃቤ-ንዋይ ታጅቦ፣ የዘመነ ሥይጣኔ

ባዶው በዝቶ ጩኸት ነግሦ፣

መንገዱን ሲያጨናንቀው፤

ንፁህ አንጐልን ይዞ፤ በእግሩ መንገድ መሄድ ነው!

በእግር መንገድ በመሄዴ፣ አትፍረዱብኝ አደራ!

ፅዱ ግጥም እንደሣር ነው

መከርከም ካላበዙበት፣ የሚበቅለው ልብ ላይ ነው

የነፃነት ምልክት ነው!

በጐች ሁሉ የሚግጡት፣ ግጦሽ ሜዳ ስመለከት

ዋኔዎች የሚበርሩበት፣ ነፃ ሰማይ ሲመለከት

በእግር መንገድ መሄድ ስችል፣ ተራ ሰው በሚኝበት

የአገት አድባር ትጠብቀኝ፤ አለሁ ትለኝ ይመስለኛል

አገር ያለኝ ይመስለኛል!

ነ.መ.

(አገር ለላቸው)

ሐምሌ 2004

 

 

Read 5542 times Last modified on Saturday, 21 July 2012 14:02