Saturday, 26 September 2020 00:00

“አሃዳዊነት” የፖለቲካ ሟርት ነው

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(1 Vote)

   ዴቪድ ብሩክስ የተባለ አሜሪካዊ ጸሐፊ፤ “የዘመናችን የአስተዳደር/የፖለቲካ ካንሰር”፣ በማህበራዊ ሜዲያ የሚነዳ “መንጋ” (Mob) መሆኑን ይነግረናል። የምንኖረው በልዩነት በተሞላ ትልቅ ማኅበረሰብ ውስጥ ነው። በእንደዚህ ዓይነት ሰፊ ልዩነት ባለው ማህበረሰብ ውስጥ ህግና ሥርዓትን ለማስፈን በዋናነት ሁለት መንገዶች መኖራቸውን ይነግረናል - ብሩክስ፡፡ እነሱም አንደኛ፡- “ፖለቲካ ወይም አምባገነንነት”፤ ሁለተኛ፡- “ውይይት ወይም ኃይል” ናቸው ይላል ዴቪድ ብሩክስ። “ስልጡኖች ፖለቲካን” እንደሚመርጡም ይነግረናል ይኸው ጸሐፊ፡፡
ፖለቲካ በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ የተለያዩ ቡድኖች፣ ፍላጎቶችና አስተሳሰቦች አንድ ላይ ተቻችለው መኖራቸውን የምንገነዘብበት እንቅስቃሴ ነው፡፡ ማድረግ የሚገባን እነዚህን ፍላጎቶች ለማመጣጠን ወይም ለማስታረቅ አሊያም ለማቻቻል ካልሆነም የብዙሃኑን ፍላጎት ለማሟላት መጣር ነው፡፡ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ደግሞ በህገ መንግስት መመራት ወይም ማህበረሰቡ በልማድ የተቀበላቸውን ህግጋት መከተል አስፈላጊ ይሆናል፡፡
ብዙዎች እንደሚስማሙት፤ በፖለቲካ ሂደት ሰዎች የሚፈልጉትን አለማግኘታቸው የመጨረሻው የፖለቲካ “ውሃ ልክ” ነው፡፡ እንዲህ ያለው ሁኔታ ደግሞ የሰዎች ጥያቄዎች ምላሽ የማያገኙበት አጋጣሚ በመሆኑ ጠቃሚ ያልሆነ የፖለቲካ ገደብ ነው፡፡ ፖለቲካ፤ ሰዎች የተጣሉባቸውን ገደቦች እንዲገነዘቡና ከፍላጎታቸው በታች የሆነ መፍትሄ እንዲያገኙ የተነደፈ ቀመር ነው፡፡ እናም በአንድ ሀገር ያሉ ማህበረሰቦችን አንድ በአንድ ማስደሰት ስለማይቻል በፖለቲካ ውሳኔዎች እርካታ ማጣት የሚጠበቅ ነው። “ይሄ ደግሞ የፖለቲካ ውበት ነው” ይላሉ የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪዎች፡፡
ሁሉም ሰው በፖለቲካ ውሳኔዎች እርካታ ሊያገኝ እንደማይችል ከተገነዘብን ደግሞ፤ ስለ ሌሎች ሰዎች ፍላጎት ማወቅ፣ ነገሮችን ከሰዎች ፍላጎት አንጻር ማየትና የሌሎች ሰዎችን ፍላጎቶች ከራሳችን ጋር ለማስማማት ያልተቋረጠ ውይይት ማድረግ አስፈላጊ ይሆናል ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያለው ሰጥቶ መቀበልን መሰረት ያደረገ ፖለቲካዊ ውይይትና የመቻቻል መንገድ በተቃራኒ ካለው አምባገነናዊ አገዛዝ የተሻለ አማራጭ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡
በርናርድ ክሪክ “ፖለቲካን በመደገፍ” በሚለው መጽሐፋቸው ላይ እንደገለፁት፤ “ፖለቲካ የሀሳብ ልዩነት ያላቸውን የተከፋፈሉ ማህበረሰቦች ያለ ብጥብጥ የማስተዳደር ጥበብ ነው”፡፡ ነገር ግን “ፖለቲካ የማስተዳደር ጥበብ ነው” ቢባልም፤ ፖለቲካን የሚጠሉ ሰዎች ቁጥር “ጥቂት” የሚሰኝ አለመሆኑም መታወቅ አለበት፡፡ ፖለቲካን “እንዲጠላ” ካደረጉት ምክንያቶች አንዱና ዋነኛው “የፖለቲካ ልምድና ብቃት የሌላቸው፣ ግትር ግለሰቦች የፖለቲካ መሪ ሆነው መቅረባቸው ነው” ይላሉ በመስኩ የተመራመሩ ሊቃውንት። “ግትር ፖለቲከኞች” ደግሞ ለድርደር ቦታ አይሰጡም፡፡ “ግትር ፖለቲከኞች” ስልጣን ለማግኘት የሚረዳቸው ከሆነ፣ የትኛውንም ህግ ለመጣስና ህጋዊ አሰራሮችን ለመደፍጠጥ ወደ ኋላ አይሉም፡፡ “ግትር ፖለቲከኞች” ሌሎች ሰዎችን መስማት አይፈልጉም፡፡ “ግትር ፖለቲከኞች” የሌሎችን ህጋዊ ፍላጎቶችና አመለካከቶች ያለመቀበል የፖለቲካ ወረርሺኝ የተጠናወታቸው ናቸው፡፡ “ግትር ፖለቲከኞች” ሁሉንም ድሎች ለራሳቸው ጠቅልሎ የመውሰድን ፍልስፍና ይከተላሉ። … እንዲህ ያለው ለፖለቲካ ፀር የሆነ ዝንባሌ በሀገራት የዲሞክራሲ ግንባታ ሂደት ላይ መጥፎ ውጤት ማስከተሉም ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡
ለፖለቲካ ፀር የሆኑ “ግትር ፖለቲከኞች”፣ ፖለቲካ ገደብ ያለው እንቅስቃሴ መሆኑን አይቀበሉም፡፡ “ግትር ፖለቲከኞች” ‘ማህበራዊ መሰረቴ’ ለሚሉት ማህበረሰብ የማይፈጸሙ ትልልቅ አጀንዳዎችን በማቅረብ ተዓምራዊ ውጤት እንደሚያመጡ በመናገር ይታወቃሉ። እነዚያ የተስፋ ዳቦዎች በተባለው ጊዜ ሳይሟሉ ሲቀሩ፣ ማህበረሰቦች ይናደዳሉ። ህዝቦች ይበሳጫሉ፡፡ ፖለቲካን የበለጠ ይጠላሉ፡፡ ፖለቲካን የሚጠላ ማህበረሰብ ደግሞ “ድርድር፣ ውይይት፣ ሰጥቶ መቀበል፣ ምናምን…” የሚሉ ነገሮች አይዋጡለትም፡፡ ተረት ተረት ይመስለዋል፡፡ እናም “ሁሉም ነገር ዛሬውኑ እውን ካልሆነ…” የሚል በስሜት የተሞላ እንቅስቃሴ ውስጥ ተገፍቶ ይገባል፡፡ እንዲህ ያለው መንገድ ደግሞ የመተማመን ስሜትን ያጠፋል፤ መግባባትን ከባድ ያደርገዋል፡፡
ከላይ የተነሱትን ነጥቦች በልቦናችን ይዘን የሀገራችንን የቅርብ ጊዜ ሁኔታዎች እንቃኝ… ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሀገራችን እሆነ ያለውን ሁኔታ ስንገመግም ባህላዊ፣ መንፈሳዊም ሆነ ሕገ-መንግስታዊ ድንጋጌዎች የማይደመጡበት ደረጃ ላይ መድረሱን መገንዘብ እንችላለን፡፡ የሰከነ ፖለቲካን እናራምዳለን የሚሉ ፖለቲከኞች፤ ለመነጋገርና ለመደራደር ግራ ተጋብተው ይስተዋላሉ፡፡ ብዙዎቹ “የሚሰማን የለም” በሚል ፍርሃት ዝምታን መርጠዋል። አንዳንድ የፖለቲካ አማተሮች ደግሞ የህዝብን ስሜት የሚኮረኩሩ፤ ወቅታዊ ያልሆኑ “ምውት” አጀንዳዎችን በማራገብ የበለጠ ጮክ ብሎ መናገርን መርጠዋል…
ብዙዎች እንደሚስማሙት፤ ዶ/ር ዓብይ ወጣ ያሉ መሪ ናቸው፡፡ ከተለመደው ፖለቲካችን ያፈነገጡ ናቸው እየተባሉም ይታማሉ፡፡ በርግጥ ዶ/ር ዓብይ ባለፉት 50 ዓመታት በሀገራችን ያየናቸው የፖለቲካ ሂደቶች እንዲሰክኑ ያደረጉ፣ ለውይይትና ለመደማመጥ እድል ይሰጥ የሚሉ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በእውቀትና በፖሊሲ አማራጭ ላይ ያተኮረ መንገድን እንዲከተሉ ፈር የቀደዱ፣ ታሪክ ላይ የተንጠለጠሉ ባህላዊ ፍትጊያዎችና የማንነት ግብግቦች በፖለቲካ አግባብ እልባት እንዲያገኙ መንገድ የቀየሱ ሰው ናቸው የሚሉም አስተያየት ሰጪዎች አሉ። ዶ/ር ዓብይ ብዙዎች እንዲሆን የሚመኙትን መንገድ ተከትለዋል ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ መንገድ ከተለመደው መንገድ ለየት ያለ መሆኑ ዶ/ር ዓብይን “ዳተኛ፣ ግድየለሽ፣ ቸልተኛ፣ ደንታቢስ…” አስመስሏቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ጉምጉምታው ከፍ ብሎ ይሰማል፡፡ ተቃውሞው በርትቶባቸዋል፡፡ “ምን እስኪሆን ነው የሚጠብቀው?!” ባዩ በዝቷል፡፡
በየሶሻል ሚዲያው (አሁን አሁን በቴሌቪዥን ስርጭቶች ጭምር) በዶ/ር ዓብይ ላይ የሚሰነዘሩትን የስድብ ዓይነቶች መዘርዘር አድካሚ ነው፡፡ እነዚህን ውርጅብኞች ያዩና የሰሙ ሰዎች “የዶ/ር ዓብይ ዝና እያሽቆለቆለ ነው” ሲሉም ይደመጣሉ፡፡ በዶ/ር ዓብይ አካሄድ የማይስማሙ ወይም ዶ/ር ዓብይ ምን እያደረጉ እንደሆነ ያልገባቸው ደግሞ ጠ/ሚኒስትሩን “ደደብ፣ ሞሮን፣ ቂል፣…” አድርጎ የማየት ድምዳሜ ላይ የደረሱ ይመስላል። “ዓብይ ለውጡን ቀልብሷል” የሚሉም አሉ። ሁሉም ስሜቱን እንዳሻው ይገልጻል፡፡ ዶ/ር ዓብይ በበኩላቸው፤ “ውሾቹ ይጮሃሉ ግመሉም መንገዱን ቀጥሏል…” በሚል መንፈስ የሚሄዱ ይመስላል፡፡
የዶ/ር ዓብይ ደጋፊዎች ከያቅጣጫው ግፊቱ ሲበዛ የፖለቲካ ሂደቱ እንዲያጥር ይመኛሉ፡፡ ዶ/ር ዓብይ በየእለቱ የለውጥ እርምጃ እንዲወስዱና በየእለቱ ውጤት እንዲያሳዩ ይፈልጋሉ፡፡ ነገር ግን እያንዳንዱ ነገር ሂደትን ይፈልጋል፡፡ ጊዜን ይጠይቃል፡፡ ፖለቲካ በጊዜ ማዕቀፍ የሚከናወን “ሂደት” (Process) ነው፡፡ የፖለቲካ ለውጥን በአጭር ሂደት፣ በአቋራጭ አመጣለሁ ማለት የማይቻል ነገር ነው፡፡ ትክክለኛውን ሂደት ያልጠበቀ ውጤት ቢመጣም፣ መጨንገፉ አይቀሬ ስለሆነ ሂደቱ ጊዜውን ጠብቆ መጠናቀቁ ዘላቂነት ያለው መፍትሄን የሚያስገኝ መሆኑም ግንዛቤ ሊያዝበት ይገባል፡፡
ዶ/ር ዓብይና ፓርቲያቸው ብልጽግና “አሃዳዊ” (Unitary/Totalitarian) ናቸው እየተባሉም ይተቻሉ፡፡ እዚህ ላይ አንድ ነገር መታወቅ አለበት፡፡ ፖለቲከኛ፤ ፖለቲከኛን መተቸቱ፣ የስም ቅጠያ መስጠቱና መፈረጁ በሀገራችን ብቻ የሚስተዋል ክስተት አይደለም። እናም አንዳንድ የፖለቲካ ኃይሎች ዶ/ር ዓብይና ፓርቲያቸው ብልጽግናን “አሃዳዊ ናቸው” ብለው መፈረጃቸው የሚገርም አይደለም፡፡ ይህ ግን የፖለቲካ ሟርት ከመሆን የዘለለ ትርጉም የለውም፡፡ ምክንያቱም በተለያዩ ሀገሮች በሚከናወኑ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሂደቶች ላይ አያሌ ፈተናዎች የተጋረጡ ቢሆንም፤ በዚህ ወቅት፣ በየትም ሀገር ያለ የፖለቲካ ሂደት ወደ ኋላ እየተመለሰ አይደለም፡፡ የእኛም ሀገር ፖለቲካ ከዓለም የፖለቲካ ሂደት አፈንግጦ ወደ ዘመነ መሳፍንት ወይም ወደ ባላባታዊ የፊውዳል ስርዓት አሊያም ወደ ኮሙኒስታዊ አምባገነንነት የማይቀለበስ መሆኑን አስረግጦ መናገር ይቻላል፡፡
በመጨረሻም አንድ ነገር ልበል፡፡ የፖለቲካ ጥያቄ መልስ የሚያገኘው በፖለቲካ ሂደት አማካይነት በሚፈጠር የፖለቲካ ውይይትና ድርድር ነው፡፡ ይህንን ሀቅ አምኖ መቀበል ግድ ነው፡፡ ቁም ነገሩ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት ሊሰሩ የሚገባቸው ተግባራትን እያከናወኑ ከሂደቱ ተጠቃሚ መሆን ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ (ሀሮልድ ላስኪ የተባለ አሜሪካዊ እንዳስቀመጠው) በዴሞክራሲ ሂደት “የማንግባባባቸውን ነጥቦች ለይተን በማስቀመጥ ጥልቅ የሆነ የመግባባት መንፈስን ማረጋገጥ” የዘመናችን የፖለቲካ እውነታ መሆኑን ልብ ልንለው ይገባል፡፡
 ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በ-ኢሜይል አድራሻቸው: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 8099 times