Saturday, 26 September 2020 00:00

በዛሬው የደመራ በዓል የተመረጡ 5ሺ ታዳሚዎች ይሳተፋሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

     - ትርኢቶች በውስን የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ይቀርባሉ
         - በአዲስ አበባ መግቢያዎች ጥብቅ ፍተሻ እየተደረገ ነው


            ዛሬ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በሚከበረው የደመራ በአል ላይ በቤተ ክርስቲያኗ መዋቅር የተመረጡ 5ሺህ ታዳሚዎች ብቻ የሚሳተፉ ሲሆን ከውጭ ተጋብዞ የሚታደም እንግዳም አይኖርም ተብሏል፡፡
ለአያሌ ዘመናት በየአመቱ መስከረም 16 ከ1 ሚሊዮን ያላነሱ ምዕመናን በተገኙበት በመስቀል አደባባይ ሲከበር የኖረው የደመራ በአል ዘንድሮ “በዘመነ ኮቪድ - 19 በውስን ታዳሚዎች የተከበረ” ተብሎ በታሪክ የሚመዘገብ ይሆናል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ ኃላፊ ሊቀ ስዩማን እስክንድር ገብረ ክርስቶስ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ በበዓሉ የሚታደሙ 5ሺህ ተሣታፊዎች ቤተ ክርስቲያኒቱ ባላት መዋቅር ከየአብያተ ክርስቲያናቱ የሚመረጡ የሰበካ ጉባኤ አባላት ይሆናሉ፡፡
ሁሉም ተሣታፊዎች በበአሉ ቦታ ያለ ፊት መሸፈኛ ጭንብል መገኘት የማይችሉ ሲሆን የጤና ጥበቃ መመሪያዎችን ባከበረ መልኩም ተገቢውን ርቀታቸውን ጠብቀው እንዲታደሙ ይገደዳሉም ተብሏል፡፡
በበዓሉ ላይ  የቅዳሴና ፀሎት ስርአቶች ተሟልተው የሚቀርቡ ቢሆንም የካህናትና የሰንበት ት/ቤት ዘማሪያን ቁጥር ግን ከዚህ ቀደም እንደነበረው አይሆንም ብለዋል - ሊቀ ስዩማን እስክንድር ገ/ክርስቶስ፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ የሚታደሙት ውስን የካህናትና የሠንበት ት/ቤት ወጣቶች ናቸው ያሉት ኃላፊው፤ እነሱም ቢሆኑ ዝማሬ ሲያቀርቡ ተገቢውን አካላዊ ርቀት ጠብቀውና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል አድርገው ይሆናል ብለዋል። ወደ በዓሉ ማክበሪያ አደባባይ የሚገቡ ታዳሚዎችም መግቢያዎች ላይ እጃቸውን በሳኒታይዘር እንዲያብሱ ይደረጋል ተብሏል።
በዓሉ በውስን ካህናት፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችና ታዳሚዎች የሚከበር ቢሆንም ከዚህ ቀደም የነበረውን ድምቀት እንደጠበቀ  እንዲከበር ሠፊ ዝግጅት መደረጉን ኃላፊው ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡ የዝማሬና የትርኢት ልምምዶችም አካላዊ ርቀትን ጠብቀው በሚካሄዱበት አግባብ ሲደረጉ መሠንበታቸውን ነው ያስገነዘቡት፡፡
በክብረ በዓሉ ላይ እንደ ወትሮው ከአለማቀፍ እህት አብያተ ክርስቲያናት ተጋብዞ የሚገኝ እንግዳ ባይኖርም በአዲስ አበባ ያሉ አምባሳደሮችና፣ የመንግስት ባለስልጣናት ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል።  
የመስቀል እና የኢሬቻ በዓል አከባበርን አስመልክቶ መግለጫ የሰጠው የፌደራል ፖሊስ በበኩሉ የይለፍ ህጋዊ ፍቃድ የሌለው አካል በአካባቢው መገኘት እንደማይቻል አስጠንቅቋል፡፡
የመስቀልና የኢሬቻ በዓላት ሠላማዊ በሆነ መንገድ እንዳይከበሩ ለማድረግ የሚንቀሳቀሱ አካላት እንዳሉ ፖሊስ ደርሶበታል ያሉት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር እንደሻው ጣሰው ለዚህም ሲባል ወደ አዲስ አበባ ሁሉም መግቢያ በሮች ላይ ጥብቅ ፍተሻ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡



Read 7865 times