Saturday, 26 September 2020 00:00

መንግስት ት/ቤቶችን ከመክፈቱ በፊት ከወላጆች ጋር ሊመክር ይገባዋል ተባለ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(2 votes)

 - “በቂ ዝግጅት ባልተደረገበት ሁኔታ ት/ቤቶችን መክፈት የበሽታውን ስርጭት ያባብሰዋል”
         - እስካሁን ት/ቤቶቻቸውን የከፈቱ የአፍሪካ አገራት ስድስት ብቻ ናቸው
                  
            በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ትምህርት ቤቶቻቸውን የዘጉ አገራት መልሰው ከመክፈታቸው በፊት ከወላጆችና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ግልጽ ውይይት ሊያደርጉ እንደሚገባ የአለም ጤና ድርጅት አሳሰበ፡፡
ድርጅቱ ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ የአፍሪካ አገራት መንግስታት የተዘጉ ት/ቤቶችን ከመክፈታቸው በፊት የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል የሚያስችል በቂ ዝግጅት መደረጉን ማረጋገጥና ከተማሪ ወላጆችና ከትምህርት ማህበረሰቡ ጋር ጥልቅ ውይይት ይካሄድ ብሏል፡፡
በቂ ዝግጅት ባልተደረገበት ሁኔታ ት/ቤቶችን መክፈት የበሽታውን ስርጭት ሊያባብሰው እንደሚችል ሊታሰብበት ይገባል ብሏል - መረጃው፡፡
የዓለም ጤና ድርጅትና ዩኒሴፍ በጋራ ያደረጉትን ጥናት መሰረት አድርገው ያወጡት ሪፖርት እንደሚያመለክተውም፤ በቂ ውሃና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች በሌሉበት ሁኔታ ት/ቤቶች እንዲከፈቱ ማድረግ ችግሩን ያባብሰዋል፡፡ ሁለቱ ድርጅቶች በጋራ ያደረጉት ይኸው ጥናት፤ የአፍሪካ መንግስታት ት/ቤቶችን ለመክፈት ውሣኔ ላይ ከመድረሳቸው በፊት የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር የሚያስችል ዝግጅት መኖሩን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡
ዩኒሴፍ በምስራቅ አፍሪካ አገራት አደረ ያደረገው ጥናት እንደሚጠቁመው፤ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ ልጆች ከትምህርት ገበታቸው እንዲርቁ ከተደረገ ወዲህ የታዳጊ ሴቶች እርግዝና ቁጥር እየጨመረ የመጣ ሲሆን ያለዕድሜያቸው የሚዳሩ ልጆች ቁጥራቸው እየጨመረ መሄዱ ታውቋል፡፡
ይሄን ተከትሎም ት/ቤቶች በሚከፈቱበት ወቅት ወደ ትምህርት ገበታቸው የሚመለሱ ታዳጊ ሴት ልጆች ቁጥር በእጅጉ እንደሚቀንስም ተመልክቷል፡፡
የአለም ጤና ድርጅት ይፋ ባደረገው በዚህ መረጃ፤ የአገራት መካከል በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ ያቆሙትን ትምህርት የጀመሩት 6 አገራት ብቻ መሆናቸውን አመልክተው፤ 19 አገራት ደግሞ በያዝነው መስከረም ወር መጨረሻ ት/ቤቶቻቸውን በግማሽ ለመቀነስ አቅደዋል ብሏል፡፡
የአለም ጤና ድርጅት፤ አገራት የተዘጉ ት/ቤቶቻቸውን ከፍተው ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲጀምሩ ከማድረጋቸው በፊት ትምህርት ቤቶቹ በፀረ ተህዋሲያን መድኃኒቶች እንዲፀዱ፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል በበቂ መጠን እንዲኖርና ት/ቤቶቹ ተማሪዎቹ አካላዊ ርቀታቸውን ጠብቀው ለመማር የሚችሉበትን ዝግጅት ማድረግ እንደሚኖርባቸውም አመልክቷል። ድርጅቱ ያወጣቸውን መስፈርቶች ሳያሟሉ ት/ቤቶች እንዲከፈቱ ማድረግ የበሽታውን ስርጭት ያባብሰዋል የሚል ስጋት እንዳሳደረበት ጠቁሟል፡፡
በኢትዮጵያ ት/ቤቶች በሶስት ዙር እንዲከፈቱ ምክረሃሳብ የቀረበ ሲሆን በዚሁ  መሰረትም፤ የመጀመሪያው ዙር - ጥቅምት 9 ቀን 2013 (በገጠር ወረዳና ቀበሌ፣  ቀጣዩ ዙር ደግሞ ጥቅምት 30/2012 በሁሉም ዞንና የክልል ከተሞች ጥቅምት 16 ቀን 2013 እንዲሁም በሦስተኛ ዙርም በአዲስ አበባና ኦሮሚያ ክልል ለመክፈት የሚያስችል ምክረ ሃሳብ ቀርቧል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ጥልቅ ውይይትና ምክክር ከተደረገ በኋላ ት/ቤቶቹ የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል በሚያስችል መንገድ ተማሪዎቻቸውን ተቀብለው ለማስተማር ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸው ሲረጋገጥ ትምህርት የሚጀመር መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
አዲስ አድማስ ያነጋገራቸው ወላጆች፤ አብዛኞቹ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ወላጆች፤ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት እየተስፋፋ ባለበት ሁኔታ ትምህርት ይጀመራል መባሉ ስጋት ፈጥሮብናል ብለዋል፡፡      



Read 8122 times