Saturday, 26 September 2020 00:00

በኦሮሚያና አዲስ አበባ ከ2ሺህ በላይ ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ተመስርቷል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

     በሰኔው ግርግር ከ160 በላይ ተገድለዋል፣ 46 ቢሊዮን ብር ንብረት ወድሟል

               የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ፣ በኦሮሚያና በአዲስ አበባ በተፈጠረው ሁከትና ግርግር፣ ከ160 በላይ ሰዎች መገደላቸውን፣ ከ4.6 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙን የገለፀው ፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ፤ እስካሁን ከ2ሺህ በላይ ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ተመስርቷል ብሏል፡፡
ዋና ጠቅላይ አቃቤ ህግ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስና የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ለውጭ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ፤ ሁከትና ግርግሩን ተከትሎ ለተፈጠሩ ጉዳቶች ህግ ለማስከበር ባለፉት 3 ወራት የተከናወኑ ተግባራትን አብራርተዋል፡፡
 ባለፈው ሰኔ 22 የአርቲስት ሃጫሉ ግድያን ተከትሎ፣ በኦሮሚያ የተወሰኑ አካባቢዎች አናሳ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መፈፀሙን በመግለጫቸው ያስረዱት ጠ/ቃቤ ህጉ፤ መንግስት የተቀናጀ የህግ ማስከበር እርምጃ መወሰዱን አስገንዝበዋል።
በአርቲስቱ ላይ የተፈፀመው ግድያና በኦሮሚያና አዲስ አበባ የተፈጠረውን ሁከት በትኩረት ምርመራ ሲደረግበት መቆየቱንና በዚህም ባለፉት 3 ወራት በተከናወኑ የምርመራ ተግባራት፣ በቂ ማስረጃ በተገኘባቸው ከ2ሺህ በላይ የወንጀል ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ መመስረቱን ጠ/አቃቤ ህጉ አስረድተዋል፡፡ በዚህ የምርመራ ተግባር ላይም የአዲስ አበባ፣ ኦሮሚያና ፌደራል ፖሊስ የአቃቤ ህግ ተቋማት በትብብር መስራታቸውን አመልክተዋል፡፡
በዚህ ህግን የማስከበር ሂደት ውስጥ አንድም አካል በፖለቲካ አመለካከተ ምክንያት አለመታሠሩንና ሁሉም በወንጀል ተጠርጥረው ወደ ህግ መቅረባቸውን ነው ጠ/አቃቤ ህጉ የጠቆሙት፡፡
ተጠርጣሪዎች ላይ ፈጥኖ ክስ መመስረት ያልተቻለው በተቋማት የአቅም ውስንነት መሆኑ ያስረዱት ጠ/አቃቤ ህጉ፤ ከሠሞኑ አዲስ የተሾሙ ዳኞች ይህን እጥረት በመቅረፍ ድርሻ ይኖራቸዋል ብለዋል፡፡


Read 7765 times