Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 21 July 2012 13:45

ለሳምንታት ያወዛገበውየጠ/ሚ ህመም

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ስኳር ፣ ሉኬሚያ ፣ የአንጎል ካንሰር.... ሲወራ ቆይቷል

ስለህመማቸው የተጨበጠ መረጃ የለም

የአንጐል ካንሰር አይደለም ተብሏል

ካለፉት ሁለት ሳምንታት ጀምሮ በስፋት መነጋገሪያ ሆኖ የሰነበተው የጠ/ሚ መለስ ዜናዊ መታመም በመንግሥት በኩል በይፋ ባለመነገሩ ምክኒያት ታማኝ የሚባሉ በርካታ ዓለም አቀፍ ብዙሃን መገናኛን ጨምሮ በተለያዩ የማኅበራዊ ድረ-ገፆች ጠ/ሚመለስዜናዊበጀርመንሀገርቀዶጥገናማድረጋቸውን፣በቤልጅየም ብራስልስ “Saint LUC Hospital” ተኝተው ሕክምና እየተደረገላቸው መሆኑን፣ የአንጐል ካንሰር እንዳጋጠማቸው፣ሕይወታቸው አደጋ ላይ እንደሆነ ከመዘገብ ጀምሮ ሕይወታቸው ማለፉ ሲነገር ሰንብቷል፡፡

በገዢው ፓርቲ በኩል ምስጢር ሆኖ የሰነበተው የጠ/ሚ መታመም ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ የሆነው የአፍሪካ ኅብረትን ጉባኤ ተለይተውት የማያውቁት ጠ/ሚ መለስ በዚህ ስብሰባ ባለመገኘታቸው እና የሴኔጋሉ ፕሬዝደንት ማኪ ሳሊ ስለ ጠ/ሚሩ መታመም ፍንጭ በመስጠታቸው ነው፡፡ከአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ በኋላም ቢሆን መንግሥት ይፋዊ መረጃ ባለመስጠቱ፤የሕወሓት የቀድሞ ታጋይ አቶ ስብሃት ነጋ ለአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ መታመማቸውን እስካረጋገጡበት ጊዜ ድረስ የተለያዩ መረጃዎች፣አስተያየቶች እና ግምታዊ መላምቶች ሲሰነዘሩ ቆይተዋል፡፡አሁንም እየተሰነዘሩ ነው፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሕመም በማስመልከት ከትናንት በስቲያ በጽ/ቤታቸው ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትሩ አቶ በረከት ስምዖን፤ የጠ/ሚሩ መታመም በይፋ ያልተነገረበት እና በጋዜጠኞችም ከአንድ ወር በፊት ቀርቦ የነበረው ጥያቄ የተስተባበለበትን ምክኒያት ሲገልፁ፤ “የገዢውን ባሕል ማወቅ ጠቃሚ ይመስለኛል” ከሚል ማብራሪያ ነው የጀመሩት፡፡እንደ አቶ በረከት ገለፃ፤ ገዢው ፓርቲ አብዛኛውን ጊዜ ዕድሜውን በበረሃ ያሳለፈ ፓርቲ በመሆኑ በማንኛውም ሁኔታ መስዋዕትነት እየከፈለ ችግሮችን ተሸክሞ ማለፍ የሚችል ፓርቲ ነው፡፡በግለሰቦች ላይ የሚያጋጥም ጉዳይ እንደትልቅ ነገር ተደርጐ የሚወሰድ እንዳልሆነ እና ሕመም እና የመሳሰሉት ችግሮች የአብዛኛው አመራር የሕይወት አካል መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

ከዚህ አንፃርም የጠ/ሚሩን መታመም በሕዝቡ ዘንድ የተጋነነውን ያህል በፓርቲው በኩል ተጋኖ ባለመታየቱ ሁኔታውን እንደቀላል ነገር በማየት ይፋ ማድረግ እንዳልፈለጉ በማስረዳት “መታመም ያጋጥማል፤መታመም በሚያጋጥምበት ጊዜ አስፈላጊ ሕክምና ከተገኘ ተመልሶ ወደ ሥራ ይገባል፤ ስለዚህ እንደመደበኛ ነገር ነው ያየነው፤ ስለዚህ ብዙ ተግተን መግለጫ አልሰጠንም፤ አስፈላጊ ሆኖ ባሰብንበት ጊዜ ይኸው ዛሬ ሰጥተናል” ብለዋል፡፡

የጠ/ሚሩን ሕመም ተከትሎ የአንጐል ካንሰር አጋጥሟቸው በሕክምና ላይ ናቸው መባሉን አስመልክቶ ማብራርያ የሰጡት አቶ በረከት፤ “ጠ/ሚ የአንጐል ካንሰር ሕመም አላጋጠማቸውም” ብለዋል፡፡ዝርዝር ነገር ውስጥ መግባት እንደማያስፈልግ የተናገሩት አቶ በረከት፤‹‹ታመው እንደነበር፤ አሁን በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ አውቀናል፤ ከዚህ ውጪ ያለው ነገር በእሳቸው እና በዶክተራቸው መካከል ብቻ የሚቆይ ነገር ነው፡፡ተገቢ እና ብቁ ሕክምና በሚያገኙበት ቦታ ሕክምና ተደርጎላቸዋል፡፡ውስን የሆነ ቀን ማስቀመጥ ባንችልም በቀናት ውስጥ ወደ ሥራቸው ይመለሳሉ››በማለት ደምድመዋል፡፡

ጠ/ሚሩ ዕረፍት የሌለው ሕይወት እንደሚኖሩ የገለፁት አቶ በረከት፤ አቶ መለስ ላለፉት 30 ምናምን ዓመታት ሥራ ላይ ብቻ የቆዩ መሪ መሆናቸውን አስታውሰው “ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ በመካሄድ ላይ ያሉት ሰፋፊ ፕሮጀክቶች በታሰበላቸው ጊዜ እና በጀት እንዲፈፀሙ ሌት ተቀን የሚሠሩ መሪ ናቸው” ብለዋል፡፡ይህንን አብዛኛው የኢሕአዴግ አመራር አባል የሚያደርገው ቢሆንም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልፋት ግን የተለየ እንደሆነ አቶ በረከት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስክርነታቸውን ሰጥተውላቸዋል፡፡

ጠ/ሚሩ በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን፤ በመላው ዓለም ኢትዮጵያ እና አፍሪካን ወክለው ከባድ ኃላፊነትን የሚጠይቁ ሥራዎች እንደሚሠሩ፣ በG7፣ በG8፣ በG20፣ በአካባቢ ጥበቃ እና በመሳሰሉት ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ በመገኘት የአፍሪካን እና የኢትዮጵያን ጥቅሞች ለማስጠበቅ የሚታትሩ ጠንካራ መሪ መሆናቸውን በመግለፅ፤ ካለባቸው ከባድ የሥራ ጫና እና እረፍት ባለማድረጋቸው የተነሳ የጤና ችግር አጋጥሟቸው እንደነበር አቶ በረከት ተናግረዋል፡፡

የአቶ መለስን ሕመም እጅግ ቀላል አድርገው ለማስረዳት የሞከሩት አቶ በረከት፤ አቶ መለስ አስፈላጊው የሕክምና እርዳታ ሲደረግላቸው መቆየታቸውን ገልጸው የሕክምና እርዳታ በሚሰጧቸው ባለሞያዎች በጣም ከፍተኛ የሥራ ጫና ውስጥ የቆዩ መሪ መሆናቸውን እና በጣም ለረጅም ጊዜ ከሥራ ውጪ እረፍት አድርገው እንደማያውቁ በመገንዘብ እረፍት እንዲያደርጉ በሐኪሞቻቸው መታዘዛቸውን ገልፀዋል፡፡

የአቶ መለስን ያለ እረፍት መሥራት እና መታመም በሚመለከት ለአዲስ አድማስ አስተያየታቸውን የሰጡት የመድረክ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኢ/ር ዘለቀ ገሠሠ “ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መታመም ዋነኛ ችግር ሁሉንም ነገር ጠቅልለው በመያዝ፣ በራሳቸው ላይ ጫና በማሳደር ራሳቸውን ለመታመም ማዘጋጀታቸው ነው” ይላሉ፡፡

የአንድነት ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር ኃይሉ አርአያ በበኩላቸው፤ሕመሙ በጫና ምክኒያት የመጣ ሊሆን እንደሚችል ያላቸውን ግምት በመግለፅ “አንድ ሰው ሁሉንም መሆን አይችልም” ብለዋል፡፡

የአንድነት ፓርቲ ዋና ጸሐፊ እና ብቸኛ የተቃዋሚ የፓርላማ አባል አቶ ግርማ ሰይፉ ደግሞ “እስካሁን አለመታመማቸው ትንግርት ነው” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ለመታመማቸው ምክንያት ከሆነው የሥራ ጫና ውጪ የሕመማቸውን ዓይነት እና የተደረገላቸውንም ሕክምና ምንነት “የጠ/ሚሩና የዶክተራቸው የግል ጉዳይ ነው” በማለት ምንም ማብራሪያ መስጠት ያልፈለጉት አቶ በረከት፤ ጠ/ሚ መለስ ተሽሏቸው ወደ ሥራ የሚመለሱት መቼ እንደሆነ በጋዜጠኞች ቢወተወቱም “የታዘዘላቸውን እረፍት አጠናቀው በቀናት ውስጥ ወደ ሥራቸው ይመለሳሉ” ብለዋል፡፡

የአቶ መለስን ህመም ተከትሎ በኢሕአዴግ የአመራር አባላት መካከል የሥልጣን ሽሚያ ስለመኖሩ የተጠየቁት አቶ በረከት፤‹‹ኢሕአዴግ እንደዚህ ዓይነት ባሕል ጎልቶ የሚታይበት ድርጅት አይደለም፤ ዋናው የሁሉ ሰው ዓላማ እና ትኩረት ለእኔ የትኛው ቦታ ደረሰኝ የሚለው አይደለም፤ የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ እንዴት ይፈጸማል፤ በአፈጻጸም ደረጃ የሚታዩ ችግሮች እንዴት ነው የሚሻሻሉት፤ ኅብረተሰቡ በተቀመጠለት አቅጣጫ ወደተሻለ ነገር ለመምራት ምን እናድርግ ወደሚል ጉዳይ ነው›› ብለዋል፡፡

 

 

Read 45334 times Last modified on Saturday, 28 July 2012 14:23