Saturday, 26 September 2020 00:00

17100 በኮሮና የተያዙ ሰዎች ራሳቸውን አግልለው በቤታቸው እንዲቆዩ ተደርገዋል

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(0 votes)

በኮሮና ቫይረስ የተያዙና በጽኑ ያልታመሙ ሰዎች በቤታቸው ራሳቸውን ለይተው እንዲቆዩ ማድረግ ከተጀመረ ወዲህ፤ 17ሺ አንድ መቶ ሰዎች ወደ ህክምና ማዕከል ሳይገቡ ራሳቸውን በቤታቸው አግልለው እንዲቆዩ መደረጉ ተገለፀ፡፡
የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ራሳቸውን በቤታቸው ለማቆየት ከፈለጉ ማቆየት እንደሚችሉ የሚገልፀው መመሪያ ከወጣ ጀምሮ እስከ መስከረም 14 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ 17100 ሰዎች ራሳቸውን አግልለው በቤታቸው እንዲቆዩ ተደርገዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል 11ሺ122 የሚሆኑት ከበሽታው ያገገሙ ሲሆን 6005 ሰዎች ደግሞ አሁንም በቤታቸው ተገልግው ለራሳቸው ክትትል በማድረግ ላይ ናቸው ተብሏል፡፡ 135 ሰዎች ደግሞ በበሽታው በጽኑ ታመው ወደ ህክምና ማዕከል መግባታቸውንና አምስት ሰዎች መሞታቸውን መረጃው አመልክቷል፡፡
በያዝነው መስከረም ወር ብቻ በቤኒሻንጉልና በጋምቤላ 40 የህክምና ባለሙያዎች በቫይረሱ ተይዘው ራሳቸውን አግልለው እንዲቆዩ መደረጉንም ታውቋል፡፡
በተያያዘ ዜናም፤ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በምስራቅ አፍሪካ አገራት ፈጣን ዕድገት እያሳየ መሆኑንና በአንድ ሳምንት ብቻ በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በ5 በመቶ የሞት መጠኑ ደግሞ በ7 በመቶ እየጨመረ መሄዱን የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት መረጃ ይጠቁማል፡፡ በያዝነው የመስከረም ወር ኢትዮጵያና ኬኒያ የቫይረሱ ስርጭት መጠን እየጨመረ ከመጣባቸው የምስራቅ አፍሪካ አገራት ቀዳሚዎቹ ሲሆኑ ጅቡቲ ሱዳንና ሱማሊያ ስርጭቱ የቀነሰባቸው አገራት ናቸው ተብሉል፡፡ ኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች በብዛት ከሚገኙባቸው የአፍሪካ አገራት በአራተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሲሆን 665ሺ 188 ዜጐቿ በቫይረሱ የተያዙባት ደቡብ አፍሪካ በአንደኛነት ትመራለች፡፡ ሞሮኮ 107ሺ743 ዜጐቿ በበሽታው ተይዘውበት ሁለተኛ፤ ግብጽ 102ሺ375 ዜጐቿ ቫይረሱ ተገኝቶባቸው ሶስተኛ፣ ኢትዮጵያም 71 ሺ 083 ዜጐቿ በቫይረሱ ተይዘውባት በአራተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡
እስከ ትናንት በስቲያ ባለው መረጃ፤ በአገራችን 1141 ያህሉ ደግሞ በዚሁ በሽታ ሳቢያ ህይወታቸው አልፏል፡፡   


Read 792 times