Thursday, 24 September 2020 00:00

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ ቋንቋና አብዮት

Written by  (መስፍን ወልደ ማርያም)
Rate this item
(2 votes)

ሁለት የአብዮት መሪዎች፣ ሌኒንና ማኦ ስለ ቋንቋና ሰለ አብዮት እየተበሳጩ ጽፈዋል፤ አብዮት ስድነትን አዝሎ ይመጣል፤ ስለዚህም አብዮተኛ ሁሉ ቋንቋ ፈጣሪና የቋንቋ ወጌሻ ይሆናል፤ አብዛኛዎቹ የቋንቋ ወጌሻዎች ገና ከመሀይምነት በቅጡ ያልወጡ ናቸው፤ ነገር ግን እነዚህ ጊዜ የሰጣቸው መሀይሞች ተማርን በሚሉት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አሳድረዋል፡፡ በዚህ የቋንቋ ትርምስ ውስጥ ያልገባች ኤርትራ ብቻ ትመስለኛለች፤ ምክንያቱ ይቆየን፤ ግን እንደምሰማውና እንደማነብበው አገሩ ዛሬም ኤርትራ ነው፤ ሕዝቡም ዛሬም የኤርትራ ሕዝብ ነው፤ ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ የአገሩን ስም ገና አልነኩትም፤ ኢትዮጵያውያን ግን ‹‹ሕዝቦች›› ሆነዋል፤ በተለይ መሀይሞቹ ሎሌዎች (ካድሬዎች) ሲናገሩ ኩራትና ደስታ በተቀላቀለበት ስሜት ነው፤ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝቦች›› የሚሉት! የኢትዮጵያን ሕዝብ ከሰነጣጠቁት በኋላ ለስንጥቅጥቁም ሰም አውጥተዋል፤ ትግሬ ትግራዋይ ሆነ፤ መቀሌ መቐለ ሆነ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ሽንጡን ገትሮ ሲከራከር የነበረው የሪፖርተር ‹ጋዜጠኛ› ትዝ ይለኛል፤ ስለባቔላ አያውቅም! ጋላ ማለት ነውር ሆነና ኦሮሞ ተባለ፤ ጉራጌ ተበታተነና ብዙ ስሞች ተሰጡት፤ እንዲያውም ጉራጌ የቀረው ዓጽሙ ብቻ ነው ለማለት ሳይቻል አይቀርም፤ ወላሞ ወላይታ ተባለ፤ እስላም ሙስሊም ተባለ፡፡ ዛሬ ጥቁር አሜሪካኖችን ኒግሮ ማለት ነውር ሆኗል፤ ኒግሮ ጥቁር ማለት ነው፤ አሜሪካኖቹ ጥቁር አይደለንም ማለታቸው አይደለም፤ ጥቁሮች ባሪያ ስለነበሩ ከባርነት መውጣታቸውን ለማረጋገጥ የባርነት ስያሜን አንቀበልም ማለታቸው ነው፤ እኛ ዘንድ ምኑ ምን ሆኖ ነው የሚለወጠው! ለስድብ ከሆነ የትኛውም ስያሜ ያገለግላል፤ ጎንደሬ ብሎ መሳደብ ይቻላል! ጎጃሜ ብሎ መሳደብ ይቻላል! ትግሬ ብሎ መሳደብ ይቻላል! ኦሮሞ ብሎ መሳደብ ይቻላል! ጉራጌ ብሎ መሳደብ ይቻላል! ነጭ ብሎ መሳደብ ይቻላል! ስድብን የሚገልጸው ቃሉ አይደለም፤ ስድቡን የሚያመለክተው በተናጋሪው ውስጥ ባለው የሚከረፋ ቆሻሻ ተለውሶ ሲወጣ ነው! ስድቡ ያለው ቃሉ ላይ ሳይሆን ቃሉ የለበሰው ስሜት ላይ ነው፤ ያንን ስሜት የትኛውም ቃል ላይ መደረብ ይቻላል፡፡ ለስድብ አብዛኛውን ጊዜ መልስ አለው፤ በተማሪ ቤት አንዳንድ ልጆች አጋሜ ሲባሉ ከአጋሜ ያልተወለደ ባሪያ ወይም ጠይብ ነው ይሉ ነበር! ስለ ስም አጻጻፍ እንዲያው ዝም ብሎ ብዙ ታላላቅ ሰዎች ስማቸውን መጻፍ እንደማይችሉ ተናግሮ ማለፍ ይበቃል፤ ምናልባት አንድ ሰው ስሙን አባይ ብሎ እንደጻፈ ማየቴን ብገልጽ ጉዳዩን ያብራራ ይሆናል፤ ዓባይ ብለው ያወጡለትን ስም አባይ ብሎ ሲለውጠው ወላጆች ቢያውቁ ያዝናሉ፡፡
(ጳጉሜን 2012)

Read 12592 times