Sunday, 20 September 2020 00:00

የኮቪድ ወረርሽኝና ግራ የተጋባው የትምህርት ሥርዓታችን

Written by  ከጀሚላ ሰዒድ
Rate this item
(2 votes)

            • ትኩረት ያልተሰጣቸው ሦስት የትምህርት መስጪያ አማራጮች?
            • ወላጆች ያለ ስጋት ልጆቻቸውን ወደ ት/ቤት እንዴት ሊልኩ ይችላሉ?
              
           ባለፈው ዓመት፣ በወርሃ መጋቢት መባቻ ላይ ኮቪድ 19 ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት አወጀ፡፡ ከዚያም ቀጥሎ በሀገራችን የመጀመሪያው የኮቪድ ቫይረስ ተጠቂ መገኘቱን ተከትሎ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ተደረገ፡፡ ይህ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ በሀገራችን ብቻ ሳይሆን በሌሎች ሀገራትም በትምህርት ስርአት ላይ ከፍተኛ የሆነ ቀውስን ፈጥሯል፡፡ ይሁንና ካደጉት ሀገራት በተለየ በሶስተኛው ዓለም ያሉት ሀገራት ላይ ከቴክኖሎጂው አለመስፋፋትና ተደራሽ አለመሆን ጋር ተያይዞ, ይህ ተግዳሮት በትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ላይ ጫና ፈጥሯል፡፡ ቢሆንም በሽታው ምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ ስለማይታወቅ ትምህርት ቤቶች በያዝነው አመት እንዲከፈቱ መንግስት ይሁንታውን አሳይቷል፡፡ ይሁን እንጂ በርካታ ያልተፈቱ ችግሮችን የተሸከመው የትምህርት መስክ፤ ችግሮቹ ሳይቃለሉ እንዲከፈት መደረጉ ስጋት የፈጠረባቸው ወላጆች በርካታ ናቸው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በርካታ የግል ትምህርት ቤቶች ያሳለፍነውን ዓመት ለመሻገር መንገዳገዳቸው እሙን ነው። በርካታ መምህራን ከስራ ገበታቸው መነሳታቸውም ይነገራል፡፡ ከፊሎቹም ደሞዝ እንዲቀነስባቸው ሆኗል፡፡ ወላጅ የትምህርት ቤት ክፍያን ለምስክር ወረቀት ሲል ከፍሏል። የዓመቱን ግማሽ ያህል ብቻ ተምሮ ወደ ቀጣዩ የትምህርት ክፍል እንዲያልፍ የተደረገው ተማሪ (የዘቀጠው የትምህርት ስርአታችን ተጨምሮበት)፤ ከድጡ ወደ ማጡ ተምዘግዝጓል… የወረርሽኙ መዘዝ ሁሉንም ነካክቷል፡፡
ትምህርት ቤት መከፈቱ ካልቀረ አማራጮች…
ቀጣዩን ዓመት መዝጋት ከተማሪዎችም ከትምህርት ቤቶችም አንጻር እንደ ሀገር አዋጭ አይደለም፡፡ ከተወሰኑ ትምህርት ቤት አስተዳደሮች ጋር ባደረግሁት ኢ-መደበኛ ውይይት፤ በርካታ ተማሪዎች (በተለይም በትምህርታቸው ጥሩ ውጤት የሚያመጡ ተማሪዎች) በትምህርት ዓለም ውስጥ ተስፋ ማጣታቸው ህይወታቸው በድብርት እንዲሞላ አድርጎታል ይላሉ፡፡ ለወትሮውም “ተምሬ ምን እጠቀማለሁ?” የሚለውን ጥያቄ መመለስ የማይችል ስርአት በናኘባት ሀገር ላይ ተስፋ ቆርጦ በአቋራጭ ለመበልፀግ ጥረት የሚያደርገው ሰው መብዛቱ የሚጠበቅ ነው። ይህ ተስፋ መቁረጥ የሚወልደው ሥርአት አልበኝነትን፣ ስደትንና ያለ እድሜ ጋብቻን ሆኗል፡፡ ይህ ትልቅ ችግር በወረርሽኙ የተነሳ በትምህርታቸው ላይ ተስፋ የሚያደርጉትን ተማሪዎችም ማጥቃቱ እንደ ሀገር ትልቅ አደጋ ነው፡፡
የመንግስት ትምህርት ቤቶች በአግባቡ ተደራሽ ባልሆኑባት ሀገር ውስጥ ስለምንኖር የግል ትምህርት ቤቶች ተሳትፎ በሀገሪቷ የትምህርት ስርአት ውስጥ የማይናቅ ድርሻ አላቸው፡፡ ምንም እንኳ እነዚህ የግል ትምህርት ቤቶች በአብዛኛው ከተማው ላይ ቢያተኩሩም ከነችግራቸው የትምህርት ስርአቱ ማገር ናቸው፡፡ እነዚህን ተቋማት በኪሳራ መበተን ከኢኮኖሚ አንጻር ብቻ ሳይሆን ከትምህርት ስርአቱ እድገት አንፃርም  ከባድ ኪሳራ ነው፡፡ በተለይም ሀብት ለማጋበስ ሳይሆን “ማህበረሰብን ማገልገል” በሚል መርህ ያለ ትርፍ የሚሰሩትንና ወደ ሴክተሩ የገቡትን አዳዲስ ት/ቤቶች በተስፋ መቁረጥ እንዲርቁ ያደርጋቸዋል፡፡
መንግስት እነዚህን ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት ትምህርት ቤቶችን እንዲከፈቱ ይሁንታውን ማሳየቱ ተገቢ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ አፈፃፀሙን በሚመለከት መንግስት ጥርት ያለ አመራርና መግለጫ ባይሰጥም የፈረቃ ትምህርትን እንደ አማራጭ መያዙን በገደምዳሜ አሳውቋል፡፡ የፈረቃ ትምህርት ከልጆቹ የትምህርት ጊዜ ላይ ተቀንሶ የሚሰጥ በመሆኑ በትምህርት ጥራቱ ላይ ጉድለትን ማምጣቱ አይቀርም። በተለይ በቅድመ መደበኛና በአንደኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ተማሪዎች የከሰአት በኋላውን ትምህርት በንቁ አዕምሮ ለመከታተል ያዳግታቸዋል፡፡ ይህንን ችግር ከመቅረፍ አኳያ መንግስት ያልተመለከታቸውን ሦስት አማራጭ የትምህርት መስጫ መንገዶችን እንመልከት፡፡
የቤት ውስጥ ትምህርት (Home schooling)፡-
ባደጉት ሀገራት ልጆችን በቤት ውስጥ የማስተማር ዘዴ የተለመደ ነው፡፡ ይህ ዘዴ የሚተገበረው ልጆች በቤታቸው ሆነው ትምህርትን እንዲማሩ በማድረግ ሲሆን በመጨረሻም የሚመጥናቸውን ክፍል በፈተና እንዲቀላቀሉ ይደረጋል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባለ እጅግ አሰቃቂ የሚባል የተማሪና አስተማሪ ጥመርታ ባለበት ሀገር ላይ መሰል ችግሮችን ለመፍታት የመፍትሄ ሀሳብ ሆኖ መምጣት የሚችለው ትልቁ አማራጭ የቤት ውስጥ ትምህርት (Home schooling) ነው፡፡ የችግሩን መጠን ለማሳየት በ2012 ላይ የወጣ ጥናት ያቀረበውን እውነታ እንመልከት፡፡ በቦሌ ክፍለ ከተማ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ዘጠና አምስት በመቶ (95%) የሚሆኑት ከተፈቀደላቸው የተማሪ ቁጥር በላይ እንደሚቀበሉ በዚህ ጥናት ላይ ተገልጧል፡፡ ለቅድመ መደበኛና ከ1-4ኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች እንደሚሰራ የሚነገርለት የቤት ውስጥ ትምህርት፤ አተገባበሩን በሚመለከት ተማሪዎች የሴሚስተሩን ቁሳቁስ (የቤት ስራና የሙከራ መልመጃዎችን በማካተት) ለወላጆች በመስጠት ወላጅ/አሳዳጊ እራሱም ሆነ አስጠኚ በመቅጠርና ዓመቱን ሙሉ እንዲያጠና በማድረግ ለቀጣዩ ዓመት ብቁ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል። የግል ትምህርት ቤቶችም ተማሪዎችን በመመዝገብ፣ በመፈተንና አስተማሪ የሚሹ ተማሪዎችን ከራሳቸው አስተማሪዎች በመመደብ የገቢ ምንጫቸው እንዳይቋረጥ ማድረግ ይችላሉ። ተማሪዎች ለቀጣዩ ዓመት ብቁነታቸውን የሚያረጋግጥ የምስክር ወረቀት ማምጣትን ግዴታ በማድረግ የተማሪውን አቅም በሚመጥነው የክፍል ደረጃ እንዲገቡ ማድረግ ይቻላል፡፡ በዚህም ወላጆች ያለ አግባብ እንዳይበዘበዙ፣ እግረ መንገድም በርካቶች የትርፍ ጊዜ ስራን እንዲያገኙ ብሎም ትምህርት ቤቶችም እንዳይዘጉ ይረዳል፡፡ የኮሮና ቫይረስንም ተስፋፊነት መቆጣጠር ይቻላል፡፡ ተጨማሪ የማስተማሪያ ቦታዎችን በመፍጠር ት/ቤቶችን ከመጣበብ ይታደጋል። መንግስት ያላየው አንደኛው የትምህርት መስጫ አማራጭ ይሄ ነው፡፡
2. የርቀት ትምህርት፡-
ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያለው አብዛኛው ተማሪ ትምህርትን ስለሚፈልገውና የትምህርት ትርጉም ስለሚገባው ትምህርቱን በርቀት ትምህርት እንዲከታተል ማድረግ ይቻላል፡፡ የርቀት ትምህርትን ቁሳቁሶች (ማቴሪያል) አሟልቶ በማስቀመጥና በተለይም ስራ ተኮር የቤት ስራዎችንና ፕሮጄክቶችን ለየትምህርት አይነቶቹ በመስጠት ማስተማር ይቻላል፡፡ ተማሪዎቹን በቅርበት ለመገምገም የሚያስችሉ መንገዶችን በመፈለግ (ለምሳሌ በየሁለት ሳምንቱ ፈተናና የሙከራ የቤት ስራዎችን በመስጠት) ተማሪዎች ዋነኛ ትኩረታቸውን ትምህርቱ ላይ እንዲያነጣጥሩ ማድረግ ይቻላል፡፡ ሳምንታዊ ፈተናዎችን ቅዳሜና እሁድ በማድረግ በተለያዩ ማዕከላት በትኖ መፈተን ይቻላል፡፡ ይህንን አማራጭ ሁለት በሉ!
3. ለአጭር ጊዜ የሚሰጥ አዳሪ ትምህርት
    ቤት (Boot Camp):-
ይህ የትምህርት መስጫ ዘዴ ተማሪዎች ከማደሪያቸው ሳይወጡ እዛው ሆነው ተፅዕኖ በሚፈጥር መልኩ ለአጭር ጊዜ የሚሰጥ የትምህርት ዘዴ ነው፡፡ ይህ የማስተማሪያ ዘዴ በወታደራዊ ካምፖች የተለመደ ነው። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የሚማሩበትን የትምህርት ጊዜ በማሳነስና ለሁሉም ተማሪዎች ማደሪያ (ዶርም) በመስጠት ማስተማር ይቻላል፡፡ በዚህ ዘዴ ለማስተማር ሁሉም ተማሪዎች ኮቪድን ተመርምረው እንዲገቡ በማድረግ፤ የገቡት ተማሪዎች ከገቡበት ት/ቤት (ካምፕ) ሳይወጡ ለአጭር ጊዜ ተምረው ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲሄዱ ማድረግ ነው። ጊዜውን አጭር ማድረጉ ተማሪዎቹ ከማህበረሰቡ የተነጠሉ እንዳይሆኑ ይረዳል። በዚህ መንገድ ትምህርት በሚሰጥበት ወቅት ተማሪዎቹ የተማሩትን ተግባራዊ የሚያደርጉበት ፕሮጀክቶችን መስጠትና አካላዊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉበት ማዕከላትን በትምህርት ቤቶቹ ውስጥ ማቋቋም አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ የማስተማሪያ ዘዴ በ2ኛ ደረጃ እና በዩንቨርስቲዎች ተግባራዊ ሊደረግ የሚችል ነው፡፡
እግረ መንገዴን... ስለ የአፍ መፍቻ ቋንቋና የገዳ ስርአት
የትምህርት ስርአታችን ለሀገር በቀል እውቀቶች ትኩረት መስጠቱ ይሁን የሚባል ቢሆንም፤ አብዛኛዎቹ የትግበራ ጥድፊያዎች ከእሳት ማጥፋት ጋር የተያያዙ መሆናቸው ተፅዕኖ ፈጣሪ (assertive) እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ ፖለቲካው የትምህርት ስርአቱን እንዲዘውረው መፍቀዳችን የስህተታችን መጀመሪያ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ቋንቋና ሀገር በቀል እውቀቶችን የሚመለከቱ ግድፈቶችን በወፍ በረር እንመልከት፡፡
ህፃናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ የሚያበረታታው የትምህርት ስርአታችን ዓላማ ተማሪዎቹ የትምህርቱን ፅንሰ ሀሳብ በደንብ እንዲገባቸው ለማድረግ ቢሆንም፤ ከውጭ የተቀዳው ይህ ስርአት ተማሪው በማያውቀው አገር ተጨባጭ ሁኔታ ላይ መመስረቱ ነገሩን የባሰ ሲያወሳስበው ይስተዋላል፡፡ የትምህርቶቹ አንዳንድ ቃላት አቻ የአማርኛ ፍቺ የሌላቸው ተደርገው መታሰቡና የእንግሊዝኛውን መሰረታዊ ትርጉም ሀገራዊ ቅኝት ሳይሰጡ ቀጥተኛ ትርጉም መስጠት ለክፍተቱ መፈጠር ዓብይ ምክንያቶች ናቸው፡፡
ከመደበኛ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ውጪ በሆኑ ቃላት የተተረጎሙ የሳይንስ ቃላትን ተምረው 6ኛ ክፍልን ያጠናቀቁ ተማሪዎች፤ ከ7ኛ ክፍል ጀምሮ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸውን ትተው ያለ ምንም መንደርደሪያና መሰረታዊ ፅንሰ ሀሳቦች በአግባቡ ሳይብራራላቸው በእንግሊዝኛ መማር ይቀጥላሉ፡፡ ለምሳሌ፡- ሂሳብ በአማርኛ “ዝርጥ አንግል” የሚል ቃል ተምረው መጥተው ሂሳብ በእንግሊዘኛ “Obtuse Angle” ብሎ ሲቀጥል ተማሪው የሁለቱን ሀሳቦች አንድነትና ልዩነት ሳይረዳ ነው ትምህርቱ የሚቀጥለው፡፡ በዚህ መልኩ ወደ 2ኛ ደረጃ የተሸጋገረ ተማሪ ዩኒቨርስቲ ሲገባ ምርምር እንዲያደርግ የሚገደደው በእንግሊዘኛ መሆኑ ደግሞ ተማሪውን ግዴለሽ እንዲሆንና “እድሜ ለጎግል” ብሎ “በኮፒ ፔስት” እንዲመረቅ ያደርገዋል። ይህ ውዥንብር አለመጥራቱ ይበልጥ ግልፅ የሚሆነው በትምህርት ሚኒስቴር ስር የሚታተሙ በኛ አገር ካሪኩለም ውስጥ ያሉ የእንግሊዘኛ መጻህፍት ገበያው ላይ መገኘታቸው ነው፡፡
ወደ ገዳ ስርዓት መማር እንለፍ… በያዝነው ዓመት ይተገበራል የተባለው የገዳ ስርአትን የማስተማር ጉዳይ በዚህ ሰሞን መነጋገሪያ ከሆኑ ክስተቶች አንዱ ነው። የገዳ ስርአትም ሆነ ሌሎች ሀገር በቀል ትውፊቶች የኢትዮጵያውያን ብሎም የሰው ልጆች ሁሉ የማይዳሰሱ ሀብቶች ናቸው። እናም የኦሮሚያ ወጣቶች ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ስለ የገዳ ስርዓት መማር ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይህም ሲሆን ሀገሪቷ ላይ ያሉ ችግሮችን መፍታት የምንችልበት ሀገር በቀል መፍትሄ አምራች ትውልድ ለመፍጠር ያስችላል፡፡
የኦሮሚያ ወጣቶች ብቻ የመማሪያ ጊዜ (credit hour) ተመድቦላቸው ስለ የገዳ ስርዓት እንዲማሩ ማድረግ ግን ይህ የመማሪያ ክፍለ ጊዜ ከሌሎች የትምህርት አይነቶች ላይ ተቀንሶ የሚመደብ ስለሚሆን፤ የኦሮሚያ ተማሪዎች የመማሪያ ጊዜ ሳይቀነስባቸው ከሚማሩ ተማሪዎች ጋር እኩል መወዳደር እንዲከብዳቸው ያደርጋል። ቀድመው ለብቻቸው መማራቸውም በዘርፉ ላይ ወደፊት ምርምር እንዲያደርጉ አያበረታታቸውም፡፡ ስለሆነም የገዳ ስርዓትን ለኦሮሚያ ተማሪዎች ብቻ ለማስተማር የተላለፈው ውሳኔ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ካለው ፋይዳ አኳያ ቢታይ መልካም ነው፡፡
እንደ ማጠቃለያ…
በሀገራችን በትምህርቱ ዘርፍ ከፍተኛ ክፍተት መኖሩ ይታያል፡፡ ይህንን ክፍተት ለመድፈን በፈጠራና ምርምር ላይ የተካኑ፣ በውይይትና ንግግር የሚያምኑ፣ ሀገራቸውን የሚወዱ፣ አምባገነንነትን የሚጠየፉና ለዲሞክራሲ መጎልበት የሚተጉ፣ ማንነታቸውን ጠንቅቀው የሚገነዘቡና የሚከባበሩ ወጣቶችን ማፍራት የትምህርት ተቋማት ቀዳሚ ዒላማ ሊሆን ይገባል፡፡ ትምህርት ቤት ትውልድ የሚቃናበትም ሆነ የሚጎብጥበት ዋነኛ ማዕከል ነውና ለየት ያለ ትኩረት ያሻዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ የመንግስት ብቻ ሳይሆን የሲቪል ማህበራት፣ የመምህራን፣ የወላጆችና የሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ ነው እላለሁ፡፡



Read 3034 times