Saturday, 19 September 2020 13:59

ከሰውነት መጉደል

Written by 
Rate this item
(4 votes)

    “በኢትዮጵያ ተደጋግመው የተከሰቱ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ እነርሱም አለመተማመን፤ ዘረኝነት፤ መናናቅ፤ የኢኮኖሚ አለመመጣጠን፤ ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር፤ የቤተ እምነትን ማጣጣል፣ የዝምድና ሹመት፣ የሕዝብና የመንግስት ሀብት ምዝበራ፤ ብሔር ተኮር ጥፋቶች፣ ለክፉ ዓላማ ወጣቶችን ማደራጀት፣ ግጭት መፍጠር፤ ዜጐችን ማፈናቀል፤ ጾታዊ ትንኮሳና አስገድዶ መድፈር፣ እናትና ልጅን አብሮ ማቃጠል፣ በመንጋ ፍርድ ሰውን ዘቅዝቆ በጠራራ ፀሐይ መስቀል፣ እንደ በግ ማረድ፣ በድንጋይና በብረት ወግሮ መግደል፤ የጥላቻና ጸያፍ ንግግሮች፣ ብሔርና ሃይማኖት ተኮር ጽሑፎችን ማሰራጨት፤ መስጂድንና ቤተ ክርስቲያንን በሌሊት ማቃጠል፤ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ሳይጨርሱ፣ ታማሚዎች ከሕመማቸው ሳያገግሙ፣ አራሶች ወገባቸው ሳይጠና ቤት በላያቸው ማፍረስ፣ በተዘጉ መንገዶች ምክንያት ወደ ጤና ጣቢያ መድረስ ያልቻሉ እርጉዞች ጐዳና ላይ እንዲወልዱ ማድረግ፣ የምስኪኖችን ንብረት ማውደም፣ ለዘመናት የለፉበትን ጥሪት በአንድ ጀምበር ማቃጠል፣ በእነዚያ ድርጅቶች ተቀጥረው የሚሠሩ ዜጐችን መድረሻ ማሳጣት፣ ምንም የማያውቁ ሕፃናትን ሜዳ ላይ እንደ ጠጠር እስከ መበተን…ድረስ በተለያዩ የአገራችን ከተማዎች…ተነግሮ የማያልቅ ግፍ ከሰውነት በጐደሉ የአረመኔ ሰዎች እጅ ተፈጽሟል፡፡
የነገዋ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ፣ በፖለቲካዊና በመንፈሳዊ የተሻለች እንድትሆን ካስፈለገ እስከ ዛሬ የመጣንባቸውን የሴራ ፖለቲካ፣ አክራሪ ብሔርተኝነትና ሃይማኖተኝነትን ከላያችን ላይ ማራገፍ ይጠበቅብናል፡፡ ካልሆነ ግን ታሪክን ወደ መድገም እንጂ ታሪክን ወደ መሥራት አንሸጋገርም፡፡ በጐ ታሪክን ለመጻፍ መሻቱ ካለን፣ ከገባንበት የሥነ - ምግባር ዝቅጠትና አዙሪት በፍጥነት መውጣት አለብን፡፡ ከታሪክ የምንማረው በርካታ አገራትና ሕዝቦች አሁን የደረሱበትን ከፍታ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ከእኛ የከፋ ነገርም ገጥሟቸዋል፡፡ በእኛ የደረሰም በእነርሱ ደርሷል፡፡ አሁን በአንጻራዊነት ያገኙትን ሰላም፣ ብልጽግና፣ ዕድገት በሁሉም አቅጣጫ ስንመለከተው ተጋርጦባቸው የነበረውን የመፍረስ፣ የመበታተን አደጋ አትኩሮትና ጥንቃቄ የተሞላበት ምላሽ በመስጠታቸው ያለ ጥርጥር እንደተሻገሩት እንረዳለን፡፡
ዛሬም አገራችን መንታ መንገድ ላይ ነች። ችግራችን እንደ ድር ለምን ተወሳሰበ? መፍትሔ መስጠት የተሳነን ለምንድን ነው? በውስጥና ውጪ ያሉ ፖለቲከኞች፤ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ አክቲቪስቶች፣ ጦማሪያን፣ የሚዲያ ባለሙያዎች…ለአገራቸው ውድቀት ነው ወይስ ብልጽግና ነው የሚዳክሩት? ስብከታቸው ምንድን ነው? እዚህ ያለውን ሕዝብ ተነስ የሚሉት ለልማት ነው ለጥፋት? ጥላቻን በለፈፉበት ግለት ያህል ስለ ፍቅር ምን ብለዋል? ብሔርተኝነትን ባጐኑት ልክ ስለ አንድነት ምን ተንፍሰዋል? ስለ ምን ተናግረው ስለ ምን ዝም ብለዋል? ታዝበናል? ወይስ ሁላችንም በማውራት ላይ ስለምንገኝ መደማመጥ አልቻልንም? ዝም ማለት ለአገር ትልቅ ውለታ የሚሆንበትም ጊዜ አለ እኮ። በወረኞች መንደር ፀጥታን መርሁ ካደረገ ሰው በላይ ጠቢብ የለም፡፡
አገራችንን ጠፍሮ የያዛት ችግር ምንድነው? መንስዔውና ውጤቱስ? የቱ ጊዜያዊና ቋሚ ነው? ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ ኢትዮጵያ ሕዝቦቿ ከመከራ ለአፍታ እንኳ ሳይላቀቁ መሪር ሕይወት የሚገፉባት ምድር የሆነችው ለምንድን ነው? በዋናነት ሰዎች ከተለያዩ ችግሮች ጋር የሚጋመዱት በሦስት መንገዶች ነው፡፡ የዶክተር ጠና ደዎ ሐተታ በችግር ፈጣሪነት፣ በሰለባነትና በመፍትሔ ሰጪነት ያጠቃልላቸዋል፡፡ በአገራችን ላሉ ችግሮች ደራሲውና ተዋናዩ እኛው ሕዝቦቿ ነን፡፡ ማናችን በችግር መንስዔነት፣ በተጐጂነት፣ በመፍትሔነት እንደተሰለፍን ራሳችንን በግልጽነት እንጠይቅ፡፡ ከመጣነው መንገድ እንማር፡፡ አሰላለፋችንን እናጢን፡፡ ታላቁ ፈላስፋ አፍላጦን፤ “የሰው ልጅ በጐ ትምህርት ካገኘ የተሻለ ይሆናል፡፡ መልካም ትምህርት ካላገኘ ግን የከፋ ይሆናል፡፡” ይለናል፡፡ ከምንጊዜውም በላይ ግብረገብ ዐቢይ የቤት ሥራችን እንደሆነ የተረዳንበት ወቅት ላይ ነን፡፡ አልበርት ካሙ፤ ከግብረገብ ውጪ የሚመላለስን ሰው በጫካ ውስጥ ግዳይ ሊጥል ከሚንጐማለል አረመኔ አውሬ ለይቶ እንደማያየው “A man without ethics is a wild beast loosed upon this world.” ሲል ይነግረናል፡፡”
(ከዮናስ ዘውዴ ከበደ "አልገባኝም" አዲስ መጽሐፍ የተቀነጨበ)

Read 2909 times