Saturday, 19 September 2020 13:58

በአለማችን በ1 ቀን ብቻ 308 ሺ የኮሮና ተጠቂዎች ተገኝተዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

       የኮሮና ተጠቂዎቸች ቁጥር ከ30 ሚሊዮን አልፏል

            የአለም የጤና ድርጅት ባለፈው እሁድ ብቻ በመላው አለም 308 ሺህ ያህል የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች መገኘታቸውንና ይህም ቁጥር ወረርሽኙ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ ከፍተኛው እንደሆነ አስታውቋል፡፡
በዕለቱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች የተገኙባቸው ቀዳሚዎቹ የአለማችን አገራት ህንድ፣ አሜሪካና ብራዚል መሆናቸውን የጠቆመው ድርጅቱ፤ በህንድ 94 ሺህ 372፣ በአሜሪካ 45 ሺህ 523 እና በብራዚል 43 ሺህ 718 የቫይረሱ ተጠቂዎች መገኘታቸውንም አመልክቷል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስ በበኩላቸው፤ ኮሮና ቫይረስ ከቁጥጥር ውጭ መሆኑንና የአለማችን ቀዳሚው የደህንነት ስጋት መሆኑን በመጥቀስ አለማቀፉ ማህበረሰብ ቫይረሱን ለመዋጋት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ተተባብሮ እንዲሰራ ባለፈው ረቡዕ በሰጡት መግለጫ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እስካለፈው ሃሙስ አመሻሽ ድረስ በመላው አለም ከ30.1 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ማጥቃቱንና ወደ 947 ሺህ የሚጠጉ ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት መዳረጉን እንዲሁም ከቫይረሱ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር ወደ 21.9 ሚሊዮን መጠጋቱን ዎርልዶ ሜትር ድረገጽ ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡
አሜሪካ ከ6.8 ሚሊዮን በላይ ተጠቂዎችና ከ201 ሺህ በላይ ሟቾች ከአለማችን አገራት በቫይረሱ ክፉኛ የተጎዳች ቀዳሚዋ አገር ስትሆን፣ ህንድ ከ5.1 ሚሊዮን በላይ ተጠቂዎች፣ ብራዚል ከ4.4 ሚሊዮን በላይ ተጠቂዎች ይከተላሉ፡፡ ብራዚል በ134 ሺህ ሟቾች በሁለተኛ ደረጃ ላይ ስትገኝ፣ ህንድ ከ83 ሺህ በላይ ሟቾች ሶስተኛውን ደረጃ ይዛለች፡፡
ወደ አፍሪካ ስናመራ ደግሞ፣ በአህጉሪቱ ላለፉት ሶስት ተከታታይ ሳምንታት በኮሮና ቫይረስ ከተያዙ ሰዎች መካከል የሚያገግሙት በአማካይ 82 በመቶ ያህሉ እንደሆኑ የአፍሪካ የበሽታ መከታተልና ቁጥጥር ማዕከል ባለፈው ሃሙስ ባወጣው መግለጫ ማስታወቁን እናገኛለን፡፡ በመላው አፍሪካ 13 ሚሊዮን ያህል የኮሮና ቫይረስ ምርመራዎች መደረጋቸውን፣ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ከ1.37 ሚሊዮን በላይ መድረሱን፣ የሟቾች ቁጥር ወደ 33 ሺህ 251 ከፍ ማለቱንና 1.127 ሚሊዮን ያህል ታማሚዎች ደግሞ ማገገማቸውንም ማዕከሉ አክሎ ገልጧል፡፡
የአለም የጤና ድርጅት በበኩሉ፣ በመላው አለም በኮሮና ቫይረስ ከተጠቁ 7 ሰዎች መካከል በአማካይ አንዱ የጤና ባለሙያ መሆኑን ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ ያስታወቀ ሲሆን፣ ይህ ቁጥር በአንዳንድ አገራት ከዚህ በላይ እንደሚሆንና ከ3 ተጠቂዎች አንዱ የጤና ባለሙያ እስከመሆን እንደሚደርስ መግለጹንም አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
የአለም ባንክ ዋና የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ካርሜን ሬንሃርት፤ አለማችን በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ ካጋጠማት የኢኮኖሚ ቀውስ ለማገገም እስከ 5 አመት ያህል ጊዜ ሊፈጅባት እንደሚችል ማስታወቃቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የአሜሪካ መንግስት ፍቱንነቱ የተረጋገጠ የኮሮና ቫይረስ ክትባት በሳምንታት ጊዜ ውስጥ ስራ ላይ እንደሚውልና ክትባቱን ለሁሉም ዜጎቹ በነጻ ለማዳረስ ማቀዱን ባለፈው ረቡዕ ማስታወቁ የተዘገበ ሲሆን የአሜሪካው ሲዲሲ በበኩሉ፤ ከክትባት ይልቅ የፊት ጭምብል ኮሮናን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚከላከል በጥናት ማረጋገጡን ይፋ አድርጓል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ በበኩሉ፤ ከአለማችን አጠቃላይ ተማሪዎች ግማሽ ያህሉ ወይም 872 ሚሊዮን የሚሆኑት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ወደ ትምህርት ገበታቸው አለመመለሳቸውን ያስታወቀ ሲሆን፣ በመላው አለም በቫይረሱ ሳቢያ ትምህርታቸውን ያቋረጡ ተማሪዎች ቁጥር 1.6 ሚሊዮን እንደሚደርስም አመልክቷል፡፡

Read 3321 times