Saturday, 19 September 2020 13:29

ዘንድሮ አገራዊ ምርጫን ማካሄድ እንደሚቻል ተገለፀ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(6 votes)

   ትምህርት ቤቶችን መክፈት እንደሚቻል ምክረሃሳብ ቀርቧል
                 
            በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሳቢያ ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሞ የቆየውን ስድስተኛ አገራዊ ምርጫ በአሁኑ ወቅት ቅድመ ሁኔታዎች አሟልቶ ማካሄድ እንደሚቻል የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ። የአለም ጤና ድርጅት ያስቀመጣቸውን መስፈርቶች ተግባራዊ በማድረግ፣ እንደየ አካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ትምህርት ቤቶችን መክፈት እንደሚቻልም ምክረ ሃሳብ ቀርቧል።
የጤና ሚኒስቴር፤ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምላሽና ቀጣይ እርምጃዎችን በተመለከተ በትናንትናው እለት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርትና ምክረ ሃሳብ ላይ እንደተገለፀው፤ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እየቀነሰ ባይሆንም፤ የቅድመ መከላከሉና ስርጭቱን ለመግታት የሚደረገውን ጥረት በተለያዩ መንገዶች ለማሳደግ ተችሏል። በአገሪቱ ወረርሽኙ በሁሉም ክልሎች የተሰራጨ ሲሆን በአገር አቀፍ ደረጃ በሽታው ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል 95 በመቶ የሚሆኑት የታወቀ የጉዞ ታሪክ የሌላቸው እንደሆኑና በሽታው በማህበረሰቡ ውስጥ በስፋት መሰራጨቱ እንደተደረሰበት ተመልክቷል።
እስከ መስከረም 6 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ 1 ሚሊዮን 165 ሺ 647 ለሚሆኑ ሰዎች የላብራቶሪ ምርመራ እንደተደረገላቸውና ከእነዚህ መካከልም 66 ሺ 224 ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው መረጋገጡን የጤና ሚኒስቴር ሪፖርት አመልክቷል። 1ሺ 45 ሰዎች  በዚሁ ቫይረስ ሳቢያ ህይወታቸውን ማጣታቸውም ተጠቁሟል። የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ስርጭትን በተሻለ መጠን ለማወቅ ከመቻሉም በላይ የመከላከልና የመቆጣጠር አቅም በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ሪፖርቱ ይጠቁማል።
የቀጣዩ ወራት ትንበያ፤ በበሽታው የሚያዙና በበሽታው ሳቢያ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ የሚጨምርበትና ወረርሽኙ ከፍተኛ ጣሪያ ላይ የሚደርስበት ጊዜ ቢሆንም፣ ይህንን ሁኔታ የሚመወስነው አካላዊ ወራራቅ፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎችን በአግባቡ መጠቀምና የእጅን ንፅህና በአግባቡ መጠበቅ የሚተገበርበት ሁኔታ መሆኑም በሪፖርቱ ተገልጿል።
አገራዊ ምርጫን በማካሄድ ሂደትን በተመለከተም በርካታ የአለም አቀፍ ተሞክሮዎች ምልከታ መደረጉን ያመለከተው የጤና ሚኒስቴር ሪፖርት በኢትዮጵያም የበሽታውን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችለው ዝግጅት ዝቅተኛ በነበረበት ወቅት ምርጫን ማከናወኑ ስጋቱን የሚያባብሰው በመሆኑ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም መወሰኑን አስታውሷል። ወረርሽኙ አሁንም የጤና ስጋት መሆኑን የቀጠለ ቢሆንም በሽታው ረዘም ላለ ጊዜ አብሮን ሊቆይ የሚችል በመሆኑና አንፃራዊ በሆነ ደረጃ ስለ ስርጭቱ የተሻለ መረጃ ያለን በመሆኑ ቅድመ ሁኔታዎችን ተግባራዊ በማድረግ ምርጫውን ማካሄድ እንደሚቻል ሪፖርቱ ገልጿል። ምርጫው ከዚህ በፊት ከነበረው የምርጫ ሂደት በተለየ መልኩ የበሽታውን ወረርሽኝ መከላከልን ከግምት ውስጥ ያስገባ የምርጫ ስነምግባርና ደንብን እንዲሁም ማስፈፀሚያ መመሪያዎችን ማዘጋጀትና በዚሁ ዝርዝር መሰረት ወደ ተግባራዊ ሂደት በመሄድ ምርጫውን ማካሄድ ይቻላል ተብሏል።
በዚሁ ወረርሽኝ ሳቢያ የተቋረጠው ትምህርትም የአለም ጤና ድርጅት ያወጣቸውን መስፈርቶች ተግባራዊ በማድረግ፣ እንደየ አካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ትምህርት ቤቶችን መክፈት እንደሚቻልም የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ምክረ ሃሳብ ገልፀዋል። ትምህርት ቤቶቹ ሥራውን ከመጀመራው በፊት ግን የአለም ጤና ድርጅት ያወጣቸው መስፈርቶች በአግባቡ መከናወናቸውን የሚያረጋግጥ ግብረ ሃይል በየትምህርት ቤቶቹ ሊቋቋም ይገባል ተብሏል። የጤና ሚኒስቴር ትላንት ባቀረበው ሪፖርትና ምክረ ሃሳብ ላይ ምክር ቤቱ ከተወያየ በኋላ ለዝርዝር እይታ ለየሴቶች ሕፃናት ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንዲሁም ለህግ ለፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል።

Read 17875 times