Print this page
Saturday, 19 September 2020 13:20

የጥቃትና የጐርፍ ሰለባ ለሆኑ ዜጐች መንግስት ትኩረት እንዲሰጥ ኢዜማ ጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

   ፓርቲው ለተጐጂዎች የ150 ሺህ ብር ድጋፍ አድርጓል

           መንግስት በግጭትና ጥቃት፣ በጐርፍና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ከቀዬአቸው የተፈናቀሉትን በአፋጣኝ እንዲያቋቁም የጠየቀው ኢዜማ፤ ለተጐጂዎች የማቋቋሚያ ተግባር የሚውል የ150ሺህ ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡
ባለፈው ሰኔ 23 እና 24 በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ሁከቶችና ግርግሮች ያስከተሉትን ጉዳት ኮሚቴ አቋቁሞ ወደ ስፍራዎቹ በአካል በመሄድ ማጥናቱን የጠቆመው ኢዜማ፤ ተጐጂዎች እስካሁን በመንግስት በቂ ትኩረት አልተሰጣቸውም ሲል ወቅሷል፡፡
በወቅቱ የከፋ ጉዳት ወደተከሰተባቸው አካባቢዎች ተንቀሳቅሶ ማጣራቱንና ከተጐጂዎች ጋር ውይይት ማድረጉን እንዲሁም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አፋጣኝ መፍትሔ እንዲያበጅ ማሳሰቡን ኢዜማ በመግለጫው አስታውሷል፡፡
ቡድኑ ከነሐሴ 12 እስከ 14 ቀን 2012 በተለይም በሻሸመኔና አርሲ ዴራ ባካሄደው ቅኝት በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች ለ50 ቀናት ያህል የትኛውንም የመንግስት ወገን ድጋፍ ሳያገኙ መቆየታቸውን ማረጋገጡንና አሁንም ድረስ ዜጐች የተለያየ ዛቻና  ማስፈራራት እየተፈፀመባቸው መሆኑን መረዳቱን አስገንዝቧል፡፡
የክልሉ መንግስት ተጐጂዎችን ከተጨማሪ ጥቃት በመከላከልና መልሶ በማቋቋም በኩል እየወሰደ ስላለው እርምጃ ማብራሪያ ይሰጥ ዘንድ በተደጋጋሚ ቢጠየቅም ምላሽ መንፈጉን ያስታወቀው መግለጫው፤ የፌደራል መንግስትም ለደረሰው ጉዳት ይፋዊ ይቅርታ ከመጠየቅ መቆጠቡ ለጉዳዩ የሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑን ያመለክታል ብሏል፡፡
በቀጣይ መንግስት ተጐጂዎች ያሉበትን ሁኔታ እንዲያሳውቅና ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቋል - ፓርቲው፡፡
ኢዜማ በዚህ መግለጫ ሌላው የተመለከተው ጉዳይ የጐርፍ አደጋ ተጠቂዎችን ሲሆን ከፍተኛ የጐርፍ ጉዳት የደረሰበት የአፋር ክልልን ጨምሮ በጋምቤላ፣ አማራ፣ ኦሮሚያና  በሌሎች አካባቢዎች ለደረሱ የጐርፍ አደጋዎች መንግስት ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ ዜጐችን እንዲታደግ አሳስቧል፡፡
የኢትዮጵያ ዜጐች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በጐርፍና በጥቃት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጐች ድጋፍ ይውል ዘንድም የ150ሺህ ብር ድጋፍ በአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በኩል መስጠቱንም አስታውቋል፡፡ ሌሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትም የድጋፍ ርብርብ እንዲያደርጉ ፓርቲ ጥሪ አቅርቧል፡፡



Read 5049 times