Saturday, 19 September 2020 13:17

ምርጫ ቦርድ የኦነግን ጉዳይ መርምሬ ውሳኔ እሰጣለሁ ብሏል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኦነግ የአመራር ውዝግብ ጉዳይ የግንባሩን የመተዳደሪያ ደንብና  የፓርቲዎች ማቋቋሚያ ህግን መሠረት አድርጐ ጉዳዩን በመርመር ውሣኔ እንደሚሰጥ አስታወቀ።
በእነ አቶ አራርሶ ቢቂላ የሚመራው የኦነግ አመራር ቡድን፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ሊቀመንበር የሆኑትን አቶ ዳውድ ኢብሳን ማገዱን ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ  በደብዳቤ ያሳወቀ ሲሆን ከአቶ ዳውድ ኢብሣ በኩል ግን የቀረበ አቤቱታ አለመኖሩን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በእነ አቶ አራርሶ ቢቂላ የሚመራው ቡድን፣ አቶ ዳውድ ኢብሳ ከፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ ውጪ በመንቀሳቀሳቸውና የዲሲፒሊን ጥሰት በመፈፀማቸው ከሊቀ መንበርነታቸው መታገዳቸውን ለቦርዱ በፃፈው ማመልከቻ የገለፀ ሲሆን አቶ ዳውድ ኢብሣ በበኩላቸው፤ ኦነግን ወክሎ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር የሚገናኙ ተወካዮችን በደብዳቤ ከመለወጥ በቀር ያስገቡት አቤቱታ አለመኖሩን ኃላፊዋ አስረድተዋል፡፡
አቶ ዳውድ ኢብሣ ለቦርዱ የፃፉት ደብዳቤ፤ ከቦርዱ ጋር ኦነግን ወክለው መደበኛ ግንኙነት የሚኖራቸውን ከማመላከት ውጪ ፓርቲው በእሣቸው እየተመራ ስለመሆኑ ማሳወቂያ እንደማይሆንም ተጠቁሟል፡፡ ከእነ አቶ ዳውድ በኩል እገዳን በተመለከተ ለቦርዱ የቀረበ አቤቱታ አለመኖሩንም ከቦርዱ መረዳት ተችሏል፡፡
የኦነግ ም/ሊቀመንበር በነበሩት አቶ አራርሶ ቢቂላ  የሚመራው ቡድን፣ ለቦርዱ ያቀረበውን የእገዳ ማመልከቻ መሠረት በማድረግ ውሣኔ ይሰጠን በሚል የጠየቀ አካል ባይኖርም፣ ቦርዱ ጉዳዩን መርምሮ ውሣኔ እንደሚሰጥ የኮሚኒኬሽን አማካሪዋ ሶሊያና ሽመልስ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡
በዚህ መሠረት ቦርዱ የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብና የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅን አመሳክሮ መርምሮ ውሣኔ ያሳልፋል ብለዋል፤ አማካሪዋ፡፡
የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ፣ የፓርቲውን የስነምግባር መመሪያ በመጣስ ከሠላማዊ ትግል ውጪ ሲንቀሳቀሱ ተገኝተዋል በሚል ከሊቀ መንበርነት መታገዳቸውን በእነ አቶ አራርሶ ቢቂላ የሚመራው ቡድን ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ 

Read 1099 times