Saturday, 19 September 2020 12:59

ከ1.5 ሚሊዮን ብር በታች የሆነ ገንዘብን በህገወጥነት መያዝ አይቻልም ተባለ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

  • በተለያዩ ባንኮች ገንዘብን በትኖ ለማስቀመጥ መሞከር ያስወርሳል
     • አገር አቋራጭ አውቶብሶች ወደ አገር ውስጥ ሲገቢ ከ1ዐሺ ብር በላይ ይዘው መግባት አይችሉም
             የፀጥታ ኃይሎች ከ1.5 ሚሊዮን ብር በታች የሆነ ገንዘብን በህገወጥነት መያዝ እንደማይችሉና በዚህ መጠን ገንዘብ ይዘው መንቀሳቀስ የሚፈልጉ ሰዎች ያለመሳቀቅ መንቀሳቀስ እንደሚችሉ ተገለፀ።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴና የብሔራዊ ባንክ ገዢው ዶ/ር ይናገር ደሴ ትላንት በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ ከገንዘብ ኖት ለውጡ ጋር በተያያዘ በፀጥታ ኃይሉም ሆነ በህብረተሰቡ ውስጥ የተለያዩ ውዥንብሮች ተፈጥረዋል። የፀጥታ ኃይሎች ሰዎች በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ ይዘው በሚንቀሳቀሱበት ወቅት “ህገወጥ ናችሁ” በማለት እየያዙ መሆኑን መረጃዎች እንደሚያመለክቱ የጠቆሙት ኃላፊዎቹ፤ ይህም ተገቢ አለመሆኑንና እስከ 1.5 ሚሊዮን ብር ድረስ ማንኛውም ሰው ይዞ መንቀሳቀስ እንደሚችል አመልክተዋል። እንደ ነዳድ ማደያና ሌሎች ከፍተኛ ሽያጭ የሚከናወንባቸው ተቋማት፣ ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ ሊይዙ እንደሚችሉ ያመለከተው መግለጫው፤ ባለ ሀብቶች በእነዚህ ተቋማት በኩል ገንዘባቸውን ለማስገባት ቢሞክሩ ግን ጠበቅ ያለ እርምጃ ይወሰድባቸዋል ብሏል። የተቋማቱ የሽያጭ ታሪክ ክትትልና ቁጥጥር ስለሚደረግበት በተቋማቱ በኩል ለማስገባት መሞከር ለከፋ ችግር ያጋልጣል ተብሏል።
መመሪያው ባንኮችንና ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትን የሚመለከት መሆኑን የጠቆመው መግለጫው፤ አንዳንዶች መመሪያው ባንኮችን ብቻ የሚመለከት ነው በማለት በማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት በኩል ገንዘባቸውን ለማስገባት ሙከራ እያደረጉ መሆኑ እንደተደረሰበትና ይህም ተገቢ እርምጃ እንደሚወሰድበት ተጠቁሟል፡፡
ገንዘባቸውን በተለያዩ ባንኮች በኩል ሂሳብ እየከፈቱ በታትነው ለማስቀመጥ የሚሞክሩ ግለሰቦች ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡና ይህንን የሚቆጣጠር ግብረሃይል ተቋቁሞ በስራ ላይ መሆኑን መግለጫው አመልክቷል። ይህንን ድርጊት ሲፈፅሙ የተገኙ ሰዎች ገንዘባቸው ሊወረስ የሚችል መሆኑንም ተገልጿል።
አገር አቋራጭ ተሽከርካሪዎች ማለትም ወደ ጅቡቲ፣ ሶማሊያና ሱዳን የሚጓዙ አሽከርካሪዎች በርካታ ገንዘብ ይዘው መንቀሳቀስ እንደማይችሉ የተጠቆመ ሲሆን አሽከርካሪዎቹ ከአገር ሲወጡ እስከ 30 ሺ ብር ሲገቡ ደግሞ እስከ 10 ሺ ብር ብቻ መያዝ እንደሚችሉ ተገልጿል። ነገር ግን በህገወጥ መንገድ ገንዘብ በተሽከርካሪዎች ውስጥ ደብቆ ለማስገባት መሞከር ለከባድ ቅጣት ይዳርጋል ተብሏል -የተያዘው ገንዘብም እንደሚወረስ በመግለጽ።


Read 1136 times