Saturday, 12 September 2020 14:48

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by  (በዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ)
Rate this item
(2 votes)

   ዛሬ በይቅርታ ላይ ስናፌዝ ዋልን!
                  
                 የሀገሬ ሰዎች ለይቅርታ (ለመጠየቅም፣ ለማድረግም) ንፉግ ናቸው፡፡ ‹‹ሳላውቅ ያስቀየምኳቸሁ፣...›› ብሎ ይቅርታ መጠየቅ:: መጀመሪያ እስቲ አውቀን የበደልናቸውን ይቅርታ እንጠይቅ፡፡ አውቄ የበደልኩት የለም ለማለት ነው? በየአንዳንዳችን ልብ የበደል ቁልል አለ፤ ያንን ለመናድ መድፈር ነው ይቅርታ፡፡ የበደልከውን ሰው፣ ‹‹ይህን ስላደረግኩህ ይቅር በለኝ›› ብለህ መጋፈጥ፡፡ በደለኛነትን ሸሽጎ በይቅርታ መንጻት አይቻልም፡፡
.ይቅርታ በጅምላ አይሆንም፡፡ መሪዎች የገደሉትን፣ ያሰሩትን፣ ያፈረሱበትን፣ የወረሱትን፣ …ወዘተ. በስም እየጠሩ ይቅርታ መጠየቅ አለባቸው፣ እውን ይቅርታ ከፈለጉ:: ጎንደር ላይ ወጣት ሲረሽን የነበረ፣ ተነስቶ የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ የሚጠይቅበት ምክንያት የለም፤ የገደለውን ያስገደለውን በስም እየጠራ፣ የሟች ቤተሰቦችን  ነው ይቅርታ መጠየቅ ያለበት፡፡ ደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ ስትላቀቅ የተደረገው ይኸውም ነው፡፡ በሀገር ላይ የተሰራ በደል ካለ (ለምሳሌ ኢትዮጵያን የባህር በር እንደ ማሳጣት አይነት) ህዝብ ይቅርታ ይጠየቃል፡፡ አንድ ተማሪ የበደለ መምህር ክፍል ገብቶ ‹‹ያስቀየምኳችሁ ይቅርታ›› ሲል፣ ፐ! ይቅርታ ጠየቀ ይባልለታል:: በፍጹም፤ ይቅርታ አልጠየቀም፡፡ ስሙን ጠርቶ፣ የበደለውን ገልጾ ነው ይቅርታ መጠየቅ ያለበት፡፡
.ይቅርታ መጠየቅ ነው ማግኘት ቁም ነገሩ? እንዴ ይቅርታችንን ተበዳይ መቀበል አለመቀበሉን ማወቅ የለብንም? ካለብን ከበደልነው ጋር መጋፈጥ የግድ ነው፡፡ የጎረቤቴ ልጅ በተገደለ፣ በታሰረ እናት አባቱ እንጂ እኔን ማን ይቅርታ አድራጊ አደረገኝ?
.ደግሞ አንዳንዱ ይገርማል፤ እራሱን ከእየሱስ መስቀል ላይ ሰቅሎ መሀሪ ይቅር ባይ መሆን ያምረዋል፤ ይቅርታ እኮ ዝቅ ማለት ነው:: ‹‹ሳላውቅ በድያችኋለሁ ይቅርታ አድርጉልኝ፤ እናንተ ግን አውቃችሁ በድላችሁኛል፣ ይሁንና ይቅር ብያችኋለሁ››፡፡ እኔ ንጹህ፣ እናንተ ሀጥያተኞች ማለት እኮ ነው፡፡ እስቲ የሚከተለውን ይቅርታ እንመልከት፡፡
‹‹...እስከዛሬዋ ቀን ድረስ ባለማወቅ ለበደልኩት ለማንኛውም በደል ይቅርታን በትህትና እጠይቃለሁ። እኔንም ለበደሉኝ፤ ያለ በደሌ ለከሰሱኝ፣ ያለ ተግባሬ መጥፎን ስም ሰጥተው ላሳጡኝ፤ ሕዝብን ለማገልገል በምተጋበት ወቅት አላስፈላጊ ጦርነትን በመክፈት ሲያደክሙኝና አላሠራ ሲሉኝ ለነበሩት ሁሉ ከልብ የሆነ ይቅርታን አድርጊያለሁ።››
አሁን እዚህ ውስጥ ምን የይቅርታ መንፈስ አለ? ይቅርታ ጠያቂው፣ አውቆ የበደለው አንድም ነገር የለም፡፡ እሱ ላይ የተደረገውን በደል ግን ሆን ተብሎ፣ ታቅዶ እንደተደረገ በዝርዝር ተቀምጧል፡፡ ምናለ የእነሱንም፣ ‹‹ሳታውቁ ለበደላችሁኝ›› ብሎ ቢያልፈው? ወይ የእሱንም ቢዘረዝረው?
.እና እባካችሁ ያልደረስንበትን እንተወው፤ ቢያንስ ጽንሰ ሀሳቡ ለልጆቻችን ይቀመጥ፤ እነሱ ይደርሱበት ይሆናል፤ የልጅ ልጆቻቸውም ቢሆኑ፡፡

Read 25576 times