Print this page
Saturday, 12 September 2020 13:37

“Who is the Master?” - ማነው ጌትየው (ውሻው ወይስ ሰውየው?)

Written by  በተስፋዬ ድረሴ
Rate this item
(0 votes)


            በዘመነ ኮሮና “ጌትየው” ማነው፤ መንግሥት ወይስ “ህዝቡ?” ይላል ጥያቄዬ፡፡ ለመግቢያና ለመግባቢያ እንዲሆነን አንድ ወግ ላስቀድምላችሁ፡፡
ቦታው ካናዳ ነው፡፡ ጊዜው ቆየት ብሏል፡፡ የማጋራችሁ አንድ መጽሄታቸው ላይ በካርቱን ስዕል ተደግፎ የወጣ ጽሁፍ ይዘትን ነው፡፡ እነሆ-፡  ጌታው ውሻውን ሊያናፍስ ከቤቱ ግቢ ወጣ ይላል፡፡ ውሻው ገና በሩ ገርበብ ሲልለት፣ አፍንጫውን አስቀድሞ ነው የውጪውን አስፋልት የረገጠው፤ ጌታውን ባለ በሌለ አቅሙ እየጎተተ፡፡
ሰውየው የውሻውን መጸዳዳት አይቀሬነት ታሳቢ አድርጎ ካካ መዛቂያ አካፋ፣ ጓንትና ፌስታል ብጤ በእጁ ይዟል፡፡ እንደኛ አገር በውሻ ካካ ቀዬ በክሎ “ውሻዬን አናፍሼው መጣሁ” - ብሎ ነገር ካናዳ ውስጥ አይሰራም፡፡ አዎ፤ እንደዚያ ነው:: እያንዳንዱ ነዋሪ የውሻውን ቆሻሻ የማጽዳት ህጋዊ ግዴታ አለበት፡፡ ልብ አድርጉልኝ፤ ህጋዊ ግዴታ ነው ያልኳችሁ:: ግዴታው የተመሰረተው በግለሰቦች የህሊና ፍርድ ላይ (ብቻ) አይደለም:: እዚህ ላይ፣ “ስልጣኔ” የህግ ጥበቃ የተደረገለት የሰዎች የባህሪ መገለጫ መሆኑን ያስተውሏል::   እግረመንገድ ለማስታወስ ያህል፡- ሲስተም (ሥርዓት - መዋቅራዊ አሰራር) ይሉት ነገርኮ ጭብጡ ይኸው ነው፡፡ አንድ ሰው በህሊናው ተመራ አልተመራ እንዲያደርግ የሚጠበቅበትን ነገር ፈጽሞ ካልተገኘ የሚጠይቀው ተቋም አለ:: ሲስተም ሲኖር ዜጎች ለህግ አስከባሪ “አቤት” ለማለት ይበረታታሉ፡፡  “አቤት” የተባለለት ተቋም ተገቢውን ምላሽ ካልሰጠ፣ ወደ ሌላ አካል አቤት ይባልበታል፡፡ ካናዳውያን ይህን ለማድረግ ይችላሉ፡፡ “የማንም ውሻ ደጄ መጥቶ ሲፀዳዳ እያየሁ ዝም አልልም፤ በንጹህ አካባቢ የመኖር መብቴ ተደፍሯል” ብለው ሲያምኑ ለፖሊስ ይደውላሉ፡፡ ፖሊስም ምላሽ ይሰጣል፡፡ ምላሽ ሳይሰጥ ቢቀር የሚጠየቅበት ሌላ መንገድ አለ፡፡ ብቻ፣ የእያንዳንዱ ከተማ ነዋሪዎች በተሳሰረ መዋቅር እርስ በርስ ተጠባብቀው ነው የሚኖሩት፡፡ በየመንገዱ የተተከለ ካሜራ በመኖሩ ደግሞ መጥሪያ ደርሶት ፍ/ቤት ሲቀርብ “አረ እኔ እቴ፤ በተባለው ቀን ውሻዬ እንኳን ሊጸዳዳ ፈሱን እንኳ ቁቅ አላደረገም” ብሎ የቀረበን ክስ ሽምጥጥ አድርጎ ለመካድ አይሞከርም፡፡ ሰዉም መዋሸት ለሌላ ቅጣት እንደሚያጋልጠው ያውቃል፡፡
እና፡- ውሻው አስፋልቱን የሸፈነውን ስኖው snow (እንደ ጥጥ ቁጢት ብን እያለ “ዘንቦ” የተከመረ በረዶ) ለወጉ ያህል ብቻ በኋላ እግሮቹ  ቧጨር፣ ቧጨር ያደርግና ቁጢጥ ብሎ ይፀዳዳል፡፡  ሰውየው የውሻውን ካካ በአካፋው እየዛቀ ወደ ፌስታሉ ይከታል፤ ይቋጥራል፡፡ ውሻው እንደ መሮጥ ሲል፤ ጌታው በሰንሰለቱ ገታ አድርጎ ያስቆመዋል፡፡ ውሻው፣ ቁጢጥ፣ ጭብጥ ኩርምት ብሎ ካካውን እዚያም መጣሉን ይቀጥላል፡፡ ጌታው መዛቁንና ካካውን ፌስታል ውስጥ እየከተተ መቋጠሩን አያቋርጥም፡፡ ይህ ወሬ፣ ውሻው በየቦታው ቆም ብሎ እያነፈነፈ የድንበር መከለያ ሽንቱን ጭርቅ፣ ጭርቅ ባደረገ ቁጥር ጌታው ቆሞ እንደጠበቀው አይጨምርም::
አሪፉ ጨዋታ እነሆ፡- ከላይ የገለጽኩላችሁን ትዕይንት መደጋገም ያስተዋለ ሌላ ሰው በማግስቱ  የሰውየውንና የውሻውን ባለቤት ፎቶግራፍ ጋዜጣ ላይ ገጭ አድርጎ ምን ብሎ ቢጽፍ ጥሩ ነው? “Who is the Master?” (ማነው ጌትየው - ውሻው ወይስ ሰውየው? ማለቱ ነው፡፡) አሪፍ ርእስ አይደል?
ሰው መቼም “ማሰቢያው፤ ነገሮችን መተንተኛው፤ ብዙ ነው አይደል እንግዲህ? እንደ “ጌታ” መሆን ያለበት ተቋም ወይም ሰው እንደ “ሎሌ” ሆኖ ባየሁ ቁጥር ይህ ርዕስ ትዝ ያለኛል፤ Who is the Master?  
አንዳንድ ቤተሰብ ውስጥ ልጆች “ጌታ”፣ ወላጆች “ሎሌ” ሆነው ያጋጥመኛል፡፡ ልጅ ከልክ ያለፈ ይቀብጣል፣ ለምሳሌ፤ “ግዙልኝ ያልኩዋችሁን ነገር አሁኑኑ አምጡ” እያለ ይገረምማቸዋል፣ ያንባርቅባቸዋል፡፡ ወላጅ፣ በተለይም እናት፣ “እሺ ... ቆይ!” እያለች ትለማመጣለች፡፡ “እንዲህማ ፊት አትስጪው” ስትባል፤ “ምን ላርግ ብላችሁ ነው? እምቢ ካልኩት ደሞ ያለቅሳል፣ እቃ ይጨርሳል፣ መሬት ላይ በመንፈራፈር ራሱን ይጎዳል...” አይነት ገለጻ ትጀምራለች፡፡ እየሰማት ይህን መናገሯ ራሱ ለልጇ የቅብጠት ሊቼንሳ (ላይሰንስ) መስጠቷ መሆኑን አታስተውልም፡፡ እንዲያ እንዲያ ይሆንና፣ ልጇ ጌታ - ያውም ጨካኝ ጌታ - እሷ ሎሌ እንደሆኑ ይኖራሉ፡፡  ይህን መሰል፣ ልክን ያለማወቅና፣ ያለማሳወቅ ሁኔታ ብዙ ወላጆችና ልጆችን አላስፈላጊ ግጭት ውስጥ ይከታቸዋል፡፡ በነገራችን ላይ፣ የልጅ ተብዬው እድሜ ከሁለት አመት እስከ ሀያ አምስት አመትና ከዚያም በላይ የዘለለ ሊሆን ይችላል፡፡
በተቋም ደረጃም Who is the Master? ወደ አይምሮዬ ከተፍ እንዲል የሚያደርጉ ነገሮችን ታዝቤ አውቃለሁ፡፡ እነሆ ምሳሌ፡- ከጥቂት አመታት በፊት የጎዳና ተዳዳሪ ህፃናት መርጃ ፕሮጀክት ውስጥ ስሰራ እንዲህ ሆነ፡፡ የአንድ የመሰል ፕሮጀክት ሶሻል ወርከር (ባህሪ ሊያርቅ፣ ፍላጎታቸውን ሊያጣራ የተቀጠረው ባለሙያ ማለት ነው) አጠገባቸው ሆኖ ሳለ “ተረጂዎቹ” ህፃናት ሲጋራ ለኩሰው ሲያጨሱ፣ የብልግና ስድብም እርስበርስ ሲወራወሩ አየሁና ተገርሜ፤ “እንዲህ ሲቀብጡ ዝም አልካቸውሳ?” አልኩት፡፡ “ምን እባከህ፣ ብትመክራቸው መች ይሰሙሃል? እነሱኮ ለምንም ነገር ሀጃ (ጉዳይ፣ ግድ) የላቸውም፤ ብናገራቸው ፕሮጀክቱን ጥለው ነው የሚሄዱት!” ብሎኝ እርፍ፡፡ እዚህ ላይ ነዋ ጌትየው ማነው? ብሎ መጠየቅ፡፡ ሰውየው ስላሳዘነኝ የራሴን ተሞክሮ አካፈልኩት:: በኛ ፕሮጀክት ታቅፈው የሚረዱ ህፃናት ነፃነት እንዲሰማቸው እንጂ እንዲቀብጡ እድል አንሰጣቸውም፤ “ጌትየው” እኔ ነኝ እንጂ “እነሱ” አይደሉም” ብዬ አስረዳሁት፡፡ ተግባብተን ተለያየን፡፡
አሁን ወደ ኮሮና ነክ መራራ እውነታዎች እንምጣ፡፡ ኮሮናን ለመከላከል ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ “ህዝቡ” ራሱን  እንዲጠብቅ መመሪያ እየተላለፈ ነው፡፡ የባሰ ጉዳይ የሌለበት ሰው ከቤቱ እንዳይወጣ ምክር፣ ትምህርት በመሰጠት ላይ ይገኛል፡፡ እ፡- ማንኛውም አዋቂ እግረኛ የፊት መሸፈኛ ማስክ (ብዙዎች ማክስ እያሉት ነው - በስህተት) ሳያደርግ መንገድ ላይ አይታይ ... እየተባለ ነው፡፡ በየቡና ጠጡ ቤትና በመሰል ቦታዎች መሰብሰብ፣ መጠጋጋትም ተከልክሏል:: ይህ መመሪያ፣ ትምህርት፣ ትዕዛዝ መተግበር ነው ያለበት፡፡ ግድየለሾች በሚያመጡት ጣጣ፣ ጠንቃቆች ማለቅ የለባቸውም፡፡ በሰነፎች ጦስ፣ ጎበዞች መጎዳት የለባቸውም፡፡ ነገር ግን፣ እንዲህ የሚባል ነገር አለ፤ “...ሰው የእለት እንጀራ ፈላጊ ስለሆነ፣ ... ማስክ መግዣ ካለውማ ምኑን ደሃ ይባላል...?” ወዘተ፡፡ እነዚህን የመሰሉ አስተሳሰቦች ናቸው ሎሌውን እንደ ጌታ፣ ጌታውን እንደ ሎሌ እንዲተውን (እንዲኖር) የሚያደርጉት፡፡
የተቸገረ ሰው፣ እርዳታ ይጠይቅ፡፡ ይህ ተቀባይነት ያለው ነገር ነው፡፡ ቀበሌ ሄዶ፣ የጎረቤቱን የግቢ አጥር አንኳኩቶ “ይህን የመከራ ጊዜ የማልፍበት ብር አበድረኝ፣ ... ከቀለብህ አካፍለኝ” ይበል፡፡ ስለ ችግሩ፣ ኮሮናን አስመልክቶ ለተቋቋሙ የእርዳታ ኮሚቴዎች ያሳውቅ፡፡ ይህን በማድረግ ፈንታ፣ “ ... ቤቴ ቁጭ ብዬ ረሀብ ከሚገድለኝ፣ መንገድ ላይ እየተንገላወድኩ ኮሮና ቢይዘኝ ይሻላል” አይነት “መከራከሪያ” ራስን ከሎሌነት ወደ ጌታነት የማሸጋገሪያ የቀበጦች ስልት መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡
ዜጎች፣ እጅግ ተራ የሆነ የጥንቃቄ እርምጃ ለመውሰድ ፈቃደኛ ባልሆኑበት አገር፣ መንግሥት የቱንም ያህል ቢለፋ ውጤታማ ሊሆን አይችልም፡፡ “ጌትየው እኔ ነኝ” ለማለት መድፈር፣ ጌታነቱን ለማሳየትም ኮስተር ማለት ነው ያለበት፡፡ ይኸው፣ ይቺን ሰሞን እንኳ “ማስክ ያላደረጉ ሰዎች ታፈሱ” ሲባል ተሰምቶ መንገደኛ ሁሉ ተሸፋፍኖ መሄድ ጀመረ አይደል? ለተቸገሩ ሰዎች የተሟላ እርዳታ መፈለግ የመንግሥትም ሆነ አቅም ያላቸው ዜጎች ሁሉ ኃላፊነት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ “ችግረኛ ነኝ” በሚል የመቅበጫ ሊቼንሳ፣ ዜጎች የሃላፊነት ጭነታቸውን ወደ መንግሥትና “ህዝብ” ሲያሸጋግሩ ማየት ግን ያሳምማል፤ በተለይ Who is the Master? የሚለው ጥያቄ ለሚከነክነው፣ ለእንደኔ ዓይነቱ ሰው፡፡
የሚገርምኮ ነው! ጫት መቃሚያ ቤት፣ ሺሻ ማጬሻ ቤት ተዘጋ ሲባል ጭለማን ተገን አድርገው እንደ ቀድሟቸው መጠጥ የሚቸበችቡ፣ “ፈቀቅ፣ ፈቀቅ ብላችሁ ተቀመጡ” የሚል ማስታወቂያ ለመለጠፍ እንኳ ፍላጎት የሌላቸው መሸታ ቤቶች ይፈላሉ፡፡ ጎረቤታሞች ተጠራርተው ይበላሉ፣ ይጠጣሉ፡፡ ዛሬም ልደት የሚያከብሩ፣ ከቀብር መልስ ድንኳን ሞልተው ተቀምጠው የሚያስተዛዝኑ፣ በተዝካር ምክንያት የሚሰባሰቡ፤ ምናልባትም አመታዊ የቤተሰብ ሸንጎ ጉባዔያቸውን የሚያካሂዱ ወዘተ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ ምን ይሄ ብቻ! ሰርግም የሚደግሱ አሉ፡፡ እና፣ ምን እየተሆነ ነው?  መንግሥት እስከ መቼ ነው እየዞረ ሎሌ የሚሆነው? ነው ጥያቄው፡፡ የተወሰኑ ዜጎች ይቀብጣሉ፣ በሽታው ሲይዛቸው የጤና ባለሙያዎች ላይ ይወድቃሉ:: በቀን ከስምንት ሰዓት በላይ እንደ ቀፎ ቆራጭ ፊታቸውን ተሸፋፍነው፣ እግራቸው እስኪንቀጠቀጥ ድረስ ታማሚዎችን ሲንከባከቡ የሚውሉ (የሚያድሩ) የጤና ባለሙያዎች በምን እዳቸው ነው፣ አንድ ማስክ ገዝተው አፍንጫና አፋቸውን ለመጋረድ ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች የሚያመጡባቸውን አበሳ የሚሸከሙት?
ሀሳብ መጣልኝ እናንተ፡- መንግሥት የጥቆማ ኮሚሽን ቢያቋቁምስ? ኮሚሽኑ የሚተዳደረው ደንብ ከተላለፉ ዜጎች፣ ተቋማት በቅጣት ከሚሰበሰብ ገቢ ይሆናል፡፡ ለኮሚሽኑ ጥቆማ የሚሰጠው ማነው? ከተባለ፤ “ማንኛውም ዜጋ” የሚል ነው መልሱ፡፡ ሥራ አጥ ወጣቶች ገንዘብ በማግኘት ብቻ ሳይሆን አካባቢያቸውንም ከኮሮና ጥቃት በመጠበቅ ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት የፈለገና ለአካባቢው ደህንነት ዘብ የሚቆም ማንኛውም ሰው ይህን ሚና ሊጫወት ይችላል፤ ሀብታምም ቢሆን ማለት ነው፡፡ በበኩሌ፣ የሰፈሬ ባለሱቅ ላይ ነው የምጠቁመው፡፡ ለስሙ ሲባጎ ወጥሮ “አትጠጉኝ” ካለ ቢቆይም፣ ከመስኮቱ ግራና ቀኝ ማስክ ያላደረጉ ጎረምሶች ቆመው ወሬያቸውን ሲሰልቁ ዝም ነው የሚላቸው፡፡ ደንበኛ ሲመጣ እንደ ምሰሶ ከግራና ቀኝ ከቆሙ ጎረምሶች መካከል መቆም ይገደዳል፡፡ ርቀቱን ለመጠበቅ አይችልም፡፡ ደጋግሜ ነግሬው እምቢ ስላለኝ ነው ጠቁሜ የማስጠብሰው፡፡ አይኑ እያየ ነው ከማገኘው ኮሚሽን፣ ከራሱ ላይ የስልክ ካርድ ግዝት የማደርገው፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ የመንግሥት መዋቅሮች ክፍለ ከተማዎች፣ ወረዳዎች መረጃን የማነፍነፍና ቅጣቱን የማስፈፀም ሀላፊነት ሊሰጣቸው ይችላል፡፡ ለምሳሌ፤ ሰው አየኝ አላየኝ ብሎ ሰርግ የደገሰ፣ መልስ የጠራ ቤተሰብ ቢኖር ጉዳዩን ተከታትሎ ማስቆም፣ መቅጣት ያለበት መንግሥታዊው ተቋም ሊሆን ይችላል - ለነዚህ ተቋማት ጥቆማ የሰጠ ይከፈለዋል። ፓ! ቀጪዎቹ ደግሞ ደረሰኝ ይዘው ነው የሚዞሩት፤ እዚያው ቅጥት፣ እዚያው ቅብል፡፡ ጉቦ የበላ የመንግሥት መልዕክተኛ ካለ ደግሞ እሱም ላይ ጥቆማ ማቅረብና ማስቀጣት ...! አይ የቸገረው ሰው! ስንቱን አሳሰበኝ? በሉ፤ከመጠንቀቅ ቸል አንበል፡፡
በዓሉን በሃላፊነት እናክብር፡፡
መልካም አዲስ ዓመት!

Read 1736 times