Saturday, 12 September 2020 13:23

በማርሽ ባንድ የደመቀው የሸገር ፓርክ ምረቃ

Written by 
Rate this item
(7 votes)

   “ለአዲስ ዓመት የተበረከተ ስጦታ ነው” - የቻይና አምባሳደር

           “ዛሬ ድንቅ ቀን ነው፤ ታሪካዊ ቀን ነው፤ ዛሬ የኢትዮጵያውያን አዲስ ዓመት ዋዜማ ነው፤ ስለዚህም መልካም አዲስ ዓመት እመኝላችኋለሁ፡፡” በማለት ነው በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ንግግራቸውን የጀመሩት፤ በሸገር ፓርክ የወንድማማችነት አደባባይ የምረቃ ሥነስርዓት ላይ፡፡   
ብዙዎችን ባስደመመው የሪፐብሊካን ጋርድ ልዩ ወታደራዊ ትዕይንቶች በታጀበውና በደመቀው የሸገር ፓርክ የወንድማማችነት አደባባይ የምረቃ ሥነሥርዓት ላይ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድና ባለቤታቸው ቀዳማይት እመቤት ዝናሽ- ም/ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንና ፕሬዚዳንት ሳለህለወርቅ ዘውዴ እንዲሁም  የሃይማኖት አባቶችና ሌሎችም  እንግዶች ታድመው ነበር፡፡  
“ዛሬ እዚህ የተገናኘነው ለመጠናቀቅ የተቃረበውን የፓርክ ግንባታ ለመመረቅ ነው፤ ሁላችንም እንወደዋለን ብዬ አምናለሁ፡፡ እናንተ - እኔ - ጠ/ሚኒስትሩ - ምክትል ጠ/ሚኒስትሩ - ፕሬዚዳንቷ - እዚህ ያለው ሰው በሙሉ - ይወደዋል የሚል እምነት አለኝ” አሉ - የቻይናው አምባሳደር፤ በልበ-ሙሉነት፡፡  
የወንድማማችነት አደባባይ ለዚህ አዲስ ዓመት የተበረከተ ወቅቱን የጠበቀ ስጦታ ነው ማለት ይቻላል ያሉት አምባሳደሩ፤ የአዲስ አበባ አዲሱ መለያ ገጽታም ይሆናል ብለዋል፡፡ የወንድማማችነት አደባባይ የዚህችን ታላቅ አገር - የኢትዮጵያን - ሥልጣኔ፣ የባህል ብዝሃነትና አንድነትን የሚያንጸባርቅ ነው ሲሉም ገልጸውታል፡፡  
ሁለተኛው የግንባታው ምዕራፍ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከል በስተቀኝ በኩል፤ የሰርግ ሥፍራና የህፃናት ፓርክ ደግሞ በስተግራ በኩል ይኖረዋል ሲሉ በተነቃቃ መንፈስ ተሞልተው ያስተዋወቁት አምባሳደሩ፤ እንደ ሸገርና እንጦጦ ያሉት ፓርኮች አዲስ አበባን ለኑሮ ምቹ ብቻ ሳይሆን ተወዳጅም ያደርጓታል ብለዋል፡፡
በሥነስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በበኩላቸው፤ ባዩት ነገር በእጅጉ መደመማቸውን ጠቁመው፤ ከጥቂት ወራት በፊት ወደዚህ ሥፍራ መጥተው የነበረ ቢሆንም፣ በዚህ ፍጥነት ይጠናቀቃል ብለው እንዳልጠበቁ ተናግረዋል፡፡ “የሸገር ፓርክ የወዳጅነትና የአንድነት ማሳያ ነው” ሲሉም ገልፀዋል፡፡ ፓርኩ የአገሪቱንና የከተማዋን በጐ ገጽታ ከመገንባቱም ባሻገር፤ተባብረን ስንሰራ የምናመጣውን ድንቅ ውጤት ማሳያም ነው ብለዋል፤ፕሬዚዳንቷ፡፡
በምረቃ ሥነስርዓቱ ላይ የቀረቡት የሪፐብሊካን ጋርድ ልዩ ልዩ ወታደራዊ ትዕይንቶች፤ የእንግዶችን ቀልብ የማረኩ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ በመጨረሻም የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፤ #አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የደስታና የጤና ይሁንልን; ሲሉ ተመኝተዋል፡፡


Read 9761 times