Sunday, 06 September 2020 16:47

መለኮታዊነትን የተላበሰው የነገው ሰውና አጀንዳዎቹ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  ርዕስ፡- ሆሞ ዴዩስ -
የመጪው ዘመን አጭር ታሪክ
ደራሲ:- ዩቫል ኖኅ ሀራሪ
ትርጉም:- ዳግም ጥላሁን
እንግሊዝኛ:- 2016 እ.ኤ.አ
አማርኛ ትርጉም:- ሐምሌ 2012 እ.ኤ.አ
የመጽሐፍ ዳሰሳ:- ኤልሳ ሙሉጌታ


          የእስራኤሉ ሂብሪው ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ፕሮፌሰር የሆነው ዩቫል ኖኀ ሀራሪ ከጻፋቸው ሦስት መጽሐፍት መካከል አንዱ ነው። ሆሞ ዴዩስ በበርካታ ቋንቋዎች በመተርጎሙ እጅግ በርካታ ተደራሲያን ጋር ሊደርስና ሊነበብ ችሏል። መጽሐፉ በአጭሩ በሚከተሉት ነጥቦች ዙሪያ ያጠነጠነ ሲሆን፣ ከእነዚህ ለሚመነጩ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ይሞክራል።
1ኛ - በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ችግር የነበሩት ወረርሽኝ፣ ጦርነትና ረኀብ ሲወገዱ፣ የሰው ልጆች አጀንዳ በምን ይተካል?
2ኛ - ከሆሞ ሴፒየንስ ቀጥሎ የሚመጣው ሆሞ ዴዮስ (በላቲን ትርጉሙ - ሆሞ = ሰው፤ ዴዩስ = አምላክ) ማለትም ከአምላካዊው ሰውና የተሻሻለው የሰው ልጅ ዝርያ ችሎታዎቹን ከፍና ላቅ በማድረግ አጀንዳዎቹን ወደ ዘለዓለማዊነት፣ ሀሴትና መለኮታዊነት እንዴት ይቀይራል?
3ኛ - ከዋሻ ዘመን ሰዎች ጀምሮ አሁን እስካለንበት ጊዜ ያሉ የሰው ልጅ ዝርያዎች አዕምሯዊና ማኅበራዊ ዕድገት ታሪኮች እንዲሁም በሰው ልጆች ታሪክ ትልቁ አብዮት ከነበረው ከዛሬ 70,000 ዓመት በፊት ከተካሄደው የእሳቤ አብዮት (Cognitive  Revolution) በዘመናችን እስካሉ እንደ ማርክሲዝምና ካፒታሊዝም ያሉ አብዮቶችና በየጊዜው ስለተነሱ ርዕዮተ-ዓለማት በሠፊው ይዳስሳል።
4ኛ - ከደቂቅ ዘአካላት ተነስቶ ስለተዋቀረው የትልቁ ሕዋ ቀመር፤ ራሳችንን ከምናውቀው በላይ ስለሚያውቁን ቀመሮች ስርዓት ሂደት በተጨባጭ ማስረጃዎች እያስደገፈ ያሳያል።
5ኛ - የውሂብ እምነት (Dataism) ዓለማችን በውሂብ ፍሰት (Data flow) እንደተሞላች እናም የማንኛውም ክስተትና ኃይል ዋጋ ለውሂብ ፍሰት ባደረገው አስተዋፅኦ እንደሚመዘን ይገልጻል። “ዳታይዝም” ስለተባለውና መረጃ ስለሚመለክበት አዲሱ የዓለማችን እምነትና በአጠቃላይ ስለ ሰው ልጅ መፃኢ ዕድሎች ሠፊ ዘገባዎችንና ትንበያዎችን ያካትታል።
ይሄ ሥራ በቅርቡ በአማርኛ ቋንቋ ተተርጉሞ ለገበያ በቅቷል። የትርጉም ሥራ ከዋናው ጸሐፊ ሐሳብና ቅርጽ ሳይርቁ፣ የራስን ፍላጎት ወደ ጎን በመተው፣ ደራሲው ያስቀመጠውን ይዘት በጥሩ ቋንቋና ሁኔታ በጥንቃቄ መቅዳት መሆኑ እሙን ነው። አሁን አሁን በሀገራችን እየወጡ ያሉት የትርጉም ሥራዎች ውስጥ በአንዳንዶቹ የሚስተዋለው የሥነ-ጽሑፍ ሥራውን ይሄኛው ማኅበረሰብ ወደ ራሱ ቋንቋ ተመልሶለት ቢያነበው ይጠቅመዋል በሚል ቀና ሐሳብ መነሻነት ሳይሆን በዋናነት ለገበያው አቅርቦት ወይንም ገንዘብ ማስገኛነቱ ላይ በማተኮር የሚሠሩ በመሆናቸው፤ ከጥቂት የትርጉም ሥራዎች በስተቀር አብዛኞቹ የጥንቃቄ ጉድለቶች፣ በርካታ የቃላት ግድፈቶች እንዲሁም ትልቅ የግንዛቤ ክፍተቶች የሚስተዋልባቸው ናቸው።
ብዙዎቻችን በትርጉም ሥራ ተስፋ በቆረጥንበት በዚህ ወቅት፣ ወጣቱ ዳግም ጥላሁን፣ ይህንን ያለፉ ጊዜያት ታሪኮችን በመመርኮዝና በመተንተን ነገአችንን በአመንክዮ የሚተነብየውን መጽሐፍ ጥንቅቅ ባለ መልኩ ከእንግሊዘኛ ቋንቋ ወደ አማርኛ መልሶታል።
ተርጓሚው ያደረገውን ጥንቃቄና ጥረት ገና መጽሐፉን በእጃችን ስንይዝ የምናስተውለው ነገር ነው። የፊት ገጽ ሽፋኑ፣ የውስጥ ዲዛይንና የወረቀት አመራረጡ (ክሬም ቀለም መሆኑ) ማራኪ፣ ለዕይታና ረዘም ላለ ጊዜ ንባብ ተስማሚ በመሆኑ በአጠቃላይ ለንባብ ምቹ እንዲሆን አድርጎታል።
ከሌሎች የትርጉም ሥራዎች በተለየ ተርጓሚው ከደራሲው ሐሳቦች ጋር የራሱን ዕይታ በመጨመርና ሀገራዊ ዘይቤዎችን፣ ሀገርኛ ገጸ-ባህርያትንና ታሪኮችን በመጨመር ዋናውን የደራሲውን ሐሳብ በእኛ ነባራዊ ሁኔታ አንባቢው በቀላሉ እንዲረዳው በማድረግ አዳብሮታል። ይህ ደግሞ ለትርጉም ሥራው ማማር የሄደበትን ርቀትና በጥልቅ እንዳሰበበት ማሳያ ነው። ለዚህም ያግዘው ዘንድ የደራሲ ስንቅነህ እሸቱን፣ አዳም ረታንና ስብሃት ገብረእግዚአብሔርን ጨምሮ ዐሥራ አንድ ያህል መጽሐፍትን በዋቢነት ያጣቀሰ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ዐሥሩ የሀገራችን መጽሐፍት ናቸው።
ለምሳሌ ገጽ 111 ላይ ስለ እውን-መሰል-ዓለም (Virtual world) ሲተነትን፤ ከታላቁ ደራሲ ስብሃት ገብረእግዚአብሄር ‘ስምንተኛው ጋጋታ’ ድርሰት ውስጥ የታዋቂው ገጸ-ባህርይ አጋፋሪ እንደሻው ልጅ የሆኑት አቶ አላዛር፣ ከሰይጣን ጋር የሚያደርጉትን የስልክ ምልልስ ይጠቅሳል። በተመሳሳይም፤ በገጽ 215 ላይ የመካከለኛው ዘመን ምሁራን ሙዚቃ የፈለክ (ኮስሞስ) መለኮታዊ ዜማ በማስተጋባት ሂደት ውስጥ የሚፈጠርና በመለኮታዊ መነቃቃት የሚቀመር አድርገው ያስቡ እንደነበር በሚያትተው ክፍል ውስጥ ተርጓሚው የጽሑፉን ይዘት አንባቢ የበለጠ በሚረዳው መልኩ፣ የኢትዮጵያዊውን የዜማ ሊቅ ታላቁን ማህሌታይ ያሬድ ዜማዎች የድርሰት ታሪክ ዋቢ ያደርጋል።
እነዚህ ለምሳሌ ያስቀምጥኳቸውና ሌሎችም በትርጉም መጽሐፉ ውስጥ እንደ አጋዥ የተቀመጡ ተመሳሳይ ታሪኮችና የገቡ ገጸ-ባህርያት ከላይ ስለ ትርጉም ካስቀመጥኩት “የትርጉም ሥራ ከዋናው ጸሐፊ ሐሳብና ቅርጽ ሳይርቁ፣ የራስን ፍላጎት ወደ ጎን በመተው፣ ደራሲው ያስቀመጠውን ይዘት በጥሩ ቋንቋና ሁኔታ በጥንቃቄ መቅዳት” ከሚለው መሠረታዊ ሐሳብ ጋር የሚጣረስ ቢመስልም፣ የዳግም የትርጉም ሥራ ውስጥ የገቡት የራሱ ፍላጎቶች፣ ቅርጾችና ማጣቀሻዎች የዋነኛውን የመጽሐፉን ቅርጽና ይዘት የሚቀይሩ ሳይሆኑ እንደ አጋዥ ወይንም እንደ ምሳሌ ልንወስዳቸው የምንችላቸውና የሚያዳብሩት በመሆናቸው ከቀደመው የትርጉም ሐሳብ ጋር ስምም ነው።
ከዚህም በተጨማሪ ዐሥራ ስምንት ያህል መዝገበ-ቃላትን በማጣቀሻነት የተጠቀመ ሲሆን ይህም በትርጉም ሥራው ላይ ስለተጠቀመበት እያንዳንዱ ቃል የወሰደውን ጥንቃቄ ያሳየናል። ተርጓሚው ይህንን በማድረጉ ለአንድ ቃል ከሚያገኝለት የተለያየ ፍቺ ውስጥ እጅግ ጥሩውን መርጦ በመውሰድ፣ የትርጉም ሥራው በተመረጡ ቃላት የተዋበ ለመሆኑ ያገላበጣቸው መዝገበ-ቃላት ምስክር ናቸው።
በማንኛውም ጽሁፍ ውስጥ ማብራሪያ የሚፈልጉ ጉዳዮች ሲከሰቱ፣ ትንታኔዎችን በግርጌ ማስታወሻ ማቅረብ የተለመደ ነው። በዚህ መጽሐፍ ውስጥም የግርጌ ማስታወሻዎች የተቀመጡ ሲሆን በተለየ መልኩ ግን የግርጌ ማስታወሻዎቹ በወካይ አራት ምልክቶች ተከፍለዋል። እነርሱም:-
1) በሌጣ ቁጥር (1፣2፣3 ወ.ዘ.ተ) የተወከሉት ደራሲው በዋቢ መጽሐፍት ያስቀመጣቸው ምንጮች ናቸው።
2) በአበባ ቅርፅ (️) እና በቁጥር የተገለጹት ምልክቶች፣ ተርጓሚው በተጨማሪ ማብራሪያ ያስፈልጋቸዋል ብሎ ላመነባቸው ቃላት የተጠቀመባቸው ናቸው።
3) በልብ ቅርፅ () እና በቁጥር የተገለጹት ምልክቶች፣ ደራሲው ተጨማሪ ማብራሪያ ያስፈልጋቸዋል ብሎ ያመነባቸው ቃላትና ሐሳቦች ናቸው።
4) በአልማዝ ቅርፅ () እና በቁጥር የተቀመጡት ምልክቶች፣ ተርጓሚው በተጨማሪ ላስገባቸው ማጣቀሻዎች ብሎም የተቀየሩ ስያሜዎችን ማመላከቻዎች ናቸው።
እነዚህን አራት ምልክቶች ከቁጥሮች ጋር ተጣምረው ስናገኛቸው፣ ምልክቶቹን በማስተዋል የዋቢ መጽሐፍት ምንጮች፣ የተርጓሚው ማብራሪያዎች፣ የደራሲው ሐሳቦች ወይንም ተርጓሚው ያካተታቸው ምሥሎችና ማጣቀሻዎች መሆናቸውን በቀላሉ መለየት እንችላለን።
የግርጌ ማስታወሻዎችን በተመለከተ እንደተለመደው የግርጌ ጽሑፎቹ መግባት ባለባቸው ገጽ ግርጌ ላይ የሚገኙ ቢሆንም፣ በተለየ ሁኔታ ደግሞ በመጽሐፉ የመጨረሻ ገጾች ላይ እያንዳንዱ የግርጌ ማስታወሻ በቅደም ተከተል ተቀምጦ ይገኛል። ይህም እንደ ዘበት መጽሐፉን ለሚገልጥ እና እዚያ ገጽ ላይ ዐይኑ ለሚያርፍ ሰው እንደ መዝገበ-ቃላት ሊያነበው የሚችል ከመሆኑም ባሻገር ሁሉም የግርጌ ማስታወሻዎች አንድ ላይ መቀመጣቸው የመጽሐፉን ዳሰሳ ለሚሠሩ ሰዎችም ቀላል ትብብር ይሆናል። ይሄም ተርጓሚው ከሠራው ውለታ እንደ አንዱ ሊታይ ይችላል።
የመጽሐፉን ይዘት በተመለከተ ደራሲው ያስቀመጣቸው ትንታኔዎችና ትንበያዎች ከእንደኛ ዓይነት በሃይማኖት ዶግማዎችና በባህል ሕጎች መካከል ተጠፍሮ በሚኖር ማኅበረሰብ ተቀባይነትን ለማግኘት ትንሽ የሚፈትኑ ቢሆኑም፣ የደራሲው አመንክዮ ከተርጓሚው የማስረዳት አቅም ጋር ተጣምረው ለቴክኖሎጂና ለአዳዲስ ነገሮች ግኝት ማንገራገር የለመድነውን እኛን በጥሩ ሁኔታ ልንቀበላቸው የምንችላቸው ሆነውልናል።
በተጨማሪም መጽሐፉ ላይ እንደ ጣዕመን፣ ነዋዔ-ልቦና፣ ልቡሰ-ልቦና፣ አስራቤቴዎች ወዘተ ያሉ ከሌሎች መጽሐፍት በተውሶ የመጡና የትርጉም ደረጃውን ከፍ የሚያደርጉ ቃላትን ተርጓሚው የተጠቀመ ሲሆን፤ የተርጓሚው ፍጡር ቃላት የሆኑ ሌሎች አዳዲስ ቃላትንም እናገኛለን። ከእነዚህም መካከል የእንሰሳትን ራስ-አወቅነት ወይንም ነቃዔ-ልቦና እንዲወክል የገባውና Animal Consciousness የሚለውን የእንግሊዘኛ ቃል የተካው ‘እኜ’፣ ለAlgorithm የተጠቀመው ‘ስልተ-ቀመር’ የሚል ፍቺ፣ Numerologyን ፍካሬ-አኀዝ በማለት እና ለPermutation  የተሰጠው ‘ስዳሬ’ የተባሉት የትርጉም ቃላት ይገኙበታል። ይህ የአዳዲስ ቃላት ፈጠራ በአንድ ስነ-ጽሑፍ ውስጥም  ሆነ ስነ-ጽሑፉ ለቀረበበት ቋንቋ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል።
የመጽሐፉ ይዘት
መጽሐፉ በሦስት ክፍሎች የተከፋፈሉ ዐሥራ አንድ ምዕራፎች አሉት። መግቢያና ዋቢ መጽሐፍቱን ጨምሮ 420 ያህል ገጾች ያሉት ሲሆን፤ ከመጀመሪያው ምዕራፍ ጀምሮ የታሪክ ፍሰቱን የጠበቀና አንዱ ምዕራፍ ለሌላኛው ባዳ ያልሆነበት ቆንጆ የአተራረክ ፍሰት ያለው ነው።
ሦስቱ ክፍሎች በጨረፍታ፡
ክፍል አንድ፤ አዲሱ የሰው ልጅ አጀንዳ በሚል ርዕስ ከቀረበ መንደርደሪያ ምዕራፍ የሚከተል ሲሆን፤ የሰው ልጆች እስከ አሁን ድረስ ስለገጠሟቸውና ዋነኛ አጀንዳዎቻቸው ስለነበሩት ረኀብ፣ ወረርሽኝና ጦርነት ያነሳል። እነዚህ የሰው ልጆች ችግር የነበሩ አጀንዳዎች መፍትሔ የሚያገኙበት ቀን ሩቅ አለመሆኑንም በማሳየት፣ ቀጥሎ የሚመጣው የተሻሻለው ሰው ሆሞ ዴዩስ (አምላክ መሰል ሰው) የተባለው ዝርያም ትልልቅ አጀንዳዎቹን ወደ ህያውነት፣ ፍሰሃና መለኮታዊነት እንደሚያዞር ያትታል። በተጨማሪም የሰው ዘር ከሌሎች እንስሳት ጋር ስለነበረው መስተጋብር ይነሳበታል።
በሁለተኛው የመጽሐፉ ክፍል፤ ሰዎችን ከሌሎች እንስሳት ልዩ ስለሚያደርጋቸው መሠረታዊ ባህርያት በሠፊው ይወሳል። በተለይ ሰዎች የጋራ ምናባዊ ተረክን በመፍጠር እንደ ገንዘብ፣ ሀገር፣ ኩባንያዎችና መንግሥታት ያሉ አካላትን ፈጥረው መተባበር መቻላቸው፣ ለሰው ልጅ ኃያልነት የነበረውን ሚና በሠፊው ያብራራል።
ክፍል ሦስት፤ ሆሞ ሴፒየንስ ጊዜው እያለፈበት የመጣ ዝርያ መሆኑንና ለሰው ልጆች ጣዕመን (Experiance) ትልቅ ስፍራን የሚሰጠው የሊበራል እምነት ወድቆ በአዲስ እምነት እንደሚተካ ይነግረናል። ሰዎች ራሳቸውን ከሚያውቁት በበለጠ ሰዎችን የሚያውቁ አዳዲስ ስልተ-ቀመሮች (Algorithms) እንደሚመጡና ሆሞ ሴፒየንስ (ብልሁ ሰው) ወደ ሆሞ ዴዩስ (አምላክን የመሰለው ሰው) ማደጉ አይቀሬ ክስተት ነው፤ በማለት ሳይንሳዊ ትንበያውን ያስቀምጣል።
ዳግም ይህ የትርጉም ሥራው የመጀመሪያው ቢሆንም፣ ከዚህ ቀደም ከለመድናቸው የትርጉም ሥራዎች በተለየ በሚገባ አስቦበትና ተጠንቅቆ በኃላፊነት የሠራው በመሆኑ፣ ለአንባቢያን ብቻም ሳይሆን በትርጉም ሥራ ዘርፍ ለተሰማሩ ሰዎች ጥሩ ትምህርት የሚሰጥ ይመስለኛል።


Read 670 times