Sunday, 06 September 2020 00:00

የአመቱ የአለማችን አገራት የኢንተርኔት ፍጥነት ደረጃ ይፋ ተደረገ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ሊቸትንስቲን በሰከንድ 229.98 ሜጋ ባይት 1ኛ፣ ደ/ ሱዳን በሰከንድ 0.58 ሜጋ ባይት መጨረሻ ሆነዋል

            ከአለማችን አገራት በብሮድባንድ ኢንተርኔት ፍጥነት ሊቸትንስቲን በ1ኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ፣ ደቡብ ሱዳን በአንጻሩ የመጨረሻውን ደረጃ መያዟን፣ ኬብል የተባለው የእንግሊዝ ተቋም ከሰሞኑ ባወጣው የአመቱ የአገራት የብሮድባንድ ኢንተርኔት ፍጥነት ደረጃ ሪፖርት አስታውቋል፡፡
ተቋሙ በአለማችን 221 አገራት ላይ የሰራውን ጥናት መሰረት አድርጎ ባወጣው የ2020 የፈረንጆች አመት የአገራት የብሮድባንድ ኢንተርኔት ደረጃ ሪፖርት እንዳለው፣ ሊቸትንስቲን ከአለማችን አገራት በአንደኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው በሰከንድ 229.98 ሜጋ ባይት ፍጥነት  ሲሆን፣ ደቡብ ሱዳንን ውራ ያስወጣት ደግሞ በሰከንድ 0.58 ሜጋ ባይት አዝጋሚ ፍጥነቷ ነው፡፡ ጀርሲ በ218.37፣ አንዶሪያ በ213.41፣ ጂብራልታር በ183.09፣ ሉግዘምበርግ በ118.05 ሜጋ ባይት በሰከንድ የብሮድባንድ ኢንተርኔት ፍጥነት እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ የያዙ የአለማችን አገራት መሆናቸውም ተነግሯል፡፡
በኢንተርኔት ፍጥነት አነስተኛነት ከደቡብ ሱዳን በመቀጠል እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ የያዙት አገራት የመን፣ ቱርኬሚኒስታን፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ እና ሶርያ መሆናቸውንና ኢትዮጵያ በ1.12 ሜጋ ባይት በሰከንድ ፍጥነት ከ221 የአለማችን አገራት በ214ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝም ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
የ2020 የፈረንጆች አመት አለማቀፍ አማካይ የብሮድባንድ ኢንተርኔት ፍጥነት በሰከንድ 24.83 ሜጋ ባይት መድረሱን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ጥናቱ ከተሰራባቸው 48 የአፍሪካ አገራት መካከል 45ቱ አነስተኛ ፍጥነት ካላቸው የአለማችን አገራት ተርታ እንደሚሰለፉም አመልክቷል፡፡

Read 2863 times