Wednesday, 02 September 2020 00:00

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ወደ ኋላ ወይስ ወደፊት?
                                 (ሙሼ ሰሙ)

           ትናንትን በሚመለከት ሁላችንም በደመቀ እልልታ የምንቀበለው አንድ ዓይነት ሀቅ እንደሌለን አምናለሁ። ሀገራችን የሁላችንንም ገመና በእኩልነት፣ በአንድነትና በሚዛናዊነት መሸፈን አልቻለችም።
ለውጤቱ ደግሞ፣ የፍላጎት ሳይሆን የሁሉም ዓይነት አቅም መጉደል ያመዝንብኛል። በኢትዮጵያ ታሪክ በአንድ ወቅት ላይ አንዱን ያልገፋና በሌላ ጊዜ ደግሞ ያልተገፋ የለም። እንደ ብዝሀነታችን ሁላችንም ገፊም፣ ተገፊም አስገፊም ስለነበርን፣ ለዚህ የገመና መጋለጥ (ድህነት፣ እርዛት ጥማት፣ ቸነፈር፣ ድንቁርና ወዘተ...) መጠነ ሰፊ አስተዋጽኦ በጋራም በተናጥልም አበርክተናል።
“ትናንት” በራሱ ነባራዊ ሁኔታ ላይ ተመስርቶ ለአንዳንዱ አኩሪ ትዝታውን፣ ለሌላው ጠባሳውን፣ ለአንዱ መዋቅራዊ ፈተናውን፣ ለሌላው ኢኮኖሚያዊ ጥገኝነትን፣ ለአንዱ የሀገር ባለቤትነት፣ ለሌላው ተለጣፊነትን፣ ለአንዱ ከነዘር ማንዘሩ መደምሰስን፣ ለሌላው መዋጥ መሰልቀጥን፣ ለሁላችንም ደግሞ ከእነ ጎዶሎዋም ብትሆን አንድ ሀገርን አውርሶን አልፏል። ዛሬ እዚህ እውነታ ላይ እንገኛለን። ጥያቄዬ ጉዟችን ወዴት ይሆን ነው? ወደ ኋላ ወይስ ወደፊት? ወደ ኋላ ከሆነስ ለስንት ዓመት? ወደፊት ከሆነስ በየእለት፣ እግር በእግር ወይስ አንድ እርምጃ ወደፊት፣ ሁለት እርምጃ ወደ ኋላ? የሁላችንንም መልስ ይጠይቃል?
የትናንትን ታሪክ ከመማሪያነቱና ኢ-ፍትሃዊነትን ለማረም መንደርደርያ ከመሆን ባለፈ ተጋኖ፣ ተንዛዝቶ፣ ተለጥጦና የዘር ግንድ እየተቆጠረ ሲተረክ፤ በሂደት ወደ ሂሳብ ማወራረድ መዝቀጡ አይቀርም። የታሪክ ሂሳብን ማወራረድ ማለት ደግሞ ሌላ ትርጉም የለውም፤ ዛሬን ትናንት ለማድረግ መፍጨርጨር ማለት ነው። መጀመርያም ሆነ መጨረሻ የሌለው የቁልቁለት ጉዞ! በዚህ ጉዳይ ዓለም ላይ የናኙ የዘር ጥፋቶችን መቃኘት ስንቅ ይሆናል!
የሰው ልጅን ሕይወት ለመለወጥም ሆነ ለማሻሻል ከትናንት ይልቅ ዛሬ ትልቅ ዋጋም ሆነ ሰፊ እድል አለው። ትናንትን በትናንት ነባራዊ ሁኔታና ማዕቀፍ ውስጥ እየመዘንን፣ ዛሬን ግን ለለውጥ ለእድገት ለመሻሻል መጠቀም አስተዋይነት ነው። ብዙ ወደ ኋላ ከማለም፣ ጥቂትም ቢሆን ወደፊት ማለም ያዋጣል።
“ወደ ኋላ እየሄድሽ በሃሳብ ከማለም”
ቀኑ እንዳይመሽብሽ ትናንት ዛሬ አይደለም”
--ብሏል ዕውቁ አቀንቃኝ ሙሉቀን መለሰ።



Read 2644 times Last modified on Tuesday, 01 September 2020 11:14