Tuesday, 01 September 2020 10:55

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

እንዴት ነህ ህዝቤ? ዘውድአለም ታደሠ

           (አማን መዝሙር)
እንዴት ውለሃል አንተ ስመ ብዙ ህዝብ? ሐገር አማን ነው ወይ? እንደው አንተን ህዝብ ዝም ብዬ የጎሪጥ ስሾፍህኮ እያናደድክ ታሳዝነኛለህ፤ የምር! ደሞ የስምህ ብዛት ... ከሃምሳ ምናምን አመት በፊት ጃንሆይ ያቺን የባቄላ ፍሬ የምታህል ውሻቸውን ፀጉር ዳበስ እያደረጉ «ኩሩው ህዝባችን» ብለው የጠሩህ .. ደርግ መጥቶ ኩሩው የሚለውን ስም ላሽ ብሎ «ጭቁኑ» እያለ የሰየመህ!
በመራራ ትግል ደርግን ጥሎ የመጣው መንግስት ደግሞ ምስኪኑ .. ሰላም ወዳዱ ... ልማታዊው ምናምን እያለ የወል ስም የሰጠህ ... አንዳንዱ ደግሞ እንደ ሰንበቴ ድፎ እየቆራረሰህ ትምክህተኛ፣ ጠባብ፣ ዘረኛ፣ እያለ እንደ ክርስትና ልጁ ስም ሲያወጣልህ አሜን ብለህ የኖርክ፣ ወሰድ ሲያደርግህ ደግሞ ባወጡልህ ስም እየተጠራራህ ስትቧቀስ የከረምክ! ጥሪትህ ትንሽ ስምህ ብዙ የሆንክ፤ እንደ ኬኔዲ መንገሻ ድምፅ አንጀት የምትበላ ህዝብ! ኑሮ ካሉት መቃብር ይሞቃል የሚል ተረት እየተረትክ፣ ስትፅናና የመቃብር ስፍራ 40 ሺ ብር ገብቶብህ ግራ የገባህ! ትከሻህ እንደ ሴቶች ቦርሳ ሁሉን የሚሸከም፤ የችግር ቤተ-ሙከራ የሆንክ ህዝብ እንዴት ነህ?
ለዘመናት ረሀብና ችጋር መሃል ባልገባ እየተጫወተብህ «ጎተራው ሙሉ፣ ሐገሩ ጥጋብ» ምናምን በሚል ዘፈን ወገብህ እስኪሰበር እስክስታ የምትወርድ፣ ውሃ እንደ ሌባ በሌሊት መጣች አልመጣች ብለህ ተሰልፈህ እየቀዳህ «እምዬ ሐገሬ ፏፏቴሽ ማማሩ» በሚል ዘፈን የምትቦርቅ፣ ጎንህን የምታሳርፍበት ሃሳብ መስጫ ሳጥን የምታህል ጎጆ ተነፍጎህ «ጋራው ሸንተረሩ» ምናምን እያልክ ራስህ ላይ ሙድ የምትይዝ .. የአለም ቀበሌ “የደሃ ደሃ” የሚል መታወቂያ የሰጣት ሐገር ላይ እየኖርክ፣ ዘፈን ላይ ያለችውን ጥጋብ በጥጋብ የሆነች ሐገር የሙጥኝ ብለህ ግራ ተጋብተህ አለምን ግራ የምታጋባ፣ ዘጠኝ የኔታ የማይፈታህ ቅኔ የሆንክ ፍጡር!
ሐገር ውስጥ አቧራና ትቢያ አማሮህ በሊቢያ አቆራርጠህ፣ ባህር ማዶ ከተሻገርክ በኋላ «የኩበቱ ሽታ ናፈቀኝ» እያልክ የምታለቃቅስ ፕሮፌሽናል አዝግ ህዝብ! የተሾመ ሁሉ ቫንዳም ቫንዳም ሲጫወትብህ፣ የእድር ዳኛ እንኳ ባቅሙ አናትህ ላይ ሱቅ ካልከፈትኩ እያለ ሲያማርርህ፣ ሐገርህ ላይ ሶስት ምስክር ጠርተህ ካገኘኸው የቀበሌ መታወቂያ ውጪ ቤሳ ቤስቲ አጥተህ እንዳልኖርክ ሁሉ፤ ሰው ሐገር ሄደህ እህል በልተህ ነፍስህ መለስ ስትል «ምን አለኝ ሐገሬ?» እያልክ ነጠላ ዜማህን የምትለቅ አላጋጭ ፍጥረት!
ዋሽተህ አጣልተህ ዋሽተህ የምታስታርቅ፣ እንደገና ዋሽተህ የምታጣላ ስራ ፈት፣ እንቦጭን በሚያስንቅ የመራባት ጥበብህ መቶ ሚሊዮን የዘለልክ! የምትበላው ሳይኖርህ የሚበሉ ልጆች ፈልፍለህ የምታሳድግ ታምረኛ ዜጋ! ምን የመሰለ የፍቅር ዘፈን ላይ ጦርና ጎራዴ ይዘህ የምትሸልል ጀብደኛ ማህበረሰብ! ብዙ ሰው ከፈወሰው አክሊሉ ለማ ይልቅ ብዙ ሰው የገደለን ሽፍታ የምታወድስ! «ገዳይ ገዳይ ያልሽው አባትሽ አይገድል፣ አርሶ ያብላሽ እንጂ ሆድሽ እንዳይጎድል» እያልክ ከገበሬ ይልቅ ነፍሰ ገዳይነትን ሙያ አድርገህ በረሃብ የምታልቅ ምስኪን ማህበረሰብ!
አያትህ ድንጋይን እንደ ዝግባ ዛፍ ጠርቦ፣ የኪነ-ህንፃ ህግን በመሻር ከላይ ወደ ታች ቤተ መቅደስ ቀለሰ፣ አለት እንደ ቢላዋ ሞርዶ ጡብ እንደ እርሳስ ቀርፆ ስልጣኔውን በአንድ ሃውልት ላይ አተመ፣ ከቅጠላ ቅጠል ውብ ቀለማትን ጨምቆ ፍልስፍናውን በብራና ላይ አኖረ! አንተ ድንጋይ ስታይ ወደ ጭንቅላትህ የሚመጣው ግዙፍ ቤተ መቅደስ መቀለስ ሳይሆን እንደ ቃየን ወንድምህን መፈንከት ነው! አዎ አባትህ ንፋስ ስልክ ቀለም ፋብሪካ ከመፈጠሩ ከሺህ አመታት በፊት ከዛፍ ቅጠል ውብ ቀለማትን ፈጥሯል! አንተ ልጄ በለጬ ወይም ገለምሶ ካልሆነ ወደ ቅጠል ፊትህን አታዞርም! ላንተ ቅጠል ሁሉ የሚከፈለው በሁለት ነው ... የሚቃምና የማይቃም! አያቶችህ ከሺህ አመታቶች በፊት “ገዳ” የሚባል ድንቅ ስርአት ዘርግተው አለምን አስደመሙ! ከአለም ቀድመው ዘመኑ፣ ከአለም ቀድመው የሞራል ልእልናቸውን አስመሰከሩ! አለምን አስተማሩ! አለም “Adoption”ን ከማወቋ በፊት አያቶችህ “ጉዲፈቻ” ብለው ጀምረውታል! አሜሪካ asylum መስጠት ከመጀመሯ በፊት አያቶችህ “ሞጋሳ” ብለው በቀለምና በባህል ለማይመስላቸው ስደተኛ መኖሪያ ስፍራና ዜግነት ይሰጡ ነበር! አንተ ዘንድሮም ስለ ሰው ልጆች አልገባህም፣ ሁለት የህዝብ ሽንት ቤትና አንድ ቦኖ ውሃ ካላት ቀበሌዬ ውጡ እያልክ ወገኖችህን ታሳድዳለህ! አያቶችህ ግን በገዳ ህግ ውስጥ ከሺህ አመታት በፊት ስለ እንስሳት መብትና አያያዝ አርቅቀው ነበር!
አያቶችህ ፊደል ቀርፀው እውቀትና ጥበባቸውን በራሳቸው ቋንቋ ውስጥ ሸሸጉ፤ ግእዝ ፣ እዝል ፣ አራራይ ብለው የራሳቸውን ዜማ ቀመሩ፣ ሰባቴ በወደቁ ጊዜ ከትሏ መነሳትን ተማሩ! ጥጥ አቅጥነው የራሳቸውን አልባሳት ፈበረኩ፣ ሸንበቆ ቦርቡረው ዋሽንት ሰሩ፣ ጅማት ወጥረው መሰንቆ ፈለሰፉ፣ ቆዳ ፍቀው ከበሮ ወጠሩ፣ አያቶችህ በራሳቸው ፍቅር የወደቁ፣ ማንንም የማይኮርጁ፣ ማንንም የማይመስሉ ነበሩ! ቋንቋቸው ፣ ህጋቸው፣ አልባሳቸው፣ የሙዚቃ መሳሪያቸው፣ ዜማቸው ... ሁሉ ማንንም አይመስልም ነበር! አያቶችህ የሰውን የፈጠራ ውጤት እንደ መና ተቀምጠው የሚጠባበቁ አልነበሩም! ራሳቸው ፈጣሪዎች ነበሩ! ፈላስፋና ልሂቃን ነበሩ!
አንተስ? በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን “ከተፀዳዳህ በኋላ እጅህን ታጠብ” ተብለህ የምትመከር፣ ከኢኳቶሪያል ጊኒ ቀጥሎ በመሀይምነት አንደኛ ወጥተህ (ጊኒን ግን እንዴት በለጥካት?) ፤ፖለቲካን ከፖለቲካ ልሂቃኑ በላይ ተዘፍዝፈህ የምትተነትን ደፋር! ጀነን ብለህ አደባባይ መሃል የመንግስት ስልክ እንጨት በሽንትህ የምታጠጣ “ሐገር ወዳድ” ህዝብ! «ጫልቱ»ን የመሰለ ውብ ስም ስድብ መስሎህ ልታንጓጥጥ የምትሞክር፣ የኢትዮጵያ ፓስፖርት ይዘህ “ዳውን ዳውን ኢትዮጵያ!” ስትል የምትውል፣ «ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ» ስትል እየዋልክ ሱርማውን፣ ከፊቾውን፣ ሽናሻውን፣ መዠንገሩን፣ ከእነ መፈጠራቸው የማታውቅ፣ አንድ ደሃ በቆንጨራ ገድለህ ብሔርህን ነፃ ያወጣህ የሚመስልህ፣ ባጭሩ ብሔርተኝነቱንም፣ አሃዳዊነቱንም በቅጡ ሳትችልበት ቀርተህ፣ የአለም መዝናኛ ሆነህ የቀረህ ድፍን መንጋ!
ኑሮ እንዴት ይዞሃል? ረሃብና ድህነት እንዴት እያደረገህ ነው? አሁንም ፀጉርህን በተልባ ፈርዘህ ቺክ ትጀነጅናለህ ወይ? አሁንም የነጋዴ በግ ቀምተህ ሆድህን ትሞላለህ ወይ? አሁንም ሽማግሌን በጠረባ እየጣልክ ቫንዳም ቫንዳም ትጫወታለህ ወይ? አሁንም ዋሊያ ቢራ ጠጥተህ ቆርኪውን ትፍቃለህ ወይ? አሁንም “እኔ ነኝ ያለ” በሚል ዘፈን ልብህ ተነፍቶ፣ በባዶ ሜዳ ትወራጫለህ ወይ? አሁንም ሰው ለፍቶ የገዛውን ቦቴ መኪናና ግሮሰሪ እያቃጠልክ ሰልፊ ትነሳለህ ወይ? አሁንም ኳስ ሜዳ መሀል ምስኪን ዳኛ ደብድበህ፣ በኩራት ትንጎራደዳለህ ወይ? ደህና ነህ ወይ? አማን ነህ ወይ?

Read 1537 times Last modified on Thursday, 03 September 2020 16:29