Saturday, 21 July 2012 11:44

ሀኪሞችን ያቃለሉት የፊልም ባለሙያዎቻችን

Written by  ሱራፌል መካሻ (አዳማ ዩኒቨርሲቲ)
Rate this item
(0 votes)

የፊልሞቻችን በቁጥርና በጥራት እየበዙና እያደጉ መምጣት ይበል የሚያሰኝ ነው:: በዚህ ፅሁፍ  የምናነሳቸው አንዳንድ ስህተቶች ከተስተካከሉ ደግም የበለጠ እየተሻሻሉና እየላቁ እንደሚመጡ እምነቴ ነው:: ሰሞነኞቹም ሆነ ቀደምቶቹ ፊልሞችና ድራማዎች ላይ የህክምና ጽንሰ-ሀሳብና የሃኪሞች ገጸባህርያትን በተደጋጋሚ ተመልክቻለሁ:: የእነዚህ ገጸባህርያት መግባት ፋይዳው እምብዛም የሆነብኝ ግን በአንድና ሁለቱ ፊልሞች ላይ አይደለም:: በአብዛኛዎቹ ላይ ያየሁት ችግር ታዲያ የህክምናን ስነምግባር ፣ የሃኪሞችን የአኗኗር ዘይቤ እንዲሁም ከሌሎች የማህበረሰባችን ክፍሎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ሳያውቁና በደንብ ሳይረዱት የሃኪሞችን ገጸ ባህርያት ለመሳል መሞከር ላይ ነው::

እስኪ ትንሽ ወደ ኋላ መለስ ልበልና ከአመታት በፊት የወጣ አንድ ፊልምን ላስቃኛችሁ:: የሀኪሙ ገጸባህርይ ሲሳል ክፉ ተደርጎ ነው:: ክፉ! ለህመምተኞች የእንቅልፍ ኪኒን ፣ ማደንዘዣ ይሰጣል:: ህጻን ወጣት፣ አሮጊት ሳይል ሴት የተባለችውን ፍጥረት ሁሉ ይደፍራል:: ርህራሄ የሚባል ነገር ያልፈጠረበት አረመኔ፣ የዲያብሎስ ታናሽ ወንድም ነው:: ከኢትዮጵያዊ ጨዋ ባህላችን የወጣ የኢትዮጵያዊ ሃኪም ገጸባህርይ!   ሌላ አንድ ፊልምም ትዝ ይለኛል:: ኩላሊት ሻጩ ዶክተር፣ ኩላሊትን እንደ ስኳርና ምስር የሚቸረችር ! እንደ በሬ ስጋ የሚመትር! እንደ አፋር ጨው የሚቸበችብ! ሆኖ ነው የተሳለው::   በዚህ ፊልም ላይ በሌሎች የውጭ አገራት  እንጂ በአገራችን  ኢትዮጵያ  ያልተለመደውን ተግባር  ያውም በጣም ተጋንኖ  ቀርቧል:: በቅርቡ በቴሌቪዥናችን ያየነውስ ድራማ? ያለ ልጅቷ ፍቃድ በእናትየው ገፋፊነት ለገንዘብ ብሎ የሚያስወርድ መድሃኒት የሰጠውስ ሃኪም! እጅግ እጅግ የሚሰቀጥጥና ለህሊና  የሚከብድ ስራ የሰራ አይደለምን?

ህዝባችን ይሄን ካየ በኋላ ሃኪሞችን እንዴት አድርጎ የሚስላቸው ይመስላችኋል? ክፉ፣ አረመኔ፣ ጨካኝ፣ ለሰው የማያስቡ፣ ለገንዘብ ሲባል ማንኛውንም ነገር የሚፈጽሙ አውሬዎች! እውነታው ግን ሃኪሞቻችን ከሌሎች የህብረተሰባችን ክፍሎች የሚለያቸው ብቸኛው ነገር  ህክምና መማራቸው ብቻ ነው :: እነሱም ውስጥ ኢትዮጵያዊነት በክብር ተቀምጧል:: እነሱም ውስጥ ፈሪሃ እግዚአብሔር ይገኛል:: እነሱም ውስጥ ኢትዮጵያዊ ምግባራት ቦታ አላቸው:: በህክምና ትምህርት ውስጥ ደግሞ ርህራሄን የሚያጠፋ፣ ጨዋነትን የሚያጎድል፣ ፍቅርና መተሳሰብን የሚያርቅ አንድም ኮርስ አይሰጥም:: አንድም! የህክምናው ስነምግባርም ሆነ የሒፖክራተስ ቃለመሃላ (Hippocratus Oath) ለሰው ልጆች ጥቅምና ጤንነት እስከ መጨረሻው ድረስ መቆምን እንጂ ለገንዘብ ሲሉ ኩላሊት መቸብቸብንም ሆነ ውርጃ ማካሄድን አይደግፉትም::  ሀኪሞች እኮ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የሚገኙ ድልድዮች ናቸው::   የሰዎች መዳን የሚያስደስታቸው፣ የሰዎች ስቃይ የሚያሰቃያቸው፣ የሰዎች ህመም የሚያማቸው ሰዎች ናቸው:: ይህን ስል ግን ከስነ ምግባሩ የወጡ ሀኪሞች የሉም ማለቴ አይደለም:: በስንዴ መሃል እንክርዳድ፣ በጥሩ ዘር መሃል አረም እንደማይጠፋ ሁሉ  በሃኪሞችም መሃል መጥፎ  ስራ የሚሰሩ ሀኪሞች ይኖራሉ:: ግን ሁላችንም እንደምናውቀው ስንዴው  ከእንክርዳዱ፣ዘሩም ከአረሙ በቁጥር እጅጉን ይልቃል:: በትንሽ እንክርዳድ ምክንያት ሙሉ ስንዴውን፣ በትንሽ አረም ምክንያት ሙሉ ዘሩን መጣል የለብንም:: ጥፋቱም የሙያው አይደለምና እንደዚህ ተጋንኖ መቅረብ የለበትም::

ሌላው የፊልሞቻችን ስህተት ሃኪሞች ከሌላው የህብረተሰብ ክፍል ጋር ስላላቸው ግንኙነት አለመገንዘባቸው ነው:: በተለይ በተለይ ጾታዊ ግንኙነትን በተመለከተ የሚቀርጿቸው ገጸባህርያት፣  ፍጹም የተዛቡና  ከእውነታው የራቁ ሆነው  እናገኛቸዋለን:: ለምሳሌ አንድ ቀን እኔና ጓደኞቼ ስላየነው ፊልም ልንገራችሁ:: ዶክተሩ የታመመ አባቷን ለማሳከም የምትመላለሰውን ኮረዳ ሲግባባትና ወዲያው ሲወዳት ይታያል:: ከስንት አንድ ጊዜ የሚያጋጥም ቢሆንም ይህን እንደ ስህተት ማየት አልፈልግም::

ዋናው ችግር ያለው ዶክተሩ ለእሷ ያለውን ፍቅር የሚገልጽበት  የፍቅር ቋንቋ  ላይ ነው:: ድርሰቶች የነባራዊው ዓለም ነጸብራቆች ናቸው የሚባለው መሰረታዊ ሃሳብ እዚህ ጋር ተስቶዋል::  በተለይም መጨረሻ ላይ ፍቅሩን ስትቀበለው (እሺ ስትለው) ደስታውን የገለጸበት መንገድ እኔና ጓደኞቼን አሳፍሮናል:: ሃፍረተ ስጋውን  ሳይሸፍን በደስታ ሰክሮ ሲደንስ የቤት ሰራተኛው በትዝብት ስትመለከተው ይታያል::

እነዚህ አስተሳሰቦች የሚመነጩት ስለ ሙያውና ስለ ትምህርቱ ካለው የግንዛቤ ማነስ ይመስለኛል:: የህክምና  ትምህርት ክብደትና የሙያው በተፈጥሮው አጨናናቂ መሆን  ሃኪሞችን ከሰዎች የተለየ አኗኗር እንዲኖራቸው አድርጓቸዋል ይላሉ ፊልሞቹ:: በእርግጥ የህክምና ትምህርት አሁን በመጀመሪያ ዲግሪ ከሚሰጡ ትምህርቶች ብዙ አመታትን በመውሰድ የመጀመሪያውን ቦታ ይይዛል:: በሁለተኛም ዲግሪ ቢሆን በዛ ላሉ አመታት መልፋትን ይጠይቃል::

ትምህርቱም በተፈጥሮው የብዙ ሰአት ጥናትና ንባብ ያስፈልገዋል:: በህክምና ት/ቤቶች ውስጥ ላይብረሪዎች ስቴዲየም ይመስል ብዙ ጊዜ ሞልተው የሚታዩት በዚህ ምክንያት ነው:: በአንጻሩ ደግሞ ከሰዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት ለመፍጠር የሚሆን በቂ ጊዜ እንዳለ አምናለሁ:: ፍቅረኛ መያዝ፣ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ግንኙነት መፍጠር፣ ከጓደኞች ጋር መዝናናትና መሰል ጉዳዮች ላይ ከሌሎች ሰዎችና ቦታዎች የተለየ አኳኋን (pattern) የለውም:: ከምረቃም በኋላ ቢሆን ተመሳሳይ ኑሮ ይቀጥላል:: ከሌሎች ሰዎች ያልተለየ:: ከደራሲዎች፣ ከዳይሬክተሮችና ከተዋንያን ያልተለየ....እነዚህ ሰዎች ያልገባቸው ይሄ ነውና!

አሁን በቴሌቪዥን ከሚተላለፉት ድራማዎች በአንዱ ላይ ያየሁትም ነገር አሳዝኖኛል:: ልጅቷ በጭንቀትና ድብርት እንደምትሰቃይ ያስታውቃል:: በቤተሰቦቿ ጉትጎታ ምክንያት ሳይካትሪስት ለማማከር ትሄዳለች:: ወደ ቢሮው ከገባች በኋላ ግን ያደረገቻቸው ንግግሮች ጥሩ የሚባሉ አይመስለኝም::

ሳይካትሪስቱን (እንደውም ሁሉንም ሳይካትሪስቶች) ምንም አትችሉም ብላ ከመናገር አልፋ፣ በህክምናው ዘርፍ ታላቅ አስተዋጽኦ ያደረገውንና የብዙዎችን ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ ምስጢሮችን ግልጽ ያደረገው ሲግመንድ ፍሮይድ የተባለ ሳይንቲስት ላይ ከመዝለፍ የማይተናነስ ወቀሳ ስታቀርብ ይታያል:: እንደ እውነቱ ከሆነ አንድ ሀኪምና አንድ በሽተኛ የሚያገናኛቸው ብቸኛ ጉዳይ የበሽተኛው ህመም ነው:: ሀኪሙ ለአመታት የተማረውን ትምህርትና የቀሰመውን እውቀት ተጠቅሞ የህመምተኛውን በሽታ ለማከም ይጥራል:: በተቻለው አቅም ችግሮቹን ለመፍታት ይሞክራል:: እናም ምንም ላላጠፋና እርዳታን ለመስጠት ለቆመ  ሀኪም ከስድብ የማይተናነሱ ቃላትን መወርወር ተገቢ አይመስለኝም - ፊልምም ቢሆን::     በፊልሞቻችን ውስጥ የሚታዩት ስህተቶች በዚህ ብቻ አያበቁም:: ከበሽታዎች ስም አጠራር ስህተት ጀምሮ (ለምሳሌ ሊውኬሚያ (Leukemia) የሚባለውን በሽታ ሉኬምኒያ ከማለት) እስከ የህክምና ስርአት አካሄዶች ስህተት (ለምሳሌ ጸጉርን ሳይላጩ የጭንቅላት ላይ ቁስልን ማሸግ) ለመመልከት ችያለሁ:: ሁሉን ቢያወሩት ሆድ ባዶ ይቀራልና ለምልከታ ይሆን ዘንድ በእነኚህ ላብቃ ::

በተለያዩ ሙያዎች ዘንድ መደጋገፍና መተባበር ይገባል ብዬ አምናለሁ:: አንዱ ያለ አንዱ ቢቆም የሸንበቆን ያህል ጥንካሬ አይኖራቸውም:: ኢትዮጵያዊያን ተባብሮ የመብላት ባህላችን በስራ በመከባበርና በመደጋገፍ ላይም ቢተገበር ለሀገራችን በጎ ተስፋ  ይሆናታል:: የፊልሞቹም ደራስያንና ዳይሬክተሮች የሀኪሞቹን ገጸ ባህርያት ከመሳላቸው በፊት ስለ ሀኪሞች በቂ ጥናት ማድረግ አለባቸው ብዬ አስባለሁ::  ፊልሙ ሲሰራም አማካሪ ሀኪሞች አስገብቶ ስለ ሁኔታው አስተያየት እንዲሰጡበት ቢደረግ ተገቢ ይመስለኛል:: በህክምና ዩኒቨርስቲዎች አካባቢ ዞር ዞር ብሎም እዚያ አካባቢ ያለውን ህይወት ቃኘት ቃኘት ማደረግ ከአድሎአዊ (biased) አስተሳሰቦች ለመራቅ ይጠቅማል:: የፊልም ባለሙያዎቻችን እንደ “Gifted hands” አይነት የምርጥ ሀኪሞችን ታሪክ የሚያሳዩ ፊልሞችን ቢሰሩ አነቃቂ (Inspirational) ይመስሉኛል::

እንደ  “ER” እና  “Gray’s anatomy” የመሳሰሉ ተከታታይ ፊልሞችም ሀኪሞች ለሰው ልጆች ህይወት ያላቸውን አሳቢነት ያሳያሉ:: ኢትዮጵያውያን ሀኪሞች ያለምንም ክፍያ በቅርቡ የሰሩት ታላቅ ቀዶጥገና የሙያውን ታላቅነት ለማሳየት ብቻውን በቂ ነው:: በመጨረሻም የሀገራችን ፊልሞችም ከውጪ ፊልሞች ክብር ለሚገባው ክብር መስጠትን ቢማሩ እላለሁ::

=============================================

አሁን በቴሌቪዥን ከሚተላለፉት ድራማዎች በአንዱ ላይ ያየሁትም ነገር አሳዝኖኛል:: ልጅቷ በጭንቀትና ድብርት እንደምትሰቃይ ያስታውቃል:: በቤተሰቦቿ ጉትጎታ ምክንያት ሳይካትሪስት ለማማከር ትሄዳለች:: ወደ ቢሮው ከገባች በኋላ ግን ያደረገቻቸው ንግግሮች ጥሩ የሚባሉ አይመስለኝም:: ሳይካትሪስቱን (እንደውም ሁሉንም ሳይካትሪስቶች) ምንም አትችሉም ብላ ከመናገር አልፋ፣ በህክምናው ዘርፍ ታላቅ አስተዋጽኦ ያደረገውንና የብዙዎችን ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ ምስጢሮችን ግልጽ ያደረገው ሲግመንድ ፍሮይድ የተባለ ሳይንቲስት ላይ ከመዝለፍ የማይተናነስ ወቀሳ ስታቀርብ ይታያል::

 

 

Read 2768 times Last modified on Saturday, 21 July 2012 12:09