Sunday, 30 August 2020 00:00

ሴታዊነት፤ ለፖለቲካችን ጤናማነት ያለው ሚና

Written by  ደስታ መብራቱ
Rate this item
(1 Vote)

     ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተወደሱበት አበይት እርምጃዎች አንዱ በርካታ ሴት አመራሮችን ወደ መንግስታቸው ማምጣታቸውና በዘመናዊው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የመጀመርያዋን ሴት ርዕሰ ብሔር እንዲሾሙ ማድረጋቸው ነው። እንዲህ ዓይነቱ እርምጃ፣ የሃገራችን ሴቶች በሃገሪቱ የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ የሚኖራቸውን በጎ አስተዋጽኦ ለማበረታት ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው ይታመናል። ባለፉት ጥቂት አስርተ ዓመታት ሴቶችን በሚመለከት በህብረተሰቡ ውስጥ ያሉትን የተዛቡ አመለካከቶች በማጋለጥና በመታገል የሴቶችን ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማሳደግ የሚጥሩ ሃገር በቀል ተቋማት እየበረከቱ መምጣታቸውም አበረታች የለውጥ ምልክት ነው። እነኝህ እርምጃዎች፣ በተባበሩት መንግስታትና በአፍሪካ ሕብረት ከተወሰኑት የሴቶችን የእኩልነት መብት የማረጋገጥ ውሳኔዎች ጋር የተጣጣሙ ከመሆናቸውም ባሻገር ለሃገራዊው ፖለቲካ ጤናማነት ከፍተኛ ድርሻ ሊያበረክቱ ይችላሉ። ነገር ግን፣ እነኝህ በፖለቲካ ድርጅቶችም ሆነ መንግስታዊ ባልሆኑ የህዝብ ተቋማት የተጀመሩ ቀና እርምጃዎች ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ከተፈለገ ሴታዊነት (Feminism) ባንድ ምህዳር ውስጥ ያለውን ምሉዕ ድርሻ በመረዳት ላይ የተመረኮዙ ሊሆኑ ይገባቸዋል። ይህ ጽሁፍ  ሴታዊነት ከምህዳራዊ አስተሳሰብ አኳያ እንዴት ሊታይ እንደሚገባውና በኢትዮጵያ ሁኔታ ሊኖረን የሚገባውን አጠቃላይ አካሄድ ለማመላከት ይሞክራል።
በምህዳራዊ አስተሳሰብ መሰረት፣ የማንኛቸውም ማህበረሰብ አወቃቀር መሰረቱ ቤተሰብ ነው። ስለሆነም፣ ከሴታዊነት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ባግባቡ ለመረዳት የቤተሰብ አመሰራረት ያለፈበትን ሂደት በጥቅሉ መመልከት ይጠቅማል። የቅድመ ታሪክ ቤተሰብ አመሰራረት በአብዛኛው ሴቶችን ማዕከል ባደረገ የእማዊነት(matriarchal) ሥርዓት ላይ የተመረኮዘ እንደነበር ይነገራል፡፡ ይህ ሁኔታ በሂደት እየተቀየረ መጥቶ ቀስ በቀስ ወንዶች ይበልጥ ወሳኝ ወደሆኑበት አባዊ (patriarchal) የቤተሰብ ሥርዓት ተሸጋግሯል። በዚህ ሽግግር ምክንያት የተፈጠረው የወንዶች የበላይነት በተለያዩ የኢኮኖሚ ሥርዓት እያደገ ከመጣው የግል ሃብት ክምችት ጋር ይበልጥ እየተጠናከረ ሊመጣ እንደቻለ ይታወቃል። የሰው ልጅ አደረጃጀት ከቤተሰብ ወደ ማህበረሰብ ከዚያም ወደ ሃገር እያደገ ሲመጣ፣ የወንዶችን የበላይነት የሚያጠናክረው የአባዊነት አመለካከትም ይበልጥ ተቋማዊ  መሰረት እየያዘ ሊመጣ ችሏል። በዚህም የተነሳ፣ በመላው ዓለም ባሉ ማህበረሰቦች ውስጥ ሴቶች ሊኖራቸው የሚገባውን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ስፍራ አሳጥቷቸዋል። ይህ በመሆኑም፣ በሴቶች ላይ ከደረሱ በርካታ የመብት ጥሰቶች ባሻገር ባጠቃላይ የሰው ልጆች ከሴቶች ቀጥተኛ ተሳታፊነት ሊያገኙ የሚችሉትን ጠቀሜታዎች እንዲያጡ አድርጎታል። ለዚህም አንዱ ማሳያው ከአባዊነቱ ዘመን እየተጠናከረ መምጣት ጋር ተያይዞ እየተበራከተ የመጣው ግጭትና ጦርነት፣ በዚህም የተነሳ የተፈጠሩት በርካታ ማህበራዊና አካባቢያዊ ቀውሶች ናቸው። የኢንዱስትሪ አብዮት መምጣትን ተከትሎ፣ ሃገሮች በይበልጥ ወደ ህገ መንግስታዊ ሥርዓት እየተሸጋገሩ ሲመጡ የሴቶች የመብት ጥያቈዎችም በልዩ ልዩ መልክ መገለጽና መነሳት ጀመሩ።                    
ዘመናዊውን የተደራጀ የሴቶች የመብት እንቅስቃሴ (Feminist movement) አነሳስን ስንመለከት፣ አሜሪካዊቷ የሴኔካ ፏፏቴ መግለጫ (Seneca Falls Declaration, 1848) አዘጋጅ ወይዘሮ ኤሊዛቤጥ ስታንተንና ጀርመናዊቷ ሶሻሊስታዊ የሴቶች መብት አቀንቃኝ ወይዘሮ ክላራ ዜትኪን (1857-1933) በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ። በአስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ አካባቢ የተጀመረው የአሜሪካው የሴቶች መብት እንቅስቃሴ በቀዳሚነት ያተኮረው የሃገሪቱ ሴቶች ተነፍገውት የነበረውን መሰረታዊ የመምረጥና የመመረጥ መብት ማስከበር ላይ ነበር። ይህ እንቅስቃሴ፣ ከሰባ ዓመታት ያላቋረጠ ትግል በኋላ ልክ የዛሬ መቶ ዓመት የአሜሪካ ሴቶች መሪዎቻቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ ለመምረጥ አስችሏቸዋል።  በአንጻሩ፣ ሶሻሊስታዊው የሴቶች መብት እንቅስቃሴ የአሜሪካውን የሴቶች መብት እንቅስቃሴ የጥቂት ከበርቴዎችና ንዑስ ከበርቴዎች ስልጣን የመካፈል ጥረት አድርጎ በመፈረጅ ትኩረቱን የብዙኃን ሴት ገበሬዎችና ሰራተኞች መብትን ማስከበር ላይ ያደርጋል። ምንም እንኳን ገና በርካታ ተግባራት የሚቀሩ ቢሆንም፣ የሁለቱም ዓለም የሴቶች እንቅስቃሴዎች፣ የሴቶችን የእኩልነት መብት በማረጋገጥ ረገድ ባለፈው አንድ ምዕተ ዓመት ለታዩ አበይት ለውጦች የየራሳቸውን ድርሻ እንዳበረከቱ ይታመናል። ሆኖም፣ አሜሪካንን ጨምሮ በበርካታ ምዕራባዊያን ሃገራት የሚገኙ ሴቶች በፖለቲካም ሆነ በንግዱ አለም ተጭኖባቸው ያለውን የስልጣን ጣራ (ceiling) ሰብሮ ለመውጣት ያለባቸውን ፈተና ለተመለከተ፣ ሶሻሊስታዊ ቅኝት ያላቸው ሃገሮች ሁሉን አቀፍ የሴቶች የእኩልነት መብት መከበርን በተመለከተ በተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ መረዳት ይቻላል። ለዚህም እንደ ማሳያ፣ በተለይ ስዊድንን በመሰሉ ስካንዲኔቪያን ሃገሮች ያለውን ሰፊ የሴቶች መብት ጥበቃና የአመራር ተሳትፎ መጥቀስ ይቻላል።
ወደ ሃገራችን ሁኔታ ስንመጣ፣ ሴት እህቶቻችንና እናቶቻችን እንደ የትኛውም የዓለማችን ማህበረሰብ በተመሳሳይ የአባዊነት ሥርዓት ለሚፈጠሩ የመብት ንፍገቶችና ጥሰቶች የተጋለጡ ነበሩ። ከዚህም በላይ፣ ከተለያዩ አካባቢያዊ ልማዶችና እምነቶች ጋር ለተያያዙ ተጨማሪ አድሎዎችና ጥቃቶች ሲጋለጡ ኖረዋል። ያም ሆኖ ግን፣ በሃገሪቱ የረዥም ዘመን ታሪክ ውስጥ እጅግ ከፍተኛ ድርሻ የነበራቸው ንግስቶችና እንስት የጦር መሪዎች እንደነበሩም ይታወቃል፡፡ ከዚህም ባሻገር፣ በሃገራችን ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ ከሚሰጣቸው ነገስታቶችና የማህበረሰብ መሪዎች በስተጀርባ ብርቱ ሴቶች እንደነበሩ የሚያመላክቱ መረጃዎችም አሉ። በዚህ ረገድ፣ በታሪክ ቀደምት ከሚባሉት በርካታ ሃገሮች በተሻለ የሃገራችን ሴቶች በሃገሪቱ የፖለቲካ ህይወት ውስጥ የራሳቸውን አሻራ እንዳሳረፉ መረዳት ተገቢ ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪ፣ በአንዳንድ ማህበረሰቦች ውስጥ አንዲት ሴት በትዳር ህይወቷ የሚያጋጥሟትን ጥቃቶች ሴቶች ተሰባስበው በጋራ ለመከላከል የሚያስችሏቸው ሥርዓቶች እንዳሏቸው ይነገራል። ከሁሉም የሚያስደንቀው፣ ቀደም ካሉ ዘመናት ጀምሮ ለሴቶች መብት በግንባር ቀደምትነት በመቆም በየዘመኑ ተንሰራፍተው የነበሩ ኢ-ፍትሃዊ አሰራሮችን ማስቀየር የቻሉ ቀደምት ኢትዮጵያዊ የሴቶች መብት አቀንቃኞች የነበሩ መሆናቸው ነው። ለዚህም እንደ ማሳያ፣ በ1870ዎቹ በጉራጌ ማህበረሰብ ውስጥ ተነስተው የነበሩትን የሴቶች መብት አቀንቃኝ ወይዘሮ ቃቈ ወርድወትን መጥቀስ ይቻላል።  ይህም የሚያሳየው፣ ባሁኑ ሰዓት ባንዳንድ ወገኖች ከምዕራባዊያን ሃገሮች እንደተኮረጀ ተደርጎ የሚነገርለት የሴቶች የመብት እንቅስቃሴ በሃገራችንም ቀደም ብሎ የተጀመረ እንደነበር ነው።
በምህዳራዊ አስተሳሰብ መሰረት፣ ሴታዊነት ለማንኛቸውም ተፈጥሮአዊና ማህበራዊ ምህዳር ቀጣይነት ዋነኛው መሰረት ነው። ይህም በአበይትነት ለሴቶች በተሰጣቸው የእናትነት ምግባር የሚገለጽ ሲሆን ሌሎችም መሰረታዊ የሆኑ እና ከወንዶች በበለጠ ለሴቶች የተሰጧቸው ባህርያት አሉ። ከነዚህም ውስጥ አንዱ፣ የሌላ ሰውን ችግር እንደ ራስ ሆኖ ለመረዳትና ለመካፈል (empathy) ያላቸው ዝግጁነት ከወንዶች የበለጠ መሆኑ ነው። ሌላው፣ ኑሮን ለማሸነፍ በሚደረገው ትግል ውስጥ ካላቸው ቁልፍ ድርሻ ጋር በተያያዘ ፈታኝ ሁኔታዎችን ለመሻገር ያላቸው የስሜት (survival instinct) ዝግጁነት ነው። ይህም ባብዛኛው፣ የራሳቸውን መንፈሳዊም ሆነ ቁሳዊ ፍላጎት በመጫንና አሳልፎ በመስጠትም ጭምር የሚገለጽ ይሆናል።  ሶስተኛው፣ ተፈጥሮአዊው ዑደትን ለማስቀጠል ካላቸው ልዩ ኃላፊነትና ድርሻ ጋር በተያያዘ ከተፈጥሮአዊው ምህዳር ጋር ያላቸው ቅርበትና ተዛማጅነት (ecological sensibility) ነው። አራተኛውና ምናልባትም በሰፊው ካለብን የፖለቲካ ህመም ለመፈወስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊኖረው የሚችለው ባህሪ፣ ኃይልን መሰረት ካዳረገ (hard power) አመራርና የግጭት አፈታት ይልቅ ስሜትን በማለስለስና በማሳመን (soft power) ላይ ለተመረኮዘ መፍትሄ ያላቸው ብልህነት ነው። እነኚህና የመሳሰሉት በርካታ የሴታዊነት ባህርያት እስከ ዛሬ ድረስ በነበሩ መንግስታዊ ሥርዐቶች ውስጥ በአግባቡ ባለመካተታቸው የተነሳ የሰው ልጆች ተነግረው ለማያልቁ ጥፋቶችና እልቂቶች ሊዳረጉ በቅተዋል። ይህንን ሁኔታ መቀየር፣ ባሁኑ ሰዓት ዓለማችን የተጋፈጠችውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ አካባቢያዊና ፖለቲካዊ ፈተናዎች በድል ለመሻገርም አቢይ ድርሻ እንደሚኖረው ይታመናል።
ወደ ኢትዮጵያ ሁኔታም ስንመጣ፣ የከበቡንን ዙሪያ መለስ ፈተናዎች ባግባቡ ለመወጣት የሴታዊነት ግብአትን በሁሉም መስኮች እያጠናከርን መሄድ ይኖርብናል። ይህንን በምናደርግበት ጊዜም፣ ጥረቶቻችንን የይምሰል ሊያስመስሉ ከሚችሉና ውጤታማነታቸውን ከሚያሳንሱ (sub-optimal) አስተሳሰቦች ራሳችንን ማጽዳት ይጠበቅብናል። ከዚህ ውስጥ የመጀመሪያው፣ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማጠናከር የምንወስዳቸው እርምጃዎች የየትኛውንም ውጫዊ አካል ቅቡልነት ለማግኘት ብለን ሳይሆን መሰረታዊ ከሆነው የሴታዊነት ባህርያት ልናገኛቸው የሚገቡንን ማህበራዊና ተፈጥሮአዊ እሴቶች ባግባቡ ለመጠቀም በማሰብ መሆኑን ማመን ነው። በዚህ ላይ በመመስረት፣ ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ የማጠናከሩ ተግባር የቁጥርን ኮታ ለማሟላት ከሚደረግ ጥረት ባሻገር አመራሩና አደረጃጀቱ ከሴታዊነት ባህርያት የሚመነጩትን ጠቃሚ እሴቶች እንደ ግብዓት ለመጠቀም የሚያስችል መሆን ይኖርበታል። ከሁሉም በላይ ግን፣ በማንኛውም መንገድ የአመራር ቦታ የሚይዙ እህቶቻችን ወንዳዊ ሃይለኝነትን (machismo) እንዲላበሱ የሚያስገድዱ ሁኔታዎችን መከላከልና በሴታዊነት ልዩ ባህሪያቸው ላይ በመመርኮዝ ሊያበረክቱ የሚችሉት አስተዋጽኦ ላይ ማተኮር ይኖርባቸዋል። ይህ ፈተና፣ በወንዳዊ አስተሳሰብ  ከተቃኘው ተቋማዊ ባህላችን አኳያ ሲታይ በእጅጉ ፈታኝ ሊመስል ይችላል። ነገር ግን፣ እንደ ምሳሌ ሊወሰዱ የሚችሉ የሴታዊነት መሰረታቸውን የጠበቁ ሴት አመራሮች እያየን በመሆኑ የእነርሱን አርአያነት ማበራከት ያስፈልጋል። ባጭር አነጋገር፣ በአሁኑ ወቅት ሃገሪቱ ከሴት መሪዎቻችን በእጅጉ የምትፈልገው በሴታዊነት የተቃኘ አመራራቸውን እንጂ ወንዳዊነትን የተላበሰ መሪነታቸውን አይደለም።
ከላይ የተዘረዘሩትን አካሄዶች በዘላቂነት ተግባራዊ ለማድረግ ሴታዊነትን ከመሰረቱ ሊያጠናክሩ የሚያስችሉ ተቋማዊ እርምጃዎችም መውሰድ ያስፈልጋል። ከዚህ ውስጥ የመጀመሪያው፣ በቤተሰብ ደረጃ ሴታዊነት ያለውን በርካታ ማህበራዊ ጠቀሜታ በተመለከተ ያለውን ግንዛቤ ማሳደግና ከዚህ በተቃራኒው ያሉ ልማዳዊ አስተሳሰቦችን ማስወገድ ነው። ከዚህ በተጨማሪ፣ የትምህርት ሥርዓት አደረጃጀቱም ሆነ አሰጣጡ ለሴታዊነት አመለካከት መጠናከር በሚያስችል መልኩና በሁለቱ ጾታዎች  ማህበራዊ ባህሪያት መካከል ያሉትን በርካታ ተደጋጋፊነትና ተመጋጋቢነት በሚያጠናክር መልኩ መቃኘት ይኖርበታል።ለእነኚህ ተቋማዊ እርምጃዎች ትኩረት እንዲሰጥ በማድረግ ረገድ፣ በሴቶች ሁለንተናዊ የመብት ጥበቃ ላይ የሚሰሩ ሃገር በቀል ድርጅቶች ግንባር ቀደም ድርሻ ሊወስዱ ይገባል። በተለይም፣ በቅርቡም ሆነ በሩቁ ታሪካችን የነበሩትንና በሴታዊነት ምግባራቸው ታላቅ አርአያ ሊሆኑ የሚችሉ ኢትዮጵያውያን ሴቶችን ታሪክ ፈልፍሎ ማውጣት፣ ወጣት ሴቶችን ከማበረታታት ባሻገር በህብረተሰቡ ውስጥ ያለውን የተዛባ አመለካከት ለመለወጥ አቢይ ድርሻ ይኖረዋል። በአጠቃላይ፣ ሁለንተናዊ የሴታዊነት ድርሻን ማጠናከር ለረዥም ዘመናት በውጥረት የታጀበውን ፖለቲካችንን ወደ ተረጋጋና የሰከነ ፖለቲካ ለማሸጋገር ከማገዙም በላይ አካታችና ዘላቂ ልማትን በማረጋገጡም በኩል የራሱ ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል።
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ደቡብ አፍሪካ በሚገኘው ስታለንቦሽ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፈሰር ሲሆኑ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትም ያስተምራሉ።Read 4069 times