Tuesday, 01 September 2020 00:00

ቤዞስ ከ200 ቢ. ዶላር በላይ ሃብት ያፈሩ የመጀመሪያው የአለማችን ባለጸጋ ሆነዋል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

   የአማዞን ኩባንያ መስራች አሜሪካዊው ጄፍ ቤዞስ፤ ከ200 ቢሊዮን ዶላር በላይ የተጣራ ሃብት በማፍራት በአለማችን ታሪክ የመጀመሪያው ባለጸጋ በመሆን አዲስ ታሪክ መስራታቸውን ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት ዘግቧል፡፡
የ56 አመቱ የአለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነር ጄፍ ቤዞስ ኩባንያ የሆነው አማዞን የአክሲዮን ዋጋ ባለፈው ረቡዕ በ2 በመቶ መጨመሩን ተከትሎ፣ የግለሰቡ የተጣራ ሃብት በ5 ቢሊዮን ዶላር ያህል በማደግ፣ አጠቃላይ የተጣራ ሃብታቸው 204.6 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን ነው ዘገባው የጠቆመው፡፡
ጄፍ ቤዞስ በቅርቡ ከትዳር አጋራቸው ማካንዚ ስኮት ጋር ፍቺ መፈጸማቸውን ተከትሎ፣ ለሴትየዋ 62 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሃብታቸውን ባያካፍሉ ኖሮ፣ የሃብት መጠናቸው ከ200 ቢሊዮን ዶላር በላይ ይደርስ እንደነበርም ዘገባው አስታውሷል፡፡
የማይክሮሶፍት ኩባንያው መስራች ሌላኛው አሜሪካዊ ቢሊየነር ቢል ጌትስ፤ በ116.1 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት ሁለተኛው የአለማችን ባለጸጋ ሆነው ሲከተሉ፣ የፌስቡኩ ዋና ስራ አስፈጻሚ ማርክ ዙከርበርግ፤ በ103.1 ቢሊዮን ዶላር ሶሰተኛ ደረጃን መያዙንም ዘገባው ገልጧል፡፡


Read 2811 times