Print this page
Saturday, 29 August 2020 14:14

የፕሮፌሰር መረራ ጉዲና አወዛጋቢ የጥናት ጽሁፍ በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(2 votes)


                  "በኢትዮጵያ የሀገረ-መንግስት ግንባታ የታሪክ ዳራ፡ በእኩልነት ላይ የተመሠረተች ሀገር ለመፍጠር የተደረጉሙከራዎች፣ ያጋጠሙን የታሪክ ፈተናዎችና   ያመለጡን ዕድሎች በብሔራዊ መግባባት መነፅር ሲታይ"

               አብዛኛዎቹ የሀገራችን የታሪክ ምሁራን የኢትዮጵያ ታሪክ ከክርስቶስ ልደት በፊት፤ በአስረኛው ምዕተ ዓመት የንግስት ሳባና የንጉስ ሰለሞን ግንኙነት በሚባለው ጊዜ ይጀምራል ይላሉ፡፡
ይህ ለአንዳንዶቹ የሚታመን ታሪክ ተደርጎ የሚወሰደው፤ ለሌሎች ደግሞ ተረት እንደነበረ የሚነገረው ክስተት የማስመሳያ ትርክቱ የእስራኤል አምላክ የቀባቸው ገዥዎች ተብሎ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ንጉሦቹ ቅቡልነትን አግኝተውበታል፡፡ በትርክቱም ሀገሪቷን እስከ 1966 ሕዝባዊ አብዮት ድረስ ያለ ብዙ ጭንቀት ገዝተውበታል፡፡
የዛሬይቱ ሰፊዋ ኢትዮጵያ እንደ ሕብረ ብሔራዊ የነገስታት መንግስት (multi-ethnic empire state) የተፈጠረችው በ2ኛው የ19ኛው ክፍለ ዘመን ግማሽ፤ የዘመነ መሳፍንት ከሚባለው ዘመን በኋላ ስለሆነና ዛሬም በጣም ሰፊ ቀውስ ውስጥ የከተተን ታሪካዊ ዳራም ከዚሁ ጊዜ ጀምሮ ስለሆነ፤ ጽሑፌም ከዘመናዊ ኢትዮጵያ መፈጠር ጋር በተከሰቱ ችግሮች ላይ ያተኩራል፡፡
የዘመነ መሳፍንትን ክስተት በመለወጥ የተጀመረው የዛሬዋን ሰሜናዊ ኢትዮጵያን አንድ የማድረግ ሕልም፤ በግማሽ ምዕተ ዓመት ውስጥ ከሦስት እጥፍ በላይ የሰፋች ኢትዮጵያን መፍጠር ችሏል፡፡ ይህ የታሪክ ክስተት የሦስት ምኞቶች ዉጤት ነበር፡፡ እነዚህም፡-
1ኛ/ ተበታትና የነበረችውን የዛሬዋን ሰሜናዊ ኢትዮጵያ ሕዝቦችን ለማሰባሰብ የታለመ ምኞት፣
2ኛ/ የኦሮሞና የሶማሌ ሕዝቦችን ጨምሮ ሰፊውን የደቡብ ክፍል የማስገበር ምኞት፣
3ኛ/ አፍሪካን ለመቀራመት ከመጡት የአውሮፓ ሀገሮች ጋር የመፎካከር ምኞት ነበሩ፡፡
እነዚህን ሦስት ምኞቶች ለማሳካት የመጀመሪያ የሆነውን ሙከራ የጀመሩት አፄ ቴዎድሮስ ነበሩ፡፡
ቴዎድሮስ ሕልሞቻቸውን ለማሳካት ጠንካራና ሰፊ ሠራዊት ማደራጀት ነበረባቸው:: ለዚህም ሰፊ መሬት የያዙትን ቄሶች መሬት መቀማትና ዘመናዊ መሳሪያን ከክርስቲያን አውሮፓ ለማግኘት ጥረት ማድረግ ነበር፤ የአውሮፓ መሪዎችን ማሳመን ሲያቅታቸው ደግሞ፤ ሙያው የሌላቸው አውሮፓዊያንን ሳይቀር በቤተ መንግስታቸው ሰብስበው ከባድ የጦር መሳሪያ ውለዱ እስከ ማለት ደርሰዋል፡፡ ይህም ምኞታቸዉ ይሳካ ዘንድ በነበራቸዉ የጦር መሣሪያ የአካባቢ ገዥዎችንም ለማንበርከክ ተንቀሳቅሰዋል፡፡
ቄሶችን ለመግፋት ያደረጉት ሙከራ "እግዚአብሔርን የካዱ ንጉሥ" ተብሎ ተሰባከባቸዉ፡፡ የአውሮፓዊያንን ዘመናዊ መሳሪያ ለማግኘት ገደብ ያለፈ ጉጉታቸው ከእንግሊዞች ጋር ያለ ጊዜ አላተማቸው:: የየአካባቢውን ገዥዎች በጉልበት ለማንበርከክ እጅና አንገት በመቁረጥ የገፉበት ሙከራ ከእንግሊዞች ጋር ለመዋጋት የቁርጥ ቀን ሲመጣ፤ የትግራይ፣ የወሎ፤ የጎጃም፣ የሸዋ፣ የጎንደር ገዥዎች ሁሉም በሚባልበት ደረጃ ካዷቸው፡፡
በአጭሩ የየአካባቢዉ ገዥዎች በእንግሊዞች እጅ መሞታቸውን ሲሰሙ ከማዘን ይልቅ፤ ተገላገልን ያሉ ይመስላል፡፡ ለዚህም ይመስለኛል፤ዕውቁ የታሪክ ምሑር ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ፤ የቴዎድሮስን ሚና በተሻለ የታሪክ ሚዛን ላይ ለማስቀመጥ ሲሞክር፤ “የተወናበዱ የለዉጥ ነቢይ” (confused prophet of change) ያላቸዉ፡፡ በዚህ የቴዎድሮስ የታሪክ ሚና ላይ ብዙ ሰው ልብ የማያደርገውን የታሪክ ማስታወሻ አስቀምጬ ልለፍ፡፡ ይኸውም ቴዎድሮስ በጊዜው ለነበሩ የአውሮፓ ኃያላን መንግስታት በፃፉት ደብዳቤ ውስጥ፤ “አባቶቼ በሰሩት ኃጥአት ምክንያት እግዚአብሔር “ጋሎችን” በሀገሬ ላይ ለቆ፤ እነሱ ጌቶች ሆነው፤ እኛ የእስራኤል ልጆች የነሱ አሽከሮች ሆነን እንኖር ነበር፡፡ አሁን እግዚአብሔር ከትቢያ አንስቶኝ የኢትዮጵያ ንጉስ አድርጎኛል፡፡ እናንተ ከረዳችሁኝ በጋራ እየሩሳሌምንም ነፃ ልናወጣ እንችላለን” ማለታቸዉ ነዉ፡፡ (ትርጉም የኔ ነው)፡፡
እዚህ ላይ ሁለት ነገሮችን ልብ በሉ:: “ጋሎቹ” የሚባሉት በዘመነ መሳፍንት የጎንደርን ቤተ መንግስት በበላይነት ሲቆጣጠሩ የነበሩ የየጁ ኦሮሞዎች መሆናቸውና እየሩሳሌም በጊዜው በእስላሞች እጅ የነበረች መሆንዋን ነው:: ከዚህ አንጻር ማስታወስ የሚያስፈልገው ትልቁ ጉዳይ፤ አፄ ቴዎድሮስ የብሔረሰብ (የዘር) ፖለቲካን በግልፅ የተናገሩ የመጀመሪያዉ የኢትዮጵያ መሪ መሆናቸው ነው፡፡ ከቴዎድሮስ ሞት በኋላ ለሦስት ዓመታት በተክለጊዮርግስና ካሣ (አማቾች የነበሩ ይመስለኛል) ከተካሄደው የሥልጣን ትግል በኋላ፤ በአሸናፊነት የወጡት አፄ ዮሐንስ (ካሣ ምርጫ) ነበሩ፡፡ አፄ ዮሐንስ ከሀገር ውስጥ ከወሎ፣ ከጎጃም፣ ከጎንደር፣ ከሸዋ ገዥዎች ጋር እየተጋጩ፤ ከውጭ ደግሞ ከጣሊያኖች፣ ከግብፆችና ከሱዳን መሐዲስቶች ጋር ሲዋጉ በመጨረሻ በመሐድስቶች እጅ ወድቋዋል፡፡ በአጭሩ ዮሐንስ ለትግራይ ልሂቃን #የኢትዮጵያ ማዕከል ነበርን፤ የአክሱም ሐቀኛ ወራሾች እኛ ነን; የሚለውን የፖለቲካ ስሜት መፍጠር ቢችሉም፤ በኢትዮጵያ የሀገረ-መንግስት ግንባታ ታሪክ ውስጥ የተለየ ሚና መጫወት አልቻሉም፡፡
በማያሻማ ቋንቋ :- የዛሬዋ ኢትዮጵያ በዋናነት የተፈጠረችውና የዛሬው የታሪክ ጣጣችንም በዋናነት የተፈጠረው በአፄ ምኒልክ ነው፡፡ ምኒልክ ንጉሰ ነገስት፣ ዮሐንስን የሱዳን መሐድስቶች እስኪገድሉላቸው ድረስ ከአውሮፓ መንግስታት በተለይም፤ ከጣሊያን በገፍ ባገኙት የጦር መሳሪያ እነ ራስ ጎበና የመሳሰሉ የኦሮሞ የጦር መሪዎችን በመጠቀም በጊዜው ጠንካራ የሚባል ግዙፍ ሠራዊት መገንባት ችለዋል፡፡ ይህን  ግዙፍ ሠራዊት ከዮሐንስ ጋር በመዋጋት ከማድከም ይልቅ፡- በአንድ በኩል ዮሐንስን እየገበሩ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ያኔ የነበረችውን ኢትዮጵያ ሦስት እጅ እጥፍ የሆነ ሰፊ ግዛት መፍጠር ችለዋል፡፡ በዚህም መጀመሪያ ሳይጠቀለሉ የቀሩትን የሸዋ ኦሮሞዎችን ጠቅልለው ያዙ፡፡
እ.ኤ.አ በ1876 ጉራጌን ብዙ ሕይወት ከጠየቀ ጦርነት በኋላ አስገበሩ፡፡ ብዙ ዝርዝር ውስጥ ሳይገባ የምኒልክን የመስፋፋት ጦርነቶች እንደሚከተለው ማጠቃለል ይቻላል፡፡ይኸውም ምኒልክና ጀኔራሎቹ ብዙ የግዛት መስፋፋት ጦርነቶችን ቢዋጉም ሦስቱ ወሳኝ ጦርነቶች ነበሩ፡፡ አንደኛው በምዕራብ በኩል በእማባቦ (ዛሬ ሆሮ ጉዱሩ በሚባለው) በጎበና መሪነት እ.ኤ.አ በ1882 የተዋጉት ጦርነት ነበር፡፡ ይህ ጦርነት ኦሮሞን ጨምሮ የምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦችን ዕድልና የጎጃም መሪዎች ከሸዋ ጋር የነበራቸውን ፉክክር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የወሰነና የሸዋንም የበላይነት ያረጋገጠ ነበር፡፡ ሌላው የምኒልክ ጦርነት በአርሲ ላይ እ.ኤ.አ በ1886 የተደመደመዉ ነው:: አርሲዎች ከሌሎች የኦሮሞ አካባቢዎች በተለየ መንገድ ለአምስት ዓመታት በጀግንነት ተዋግተዋል፡፡ በመጨረሻም፤ በራሳቸው በምኒልክ በተመራ ጦር የአውሮፓ መሳሪያ በፈጠረው ልዩነት ሊሸንፉ ችለዋል፡፡ ተመሳሳይ የመከላከል ጦርነት እንዳይገጥማቸው ይመስላል፤ ምኒልክ፡- ዛሬ አለ፤ የለም የሚባለውን የአኖሌ ዓይነት የጭካኔ በትር በአርሲዎች ላይ ያሳረፉት፡፡ እዚህ ላይ ዛሬ እየተነጋገርንበት ላለው የብሔራዊ መግባባት ስኬት፤ ድርጊቱ አልተፈጸመም  ከሚለው አጉል ክርክር ወጥተን፣ የትናንትናውን የታሪክ ቁስላችንን በሚያክም መልኩ እንድናስተካክል መምከርን እወዳለሁ፡፡
ሦስተኛው የምኒልክ ትልቁ ጦርነት አሁንም በእሳቸው የተመራውና እ.ኤ.አ በ1887 የተካሄደው የጨለንቆ ጦርነት ነበር፡፡ የዚህ ጦርነት ውጤት በጊዜው የሀብታሟ የሐረር ከተማ መንግስት (the Harari city-state) ጨምሮ ምስራቅ ኢትዮጵያ ያለ ደረሰኝ ምኒልክ እጅ የገባበት ሁኔታን ፈጥሯል፡፡ ከዚህም በኋላ ከፋን፣ ወላይታን፣ ወዘተ ለመያዝ ብዙ ደም የፈሰሰባቸው ጦርነቶች ነበሩ፡፡ እንደሚባለው፤ በእንግሊዝ ተስፋፊዎችና በምኒልክ ኢትዮጵያ መካከል የመምረጥ ዕድል የገጠማቸው የቦረና ኦሮሞዎች  "ማንን ትመርጣላችሁ?" ሲባሉ፤ የፊታወራሪ ኃብተጊዮርግስ ፊትን አይተው፤ "የእኛኑ ፊት የሚመስለው ይሻላል" ብለው በሬፍረንደም እየሰፋ በመጣው የኢትዮጵያ መንግስታዊ ግዛት ውስጥ የተቀላቀሉበት ሁኔታም እንዳለ ይነገራል፡፡ እ.ኤ.አ በ1889 አፄ ዮሐንስ በመሐድስቶች ሲገደሉ፤ ኦሮሞን ጨምሮ አብዛኛው ደቡብን የተቆጣጠሩት ምኒልክ፤ ለሰሜኑ ወንድም መሪዎች ፈረንጆች እንደሚሉት “ካሮትና ዱላን” ማስመረጥ ብቻ በቂ ነበር፡፡ የሰሜኑ መሪዎች ምርጫም በማያሻማ መንገድ ካሮት ነበር፡፡ ስለ ካሮቱም በግልፅ ቋንቋ ለማስቀመጥ፤ የኦሮሞ አካባቢዎችን ጨምሮ በደቡብ የተገኘው እጅግ በጣም ሰፊ ግዛት ዉስጥ በታናሽ ወንድምነት ሹመቶችን መቀራመት ነበር፡፡
ከብሔራዊ መግባባታችን ውይይት አንፃር፤ በምኒልክ ከተፈጠረው ሰፊ አፄያዊ ግዛት ጋር የተፈጠሩ ችግሮችን ወደ ማንሳቱ ልለፍ፡፡ አንደኛው ችግር፤ እላይ እንዳነሳሁት፤ በጉልበት የግዛት ፈጠራ ላይ አኖሌን የመሳሰሉ የታሪክ ጠባሳዎች መፈጠራቸው፤ ሁለተኛውና ዋናው ነገር ግን ከማቅናቱ ጋር የተፈጠረው የፖለቲካል ኤኮኖሚው ነው፡፡ ይህም በነፍጥ ላይ የተመሰረተዉ የፖለቲካ ኤኮኖሚ ዛሬም እያወዛገበን ያለው የነፍጠኛ ሥርአት በሚባለው ላይ የተመሰረተዉ ነዉ፡፡ ለማቅናት የተሰማራው የፊውዳሉ ሥርአት ሰራዊት የገባር ሕዝቦችን ነፃነት ቀምቷል፡፡ መሬታቸዉን ዘርፏል፡፡ ሕዝቦችን በገዛ መሬታቸው ላይ ጭሰኛና አሽከር አድርጓል፡፡ ቋንቋቸውን አፍኖ “በስማ በለው” ገዝቷቸዋል፡፡ በአጭሩ እጅግ በጣም ዘግናኝና ጨካኝ የሆነ የፖለቲካ ሥርአት ጭኖባቸዋል:: አንዳንዱ ነፍጠኛ በሃያ ሺዎች የሚቆጠር ጋሻ መሬትም ነበረው፡፡---
5. በማምለጥ ላይ ያለ አዲስ የሀገረ-መንግስት ግንባታ ሙከራ፡-
አሁን እየገጠመን ያለውን የታሪክ ፈተናን ለማለፍ፤ ጨክነን በቁርጠኝነት ብሔራዊ መግባባት ውስጥ መግባት ወይም ኢትዮጵያን እንደ ሀገረ-መንግስት የምታበቃበት፣ የሚጨምር ቀውስ ውስጥ መግባት ይመስለኛል፡፡ እዚህ ላይ የሌሎች ሀገሮችን ፖለቲካ በድህረ ቅኝ ግዛት ዘመን ብቻ እንኳን በመቃኘት ብጀምር፤ ችግሮቻቸውን ለመፍታት በቁርጠኝነት የሰሩት ተሳክቶላቸዋል፡፡ ያንን ያልቻሉት ወይ ፈርሰዋል ወይም አሁንም በቀውስ ውስጥ እየዳከሩ ነዉ:: ቅኝታችንን በላቲን አሜሪካ ብንጀምር፤ አነ አርጀንቲና፣ ቺሊ፣ ፔሩ፣ ኒካራጉዋ፣ ኮሎምቢያ የመሳሰሉት ቀውስ ደርሶባቸው፣ በተለያየ ደረጃ ፖለቲካቸውን ማስተካከል የቻሉ አገራት ናቸው፡፡
ከ60 ዓመታት በላይ ለልዕለ ኃያሏ አሜሪካ ሳትበገር፣ከአሜሪካ አፍንጫ ሥር የኖረችው አስደናቂዋ ሶሻሊስት ኩባና በአሜሪካ ጣልቃ ገብነት ምክንያት አሁን በሁለት ፕሬዚዳንቶች የምትገዛዋ ሶሻሊስት ቬኔዙዌላም በዚሁ ክፍለ ዓለም ይገኛሉ፡፡ በአውሮፓ ፖርቹጋል፣ ስፓኝ፣ ግሪክ፣ ፖለቲካቸዉን ማስተካከል ችለዋል፡፡ ዩጎዝላቪያ ውድ ዋጋ ብትከፍልም ከመፍረሰ አልደነችም፡፡ ሶቭየት ህብረትና (ግማሽ አውሮፓ ነች) ቼኮዚላቫኪያ በሰላማዊ መንገድ ፈርሰዋል:: በኤሽያ፤ ኔፓል የፖለቲካ ችግሯን በብሔራዊ መግባባት ስትፈታ፤ ፓኪስታን፤ ቬየትናም፤ አሁንም ካምቦዲያና ላኦስ ደግሞ ችግሮቻቸውን በጦርነት ፈትተዋል፤ አፍጋኒስታን፣ ኢራቅ፣ ሶሪያና የመን  አሁንም በቀውስ እየተናጡ ነው፡፡
ወደ አፍሪካችን ስንመጣ፡ ደቡብ አፍሪካና ጋና ከመሳሰሉት በስተቀር አብዛኛዎቹ በይስሙላ ምርጫ ላይ የተመሠረቱ አምባገነን መንግስታት ሲሆኑ፤ የአፍሪካ ሕብረትም የዲክታተሮች ማህበር (trade union of dictators) ከመሆን አላለፈም (በኢህአዴግ ጊዜ የተከሰስኩበት አንዱ ወንጀሌ፣ "የአፍሪካ መሪዎችን ተሳደብክ" የሚል ነበር)፡፡ ሱማሊያና ሊቢያ፤ ፈረንጆች የወደቁ መንግስታት (failed states) የሚሉት ሲሆኑ፤ ሩዋንዳ ጊዜውን ጠብቆ የሚፈነዳ ሌላ ቦንብ የምትጠብቅ ይመስለኛል፡፡
በዚህ የአፍሪካ ፖለቲካ ምስቅልቅል ጉዞ ውስጥ አንዱ የሚገርመኝ፣ ላለፉት 60 ዓመታት ፖለቲካቸውን ማስተካከል አቅቷቸው በቀውስ ሲናጡ የኖሩ ሁለት ሀገሮች፤ በተፈጥሮ ፀጋ እጅግ ሀብታሟ የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐቢሊክና የሦስት ሺህ ዓመታት ዕድሜ አለኝ የምትለዋ ድሃዋ ኢትዮጵያ መሆናቸው ነው፡፡
ከንጉሱ ዘመን ጀምሮ ይህንኑ የሀገራችንን የፖለቲካ እንቆቅልሾች የተከታተለ፣ ያጠና፣ ያስተማረና ብዙ ጽሑፎችን  ያቀረበ  ጆን ማርካከስ የሚባል፣ የታሪክና ፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር፤ “Ethiopia: The Last Two Frontiers” (የኢትዮጵያ የመጨረሻዎቹ ሁለት ድንበሮች) የሚል መጽሐፍ አሳትሟል፡፡ ደራሲው ምሳ ጋብዞኝ መፅሐፉን #ለዶ/ር ዐቢይ ስጥልኝ; ብሎኝ፤ እሳቸውን ማግኘት ለሚችል የኦፒዲኦ ባለሥልጣን ልኬላቸው እንደነበርም አስታውሳለሁ፡፡  ዶ/ር ዐቢይ መጽሐፉን  ያንብቡት አያንብቡት ባላውቅም፡፡
መፅሐፉ በአጭሩ፤ የኢትዮጵያ መሪዎች የሀገረ-መንግስት ግንባታ፤ የንጉሶቹ ሞዴል (the Imperial model) የደርግ የሶሻሊስት ሞዴልና የኢህአዴጉ ፌዴራሊስት ሞዴል በሙሉ ከሽፈዋል ይላል፡፡
የከሸፉበትም ዋናዉ ምክንያት፤ የባለ ጊዜ ገዥዎችን ሥልጣን ለማሳካት የተገፋበት መንገድ፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን እኩልነት ያላጎናፀፈና የልማት ጥማታቸውንም ያላረካ በመሆኑ ነው ይላል፡፡ ይህ የፈረንጅ ምሁር እንዳለው፤ ፖለቲካችንን ማሰልጠን ባለመቻላችን ሚሊዮኖች ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ ሚሊዮኖች ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፤ ሚሊዮኖችም ተሰደዋል፡፡
እኔም ከላይ ባነሳሁት ከዚሁ ምሑር ዕይታ ተነስቼ፣ ሀገራችን ስለገባችበት የፖለቲካ ቅርቃርና በብሔራዊ መግባባት አንፃር፣ ከቅርቃሩ ለማውጣት በሌኒን ቋንቋ ምን መደረግ አለበት? (What is to Be Done?) የሚለውን መሠረታዊ ጥያቄ፣ የሀገራችን ፖለቲካ እስከገባኝ ድረስ ልመልስ፡፡
1. መሠረታዊ ችግራችን፣ በታሪክ አጋጣሚ ሥልጣን ላይ የወጡ መሪዎቻችን፣ ሀገርን የመምራት ሕልማቸው፤ ሥልጣንን ጨምድዶ ከመቆየት ሕልማቸው ጋር ሁሌ ስለሚጋጭባቸው ነው፡፡ ለሕዝብ አለን ከሚሉት ፍቅር፣ የሥልጣን ፍቅራቸው ስለሚበልጥባቸው ነው፡፡ ለዚህ ነው ንጉስ ኃይለ ሥላሴ "የሚወደንና (ሕዝቡ ምን ያህል እንደሚወዳቸዉ እንዴት እንዳወቁ ባናዉቅም) የምንወደው ሕዝባችን" ሲሉ ኖረው ለ60 ዓመታት ገደማ የገዟትን ኢትዮጵያ፣ ለ20ኛዉ ክፍለ ዘመን ሳያበቁ፤ ከዓለም ሀገሮች ጭራ ትተዋት የሄዱት፡፡ የሕዝብ ፍቅራቸውንም ደረጃ፣ በረሃብ ሳቢያ በመቶ ሺዎች ያለቀው የወሎ ሕዝብ ይመሰክራል፡፡ ይህን የመሳሰሉ የመሪዎቻችን ባዶ የሕዝብና የሀገር ፍቅር፤ የንጉሱ "ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ"፣ የመንግስቱ ኃይለማርያም "አብዮታዊት እናት ሀገር ወይም ሞት" የመለስ ዜናዊ "በቀን ሦስት ጊዜ የሚመገቡ ዜጎችን እፈጠራለሁ" ወ.ዘ.ተ መሸፈን አይችልም፡፡ አሁን ያሉ መሪዎቻችንም ሆኑ ተስፈኛ መሪዎች፤ ይህንን የታሪክ እውነታ በውል እንዲገነዘቡት እፈልጋለሁ፡፡
2. የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና የተቀሩት ልሂቃን፣ በተለያየ ደረጃ የሚጋጩ ሕልሞቻቸውን ይዘው መጓዛቸው ነው፡፡ ከመኢሶንና ኢህአፓ ዘመን አንስቶ እስከ ዛሬ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶቻችንና መሪዎቻቸው፣ ይህንን እውነታ በውል መገንዘብ ይኖርባቸዋል:: የሕልሟን ጉዳይ በፈንጆቹ አባባል ከዜሮ ድምር ፖለቲካ (Zero-Sum game Politics) የመውጣቱንና የፖለቲካ ፍላጎቶቻቸዉን በገደብ የማድረጉን ነገር በጥብቅ እንዲያስቡበት እመክራለሁ፡፡ ዋና ጉዳያችን ሥልጣን ሆኖ ከፊንፊኔ እስከ መቀሌ "ባንዳ፤ ባንዳ" እየተባባሉ መካሰሱ ሕዝባችንን ከማደናገር በላይ ብዙ የፖለቲካ ትርፍ የለውም፡፡
ዛሬ በአሜሪካና በአውሮፓ በሚደረጉ ሰልፎች ላይ በአንድ እጅ "እስክንድር ነጋ ይፈታ"፣ በሌላ እጅ "ጃዋር ሽብርተኛ ነው" የሚሉት መፈክር ዓይነቶቹ፣ ለሀገረ-መንግስት ግንባታችንም ሆነ ለብሔራዊ መግባባት ሥራችን ብዙ የሚጠቅሙ አይመስሉኝም፡፡ በኔ በኩል፤ እንዲህ ዓይነቱ ጉዳይ ስላስቸገረኝ ነበር፤ በ2008 በፃፍኩት መፅሐፍ ላይ "ለቡዳ ፖለቲካችን መላ እንፈልግ ብቻ ሳይሆን የሚጋጩ ሕልሞች ሊታረቁ ወይስ ኢትዮጵያን ሊያፈርሱ?" በሚል ግልፅ ጥያቄ የደመደምኩት:: ለኔ መፍትሄው ለአዲስቷ ኢትዮጵያ ፈጠራ የሚሆን አዲስ ማህበራዊ ውል (New Social Contract) ከመፈራረም ውጭ የተሻለ የማጂክ ፎርሙላ ያለን አይመስለኝም፡፡ ይህንን እውነታ በምኒልክ ቤተ መንግስት ያሉ የብልፅግና ወንድሞቻችንም ሆኑ ከአዲስ አበባ/ፊንፊኔ  እስከ አውሮፓና አሜሪካ ጠቅላይ ሚኒስትሩን "ግፋ በለው" የሚሉ ሁሉ እንዲረዱልኝ አደራ እላለሁ:: በቅርብ ጊዜ በተፈጠረው ቀውስ በሁሉም በኩል ላለቁትም የተሻለ የሐዘን መግለጫ የሚሆነውና ዕንባቸውን የሚያብሰው፣ የችግሮቻችን ምንጭ አዉቀን፣ ዘላቂ መፍትኼ ስንፈልግ ይመስለኛል፡፡
3. እላይ ካነሳሁት ሁለት ነጥቦች ጋር ተያይዞ፤ ሺህ ጊዜ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ እየተባለ በሕዝብ ላይ የሚሰራው የፖለቲካ ትያትር መቆም አለበት:: የንጉሱ ዘመን የምርጫ ትያትሮች፣ የደርግ ዘመን የምርጫ ትያትሮች፣ የኢህአዴግ ዘመን የምርጫ ትያትሮች በግልፅ ቋንቋ ለማስቀመጥ፤ ሲያንሱ በዴሞክራሲ ስም የተቀለዱ ቀልዶች፤ ሲበዙ ደግሞ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ የተሰሩና ታሪክ ይቅር የማይላቸው ወንጀሎች ነበሩ፡፡ በሰለጠነው ዓለም የሕዝብን ድምፅ ከመስረቅ በላይ ወንጀል የለም:: እዚህ ላይ ሁለት ነገሮችን አስታውሼ ልለፈው:: በኢህአዴግ -1- ዘመን አቶ በረከት፤ ኢህአዴግ ከስድስት ሚሊዮን በላይ አባላት አሉትና በዝረራ ያሸንፋል ብሎ ሲያስቸግረኝ፤ #አቶ በረከት፤ ኢህአዴግ ሁለት ምርኩዞች አሉት፤ አንደኛው ምርጫ ቦርድ ነው፡፡ ሁለተኛው ጠመንጃችሁ ነው፡፡ ሁለቱን ምርኩዞቻችሁን አስቀምጣችሁ ተቃዋሚዎችን ካሸነፋችሁ፤ እኔ በግሌ እናንተ የምትሉትን 20 እና 30 ዓመታት ብቻ ሳይሆን፤ ለሃምሳ ዓመታት እንድትገዙን እፈርምልሀለሁ; እንዳልኩት አሰታዉሳለሁ፡፡
በኢህአዴግ -2- ጊዜ ደግሞ ዶ/ር አቢይ በጠሩት ድንገተኛ ስብሰባ ላይ ገለልተኛ የሆነው ጠቋሚ ኮሚቴ ስምንት ሰዎች አጣርቶ ካቀረበ በኋላ አራት ሰዎች መመረጥ ስላለባቸው በተጠቆሙት ሰዎች ላይ አስተያየት እንድንሰጥ ተጠየቅን::  ሌሎች በስብሰባው ላይ የተገኙ የየድርጅት መሪዎች ያሉትን ብለዋል፤ እኔ ጨዋታው ስላላማረኝ፤ #አብዛኛዎቹን ዕጩዎች ብዙዎቻችን አናውቃቸውምና ከየት እንደመጡ እንኳ ለማወቅ የ24 ሰዓት ጊዜ ስጡኝ; ብዬ አጥብቄ ጠየኩኝ:: ዶ/ር ዐቢይ አይቻልም አሉ:: "ነገ የምናገረው እንዳይጠፋኝና ለታሪክም ቢሆን ተአቅቦ  (reservation) መዝግቡልኝ" ማለቴ ትዝ ይለኛል::
ምስክሮችም አሉኝ:: የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መጥቶ የምርጫ ቦርድ ኃላፊዎች፤ የምርጫ ጊዜውን ሰሌዳ ለማስተላለፍ በጠሩት የምክክር ስብሰባ ላይ እንደተናገርኩኝ፤ መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት (devine intervention) ነው እንዳልኩኝ ምርጫው ባይተላለፍ ኖሮ፣ የአዲሱ ምርጫ ቦርድ አካሄድ ሌላ ከባድ ቀውስ ሊያስከትል ይችል እንደነበረ ዛሬ ላይ ሆኜ በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ፡፡ ይህንኑ ደግሞ ብዙ ጊዜ በታጋይነቷ ለምናውቃት ክብርት ብርቱኳንም ጭምር መናገሬን አስታውሳለሁ፡፡ ስለሆነም የሚመጣውን ምርጫ አዲሲቷን ዴሞክራትክ ኢትዮጵያ እንድትወለድበት ካላደረግን፤ የንጉስ ማኪያቬሊ ምክር፣ የመንግስቱ ኃይለማርያም፣ የጆሴፍ ስታሊን ቀይ በትር፣ የመለስ ዜናዊ፣ የሊቀ መንበር ማኦ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ውሰት፤ ኢትዮጵያን ለመለወጥ የታሪክ ፈተናውን ለማለፍ እንዳላስቻላቸው ሁሉ፣ የዶ/ር ዐቢይም የመደመር የፖለቲካ ቀመር፣ አዛውንቱ የፈረንጅ ምሁር የሚለውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ የመጨረሻ ሁለት ድንበሮችን የሚያሻግረን አይመስለኝም:: እሱን ካልተሻገርን ደግሞ ሁሌም እንደምለው፤ ለሁላችንም የምትሆን ዴሞክራቲክ ኢትዮጵያ የምትፈጠር አይመሰልኝም፡፡
ከማጠቃለሌ በፊት፤ የብሔራዊ መግባባቱ የፖለቲካ ጥራታችን ይሳካ ዘንድ መፍትኼ የሚሹ ቁልፍ ጉዳዮችን ላስቀምጥ፡-
1. ያለ ሀገራዊ ስምምነት በዋናነት በአንድ ቡድን ሕልምና ፍላጎት (በተለይ የአንድ ቡድን ፍኖተ ካርታ (road map) የመመረቱ ጉዳይ ለውጡን አጣብቂኝ ውስጥ ማስገባቱን የማወቅ ጉዳይ፤
2. ለውጡን ለማምጣት በዋናነት የላቀ አስተዋጽኦ ያላቸው ኃይሎች (ለምሳሌ እንደ ኦሮሞ ቄሮ ዓይነቶቹ) ወደ ዳር የመገፋታቸው ጉዳይ፣
3. ለውጡን እየመራ ያለው ከራሱ ከኢህአዴግ የወጣ ቡድን ቢሆንም፤ በለውጡ ምንነት፤ ፍጥነት፣ ስፋትና ጥልቀት ላይ የተለያዩ የኢህአዴግ ክንፎች ስምምነት ማጣታቸውና በዚህም ምክንያት እያመጣ ያለው አደገኛ ሁኔታ፣
4. በሚጋጩ ሕልሞቻችን ምክንያት ላለፉት 50 ዓመታት፣ መፍትኼ ያላገኘንለት የመከፋፈል ፖለቲካችን (political polarization) ጉዳይ፤
5. ዴሞክራሲያዊ ለውጡ ለአብዛኛዉ የኢትዮጵያ ሕዝቦችና የፖለቲካ ሃይሎች ተቀባይነት ያለው፤ ሠላማዊና የተሳካ እንዲሆን የጋራ ፍኖተ ካርታ (road map) የመቀየስ አስፈላጊነት ጉዳይና፤ የተቀየሰዉን በጋራ ሥራ ላይ የማዋል ጉዳይ፤
6. ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ማለት በእርግጥም በሕዝቦች ይሁንታ ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ጨዋታ መሆኑን የመረዳት ጉዳይ፤
7. ሀገራችን እዉነተኛ ዲሞክራሲያዊ የፌደራል ሥርዓት ያስፈልጋታል ስንል፤ ከሕልሞቻችን በሻገር በሕዝቦቻችን ፍላጎት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ሥርዓት መሆኑን የማረጋገጥ ጉዳይ፤
8. ብሔራዊ መግባባቱ በተሻለ መንገድ የሚሳካው፤ በደቡብ አፍሪካና ኮሎምቢያ በመሳሰሉት
9. ሀገሮች እንዳየነው የፖለቲካ እስረኞችንና የጫካ አማፅያንን መጨመርን የማስፈለጉ ጉዳይ፤
10. የተሳካ ብሔራዊ እርቅን ለመምጣት ከሥልጣን በሻገር የምር የፖለቲካ ቁርጠኝነት (political will)
11. የማስፈለጉ ጉዳይ፤
12. ስለ ኢትዮጵያ አንድነት ያለን ግንዛቤ፣ ከፊታዉራሪ ሀብተጊዮርጊስ እይታ የሰፋና ለሀገሪቷ  ያለን ፍቅርም ገደብ የማድረጉ ጉዳይ ናቸዉ፡፡
በመደምደሚያዬም፤ እዚህ ያደረሰንን ያገራችንን ፖለቲካ ጉዞ ታሪክ ወደ ኋላ እያየሁ፤ የወደፊቱን የሀገራችንን ዕጣ ፈንታንም እያማተርኩ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩም፣ ለሁላችንም የታሪክ የግርጌ ማስታወሻ ልተው:: በቅርቡ  ጠቅላይ ሚኒስትሩ #ኢትዮጵያ አትፈርስም፤ ኢትዮጵያን የሚያፈርሷት እኛን ቀድሞ ሲያፈርሱ ነው፤ ኢትዮጵያን ለማፍረስ አይፈቀድላቸውም; ሲሉ አዳምጫለሁ፡፡ ሀገርን ለማፍረስ የሚፈልጉ ሃይሎች መጀመሪያውኑ ፈቃድ ይጠይቃሉ፤ አይጠይቁም የሚለው ክርክር ውስጥ ሳልገባ፤ በጨዋ ቋንቋ ንግግራቸውን አልወደድኩላቸውም::
ንግግራቸውንም ተከትሎ የኢሳት ቴሌቪዥን የፖለቲካ ተንታኞች የሚታወቁ የአዛውንት ምሁርን በመጥቀስ፤ (ይህንኑ ምሁር፤ መንግስቱ ሀይለማርያምም ያውቃል ብለን ስለተሰሩ የንጉሱ ባለስልጣኖች ምክር ጠይቀነው፤# ጠመንጃዉ በእናንተ እጅ ነዉ፤ የምን ምክር ትጠይቁናላችሁ; ብሎኛል ማለቱን አንብቤያለሁ) ዶ/ር ዐቢይ ጥሩ ይዘዋል፤ ሕጉንም ሰይፉንም እየተጠቀሙ ነው ያሉት፤ የበለጠ ሥጋት ፈጥሮብኛል፡፡
እዚህ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሁላችንም ደጋግመን ማሰብ ያለብን፣ ጨዋታው ከተበላሸ አብዛኛው ዓለምን በሰዓታት ውስጥ ወደ አመድነት የሚለውጥ ወይም ሕይወት አልባ ሊያደርግ የሚችል የኑክሊየር መሳርያ የታጠቀ፤ ነፍሷን ይማርና የሶቭየት ህብረት ሠራዊት፣ ዓይኑ እያየ አገራቸው መበተኗን ነው፡፡
የሀገራችንን ፖለቲካ በጋራ አስተካክለን ሁላችንንም በእኩልነት የምታስተናግድ ዴሞክራቲክ ኢትዮጵያን ለመፍጠር እግዚአብሔር ይርዳን እላለሁ።
(ለብሔራዊ መግባባት ውይይት የቀረበ ጥናት፤ ነሐሴ 2012)


Read 2009 times
Administrator

Latest from Administrator