Saturday, 21 July 2012 11:46

የቴዲ “ፍልስምና 2” መግቢያና የእኔ ግርታ

Written by  ጤርጥዮስ-ከቫቲካን
Rate this item
(0 votes)

ቴዲ ሰባኪ ቢሆንም እንኳ የሃይማኖትንና የእምነትን ፍቺ በቅጡ ሳይተነትንልን፣ እንደ አሳቢም ጉዳዩን ከምክንያት እና ውጤት አንፃር ሳያሳየን “ሃይማኖት የሰው ልጅ እጅ ሥራዎች ናቸው፣ አለ የምንለው አምላክ አንድ ከሆነም አሁን በምድር ላይ ያሉትን ሃይማኖቶች አያውቃቸውም፡፡” ይለናል፡፡ የመጀመሪያዎቹ የሰው ልጅ ሞዴል ፍጥረታት “አዳም እና ሃዋ” ከሆኑም አምላክ ለእነርሱ እምነት እንጂ ሃይማኖት ስላልሰጣቸው፤ ድርጅት መሥርተው፣ አገልጋዮች ቀጥረውና ህግ አበጅተው ከአምላክ ጋር ለመገናኘት የሚሹትን ሁሉ ይኮንናል፡፡

“ፍልስምና 2” የተሰኘውን መፅሀፍ ያቀረበልን ፀሀፌ ተውኔትና ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ በሥራዎቹ የማደንቀው ጋዜጠኛና የኪነ-ጥበብ ባለሙያ ነው፡፡ በተለይ ጋዜጠኝነቱን እወድለታለሁ፡፡ በየመፅሔቱ የሚወጡ ቃለ መጠይቆቹን ፈልጌ አነባለሁ፡፡ ቴዲ በየትኛውም ርዕሰ ጉዳይ ላይ ጉዳዩ ለሚመከለታቸው እንግዶች የሚያቀርባቸው ጥያቄዎች ጥንካሬ ስለ ነገሩ በቂ መረጃ ይዞ ስለመጠየቁና ስለ በሳልነቱ ምስክሮች ናቸው፡፡ ጋዜጠኝነቱም ወደ ማፋጠጥና ወደ ማውጣጣት ያዘነበለ ነው፡፡

ቴዲ በተለየ ሁኔታ የእኔን ቀልብ ለመያዝ የቻለበት ዓይነተኛ ጎኑ ግን በእግዚአብሔር ህላዌ ዙሪያ የሚያነሣቸው ጥያቄዎቹ ናቸው፡፡ “ፍልስምና 2” እና “ፍልስምና 2” የተሰኙት መፅሃፍቶቹ በዚያ ረገድ ያነሣቸው ጥያቄዎቹ ትሩፋቶች ናቸው፡፡ ስለ እግዚአብሔር መጠየቅ ደግሞ የጥያቄዎች ሁሉ ቁንጮ፣ የፍልስፍና ሁሉ ራስ ነውና ከዚያ አንፃር ያደረጋቸው አሰሳዎች በመፅሄት ተወስነው ባለመቅረታቸው ደስተኛ ነኝ፡፡ ሆኖም በ”ፍልስምና 2” መፅሀፉ የመግቢያ ሀተታና ብይን ላይ ቅሬታ አድሮብኛልና የአሁኑ መፃፌ ለዚያ ነው፡፡

በቅርቡ ገበያ ላይ የዋለው የቴዲ “ፍልስምና 2” ከዚህ ቀደም እሱው ቃለ መጠይቅ ያደረገላቸው ሰዎች ስለ እግዚአብሔር ያላቸዉን ዕይታ የተናገሩበት በመሆኑ እዚያ ላይ የማነሣው ጥያቄ የለም፡፡ ይሁንና ቴዲ ለቃለ-መጠይቅ መድበሉ መግቢያ ሲፅፍ ሊያስተላልፍ የፈለገው መልዕክት ግርታን አጭሮብኛል፡፡ በአቋሙ ከተጠያቂ እንግዶቹ የተለየ መሆኑን ገልፆ ሲያበቃ ከነዚያ መካከል የአንዱን ብቻ መርጦ ልክ ማስመለሱን አልወደድኩለትም፡፡

የቴዲ ግላዊ አቋም ልክ ቢሆንም ባይሆንም ሊከበርለት እንደሚገባ አምናለሁ፡፡ ግና ጠያቂው ራሱ መላሽ ሆኖና የራሱን መደምደሚያ አበጅቶ “መሆን ያለበት እንዲህ ነው!” በማለቱ፣ አምላክ መፈለግና መመለክ ያለበት ሃይማኖታዊ መዋቅር በሌለበት ሊሆን እንደሚገባ ብይን መስጠቱ ከመፅሃፉ ዕንግዶች የአብዛኞቹን መንገድ ልክ ያለመሆን በገደምዳሜ ያረጋገጠ ነው፡፡ ከነዚያም መካከል ኦርቶዶክሳውያኑን መጋቢ ሀዲስ መምህር እሸቱ ዓለማየሁን እና የቲያትር ባለሙያዋን ጀማነሽ ሰለሞንን፣ የባሂ እምነት ተከታይዋን ታየች ዓለም ግርማን፣ መስሊሙን ፀሀፊ ሀሰን ታጁንና የይሖዋ ምስክሩን አቶ ግርማይ ተወልደን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ከእነዚህ ተጠያቂዎች የአንዳቸውም ሃይማኖት መዋቅር የሌለው አይደለም፡፡ አንዳቸውም እንኳ ሥነ-መለኮታቸውን ከቀዱበት ምንጭ ቢያንስ አንድ አንቀፅ ሳይጠቅሱ  አላወሩም፡፡

ደራሲና ጋዜጠኛው ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ በመፅሀፉ ውስጥ ያነሣቸው ጥያቄዎች የግሉ ከመሆናቸው ይልቅ በዘመናት መካከል ሲጠየቁ ስለመኖራቸው፣ መልሶቹም የራሱ እንዳልሆኑ ቢነግረንም ንባባችንን ስናሣርግ የምናገኘው ብይን ግን አንድ እና አንድ ብቻ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የእኔ ግርታ መነሻም እሱው ነው፡፡

ቴዲ “አምላክ፣ ሰውና ኃይማኖት” በሚል አብይ ርዕስነት “እንደ ግል ሃሳብም እንደ መግቢያም” አድርጐ በፃፈው የመንደርደሪያ ፅሁፉ የአምላክን፣ የሰውን ልጅና የኃይማኖትን ግንኙነት በራሱ ግንዛቤ ለመቃኘት ይሞክራል፡፡ የትኞቹም ምላሾች  ግን ልብን እርፍ አድርገው የሚያስቀምጡ ባለመሆናቸው ይኸው ጥያቄ ከጥንት እስከ ዛሬ መጠየቅ መቀጠሉን ይነግረናል፡፡ ገጣሚው ሰለሞን  ደሬሣ “አንዳንድ አሥሬ የሚጠየቅ” እንዳለው የአምላክ ጥያቄም እንዲሁ መሆኑን ይገልፃል፡፡

ይሄንኑ የሰው ልጅ ጥያቄ ተከትሎም በየሰው ልቦና የመጣው ምላሽና የተሣለው አምላክ “ዥንጉርጉር” መልክ ያለው ሆኖ መገኘት፣ ሃምሣና ሥድሣ ሺህ ሃይማኖት ባለበት ዓለም ውስጥ እየተኖረም ወደ እውነተኛው አምላክ ማንነትና ምንነት ለመድረስ የመንገዶቹን ብዛትና አታካችነት ዋቢ ያደርጋል፡፡ አንዱን ስህተት ሌላውን ትክክል ማድረግ ቀላል ሥራ ያለመሆኑንም ከግምት ውስጥ እንድናስገባ ያግባባናል፡፡ ቴዲ እንዲያውም “የትክክል እና ስህተት መለኪያው ምንድነው? ለኪውስ ማነው? እንዴትስ የሰው ልጅ አዕምሮ የአምላክን ማንነትና ምንነት ለመመዘን ይችላል?” የሚሉ ፍልስፍናዊ ጥያቄዎችን አንስቶ ስለ እውነተኛው አምላክ “ይሄ ነው!” ብሎ አይን ሞልቶ መናገር ስለ መክበዱ ይነግረናል፡፡ ሆኖም ወደዚያ ጎዳናው እንዲህ የጠበበና የከበደ መሆኑን የነገረን ቴዲ፤ አፍታም ሣይቆይ ሃሳቡን ቀይሮ ጠያቂው መላሽ ሆኖ ቁጭ ይላል፡፡ መጠየቁን አቁሞ ወደ ድምዳሜ ይሻገራል፡፡ ከዓረፍተ ነገሮቹ የጥያቄ ምልክቶችን እያስቀረ በአራት ነጥብ ሃሳቡን ማደንደን ይጀምራል፡፡ ይሄኔም ቴዲ ከተፈላሳፊነት ጠያቂነቱ ይልቅ የሰባኪነትን ሚና መውሰዱ ፍንትው ብሎ ይታያል፡፡

ቴዲ ሰባኪ ቢሆንም እንኳ የሃይማኖትንና የእምነትን ፍቺ በቅጡ ሳይተነትንልን፣ እንደ አሳቢም ጉዳዩን ከምክንያት እና ውጤት አንፃር ሳያሳየን “ሃይማኖት የሰው ልጅ እጅ ሥራዎች ናቸው፣ አለ የምንለው አምላክ አንድ ከሆነም አሁን በምድር ላይ ያሉትን ሃይማኖቶች አያውቃቸውም፡፡” ይለናል፡፡ የመጀመሪያዎቹ የሰው ልጅ ሞዴል ፍጥረታት “አዳም እና ሃዋ” ከሆኑም አምላክ ለእነርሱ እምነት እንጂ ሃይማኖት ስላልሰጣቸው፤ ድርጅት መሥርተው፣ አገልጋዮች ቀጥረውና ህግ አበጅተው ከአምላክ ጋር ለመገናኘት የሚሹትን ሁሉ ይኮንናል፡፡ ቴዲ ይህን ብሎ ቢበቃው ጥሩ ነበር፣ ግና የአቋሙ ፅናት የፈረጠመ መሆኑን እናውቅለት ዘንድ “የሰው ልጆች ወደ አምላካቸው እምነት ለመመለስ መጀመሪያ ሃይማኖታቸውን ማፍረስ ይጠበቅባቸዋል፡፡” በሚል ብይኑ ከጋዜጠኝነቱ ተፋቶ “ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ!” የሚል “ነብይ” ይሆንብናል፡፡

ቴዲ “ጥያቄውም መልሱም የእኔ አይደለም፡፡” ቢልም ቀልቡ ከእንግዶቹ አንዱ በሆነው በአውራምባው ሰው ዙምራ የህይወት ፍልስፍና መሳቡን መገመት አይከብድም፡፡ ምክንያቱም ለክብር ዶክተሩ ዙምራ “ዋናው በተስኪያን” እና “ዋናው መስጊድ” ራሱ ስለሆነ በጎራ ለተከፈለና በቡድን ለተዋቀረ ሃይማኖታዊ ድርጅት ቁብ የለውማ! ዶ/ር ዙምራ ሃይማኖት የሚለውን ቃል ገሸሽ እያደረገ ግና በአንድ ፈጣሪ ማመን እንደሚገባ፣ አምላኩ የክርስቲያንና የእስላም ተብሎ እንደማይጠራ ደጋግሞ መናገሩም የ“እንግዳ” አመለካከቱ አንዱ አካል እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡

ለምሣሌ ቴዲ ለዶ/ር ዙምራ “ሃይማኖትህ ምንድነው?” በማለት ላቀረበለት ጥያቄ ዙምራ የሰጠው ምላሽ “እምነት አንድ ነው፣ ፈጣሪም አንድ ነው ብያለሁ፤ እምነት ስም የሚወጣለትና የሚነገር ሳይሆን በተግባር የሚገለጥ ነው፡፡” የሚል ነው፡፡ ጥሩ መናገር፣ ጥሩ መሥራት፣ የወደቁትን መደገፍ ወ.ዘ.ተ … እንጂ ስም አውጥቶ “እኔ የምንትስ ኃይማኖት ሰው ነኝ” ማለት እንደማይገባም ገልጿል፡፡ ቴዲ “በማህበረሰባችሁ ቤተክርስቲያንም መስኪድም የለም፣ ይህ ለምን ሆነ?” በማለት ሲጠይቀውም ዙምራ “አለ ነው የምልህ፣ ግን የሚታይ አይደለም፣ በድንጋይና በሣንቃ የተሠራ አይደለም፣ የፈጣሪ መስጊዱም ቤተስኪያኑም እኛ ነን፡፡ ዋናው መስኪድ፣ ዋናው በተስኪያን እኔ ነኝ፡፡” ብሏል፡፡

ይህ የዙምራ አባባል ሲናገሩት የቀለለና የሚጥም ነው፡፡ ሆኖም እርሱ የፈጠረው የአመለካከት ከባቢም “ማህበረሰብ” በሚል ሽፋን የተቃኘ ሃይማኖት መባል አይቀርለትም፡፡ ዙምራ የሃይማኖት መሪ ነኝ ባይልም “ሃሳቤ እየመራቸው ነው፡፡” ብሏልና ማህበረሰቡ በዙምራ “አዕምሮ” የሚመራ የእምነት ጎራ መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡ ቴዲም በመግቢያው ፅሁፉ አፈራረሰው እንጂ ነገሩ እንዲያ መሆኑን አላጣውም፡፡ የሩቁን ትተን ከቅርቦቹ ብንጠቅስ የቻይን ሶሻሊስት አብዮት የመራው ማኦሴቱንግም ሆነ የሰሜን ኮርያዎቹ ሁለቱ ኪም ጆንጐች ዛሬ ላይ ለብዙ ህዝባቸው እንደ አምላክ ከመቆጠራቸው አስቀድሞ የፖለቲካና የሃገር መሪዎች ብቻ ነበሩ፡፡ ሰዎቹ ሥጋ ለባሽ በመሆናቸው ሞተው ቢቀበሩም “የእኔ ታላቅ ጀግና ከልቤ አመሰግናሃለሁ!” እያሉ ግድግዳ ላይ በተሰቀለ ፎቶግራፎቻቸው ፊት የሚደፉ ምስኪኖችን አላጡም፡፡ ዛሬ በስም ለይተን በምንጠራቸው ልዩ ልዩ ሃይማኖቶችም ከበስተጀርባው የየራሳቸው መሪዎች ነበሯቸው፡፡ ጥያቄው መሆን ያለበት የትኛው የሃይማኖት እና የፖለቲካ መሪ ህዝቡን ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ መራ? የሚል እንጂ በሰው ልጅ የሃሳብና የመንፈስ ቅብብሎሽ ውስጥ የተጠፈሩት ልዩነቶች አሁን ላለንበት ዓለም ሁኔታ “ተፈጥሯዊ” ናቸው፡፡ ያለ ጊዜውም ልናጠፋቸው አንችልም፡፡ ህንዳዊው ሃይማኖታዊ ፈላስፋ ኦሾ በዘመኑ የሰው ልጆችን ነፃ ሆኖ የመኖር ስሜት የነጠቁት ሃይማኖት፣ መንግሥትና ፍርድ ቤቶች መሆናቸውን በመግለፅ በተለያዩ ስልቶች ለመቃወም ሞክሮ ነበር፡፡ ለእርሱ ህግና ደንብ የሚባሉ ጣጣዎች ከእነዚህ አካላት የመነጩ ትብታቦች እንጂ ህይወትን በሥርዓት ለመምራት የምንችልባቸው ሞግዚቶች እንደሆኑ አይቀበልም፡፡

“ነፃነት ማለት ምንም አካል በአንተ ህይወት ጣልቃ የማይገባበት ኃላፊነት ነው፡፡” የሚለው ኦሾ፤ “እናንተ ራሣችሁን የመሆን፣ የመንቃትና የመገንዘብ ብቃታችሁ እያደገ ከሄደ ግን የትኞቹም ተቋማት አያስፈልጋችሁም፡፡” በማለት ደቀመዛሙርቱ እግዚአብሔር እንኳ ቢሆን ጣልቃ ሊገባበት የማይችልን የነፃነት ዓለም እንዲያልሙ ያደፋፍራቸው ነበር፡፡ ይልቁንም “የችግሮቻችን መሠረቱ ቤተሰብ ነው…የእኛ ድህነት፣ የእኛ ህመም፣ የእኛ ባዶነት፣ የእኛ ዕብደትና ፍቅር የለሽነት መንስኤው ቤተሰብ ነው፡፡” ብሎ የሚያምነው ኦሾ፤ ገና በአፍላ ዕድሜያችን “አንተ አይሁድ፣ አንተ ክርስቲያን፣ አንተኛው ሂንዱ፣ አንተኛው ደግሞ ሙስሊም ነሀ” እያሉ የጎራ ፍረጃን “ሀ” ብለን እንድንጀምር ያደረጉን ቤተሰቦቻችን በመሆናቸው “እነርሱ የገነቡት ያረጀና ጊዜው ያለፈበት ሳይሆን ቤተሰብን መሠረት ያላደረገ የአኗኗር ሞዴል ለመፍጠር እስከመሞከር ደርሶ ነበር፡፡ ሆኖም ኦሾ “በቤተ-ሙከራው” ውስጥ የቀፈቀፋቸው ዋልጌ ጠባያት ተከታዮቹ ለወቅቱ ጤናማ ማህበረሰብ ጠንቅ በመሆናቸው ኃላፊነት ለሚሰማቸው ሁሉ የሥጋት ምክንያቶች ነበሩ፡፡ የኦሾ ስም በተነሣ ቁጥር ከነፃነት ናፋቂነቱና ከፈላስፋነቱ ይልቅ ነውረኛ ባህሪው ይበልጡኑ ሥፍራ መያዙም ለዚያ ነው፡፡

እርግጥ ነው ወደፊት የትኛውም ሃይማኖት፣ መንግሥታዊ አስተዳደርና ፍርድ ቤት የተሰኙ ተቋማትን ሞግዚትነት የማይሻ፣ የስብዕናን ምልዓት ወደምናገኝበት መንፈሳዊ ክበብ ውስጥ እንደምንገባ አምናለሁ፡፡ እንደ ዙምራ እና ቴዲ ሰዎች በሃይማኖት የማይለያዩበት ዘመን ፈጥኖ ቢመጣም ደስታዬ ወሰን አይኖረውም፡፡ እግዚአብሔርን አስመልክቶ በክርስትና ሃይማኖት መፅሀፌ እንደተፃፈውም “እያንዳንዱ ሰው ባልንጀራውን፣ እያንዳንዱም ወንድሙን እግዚአብሔርን እወቅ” ብሎ ሳያስተምር ሁሉም እርሱን አውቆ የሚገኝበትን የተስፋ ቃል በጉጉት እጠባበቃለሁ፡፡ አዎን አሁንም እንኳ ቢሆን እግዚአብሔር መኖሩን ለማፅናት የየትኛውንም ሃይማኖት መፅሀፍ መጥቀስ ሳያስፈልግ በህገ-ልቦናችን ህላዌውን ለመገንዘብ እንችላለን፡፡ ሆኖም የኗሪውን መኖር በተፈጥሯዊ ህሊና መገንዘብ ብቻውን በቂ አልሆነምና ሰዎች በዘመናት መካከል የእግዚአብሔርን ማንነት እና ምንነት በመፈለግ ሂደት ውስጥ ልዩነት መፍጠራቸው አልቀረም፡፡ ይህም የነፃ ፍጥረትነታቸው መገለጫ ነው፡፡ የመረጡትን የመከተልና የማመን መብታቸው አካል፡፡

ከቴዲ “ፍልስፍና 2” እንግዶች አንዱ የሆኑት የፍልስፍና መምህሩ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ እንደተናገሩት “ሃይማኖት (Religion) የሰው ልጅ ወደ እግዚብሔር የሚያደርገው ጉዞ፣ መገለጥ (Revelation) ደግሞ እግዚአብሔር ሰውን ለማግኘት (ወደ ሰው) የመጣበት ጉዞ ነው፡፡” በዚህ የዘመናት የአምላክና ሰው መፈላለግ ሂደት ውስጥ የተፈጠሩት መተላለፎች (አለመገጣጠሞች) ያስከተሏቸው ውጤቶች ልብን ደስ የማያሰኙ ብዙ ገፅታዎች ስላሏቸውም የሚያስቆጩ ናቸው፡፡ ግና በቴዲ የቅንነት ናፍቆት ብቻ በአንድ ዓረፍተነገር የምናስወግዳቸው አይደሉም፡፡

ለሰው ልጆች አብሮነት ጠቃሚ የሆነውን ውጤት ለማምጣት ሲባል የሃይማኖት ቤቶቻችንን ከማፈራረስ የመጀመር ሃሳብም ቴዲ ጭንቅ ሲለው የመጣለት አሊያም ያለ ጊዜውና ያለ እግዚአብሔር ሃይማኖትን ወጥ ለማድረግ ከታተሩት አንዳንዶች የቀዳው ኑፋቄ እንጂ የሰብዓዊው ዓለም የመንፈስ ውህደት በዚህ ዓይነቱ የሰው ዘዴ የሚሞከር አይደለም፡፡ የሰው ልጆች አንድነት ምልዓቱን እስኪያገኝም የምናፈርሰው የሃይማኖት ቤቶቻችን ሳይሆን አንዳችን ወደ ሌላችን ጥግ እንዳንደርስ ድንበሮቻችን ላይ ያኖርናቸው የሽቦ አጥሮች፣ መወገድ ያለባቸውም ያለ ፍቅር የሌሎችን ድንበር ጥሰን ለመግባት የምንደፍርባቸው የአመፅ ጉልበቶች ናቸው፡፡ አሊያስ ቴዲ ሊሠራልን የፈለገውን አዲስ የ”እምነት ቤት” አዋጪነት ሣናጣራ የምናፈርሰው የ”ቀድሞ” ሃይማኖት ቤት የለም፡፡

 

 

Read 2815 times Last modified on Saturday, 21 July 2012 11:59