Monday, 31 August 2020 00:00

ይድረስ ለኦሮሞ የፖለቲካ ልሂቃንና ፓርቲዎች!

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(2 votes)

 ጣሊያኖች ኢትዮጵያን ወርረው ለማስገበር በተነሱ ጊዜ፣ እንደ አንድ የጦር መሣሪያ ለመጠቀም ያዘጋጁት፣ ኢትዮጵያዊያንን በዘርና በሃይማኖት ከፋፍሎ፣ እርስ በእርስ በማጋጨት ማዳከም ነበር፡፡ ኦሮሞውንና ሌላውን ሕዝብ በአማራው ላይ እንዲሁም ሙስሊሙን በክርስቲያኑ ላይ እንዲነሳ አድርገዋል፡፡ ክፉዎችና በጠላት ስብከት የተሸነፉ የመኖራቸውን ያህል አስተውለው የተራመዱም ነበሩ፡፡ የጅማው አባ ጅፋር፤ ሃምሳ የአማራ ተወላጆችን መስጊዳቸው ውስጥ በመደበቅ ከጥቃት ታድገዋቸዋል:: በወቅቱ ሕይወታቸው ከተረፉ ሕጻናት ውስጥ አንዱ እድሜ ጠግበው አሁንም እንዳሉ አውቃለሁ፡፡
ጊዜያዊ ጥቅም ያስገኘው በዘር መከፋፈል ለጣሊያኖች በዘላቂነት ሊያገለግላቸው አልቻለም፡፡ የኢትዮጵያዊያን ጠላት አማራ ሳይሆን ጣሊያን መሆኑን ሲገነዘብ፣ሁሉም በጣልያን ላይ ዘመተ፡፡ በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥም ሽንፈቱን ተከናንቦ ኢትዮጵያን ለቆ እንዲወጣ ተገደደ፡፡ ኢትዮጵያም ነጻነቷን ለመቀዳጀት ቻለች፡፡
ባለባታዊውንና መሣፍንታዊውን ሥርዓት ከማንም በላይ ያዳከሙት ንጉሠ ነገሥቱ አፄ ኃይለ ሥላሴ  ናቸው፡፡ ንጉሡ ባላባቱንና መሣፍንቱን ትጥቅ አስፈትተዋል፡፡ የራስና  የደጃዝማች ጦር የሚባለውንም አጥፍተዋል፡፡ መደበኛ ጦርም አቋቁመዋል:: እነ ደጃዝማች ፀሐይ እንቆ ሥላሴ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተሸነፉትና ራስ መሥፍን እጅ የሰጡት እንደ ድሮው የሚያዝዙት ኃይል በእጃቸው ስላልነበራቸው ነው፡፡ ደርግ የመሬት አዋጅን ሲያውጅ ባላባትነት ሞተ የተቀበረው:: ደርግ ተሸንፎ ሕወሐት/ኢሕአዴግ ሥልጣን ሲይዝ፣ ባላባትነት ሞቶ  ከተቀበረ 17 ዓመታትን አስቆጥሮ ነበር፡፡
ደርግ ባላባታዊውን ሥርዓት በማፍረስ መሬትን የመንግሥት በማድረጉ የአልባኒያን ኮሚኒዝም የሚከተለው ሕወሐት፤ ፀረ ባላባት ለመሆን የሚችልበት እድል አልነበረውም:: ደርግ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መሠረት ያለውና የሚወክለው የህብረተሰብ ክፍል የለውም ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ በውድቀቱ ማግስት  ፀረ-ደርግ መሆን የሚያስገኘው የፖለቲካ ትርፍ አልነበረም:: ሕወኃት ገዥነቱን ለረጅም ጊዜ ለማቆየት የሚያስችለው አንዳች መሣሪያ የግድ ያስፈልገው ነበር፡፡ ስለዚህም ጣሊያኖች የተጠቀሙበትን ዘረኝነት ከተቀበረበት ጎትቶ አወጣው፡፡ ለአማራ "ነፍጠኛ" የሚል ስም ሰጥቶ፣ "ባላባት ማለት አማራ ነው" ብሎ የሞተውንና የተቀበረውን ባላባትነት መታገል ጀመረ፡፡ ባንድ ጊዜም አማራውን በኢትዮጵያ ለሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች ሁሉ ጠላት አድርጎ ፈረጀው፡፡  
ከዚያም ሕወሓት መራሹ የኢሕአዴግና የአጋር ድርጅቶች ተቀዳሚ ሥራ "ነፍጠኛ" የሚሉትን ሥርዓትና በእሱ ሽፋን የሚያሳድዱትን የአማራ ሕዝብ ማጥቃት ሆነ፡፡ በብዛት የሚገኝበት የኦሮሚያና ሌሎች ክልሎችም የአማራው ተወላጅ በስጋት የሚኖርባቸው፣ ንብረቱንና ሕይወቱን የሚያጣባቸው የአደጋ ቀጣናዎች ሆኑ፡፡ በሕወኃት/ኢሕአዴግ አገዛዝ፣ አማራውን ይወክላል የተባለው ብሔረ አማራ ዲሞክራሲ ድርጅት (ብአዴን) ሳይቀር በፀረ ነፍጠኛ ትግሉ ዋና ተሰላፊ ሆነ፡፡ እንደ አቶ በረከት ስምኦን፣ አቶ ኅላዌ ዮሴፍና አቶ አዲሱ ለገሰ  ባሉ ሰዎች የሚመራው ብአዴን፤ "እንዴት በአማራ ሕዝብ ላይ እንዘምታለን" የሚሉ አንዳንድ  አባላቱን "ትምክህተኛ" እያለ አሳደዳቸው፡፡ ይህ እስከ 2009 ዓ.ም ድረስ የቀጠለ እንቅስቃሴ ነበር:: ብአዴን ቆሜለታለሁ ለሚለው ህዝብ ተቆርቋሪነቱን ያሳየው የፋኖና የቄሮ እንቅስቃሴ ባየለበት፣ በኦሮሚያ ክልል በበደሌ ዞን በሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ላይ ጥቃት በደረሰ ጊዜ ነበር:: አሁንስ ለአማራ ክልል ተወላጆች ከልቡ የሚቆረቆር ይኖር ይሆን?
የአማራ ክልል ተወላጆች ባለፉት ዓመታት በብዙዎቹ የአገሪቱ አካባቢዎች አያሌ በደሎችና መከራዎች ደርሰውባቸዋል:: በተለይ ብዙ የአማራ ተወላጆች በሚኖሩበት ኦሮሚያ ተደጋጋሚ ጉዳቶች ገጥመውታል:: ለሞት፣ መፈናቀልና የንብረት ውድመት ተዳርጓል:: የሚገርመው ደግሞ የኦሮሞ ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ድርጅቶች፣ በአማራው ላይ በየጊዜው የሚደርሱትን ጉዳቶች የሰብአዊ መብት ጥሰት መሆኑን አምነው፣ ድርጊቱን በግልጽ ሲያወግዙ አይታይም፡፡ በነገራችን ላይ በክልሉ ለሚፈጸሙ ዘር ተኮር ጥቃቶችና ውድመቶች፣ የፅንፈኛ የኦሮሞ ልሂቃን ጥላቻ ላይ የተመሰረተ ሃሰተኛ ትርክት፣ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው መካድ አይቻልም፡፡ በየአጋጣሚው የምንሰማው "አማራና ኦሮሞ ክፉና ደጉን የተጋራ ሕዝብ ነው" የሚለው የተለመደ ንግግራቸው አፋቸው ላይ እንጂ ልባቸው ውስጥ የሰረጸ አይመስልም:: ሁልጊዜ የሚተርኩት የአማራውን አፈር ገፍቶ አዳሪነት ሳይሆን ከመቶ ሰላሳ ዓመት በፊት የተፈጸመውን ወራሪነትና አስገባሪነት ነው:: ለመተረክ የሚፈልጉትና የሚመርጡት ለማጥቂያነት የሚያገለግላቸውን የምኒልክን ወራሪነት፣ አስገባሪነትና ጡት ቆራጭነት ብቻ ነው፡፡
"የምኒልክ ጦር ጡት ቆረጠ" የሚለውን ትርክት እኔን ጨምሮ ብዙዎች ለማመን ይቸግራቸዋል፡፡ ታሪኩ "የቡርቃ ዝምታ" የተሰኘውን ልቦለድ መጽሐፍ ተከትሎ የመጣ ከመሆኑ አንጻር ወያኔ ሠራሽ ነው የሚል እምነትም አለ፡፡ በኋላ ላይ አስተባበሉት እንጂ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳም የፈጠራ ታሪክነቱን አረጋግገጠው ነበር፡፡ እንደዚህ አይነት ትርክቶች መላ ካልተበጀላቸው ወደፊትም አገርን  እያወዛገቡ፣ የግጭት መንስኤ ሆነው እንደሚቀጥሉ መዘንጋት የለብንም፡፡
በ2006 ዓ.ም መጋቢት ወር ላይ ይህ ታሪክ ግዝፈት የሚያገኝበት ኹነት ተፈጠረ:: በአኖሌ ጦርነት የምኒልክ ጦር ለቆረጠው ጡት መታሰቢያ በሚል አንድ ሰው እጅ መሐል የተቀመጠ ጡት የሚያሳይ ሐውልት አኖሌ ላይ ተሠርቶ በክልሉ ፕሬዚዳንት በአቶ ሙክታር ከድር ተመረቀ፡፡ በ2007 ዓ.ም የካቲት ላይ ደግሞ ለጨለንቆ ጦርነት መታሰቢያ አሁንም በክልሉ ፕሬዚዳንት በአቶ ሙክታር ከድር ሌላ ሃውልት  ተመረቀ፡፡ ጨለንቆ፤ ሕወሓት/ኢሕአዴግ የሽግግር መንግሥቱ መሪ፣ ኦነግ የምክር ቤት አባል በነበረበት ዘመን  የአማራ ተወላጆች እየተገደሉ ወደ ገደል የተወረወሩበት ቦታ ሲሆን ኦነግና ሕወኃት በድርጊቱ ፈጻሚነት እርስ በእርስ ሲካሰሱ የቆዩበት መሆኑ አይዘነጋም፡፡ እነዚህ ሁለት ሐውልቶች ምን በጎ ውጤት አመጡ? ብሎ መጠየቅ የአባት ነው:: እኔ ለትናንቱ ጦርነት ማስታወሻ ተብለው እንደተሠሩ ሁሉ ለዛሬው ግፍ (ወጤታቸው ይህ እልቂት ነው) ምስክር በመሆናቸው ሐውልቶቹን ማፍረስ እንደማያስፈልግ፣ ከፉ እንዲያገኛቸው እንደማልሻም ልገልጽ  እወዳለሁ፡፡
ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ተገደለ፡፡ ይህችን አጋጣሚ ተዘጋጅተው ሲጠብቁ የነበሩ የተደራጁ ቡድኖች ቆንጨራቸውን፣ ሜንጫቸውን፣ ገጀራቸውንና ነዳጅ የተሞላ ጀሪካናቸውን ይዘው ሰዎችን አሰቃይተው ለመግደልና ንብረቶችን በእሳት ለማውደም ተሰለፉ:: በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገደሉ፡፡ አቶ መንገሻ የተባሉትን ሰው ገድለው አንገታቸውን ቆርጠው፣ ዐይናቸው አውጥተው ብቻ አልተዋቸውም፤ ቤተሰቦቻቸው እንደሰለቧቸው ነው የተናገሩት፡፡ ኃይሉ የተባለው ወጣት አንገቱ መቆረጡን፣ ዐይኑ መውጣቱን፣ አፍንጫውና ጆሮው መቆረጡን እንዲሁ ቤተሰቦቹ አረጋግጠዋል፡፡ ወይዘሮ አሥራት የተባለችን ሴት ደግሞ ከተደበቀችበት የበቆሎ ማሳ አውጥተው፣ አንገቷን ቆርጠው፣ ሆዷን ቀድደው አንጀቷን መዘርገፋቸውም ተነግሯል፡፡ ስለ ክፉና አሰቃቂ ድርጊታቸው ከዚህ በላይ መናገር አያስፈልግም:: የዚህ ድርጊት ፈጻሚዎች በምን ያህል ጥላቻ እንደተሞሉ ድርጊታቸው ይመሰክራል፡፡ የዚህ ድርጊት አቀናባሪዎችና የኋላ ደጀኖች ደግሞ በአገር ውስጥም ይሁን በውጭ ያሉ ጽንፈኛ የኦሮሞ ፖለቲካ ልሂቃንና የፖለቲካ ድርጅቶች መሆናቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡
ድርጊቱ ከተፈጸመ ወደ ሁለት ወር ገደማ እየተጠጋው ቢሆንም፣ እስካሁን አንድም የኦሮሞ ፖለቲከኛና የፖለቲካ ድርጅት ድርጊቱን በግልጽ ሲነቀፍና ሲያወግዝ አልተሰማም:: ስለዚህ ጉዳይ የጠየቅሁት የኦፌኮ አባል፤ "አንድም የኦሮሞ ድርጅት ድርጊቱን ሲደግፍ ወይም ሲቃወም አላጋጠመኝም፤ ከ100 ዓመት በፊት ምኒልክ ሰብአዊ መብት ጥሷል የሚል የኦሮሞ ፖለቲከኛ፤ በ21ኛው ከፍለ ዘመን ሰው ተገድሎ እሬሳው ሲጎተት እንዴት አያወግዝም? ይህ የእኔም ጥያቄ ነው›› ሲል ምላሹን ሰጥቶኛል:: አቋምን አደባባይ አለማውጣት የፖለቲካ ጥበብ ቢሆንም፣ በእንደዚህ አይነት ጉዳይ ላይ ግልጽ አቋም አለመያዝ፣  ድርጊቱን ከመደገፍ ብዙም የራቀ አይሆንም፡፡   
ድርጊቱን ለማውገዝ ፍላጎት የማይታይባቸው የኦሮሞ የፖለቲካ ልሂቃንና የፖለቲካ ድርጅቶች ጥያቄና ማሳሳቢያ የሚደረድሩት በወንጀሉ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ሰላሉ አባሎቻቸው የእስር ቤት አያያዝና የፍትሕ ሂደት ነው:: የፍትሕ ተቋማት ወንጀል የሚሠራባቸውና ወንጀለኞችም ሽፋን የሚያገኙበት እንዲሆኑ አልፈልግም፡፡ ምንም ይሁን ምን ግን የኦሮሞ ልሂቃንና የፖለቲካ ድርጅቶች ይህን ዘግናኝ የንጹሐንን ጭፍጨፋ በግልጽ እንዲያወግዙ አጥብቆ ከመጠየቅ ወደ ኋላ አልልም፡፡
የኦፌኮው አቶ ገብሩ ገብረ ማርያም፤ አንድ የቁቤ ትውልድ እንዳለ ደጋግመው ነግረውናል:: ይህ ትውልድ በሕወኃት/ኢሕአዴግ አማርኛ እንዳይሰማ (እሳቸው አማራ ጠል አላሉም) ሆኖ ያደገ በመሆኑ እሱ ላይ መሥራት  እንደሚገባ ማሳሰባቸውን አስታውሳለሁ፡፡ እኔም ማሳሰቢያቸውን እጋራለሁ፡፡ አሁንም የኦሮሞ ልሂቃንና የፖለቲካ ድርጅቶች ይህን በጥላቻ ትረካና ቅስቀሳ የገሩትን ትውልድ፤ ስለ ኢትዮጵያ ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖረው ያደርጉ ዘንድ አሳስባለሁ፡፡
ሕዝብ የሕዝብ ጠላት ሆኖ አያውቅም:: በዚህ ክፉ አጋጣሚ የዚህኛው ወይም የዚያኛው ዘርና እምነት ተከታይ ሳይሉ ብዙዎችን ከሞት ለታደጉ፣ንብረትን ከጥፋት ለታደጉ አያሌ መልካም የየአካባቢው ነዋሪዎች ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡ ሌላ ጥፋትና ግድያ ዳግም እንዳይቀሰቀስም አካባቢያቸውን በህብረት  ነቅተው ይጠብቁ ዘንድም አደራ እላለሁ፡፡
አሁንም እናገራለሁ፤ የኦሮሞ የፖለቲካ ልሂቃንና የፖለቲካ ድርጅቶች  ድርጊቱን በግልጽ ያውግዙ፤ ይኮንኑ፡፡ ይህንን ለመስማትም በእጅጉ እጓጓለሁ፡፡
ፈጣሪ የክፉዎችን እጅና አንደበት ይያዝልን!!
ከአዘጋጁ፡- ከላይ የቀረበው ጽሁፍ የጸሃፊውን ሃሳብ ብቻ የሚወክል መሆኑን እንገልጻለን፡፡


Read 10807 times