Sunday, 30 August 2020 00:00

ሸገርን ማስዋብና ማልማትም ክፉኛ ያስተቻል! ሃሳብን በግጥም መግለጽስ?

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(0 votes)

 ከሰሞኑ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፣ ከሸገር ፕሮጀክት ጋር በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ማለታቸው የፈጠረው ስሜትና ምክንያት የለሽ ትችት ለዚህ ጽሑፍ ሰበብ ሆኖኛል፡፡
“የኢትዮጵያ ልክ - ከግቢ እስከ አገር” የተሰኘው አስደማሚ የሸገር ፕሮጀክት ዶክመንታሪ ለህዝብ ከቀረበ በኋላ በማህበራዊ ሚዲያ የተሰነዘሩ አንዳንድ አስተያየቶችን ተመልክቼ ተገርሜአለሁ፡፡ ብዙዎቹ ሚዛናዊነት የሚጎድላቸው ሲሆኑ ከፊሎቹ ደግሞ አልባሌ የሚባሉ ናቸው፡፡ ለመንቀፍ ሲሉ ብቻ የነቀፉም  አልጠፉም:: እውነት ለመናገር፤እነዚህ ጩኸቶች ከሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታዎች ያፈነገጡ ናቸው፡፡ አንዳንዶች፣ #ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስራቸው ምንድነው?; ሲሉ ይጠይቃሉ:: እነዚህ እንኳን ግራ ገብቷቸው ነው፡፡ ጠ/ሚኒስትር እንዴት ፓርክ ይሰራል? ከተማ ያስውባል? የተጠናቀቁት ፕሮጀክቶችን በቴሊቪዥን ያስጎበኛል? ወዘተ -- ከሚል ነው፡፡ አልተለመደማ! ከዚህ ቀደም እንዲህ ያሉ ጠ/ሚኒስትር አልገጠሙንም፡፡ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሦስትና አራት ደረጃቸውን የጠበቁ ውብ ፓርኮችና መዝናኛዎች ሰርቶ ማጠናቀቅ አጃኢብ ነው፡፡
ይሄን ያደረጉት ደግሞ በሰላምና በተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ አይደለም፡፡ አገሪቱ በነውጥና በለውጥ እየተናጠች ባለችበት ፈታኝ ወቅት ውስጥ ነው፡፡ ጸረ-ለውጥ ሃይሎች ለውጡን ለማደናቀፍ ቀን ከሌት እየተጉ ባሉበት ጊዜ  ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ሆነው ሸገርን ወደ ምድር ገነትነት የሚለወጥ ፕሮጀክት እውን ማድረጋቸው የሚያስመሰግን እንጂ የሚያስተች አይደለም፡፡
ሰዎች ያለ አግባብ መሞታቸው፣ ንብረታቸው በግፍ መውደሙ፣ በገዛ ሀገራቸው እየተሳቀቁ መኖራቸው ወዘተ--አፋጣኝ መፍትሄ ማግኘት ያለበት  መሆኑን አስምሬ፣ነገር ግን በተፈጠሩ ችግሮች ምክንያት ‹‹ልማት ለምን ለማ?!›› የሚለውን ጫጫታ መቀበል ያቅተኛል፡፡ ዛሬ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ለሀገራችን ብልጽግናና ለልጆቻችን የተሻለ ህይወት እንጂ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የግል ጥቅም ያለመሆናቸውን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ያንድ መሪ በዘላቂ ልማቶች ላይ ማተኮርና በየትኛውም ችግርና አጣብቂኝ ውስጥ ሆኖ ለልማት መትጋት፣ ጥንካሬና የመጪው ዘመን ዋስትና መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡
በቅርቡ በቴሌቪዥን መስኮት ያየናቸውና ሌሎችም ፓርኮች፣ ከሀገር ገጽታ ግንባታ ባሻገር የገቢ ምንጮችና የስራ ፈጠራ ስልቶች፣እንዲሁም የአየር ንብረትን ቀያሪ መዘውሮች  ናቸው፡፡ በያመቱ የሚደረገው የችግኝ ተከላም ቢሆን የሀገርን ስነምህዳር መቀየር ብቻ ሳይሆን፣የቀጣዩ ዘመን ሃብቶች ምንጮች ሆነው የትውልድን ሕይወትና ኑሮ የሚያሻሽሉ ናቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ በዓለም ላይ የደን ሀብታቸው በብልጽግና ማማ ላይ ያስቀመጣቸውን ስዊድንን የመሳሰሉትን ሀገራት  መጥቀስ በቂ ነው፡፡ ስዊድን ከመቶ ዓመታት በፊት ከተዘፈቀችበት የድህነት አረንቋ ውስጥ ጎትቶ ያወጣት የደን ሀብቷ ነው፡፡ እዚያው እስካንዲኒቪያ ውስጥ ያለችው ፊንላንድም  የደን ሀብቷ ብልጽግናዋ ነው፡፡ በመሆኑም ዛሬ ችግኞች ሲተከሉ ነገ ትልልቅ የኢንዱስትሪ ዛፎች መወለዳቸውን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡
ስለዚህ ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ ሲባል በዶ/ር ዐቢይ የልማት ሥራዎች ላይ ማፌዝና አጉል ትችት መሰንዘር ተገቢ አይደለም፡፡ ለሀገር የሚሰሩ በጎ ነገሮች ላይ የሚካሄደው ፍሬ ቢስ ተቃውሞ፣ የራስን ቤት ከማፍረስ ተለይቶ የሚታይ አይደለም:: ይህንን ስል ጠቅላዩ በየትኛውም ነገር መተቸት የለባቸውም እያልኩ አይደለም:: እኔም ራሴ ትክክል አይደሉም ባልኳቸው ነገሮች፣ ሀገሬን ችግር ላይ በማይጥል መንገድ እተቻቸዋለሁ፡፡ ይህ ማለት ግን የሚሰሩትን መልካም ስራ ሁሉ በጥላቻ ማየትና ማቆሸሽ አይደለም፡፡ ያንን ማድረግ ለየትኛውም ወገን አይጠቅምም፡፡
ይሁንና በየጊዜው የሚሰሙ የተቃውሞ  ድምጾች እንዳስተዋልኩት ፣ የፖለቲካ ሰዎች ነን ሲሉ የከረሙት ሳይቀሩ የሚያወሩት ወሬና የሚያቀርቡት ትችት፣ የሚያስገምትና ትዝብት ላይ የሚጥል ነው፡፡ ለዚህ ምሳሌ የሚሆነው በቅርብ ጊዜ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግድቡን ሸጦታል›› የሚለው አሳፋሪ ቀልድ ነው፡፡ ለመሆኑ በአጭር ጊዜ በገሃድ ሊታይ የሚችልን እውነት በአደባባይ መለፈፍ፣ ሕዝብን ከመናቅ በስተቀር ምን ሊሆን ይችላል?...የተሸጠው ግድብ ውሃ ተሞልቶ ሲገኝ ምን የሚል ምክንያት ይሰጠዋል›.ተብሎስ አይታሰብም!? ይህ የዘመናችንን ፖለቲከኞች ውድቀት የሚያሳይ የሰነፎች ተግባር ነው፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ ከሰሞኑ ባልተለመደ ሁኔታ ግጥሞች እየጻፉ በማህበራዊ ሚዲያ መልቀቃቸው ሌላኛው የትችት በር ከፋች ሆኗል፡፡ ጠቅላዩ ግጥም መጻፍ እንደሚሞክሩ #እርካብና መንበር; በሚለው መጽሐፋቸው አይተናል፡፡ ለነገሩ ማንም ሰው ስሜቱ በተለያየ ነገር ሲነካ ግጥም ይጽፋል፡፡ ይሁንና የጻፈውን ሁሉ አደባባይ አያወጣውም፡፡ እኔ የዚህ ጉዳይ ቀንደኛ ተቃዋሚ ነኝ፡፡ ግን ደግሞ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ለምን ተጻፈ ማለት ተገቢ አይደለም፡፡ ወደ መጽሐፍ ሲመጣ ግን ጥንቃቄ ያሻዋል፡፡  ገንዘብ ከፍለን ስለምንገዛውና የማይጠፋ ቋሚ ሰነድ በመሆኑም እንተቸዋለን፡፡ ስንተችም በደፈናውና በግምት አይደለም፡፡ ግጥም የራሱ አላባውያንና ባህርያት አሉት፡፡ በዚያ ነው የምንመዝነው፡፡
ስለ ጫማና እሾህ የሚተርከው ግጥማቸው፤ ድፍንፍን ያለና የገጣሚውን ግብ ያላገኘ ነው፡፡ ሆኖም ግጥሙ በበጎነት ተጠቃሽ ነገሮች እንዳሉትም መካድ አይቻልም፡፡ ለምሳሌ በቤት አመታቱ ሸጋ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ግጥሙ ለጆሮ ቤት ከመምታቱ ባሻገር፣ ቤት የመታባቸው የአናባቢ ድምጾች አቅም ያለው ድምጽ የሚሰጡ ናቸውና!!
ጫማው
መርገጫ እንጂ
እግር ነው መሄጃ፤
እሾህ
ሾህ ያጥፈዋል
ተራመድ ወደፊት
ቆመህ ጊዜ አታጥፋ፡፡
እነዚህ ሁለቱ የተሰመረባቸው ስንኞች በአናባቢ ለጆሮ ቤት የሚመቱ ናቸው፡፡ ለጥቆም አናባቢዎቻቸው ከሶስቱ ኃይለኛ ድምጽ ካላቸው አንዱ ነው፤ስለዚህ በግጥም ቤት አመታት የተመረጠ ነው፡፡ ችግሩ ስርዐተ ነጥብ እንኳ ሳይኖረው መለቀቁ ነው፡፡ ግጥም ላይ ስርዐተ ነጥብ እጅግ በጣም ወሳኝ ነው:: እዚህ ላይ ሚዛናዊ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ግጥም ለምን ጻፉ ብሎ እሪሪ  ማለት፣ ግጥም ወዳዱን ኢትዮጵያዊነትን መካድ ነው፡፡ እኔ የማልስማማው ለስሜት የተጻፉ ግጥሞች ሳይበስሉ አደባባይ አይውጡ የሚለውን  ነው፡፡ እንደዚያ ከሆነ እነ ቤንጃሚን ፍራንክሊን ስንት ቀሽም ግጥም ጽፈው የለ እንዴ!! ኤመርሰንስ ቢሆን!
እውነት ለመናገር ሰውየው የስነጽሑፍ ተሰጥዖ እንዳላቸው ለማየት በየክብረ በዓላቱ የሚጽፏቸው የመልካም ምኞት መግለጫዎችን  ብቻ መመልከት በቂ ነው:: በተለይ አንዳንዴ በሚጽፏቸው ጽሑፎች የሚታየው የቃላት ብልጽግናና የዘይቤዎች ውበት ነፍስ ያፍነከንካል፡፡ ይሁንና እነዚህ የዘይቤዎች ቁንጅና በግጥሞቻቸው ላይ ፈክተው አይታዩም፡፡ ይህ ብዙ ጊዜ የሚሆነው ገጣሚው ሃሳብ ፍለጋ ላይ በመባከን ስሜቱ ቀዝቅዞ ሲጽፍ ነው፡፡ ምናልባት የመልካም ምኞት መግለጫዎቹ የዘይቤ ከፍታ፣ በጉዳዩ ላይ ከመመሰጥ የሚመጣ ይመስለኛል፡፡
ሰሞኑን የጻፏቸው ግጥሞች የቃላት ብልጽግና ባይኖራቸውም፣ አንዳንድ የሚመሰገኑ ነገሮች አሏቸው፡፡
ለምሳሌ፤-
ሀገሬ
እምዬ
ሀገሬ
ቀለሜ
ሕልሜ
እንኳንና በሕይወት
በሞትም የማይሞት
የፈጸምነው ገድል
ያኖርነው አሻራ
ቢኖርም ዘላለም
 ካባይ ግድብ ጋራ
እምዬ
ሀገሬ
ቀለሜ
ሕልሜ
ክብርሽ ከፍ ብሎ- ከሰላምሽ ጋራ
ላለም ሁሉ እንዲታይ-እንደ ንጋት ጮራ
ክንፍ ሆነው እግሮቼ- በበረርኩ ለስራ፡፡
እዚህ ጋ አዝማች አድርገው የተጠቀሟቸው #እምዬ-ሀገሬ-ቀለሜ-ሕልሜ-; የሚሉት ቃላት ለአጽንኦት እንደሆነ ማንም ስለ ግጥም የሚያውቅ ሰው አይስተውም፡፡ ይሁንና መጀመሪያ ሀገርን በእናት መመሰላቸው፣ የእናት ያህል ሀገርን በማቅረብ፣ ጡት በማጥባት ወልዳም በማሳደግ ያላትን ዝምድና ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ ወደ ውስጥ መግባት ስለማያስፈልገኝ ጭብጡን አልመረምርም:: ግን ያን ያህል የሚያበሳጭ፣ ለምን ጻፉ የሚያሰኝ አምባጓሮ የሚያስነሳ አይደለም፡፡
በማጠቃለያዬ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹ሁሉም ነገር ውስጥ ይገባሉ; የሚለውን ትችት በተመለከተ አንድ ነገር ለማለት እሻለሁ፡፡ ለመሆኑ የብዙ ተሰጥዖ ባለቤት መሆን ያስመሰግናል እንጂ ያስተቻል እንዴ!? ኢጣልያውያን ዳቪንቺን፣አሜሪካውያን ጀፈርሰንንና ፍራንክሊንን አሞግሰዋል እንጂ ተችተዋል እንዴ? ይህ ነገር ሊመረመር የሚገባ ክፉ ሕመም ይመስለኛል፡፡ እስቲ አሜሪካውያን ስለ ቶማስ ጀፈርሰን ያሉትን እንመልከት፡-
“No man in this or any other country in the western world excepting Leonardo de vi nci-ever matched Jefferson in the range of this activities, in the fertility of his thinking, and in the multiplicity of his interest.”
በርግጥም ጀፈርሰንን ከዳቪንቺ በቀር ከማንም ጋር ልናስተያየው አንችልም፡፡ እውነትም ሰውዬው ቀያሽ፣ የሂሳብ ሊቅ፣ አርክቴክት፣ ፈላስፋ፣ የቨርጂኒያ ገበሬና የብዙ ሙያዎች ባለቤት ነበረ፡፡ የቨርጂኒያን ዩኒቨርሲቲ ዲዛይን የሰራውም እርሱ ነው:: የተዋጣለት ገበሬም ነበር፡፡ ግን ማንም "ለምን ሁሉም ነገር ውስጥ ዘው ይላል" ብሎ ለመተቸት አልዳዳውም፡፡ ይልቅስ ታላቅ ሰው አለን ብለው የኩራታቸው ምንጭ አደረጉት እንጂ፡፡ እኛ ጋ ግን በየቀዳዳው ገብቶ ሽንቁር መድፈን ለትችት ይዳርጋል:: ይህ አሳዛኝና የዕድገት እንቅፋት በመሆኑ በአጭሩ ሊቀጭ ይገባዋል፡፡ ያለበለዚያ የብልጽግና ጉዟችን ህልም ብቻ ሆኖ ነው የሚቀረው፡፡
የጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ በሳይንስና ቴክኖሎጂው ላይ መትጋት፣ችግኝ መትከልና ማስተከል፣ ሸገርን ማስዋብ የመሳሰሉት ፕሮጀክቶች ውስጥ ገብቶ ተዓምር የሚያሰኝ ውጤት ማስመዝገብ ሊያስደምመን እንጂ ሊያስቆጣን  አይገባም፡፡ ቢያድለን ልናመሰግናቸውና ሌሎች የመንግስት ባለሥልጣናትም የእሳቸውን ፈለግ እንዲከተሉልን መጸለይ ነው የሚገባን:: ብልጽግናን የሚወድድና ለብልጽግና የሚተጋ የሰለጠነ መሪ ማግኘት መታደል ነው፤ ለበጎ ሥራ ምስጋናና ክብር መስጠት ይልመድብን!!

Read 561 times