Monday, 31 August 2020 00:00

“የወላይታ ህዝብ ፍላጐት ወላይታ ክልልን መመስረት ብቻ ነው”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

          - በአሁኑ ሰዓት የዞኑ ማንኛውም ፋይናንስ እንዳይንቀሳቀስ ታግዷል
          - 5ቱ የዞኑ አመራሮች ከሃላፊነታቸው ተነስተዋል
          - የዞኑ ምክር ቤት ትላንት አዲስ አስተዳዳሪ ሾሟል

          ባለፈው ነሐሴ 3 ቀን 2012 ዓ.ም የወላይታ ዞን አስተዳዳሪን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በሶዶ ከተማ ጉተራ አዳራሽ በወላይታ የክልልነት ጉዳይ ስብሰባ ተቀምጠው ሳለ በመከላከያ ሀይሎች ተይዘው ለእስር መዳረጋቸው ይታወሳል፡፡ እስሩን ተከትሎ ህዝቡ ቁጣውን ለመግለጽ ወደ አደባባይ በወጣ ጊዜም ከፀጥታ ሃይሎች ጋር ግጭት ተፈጥሮ ነበር፡፡ ሰዎች መሞታቸውና መቁሰላቸው ይታወቃል፡፡
ከዚህ ሁሉ በኋላ የታሰሩት የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች ክስ ተመስርቶባቸው ፍ/ቤት የቀረቡ ሲሆን ፍ/ቤቱ ክሳቸው ዋስትና እንደማያስከለክላቸው በመግለፁ በዋስ ተለቀዋል፡፡ ከዚያ በኋላም የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ አምስቱን የዞን አመራሮች ከኃላፊነታቸው አንስቷቸዋል፡፡
በዞኑ ወቅታዊ ጉዳይ፣ ታገደ በተባለው የዞኑ ፋይናንስ፣ ክልል ድረስ እርቅ እናውርድ ብለው ሄደው ቀና ምላሽ አላገኙም ስለተባሉት የወላይታ የሀይማኖት አባቶች የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ ከዞኑ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ ወ/ሪት ሶሊያና አዲሎ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች፡፡   

               በአሁን ወቅት ወላይታ ዞን በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል? አጠቃላይ የዞኑ ድባብና የህዝቡስ ስሜት ምን ይመስላል?
አሁን ያለው ሁኔታ ትንሽ ለመግለጽም አስቸጋሪ ነው፡፡ አልፎ አልፎ የንግድ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ ነገር ግን ህዝቡ በጭንቀት ላይ ነው የሚገኘው፡፡ ምክንያቱም የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች ከእስር የወጡት በዋስ ነው፡፡ ይህን ተከትሎ የተለያዩ መረጃዎች ይወጣሉ፡፡ “አሁን ሊወስዷቸው ነው፤ አሁን ሊይዟቸው ነው፤ እንዲህ ሊሆን ነው፤ እንዲህ ሊደረግ ነው” የሚባል ነገር አለ፡፡ ሁሉም የዞኑ ህዝብ “ነገ ምን ይመጣ ይሆን?” በሚል ጆሮውን አቁሞ እያዳመጠና እየተጨነቀ ነው ያለው፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ ዞኑን እየመራ ያለው ኮማንድ ፖስት ነው፤ መንግስት አለ ማለት አይቻልም፡፡ ለምን ብትይኝ… አምስቱም ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች  ከሃላፊነት ተነስተዋል፡፡
የፍርድ ሂደታቸውስ?
በእስር ላይ እያሉ ክስ ተመስርቶባቸው ፍ/ቤት ከቀረቡ በኋላ አቃቤ ህግ የ14 ቀን ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ጠየቀ፡፡ ፍ/ቤት ደግሞ ጉዳዩን ካየ በኋላ “ጉዳዩ ዋስትና አያስከለክልም” ብሎ  ነሐሴ 7 በዋስ ለቋቸዋል፡፡ ነገር ግን አሁን አቃቤ ህግ ይግባኝ ጠይቋል፤ “በዋስ መፈታት የለባቸውም፤ ጉዳዩ ከባድ ስለሆነ መፈታታቸው ችግር ይፈጥራልና እስር ቤት ሆነው ይከታተሉ” የሚል፡፡
ከዚያስ?
ከዚያ በኋላ ፍ/ቤት ቀርበው ተጨማሪ 7 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸዋል፡፡ ነሐሴ 27 ሀዋሳ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ፡፡ የክልሉ ፍርድ ቤት ሶዶ ላይ ምድብ ችሎት እያለው ለምን ሃዋሳ እንዲቀርቡ እንደተፈለገ አልገባንም፡፡
የሀገር ሽማግሌዎች “ጉዳዩ በውይይት ይፈታ፤ ያሉት ነገሮች ይፈተሹ” በሚል ወደ ክልል ሄደው ቀና ምላሽ እንዳላገኙ እየተነገረ ነው፡፡ በዚህ ላይ ማብሪሪያ ቢሰጡን?
እውነት ነው፡፡ ረቡዕና ሐሙስ (ነሐሴ 13 እና 14 ቀን) “ይህ ጉዳይ ወዳልተገባ ነገር መሄድ የለበትም፤ በውይይትና በንግግር ለመፍታት የሚቻልበትን መንገድ በጋራ እንፈልግ” ብለው የክልል ባለስልጣናትን ለማነጋገር የዞኑ የሀገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶች ወደ ሐዋሳ ሄደው ነበር፡፡ የክልሉ ባለስልጣናት ሊያነጋግሯቸው አልፈለጉም፡፡ ረቡዕም ሐሙስም ቢለምኑም ቢንከራተቱም ከክልሉ ባለስልጣናት ቀና ምላሽ ሊገኝ አልቻለም፤ ሊያነጋግሯቸው ፈቃደኛም አልሆኑም፡፡ በመጨረሻም ሐሙስ ማምሻውን ወደ ዞኑ ለመመለስ ተገድደዋል፡፡
እስኪ የታሰሩትን ሰዎች ሥም ዝርዝር ይንገሩን? አሁን የዞኑ የመንግስት መስሪያ ቤቶችስ ተከፍተዋል?
የታሰሩት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳገቶ ኩምቤ፣ የዞኑ የብልጽግና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጥበቡ ዮሐንስ፤ በብልጽግና ጽ/ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊዋ ወ/ሮ ፀሐይ ገ/ሚካኤል፣ የብልጽግና ጽ/ቤት የፖለቲካ አደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊ አቶ ሚካኤል ሳኦል ናቸው፡፡ በእስር ላይ የነበሩት አሁን ስራ ላይ አይደሉም፡፡ የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ከሃላፊነት አንስቷቸዋል፡፡ የክሱም ሂደት ቀደምም ሲል እንደነገርኩሽ ፍ/ቤት ቀርበው ተጨማሪ 7 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸዋል:: ሃዋሳ የክልሉ ፍ/ቤት ነሐሴ 27 ይቀርባሉ፡፡  የመንግስት መስሪያ ቤቶችን በተመለከተ ሌሎቹ የዞን ካቢኔ አባላት አሉ:: እንዲሁም ወረዳ ላይ ያሉ አመራሮችን ስራ ለማስገባት ነበር ከኮማንድ ፖስቱ ጋር የተነጋገርነው፡፡ እንዳልኩሽ ላለፉት ጊዜያት አካባቢውን እየመራ ያለው ኮማንድ ፖስት ነው፡፡ ባለፈው ሰኞ ነሐሴ 4 “ሁሉም ሰራተኛ ወደ ስራው ይመለስ” በሚል የተለያዩ ውይይቶችን አድርገን እንቅስቃሴ ለመጀመር ሞክረን ነበር፤ ነገር ግን ማክሰኞ ነሐሴ 5 ቀን ምንም አይነት የፋይናንስ እንቅስቃሴ እንዳይደረግ እገዳ ተጣለ፡፡
ማን ነው እገዳውን የጣለው?
ከክልሉ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ተደውሎ ነው “ፋይናንስ እንዳይንቀሳቀስ” እገዳ የተጣለው፡፡ አብዛኛው ዞን ላይ ያሉ ባለሙያዎች ወረዳና ቀበሌ…  ድረስ ወርደው ነው ድጋፍ የሚሰጡት፤ በየሴክተሩ ማለት ነው፡፡ ጤናው በጤናው በኩል፣ ግብርናው በግብርናው በኩል፣ ሌሎች ሴክተሮችም በተመሳሳይ ድጋፍ የሚያደርጉት ወረዳና ከተማ አስተዳደሮች ላይ ለሚገኙ መዋቅሮች ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ አበል ተጽፎ ነው ሰራተኛ ስምሪት የሚጀምረው:: እናም ወደዚህ እንቅስቃሴ ለመግባት ስንል ነው የፋይናንስ እገዳው የተጣለው፡፡ የክልል ኢኮኖሚና ፋይናንስ ልማት ቢሮ በምን አግባብ በስልክ ደውሎ የዞኑን ፋይናንስ ሊያግድ እንደቻለ አልገባንም፤ ምክንያቱም የዞኑ ፋይናንስ ሃላፊ ተጠሪነቱ ለዞኑ አስተዳዳሪ ነው፡፡
ከዚህ በኋላ የዞኑ ፋይናንስ ሃላፊም ይህንን መልዕክት ለወረዳና ለከተማ አስተዳደሮች አስተላልፎ “ምንም አይነት እንቅስቃሴ አይኑር” ተብሎ ነው ትዕዛዝ የተሰጠው፡፡ በዚህ ምክንያት ሰራተኛውንም ወደ ስራው ማስገባት አልተቻለም፡፡ ችግሩ ከተፈጠረና አመራሮችም በዋስ ከተፈቱ በኋላ ሰው ወደ መደበኛ ሥራው እየተመለሰ ነበር፤ ነገር ግን የፋይናንስ እገዳው መልሶ እንቅፋት ሆኖብናል፡፡ ይህን ተከትሎ ሌሎች ሥጋቶችም በህዝቡ ላይ እየመጡ ነው ያሉት፡፡
ዞኑን የሚመራ ጊዜያዊ አስተዳዳሪ ተሹሟል የሚሉ ጭምጭምታዎች ነበሩ፡፡ እውነት ነው?
ይሄ እንኳን ሃሰት ነው፡፡ እስካሁን ከወሬ በዘለለ የወላይታ ዞን አስተዳዳሪ ነኝ ብሎ የመጣ አካል አልነበረም፡፡ ሌላው የዞን አስተዳዳሪን የሚሾመው ምክር ቤት ነው፡፡  አቶ ዳገቶንም የሾመው ምክር ቤት ነው፡፡ ሌላ አስተዳዳሪ መሾም ካለበትም የሚሾመው በዚህ መሰረት  ነው፡፡ እስካሁን ስብሰባ የተቀመጠም የተጠራም የምክር ቤት አባል አልነበረም፡፡ ህዝቡም ዘንድ በዚህ በኩል በግልጽ የደረሰ መረጃ አልነበረም:: በእርግጥ ትላንት ነሐሴ 12 ለውይይት ነው በሚል የምክር ቤት አባላትን ለስብሰባ ጠርተው ዶ/ር እንድሪያስ ጌታን በዞን አስተዳዳሪነት መሾማቸውን ሰምቻለሁ፡፡
የሃላፊዎችን መታሰር ተከትሎ፤ ህዝቡ ቁጣውን ለማሰማት በወጣበት ጊዜ የፀጥታ ሃይል በወሰደው እርምጃ በርካታ ሰዎች መሞታቸው ይነገራል፡፡ ነገር ግን ይሄን ያህል ነው ተብሎ በግልጽ የተቀመጠ ቁጥር የለም፡፡ ምን ያህል ሰው ሞተ? ምን ያህል አካል ጐደሎ የወደመስ ንብረት?
ንብረትን በተመለከተ አንድም ንብረት አልወደመም፡፡ ህዝቡ በሰላማዊ መንገድ ነበር ተቃውሞውን ሲያሰማ የነበረው፡፡ ህዝቡ ጋ የነበረው ስሜት አሁን ልገልጽልሽ በምችለው ልክ አልነበረም፡፡ ለምን ብትይኝ… የዞኑ ከፍተኛ ባለስልጣናት ስብሰባ ላይ እያሉ ባልተረጋገጠ መረጃ ነው ታፍሰው የተወሰዱት፡፡ የተሳሳተ መረጃ ወጥቶ ነው ያ ነገር የተፈጠረው:: አመራሮቹን ሊይዙ የመጡ ሰዎች እንኳን ተነግሯቸው የመጡትና የጠበቁት ነገር በአካል መጥተው ካዩት ነገር ጋር አይገናኝም ነበር፡፡
የወጣው የተሳሳተ መረጃ ምን ነበር?
እዚህ አካባቢ የገባ መሳሪያ እንዳለና  ሌሎች ጉዳዮች እንዳሉ ነበር መረጃው የደረሳቸው:: ነገር ግን ከመጡ በኋላ ያዩት ከተነገራቸው የተለየ ነው የሆነባቸው፡፡
ዋናው የስብሰባው ዓላማ ግን ምን ነበር?
ከክልልነት ጥያቄ ጋር የተያያዘ ነው:: እዛ ስብሰባ ላይ ሲሳተፉ የነበሩት ቅድም የጠቀስኩልሽ አምስቱ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች፣ ምሁራን፣ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች፣ የየለጋ ተወካዮች ነበሩ፡፡ ስብሰባው በክልልነት ጥያቄው ላይ ምን ሁኔታዎች አሉ? ጥያቄያችን እንዴት ይመለሳል? በሚል የምክክርና ሰላማዊ የውይይት መድረክ ነበር፡፡ ይሄ ደግሞ አዲስ አይደለም፡፡ በተደጋጋሚ ስብሰባ ሲደረግበት የቆየ ጉዳይ ነው፡፡
ኢሰመጉም ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በዕለቱ “ህገ-መንግስቱን በሃይል ለመናድ ሲንቀሳቀሱ አግኝቻቸዋለሁ” በሚል ለእስር ተዳርገዋል መባሉን ጠቁሟል:: በሌላ በኩል፤ ፌደራል መንግስትና ክልሉ ሳያውቅ “የወላይታን ክልልነት ለማወጅ የተጠራ ስብሰባ” የሚሉም አሉ፡፡ በዚህ ላይ እርስዎ ምን ይላሉ?
ይሄ ከእውነት የራቀ የወላይታን ህዝብ ማንነትና ሰብዕና የማይወክል ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም የወላይታ ህዝብ ጨዋና አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል የተማረ ነው፡፡ እያንዳንዱን መብትና ግዴታውን ጠንቅቆ የሚያውቅ ህዝብ ነው፡፡ ስለዚህ በራሳችን ደረጃ ዝግጅት አድርገን ስለጨረስን “ዛሬ የወላይታን ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትነት እናውጃለን” ብሎ የሚያስብ ሰው በዞናችን አለ ብዬ አላስብም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በየጊዜው ሰላማዊ ውይይት ሲደረግ ነበር:: ትግሉም ሲመራ የነበረው በሰላማዊ መንገድ ነው፡፡ ከሌሎች አጐራባች ህዝቦች ጋር ያለንን አብሮነት በማያበላሽ መልኩ አንዲት ብርጭቆ ሳትሰበር ይከናወን የሚል መርህ ነበር የወጣው:: ያንን በሚገባ ያሳየ ጨዋና ትዕግስተኛ ህዝብ ነው፤ የወላይታ ህዝብ፡፡ የሌላው አካባቢ አመጽና ሁከት ውጤት የታወቀ ነው፡፡ እኛ ግን ለሌላው አካባቢ ህዝብ ምሳሌ መሆን አለብን፤ በጠረጴዛ ዙሪያ ድርድርና ውይይት ተደርጐ ህገ - መንግስታዊ ጥያቄ፣ በህገመንግስት መመለስ እንደሚችል ማሳየት እንችላለን የሚለውን እምነት በህዝቡ ውስጥ አስርፀን፣ እስካሁንም በየመድረኩ ይሄ እየተገመገመ ነው እዚህ የደረሰው፡፡ ወጣቱ እንኳን በየጊዜው ስሜታዊ ሲሆን፤ ከፍተኛ አመራሮች እያበረዱ እያወያዩ ነው የመጡት፡፡ በተለይ የክልልነት ጥያቄው ለክልል ምክር ቤት ቀርቦ ምላሽ ሳያገኝ አንድ አመት በሞላበት ጊዜ፣ ወጣቱ በጣም ስሜታዊ ሲሆን ነበር፡፡ “አሁን ሰላማዊ ሰልፍ አያስፈልግም፤ እዚህ ውስጥ ፀረ ሰላም ሃይሎች ይገቡና ህዝባችን ላይ ጉዳት ይደርሳል” በሚል ታስረው የነበሩት አመራሮች ወጣቱን እያረጋጉ፣ ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር እየተወያዩና እየመሩ ነው፡፡
አሁን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ቤተ መንግስት ውስጥ ከደቡብ ክልል አመራሮች ጋር የጋራ ውይይት ነበራቸው፡፡ እዛ ላይ ግልጽ የሆነ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ አዲስ የተቋቋመ ኮሚቴ አለ፡፡ ይሄ ኮሚቴ በአጭር ጊዜ ውስጥ ግልጽ የሆነ ነገር ይዞ እንዲመጣ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ አሁንም ቢሆን የወላይታ ህዝብ ህገ - መንግስታዊ ጥያቄ፤ ወላይታ ክልል እንዲሆንለት ነው፡፡ እስካሁንም የመጣው ጥያቄያችን ህገ - መንግስታዊ ስለሆነ፤ ህገመንግስታዊ መልስ ያሻዋል የሚል ነው፡፡ ይሄ ነው የወላይታ ህዝብ ፍላጐት፤  የአመራሮች ብቻ ተደርጐ ሊወሰድ የተሞከረበት አካሄድ ትክክል አይደለም፡፡ እንዳልኩሽ ኮሚቴው የተሰጠውን የቤት ስራ ጨርሶ ሲመለስ በፌደሬሽን ምክር ቤት በኩል ቁርጥ ያለ ምላሽ ይሰጣል ተብሎ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
ቅድም ያልመለሱልኝ ጥያቄ አለ፡፡ በግጭቱ ምን ያህል ሰው ሞተ? ምን ያህልስ የአካል ጉዳት ደረሰ?
ብዙ ሰው ሞቷል፡፡ የ8 ወር ነፍሰጡር፣ የ10 አመት ታዳጊ፣ የ28 ዓመት የድግሪ ምሩቅን ጨምሮ በርካታ ሰው ሞቷል፡፡ የፀጥታ መዋቅሩ አጣርቶ ይህን ያህል ነው እስኪል ድረስ ግን ቁጥሩን በግልጽ ማስቀመጥ አልቻልንም፡፡ ገና በአግባቡም ያልተረጋጋንበት ጊዜ ላይ ነን፡፡  ሌላው በሆስፒታል በሞትና በህይወት መካከል ላይ የሚገኙ ሰዎች አሉ፤ ስለዚህ ምን ያህል ሰው ሞተ? ምን ያህሉ ተጐዳ?... የሚለውን ትክክለኛ ቁጥሩ ሲደርሰን ይፋ እናደርጋለን፡፡
ባለፈው ሌዊ ሪዞርት ስብሰባና ውይይት ምን ነበር በምንስ ተቋጨ?
በውይይቱ ላይ እነዚህን ውይይቶች ወደ ህዝብ ከማውረዳችን በፊት ጥያቄችን ይመለስ አልን፡፡ ጥያቄያችን “የዞኑ አመራሮች ክስ ይቋረጥ፤ የሰሩት ወንጀል የለም የክልልነት ጥያቄ ነው የጠየቁት፤ ይሄ ደግሞ ህገ - መንግስታዊ ጥያቄም ነው መብታችንም ነው እስካሁንም የመሩት ትግል ከፌደራል መንግስት ጋር እየተመካከሩ እንጂ ብቻቸውን አይደለም፤ የክልልነት ጥያቄ ወንጀል ከሆነ ሁላችንም ወንጀለኞች ነን፡፡ አብረን እንጠየቅ? ነው ህዝቡ ያለው፡፡
በሌላ በኩል፤ በከንቱ ህይወታቸው ለጠፋው ወገኖቻችን ሃላፊነት የሚወስድ አካል ይኑር እያለ ነው ህዝቡ፡፡ ለጠፋው ነፍስ አመራሮቹንና መላውን የወላይታ ህዝብ ሚዲያ ላይ ወጥተው ሲፈርጁ የነበሩ አካላት በሚዲያ ወጥተው ህዝቡን ይቅርታ ይጠይቀ የሚል ጥያቄ ተነስቷል::” ይሄም ምላሽ ሳያገኝ ሁሉም በእንጥልጥል ላይ ነው ህዝቡም በጭንቀት ላይ ነው” የሚገኘው፡፡


Read 1463 times