Saturday, 29 August 2020 11:17

የአገረ መንግስት ግንባታ፣ የኢትዮጵያ አንድነት፣ ብሔራዊ መግባባት?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

      ፕ/ር መረራ ጉዲና ውዝግብ ባስነሳው ጽሑፋቸው ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል

                    ባለፈው ቅዳሜ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የስብሰባ አዳራሽ በተዘጋጀው የፖለቲካ ፓርቲዎች የብሔራዊ መግባባት መድረክ ላይ ፕ/ር መረራ ጉዲና #በኢትዮጵያ አገረ መንግስት ግንባታ የታሪክ ዳራ፤ በእኩልነት ላይ የተመሠረተች ሀገር ለመፍጠር የተደረጉ ሙከራዎች፤ ያጋጠሙን የታሪክ ፈተናዎችና ያመለጡን እድሎች በብሔራዊ መግባባት መነጽር ሲታይ” በሚል ርዕስ ያቀረቡት ጽሑፍ ሲያወዛግብና ሲያስነቅፋቸው ሰንብቷል፡፡ ለምን? ለትችትና ለነቀፌታ የዳረጓቸው ጉዳዮች ምንድን ናቸው? ፕ/ሩ በጽሁፋቸው ባነሷቸው አወዛጋቢ ታሪኮች፣ በኢትዮጵያ አንድነት እንዲሁም በብሔራዊ መግባባት ጉዳዮች ዙሪያ  ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡



               ባለፈው ቅዳሜ ባቀረቡት ጽሑፍ ላይ በርካታ ትችት ተሰንዝሮዎበታል፡፡ ለምንድን ነው ተቃውሞና ትችቱ የበዛው ይላሉ?
አንተ የምትለውን ያህል ብዙ ትችት አልገጠመኝም፡፡ በሚዲያዎች አካባቢ ነው እንጂ በመድረኩ ላይ ብዙም ተቃውሞ አልገጠመኝም:: ዞሮ ዞሮ ችግሩ ምንድን ነው ከተባለ የተሰጠኝ ርዕስ ነው፡፡ አዘጋጆቹ ናቸው ርዕሱን የሰጡኝ፡፡ እንደውም ለኔ ይቀርበኝ የነበረው በፌደራሊዝም ጉዳይ ላይ ነበር፤ ነገር ግን አዘጋጆቹ፤ "የኢትዮጵያ አገረ መንግስት ግንባታ የታሪክ ዳራ" የሚለውን ርዕስ ሰጡኝ፡፡ እኔ ፈልጌ የመረጥኩት አይደለም፡፡ ግን አቅርብ ከተባልኩ ደግሞ ምንም የሚቸግረኝ ነገር ስለሌለ አቅርቤያለሁ፡፡ ሌላው በዚህ ሂደት የታዘብኩት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የእውቀት ችግር መኖሩን ነው፡፡ የእውቀት ችግር እንዳለ በግልጽ  ታይቷል፡፡
እንዴት?
ለምሣሌ የኔ ርዕስ፡- ዘመናዊ ኢትዮጵያ እንዴት ተፈጠረች? ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት የተደረጉ ሙከራዎች  ምንድን ናቸው? ለምን እነዚያ ሙከራዎችስ አልተሳኩም? የሚለውን ነው በግልጽ ቋንቋ በተሰጠኝ 20 ደቂቃ ለማቅረብ የሞከርኩት:: በተሰጠኝ 20 ደቂቃ ዋና ዋና ያልኩትን እንጂ ሁሉንም ማቅረብ አልችልም፡፡ ሳቀርብም የኔን ሃሳብ ብቻ አይደለም፤ ከሁሉም አጣቅሼ ነው፡፡ ይሄን በእውቀት መረዳት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ሶስት ነገር ነው መገንዘብ ያለብን፡፡ አንደኛው፤ ምኒልክ ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ ያደረጉት መስፋፋት ወይም ሠፊ ግዛት የመፍጠሩ ሙከራ እንዴት ነው በሚል ሶስት ትላልቅ ጦርነትን ነው ያነሳሁት፡፡ የአርሲ አካባቢ ጦርነት አንዱ ነው፡፡ ከዚህ በፊት በጉልበትና በሃይል በተፈጠረችው ኢትዮጵያ ምን አይነት የፖለቲካል ኢኮኖሚ ስርአት ተፈጠረ የሚለውን ስንጠይቅ፤ ነፍጠኛ የምንለውን ስርአት እናገኛለን፡፡ ነፍጠኛ የሚባለውን ስርአትን ስናነሳ አጉል ነገር ውስጥ እንዳንገባ መጠንቀቅ አለብን:: የዚያ ስርአት አገልጋዮች ብዙ ነበሩ:: በደም ቆጠራ ከሆነ አማራ የሚባለው እዚያ ውስጥ በቁጥር ትንሽ ነው፡፡ አማራና ነፍጠኛን ማገናኘት ግፍ ነው፡፡ የጐንደር፣ የጐጃም ገበሬ ምን እድልና አቅም ነበረውና ነው የባሌን የአርሲን ገበሬ የሚገድለው? ነገር ግን ተንቀሳቅሶ መሬት የዘረፈ፣ የጨቆነ፣ ግፍ የሠራ ደግሞ አልነበረም ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን የፖለቲካ ልሂቃኑ ለምን ነፍጠኛን ወደ አማራ እንደሚወስዱት አላውቅም:: እንግዲህ ከአብዮቱ ጀምሮ በሚደረገው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ከአማራ የፖለቲካ ልሂቃን ጋር በዚህ ጉዳይ በብዙ መልኩ እንስማማለን፤በማንስማማባቸውም ልዩነቶችን ይዘን በጋራ መስራት ባለብን ላይ እንሠራለን፡፡ ዛሬ እነዚህን መሰል በእውቀት የደረጁ የፖለቲካ ልሂቃን የሉም፡፡
ለዚህ ነው ዛሬ የእውቀት ችግር አለ ያልኩት፡፡ የቀድሞው ፖለቲካ ውግንናን ሳይሆን እውቀትን መሠረት ያደረገ  ነበር:: እኔም ሳቀርብ ያነበብኩትን፣ እውቀት አላቸው ብዬ ያመንኩባቸው የፃፉትን ነው ለውይይት ያቀረብኩት፡፡ ለምሣሌ አንዱ በጽሑፉ የጠቀስኩት ተሻለ ጥበቡ የሚባል የጐጃም ሰው፣ የፖለቲካል ሳይንስና የአፍሪካን ስተዲስ ፕሮፌሰር ነው፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፖለቲካል ሣይንስ ዲፓርትመንት ያስተምር የነበረ ምሁር ነው:: አሁን በአሜሪካ የሚኖር ሲሆን “ዘመናዊት ኢትዮጵያ ከአድዋ እስከ አፄ ኃይለሥላሴ መውረድ ድረስ; (The Making Of Modern Ethiopia) በሚል ያቀረበው ጥናት አለ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሁሉም ይሄን ጥናት እንዲያነበው እመክራለሁ፡፡ ይሄ ሰው ያቀረበው ነገር እኔ ካቀረብኩት ይበልጣል፡፡ የሱ ትንተና ሰፊ ነው፤ ኢትዮጵያ የተፈጠረችበትንና ችግሮቹን ያነሳበት መንገድ በእርግጠኝነት ከኔ የበለጠ የጠበቀ ነው፡፡ ይሄን ማንም አንብቦ ሊረዳው ይችላል:: እነዚህን መሰል እውቀትን መሠረት ያደረጉ ነገሮችን ያለማወቅም ይመስለኛል አሁን ችግር ውስጥ የከተተን፡፡
በአገረ መንግስቱ ግንባታ ላይ በልሂቃኑ መካከል ያሉት መሰረታዊ ልዩነቶች ምንድን ናቸው?
እውቀትን መሠረት አድርገን ነገሩን ከመረመርን፣ የምኒልክን የሀገረ መንግስት ምስረታ እንቅስቃሴ አንደኛው ወገን "ቀድሞ ከኢትዮጵያ ተለይተው የነበሩ ግዛቶችን መልሶ አንድ የማድረግ ስራ ነው" የሚል እምነት አለው፡፡ በምን አመናችሁ ማለት አይቻልም፤ መብታቸው ነው፤ በዚህ ፀብ ማንሳትም ትክክል አይሆንም፡፡ ሌላኛው ደግሞ "የለም አፄ ምኒልክ ያደረጉት የግዛት ማስፋፋት ነው" የሚሉ አሉ፤ ሶስተኛው ደግሞ "ነፃ ህዝቦችን በጉልበት ጨፍልቀው ነው የያዙት፤ ይህም ቅኝ ግዛት ነው" የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እነዚህ አመለካከቶች ናቸው ወደ ሚጋጩ ህልሞች የወሰዱን፡፡ ጥያቄው መሆን ያለበት እነዚህን ህልሞች እንዴት እናስታርቃቸው የሚለው ነው:: እነዚህን ተንትኖ ማቅረብ ግን ለምን እንደ ስህተት እንደሚቆጠር አይገባኝም፡፡ እነዚህን የሚጋጩ ህልሞች ማስታረቅ ካልተቻለና የሆነ ቡድን "ከእኔ በላይ ኢትዮጵያን የሚወዳት የለም፤ ሌላው ኢትዮጵያን ሊያፈርሳት ነው" ብሎ ከደመደመ አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለዚህ ሁላችንም ወርደን ነው በስርአቱ መወያየት ያለብን፡፡
ከዚህ ቀደም ብዙዎች እርስዎን "በኢትዮጵያዊነታቸው የማይደራደሩ ናቸው" ብለው ያምኑ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን "የብሔር ጽንፍ እየያዙ ነው" የሚል ትችት ይሰነዘርብዎታል፡፡ ይህንን ለውጥ እርስዎ ተገንዝበውታል?
እኔኮ ትልቅ ችግር የገጠመኝ ድሮ ለምሣሌ "ኢትዮጵያ የሚባል አናውቅም፤ የኢትዮጵያን አንድነት አንቀበልም" የሚሉ ሃይሎች ስለነበሩ "የለም ኢትዮጵያ የሁላችንም ናት፤ ችግሮቿን ማስተካከል እንጂ የጋራ ሀገር ናት" የሚለውን ለማሳመን ነበር ጥረቴ፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው ኦነግን ጨምሮ ብዙ የኦሮሞ ብሔርተኞች አሁን "ኢትዮጵያም የኛ ናት፤ ግን ተገቢ የሆነ ቦታ እንፈልጋለን" ብለው አስመራ ሳይሆን አዲስ አበባ ነው ያሉት:: ስልጣን ሊወስዱብን መጡ ካልተባሉ በስተቀር ኦሮሚያን ለመገንጠል ነው አዲስ አበባ የመጡት የሚል የለም፡፡ ስለዚህ እንደውም እኔ ስጋቴ እነዚህ የኢትዮጵያዊነት ሰርተፍኬት ሰጪ ነን የሚሉ ወገኖች፤ ሰው ያላሰበውን እንዳያሳስቡ ነው:: ዋናው ወሳኝ ጉዳይ መሃል መንገድ ላይ መገናኘቱ ነው:: የኢትዮጵያዊነት ሠርተፊኬት ሰጪና ከልካይ ለመሆን መሞከር አደጋ አለው:: የኢትዮጵያዊነት ሠርተፊኬት ሰጪና ከልካይ አድርጐ ራሱን የሾመው ሃይል ትንሽ ማሰብ አለበት፡፡ ለምሣሌ በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን እነ ማሞ መዘምር፣ እነ ጀነራል ታደሰ ብሩ አንድም ቀን ስለ ኦሮሞ መገንጠል አስበው አያውቁም፤ ነገር ግን እነሱ በግፍ ሲገደሉ የኦሮሞ አዲሱ ትውልድ ተፈጠረ፤ የመገንጠልም ሃሳብ መጣ፡፡ ሌላው የኤርትራ መገንጠልን ካየን አፄ ኃይለሥላሴ ከሌላው ጋር ለማስተካከል ፌደሬሽኑን አፈረሱ፤ እነሱ ያላሰቡትን አሳሰቧቸውና ወዲያውኑ አንድ አመት ሳይሞላ ካይሮ ላይ ጀበሃ የሚባለው የኤርትራ ነፃ አውጪ ተፈጠረ፤ በዚህ ሀገሪቱ የከፈለችውን ዋጋ ሁላችንም እናውቀዋለን፡፡
ሌሎችም ያላሰቡትን እንዳሰቡ ተደርጐ ሲገደሉ ነው የኖሩት፡፡ እንዲህ እየሆንን ነው ዛሬ የአለም ጭራ የሆንነው፡፡ ስልጣን ላይ ያለን እይታ "የሸዋ ኦሮሞ" ከሚባሉት ሃብተ ጊዮርጊስ ከነበሩበት ዘመን ይስፋ ነው የኔ ሙግት፡፡ የሸዋ ፖለቲካ በዋናነት በእነማን እንደተያዘ እየታወቀ ለምን ጉዳዩ ወደ አማራ እንደሚወሰድ ለኔ ሁሌም ይገርመኛል፡፡ ለምን የኦሮሞና አማራ ህዝቦችን ለማጋጨት እንደሚወክሉ አይገባኝም:: በተለይ ሚዲያዎቹ ይሄን እያራገቡ የማይሆን ነገር ለምን እንደሚያደርጉ አይገባኝም፡፡ እኔንም በዚህ መንገድ ለመክሰስ የሚፈልጉ ወገኖች እስቲ ለጽሑፌ ማጣቀሻ አድርጌ የተጠቀምኳቸውን ያንብቡ፡፡ ማጣቀሻዎችን ስጠቀም ሁሉንም ወገን ይወክላሉ ያልኳቸውን ፀሐፊዎች ነው የመረጥኩት:: እነሱንም እስቲ በእውቀት ይመርምሩ:: ለምሣሌ ፊታውራሪ ሃብተጊዮርጊስ ልጅ ኢያሱን ከስልጣን ለማውረድ የተጠቀሙበትን ምክንያት የወሰድኩት ከፕ/ር ባህሩ ዘውዴ መጽሐፍ ነው፡፡ ምናልባት እንግዲህ አሁን ጫጫታው የበዛው ሀገሮች እንዴት እንደተገነቡ አንብቦ በእውቀት ይረዳ የነበረው ትውልድ ስለተገፋና ፖለቲካውም ወደ ጨረባ ተዝካርነት እየተለወጠ ስለመጣ ይመስለኛል፡፡ ያለፈ የተዛባ ግንኙነታቸውን በመገምገም አስተካክለው ወደፊት የተሻገሩ የአለም ሀገሮችንም በጽሑፌ በምሣሌነት ጠቅሼአለሁ፡፡ እነዚህንም በእውቀት በደንብ መመርመር ማጥናት፣ የእነሱን ጥረትና ስኬት ማንበብ ያስፈልጋል:: ይሄ ሳይሳካላቸው ዛሬም የሚማቅቁ ሃገሮችን ችግርም መመርመር ያስፈልጋል:: እኔ ከእነዚህ ውስጥ የራሳችንን አህጉር አጣቅሼ ዴሞክራቲክ ኮንጐ ሪፐብሊክን አንስቻለሁ:: ኮንጐ በአለም ላይ አሉ የሚባሉ የማዕድናትና የተፈጥሮ ፀጋዎች ባለቤት ነች:: ከማንም ሀገር የተሻለች፣ ኒውክለር መሣሪያ ራሱ በቀላሉ መስራት የምትችል ሀገር ነበረች:: ግን ዛሬ አለም የሚያውቃት በሌላ ነው:: ለዚህ ምክንያቱ የፖለቲካ ብልሽት ነው:: ፖለቲካቸው በመበላሸቱ ህዝቡ ዋጋ እየከፈለ ነው፤ የሚራቡበት ጊዜ ሁሉ አለ፡፡
ፈረንጆች ግን አለመግባባታቸውን ተጠቅመው ሃብታቸውን እየዘረፉ ነው:: ሌላዋ የ3ሺህ አመት ታሪክ አለኝ የምትለው የኛዋ ኢትዮጵያ ነች፡፡ ላለፉት 60 አመታት ምን የፖለቲካ ስኬት አገኘች? የጦርነትና ግጭት ታሪካችን የት አደረሰን? የሚለውን ነው በጽሑፌ የጠየቅሁት:: ከችግሩ ለመውጣትም 10 ዋነኛ አመላካቾች አስቀምጫለሁ::  ሌላውም የራሱን ያስቀምጥ:: በዚህ መንገድ ነው እየተረዳዳን ወደፊት መሻገር የምንችለው:: ሃይልና ጉልበትን መተማመን የትም አያደርሰንም:: ያለፉትን ዘመናት ሞክረነው አይተነዋል፤ ወደፊት አላሻገረንም፡፡ እንኳን እኛን በኒውክሌር የበለፀገችውን፣ ሃይል የታጠቀችውን ሶቪየት ህብረትንም የጉልበት አካሄድ ከመፈራረስ አላዳኗትም፡፡ ስለዚህ አሁን ለገጠመን ፖለቲካዊ ችግር መፍትሔው ፖለቲካዊ ብቻ ነው:: በውይይት ነው መፍታት ያለብን፡፡ ሌላው በታሪካችንም ውጤት አላመጣም:: የኔ ጽሑፍ መልዕክት፡- "በሰይፍ ላለፉት 150 አመታት ተሞክሮ አላዋጣም፤ አሁን አዲስ ምዕራፍ መጀመር አለብን" የሚል ነው፡፡ ይሄን ስላልኩ ለምን ብዙ ሰው እንደጮኸ አልገባኝም፡፡ "እኛ የኢትዮጵያ ፍቅር አለን" የሚሉ ወገኖች፤ ኢትዮጵያን ከኛ የተሻለ የመውደድ መብት ቢኖራቸውም፣ የሚወረውሩት ነገር ግን ኢትዮጵያን እንዳያጠፋት መጠንቀቅ አለባቸው:: "እኛ ለኢትዮጵያ ልዩ ፍቅር አለን፤ ጠበቃዋ ነን፤ ሌሎቹ ጠላቶቿ ናቸው" የሚለውን አካሄድ ላለፉት ብዙ ዓመታት አልፈንበታል፤ ግን ውድ ዋጋ ከማስከፈል ውጭ ያመጣው ለውጥ የለም፡፡  
በኢትዮጵያ አንድነት ላይ የእርስዎ አቋም ምንድን ነው?
እኔ’ኮ በመኢሶን ውስጥ ያደግሁ ነኝ:: የኔ ዋና ጉዳይ፤ ኢትዮጵያን ለሁሉም የምትሆን አድርገን እንፍጠራት የሚል ነው:: በየትኛውም የቡድን የበላይነት የተመራች ኢትዮጵያ የትም አላደረሰችንም፡፡ እኔ አውቅልሃለሁ ማለት ኤርትራን ከመገንጠል አላዳናትም፡፡ ስለዚህ በሚያቀራርቡን ጉዳዮች ላይ ለመድረስ ችግሮችን አውጥተን በግልጽ እንነጋገር፡፡ እኔ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ከመኢሶን ጀምሮ እስካሁን ድረስ የአቋም ለውጥ የለኝም፡፡ ግን ስንተች ሰው ያላሰበውን ባናሳስብ የተሻለ ነው፡፡
በጽሁፍዎ ላይ ከተሰነዘረብዎ ትችቶች አንዱ፤ "ማስረጃ የማይቀርብበትን የአኖሌ ጉዳይ በጽሑፍዎ ማንሳትዎ ተገቢ አይደለም፤ ሃሰተኛ ትርክቶችን የፖለቲካ መወዛገቢያ ማድረግ አያስፈልግም" የሚል ነው፡፡ ለዚህ ትችት ምላሽዎ ምንድን ነው?
በጽሑፌ ላይ ይሄን አንስቻለሁ፤ ለምን በደንብ እንደማይጤን አይገባኝም፡፡ ምኒልክ ሶስት ወሳኝ ጦርነቶች ተዋግተዋል፡፡ አንደኛው ዛሬ ምዕራብ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ የሚባለው እምባቦ ላይ የተዋጉት ነው፤ ሌላው ጨለንቆ ሲሆን ሦስተኛው አርሲ - አኖሌ ነው፡፡ ይሄ ጦርነት መደረጉን የምኒልክ ታሪክ ፀሐፊዎችም ጽፈውታል፡፡ የአርሲ ጦርነት እንደ ሌሎቹ ቀላል አይደለም፡፡ በጣም ጠንካራና ተደጋጋሚ ጦርነት ነው፡፡ ከ4 አመታት በላይ ነው ጦርነት የተካሄደው:: እነ ራስ ዳርጌ ተሸንፈው የተመለሱበትና በመጨረሻ ምኒልክ ራሳቸው የዘመቱበት ጦርነት ነው፡፡ አርሲ ቀላል የማይባል የመከላከል ጦርነት አድርጓል፡፡ ምኒልክ በዚያ ተበሳጭተውም ሊሆን ይችላል፤ ተደርጓል የተባለውን ያደረጉት፡፡ ይሄ’ኮ የ100 አመት ታሪክ ነው፡፡ አያቴ የኖሩበት የታሪክ ዘመን ነው:: ሩቅ አይደለም፤ ቦታው እኮ ቅርብ ነው፤ ሄዶ የታሪክ ጥናት ዘዴዎችን ተጠቅሞ ማጥናት ብቻ ነው የሚያስፈልገው፡፡ እንኳን አያቶቻችን የኖሩበት ቀርቶ ከሺህ አመታት በፊት የነበረ ታሪክ ተጠንቶ ይፃፍ የለም እንዴ፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ደግሞ ታሪኩን በቃል ለልጅ፣ ልጅ ልጆቹ የማስተላለፍ ጥብቅ ባህል አለው፡፡ በጉዳዩ ላይ ፈረንጆችም ጽፈዋል፡፡ ከምኒልክ ሠራዊት ጋር ተጉዣለሁ ብለው የፃፉ ፈረንጆች ነበሩ፡፡
ምሣሌ ሊጠቅሱልን ይችላሉ?
"ዘ ኢምፔሪያል ማርች ቱ ታውዘንድ ኢትዮጵያ" ብለው የፃፉ ፈረንጆች አሉ:: እነሱን ማየት ይቻላል፡፡ ከዚያ ባለፈ ግን የታሪክ አጻጻፍን ከእነ ዘዴው የሚያውቁ ባለሙያዎች፣ ከ100 አመት በፊት በአያቶቻችን ዘመን የነበረን ታሪክ መፃፍና መመራመር እንዴት ይሳናቸዋል:: ለማንኛውም እኔ የጠቀስኩት አኖሌ አለ የለም የሚለው ክርክር አያዋጣንም:: ምክንያቱም እንደተደረገ የሚያምን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝብ አለ፡፡ ኦህዴድ በነበረው ንቃትም ያንን ሃውልት አቁሟል፡፡ አኖሌ የሚባለው ምንድን ነው? ምን ተፈጥሮ ነበር? የሚለውን በቦታው ያሉ ሰዎችን ጠይቆ፣ የታሪክ ጥናት ዘዴን ተጠቅሞ ማጥናት ይቻላል፡፡ እንዲሁ በደፈናው ግን ከ100 አመት በፊት የነበረን ያንተን ታሪክ የማውቀውና ልነግርህ የሚገባው እኔ ነኝ ማለት ተገቢ አይደለም፡፡ ቢያንስ ድርጊቱ ተፈጽሟል ብሎ የሚያምን በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ አለ፡፡ ከዚህ አጉል ክርክር ወጥተን ለበጐ ታሪክ እውቅና እንደሰጠነው ሁሉ ለጠባሳዎችም እውቅና እየሰጠን እየተግባባን መሄድ አስፈላጊ ነው፡፡ ሌላውም እኮ መሰል ጠባሳውን ይናገራል:: ከፋ፣ ወላይታ የየራሱ ታሪክ አለው፤ በእነዚያ ላይ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡
አኖሌ ብቻ አይደለም፤ ለምሣሌ ወደ አርሲ ሮቤ ስንሄድ አንድ የአካባቢው ሰው "ኑ አንድ ነገር ላሳያችሁ" ብሎ ሁለት ትናንሽ ኩሬ ያለበት ቦታ ወሰደን፤ ሰው ከዚህ ኩሬ ውሃ አይጠጣም:: ምክንያቱ ምንድን ነው? ስንል፣ "በምኒልክ ጊዜ ብዙ ወጣቶች የተኮላሹበት ቦታ ነው" ይላሉ ሽማግሌዎቹ:: ይሄን አሁን በዚህ ጽሑፍ አላካተትኩም:: ይሄን የሚያምን ሚሊዮን ህዝብ አለ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በታሪክ ጉዳይ አለ የለም የሚለውን ሙግት ትተን፣ ወደፊት እንዴት እንሂድ የሚለው ላይ እናተኩር ነው፤ የኔ ሙግት፡፡ እንዴት የታሪክ ቁስሎችን አስተካክለን የተስማማነውን ተስማምተን፣ ያልተስማማንባቸውን ምን አድርገን ወደፊት እንሻገር ነው የኔ ጥያቄ እንጂ የታሪክ ሂሳብ ማወራረድን አልጠየቅሁም፡፡ እንዲህ ያለውን ጥያቄም አልደግፍም፡፡
ከዚህ ቀደም “የአኖሌን ታሪክ ወያኔ ሃውልት ሠርቶ ሲያስመርቅ እንጂ እኔ አላውቀውም” እንዳሉ የሚጠቅሱ ተቺዎች፤ ዛሬ ፕሮፌሰር መረራ ምን ተገኘና ነው ያነሱት ሲሉ ይጠይቃሉ---
እኔ እንዲህ አይነት ነገር ተናግሬ አላውቅም፡፡ ፖለቲካል ሳይንስ እኮ ከታሪክ ነው የሚወጣው:: (History is the root; political science is fruit) ነው የሚባለው:: የምችለውን ያህል የኢትዮጵያን ታሪክ ለማንበብ ለመረዳት ሞክሬያለሁ:: እንደውም ፖለቲካል ሳይንስ ከታሪክ ትምህርት በተሻለ ታሪክን ለመረዳት የሚጥር የትምህርት ዘርፍ ነው፡፡ ስለዚህ እኔ የለም የምልበት ምንም ምክንያት የለኝም፤ ምናልባት "እነዚህን ነገሮች መቀስቀሱ ማራገቡ አይጠቅመንም፤ ወደፊት ማየት አለብን" ብዬ ሊሆን ይችላል::
ባለፉ የአገረ መንግስት ምስረታ ታሪኮች ላይ እንዴት ነው መግባባት ላይ የሚደረሰው? ካልተቻለ አማራጩ ምንድን ነው?
ይሄ አይነት ንትርክ እኮ ያለው እኛ ሀገር ብቻ አይደለም፡፡ ለምሣሌ ራሽያ ውስጥ "በርካቶችን የጨረሰው ጆሴፍ ስታሊን ነፍሰ ገዳይ ነው" የሚሉ አሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ "ጆሴፍ ስታሊን ታላቅ ሰው ነው፤ እሱ ባይኖር ኖሮ ዛሬ የጀርመን ቅኝ ተገዥዎች እንሆን ነበር" ብለው ይከራከራሉ፡፡ እንዲህ ያሉ የአረዳድ ልዩነቶች የትም ቦታ ይኖራሉ:: ኢትዮጵያ ውስጥ አፄ ምኒልክ በሠሯቸው ስራዎች "ዘላለማዊ ጀግና ናቸው" ብለው የሚያምኑ አሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ "ደም አፍሳሽ ቅኝ ገዥ ናቸው" ብለው የሚያምኑ አሉ፡፡ እነዚህም የኢትዮጵያ ልጆች ናቸው፡፡ ስለዚህ ዘላለማዊ ጀግና ናቸው የሚሉት አገረ መንግስት ግንባታቸው ላይ ምን እንደሠሩ ከአስተዋጽኦቸው ጋር አያይዘው መመለስ አለባቸው፡፡ በሌላ በኩል ደም አፍሳሽ ቅኝ ገዥ ናቸው የሚሉት ደግሞ ቅኝ ገዥ ማለት ምንድን ነው? እንዴት ከሁኔታው ጋር ይያያዛል የሚለውን  መመለስ አለባቸው:: ልዩነቶች አሉ:: ስለዚህ አንዱ ሌላውን ልዩነት አውቆ የታሪክ ሃሳብ ካላወራረድኩ የሚለውን ትቶ የዛሬይቱንና የነገይቱን ኢትዮጵያ ለመገንባት ምን እናድርግ ብሎ መነጋገርና አዲስ ውል መግባት ያስፈልጋል ነው አቋሜ፡፡ "ያንን ታሪክ ለምን ታነሳላችሁ?" ማለትም ትክክል አይሆንም:: ይሄ ለውይይትም ጥሩ አይደለም፡፡ ሰው የራሱ አመለካከት አለው:: እኔም አመለካከቴ ከየት እንደመነጨ በግልጽ መፃሕፍትን አጣቅሼ አስቀምጫለሁ፡፡ ስለዚህ አንዱ የሌላውን አመለካከት በማስረጃ በመረጃ በመሞገት ነው መቀራረብ የሚቻለው እንጂ ዝም ብሎ በጉንጭ አልፋ ንትርክና ስድብ የሚለወጥ ነገር የለም፡፡ የትም አያደርሰንም::
የአገራችን የፖለቲካ ልሂቃን በማስረጃና በመረጃ ተሟግተው ስምምነት ላይ ይደርሳሉ ብለው ያምናሉ?
ተነጋግረን መስማማት ከቻልን ጥሩ ነው፤ ካልተቻለ ግን የታሪክ ቁስሎችን በማይነካ መንገድ አብሮ ለመጓዝ መስማማት ያስፈልጋል:: የኔ ዋነኛ ሃሳብ፤ ከ100 አመት በፊት ከነበሩት ከእነ ፊታውራሪ ሃብተጊዮርጊስ የሰፋ እይታ ይኑረን ነው:: በሁሉም ነገር ላይ መስማማት የግድ አይሆንም፤ በሁለት ነገሮች ላይ ግን የግድ መስማማት አለብን፡፡ አንደኛው የጋራ አገር አለን በሚለው ላይ ነው፤ የጋራ አገር የለንም ከተባለ ችግር ውስጥ ተገባ ማለት ነው፡፡ ሁለተኛው ዲሞክራሲያዊ የሆነ አስተዳደር መመስረትና ሁሉንም እኩል የምታስተናግድ ኢትዮጵያን በመገንባት ላይ ከተስማማን በቂ ናቸው፡፡ እነዚህ ሁለቱ ለብሔራዊ መግባባት በቂ ናቸው:: ዛሬ "ኢትዮጵያ የኛ አይደለችም" ይሉ የነበሩ ሃይሎች ወደ መሃል እንዲመጡ ብዙ ጥረት አድርገን ተሳክቶልናል፡፡ አንዱ ያልተመዘገበልኝ ይሄ ጥረቴ ይመስለኛል:: ይሄን አይነት መቀራረብ ማጠናከርና ቢያንስ አስቀድሜ በጠቆምኳቸው ጉዳዮች መስማማት በቂ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን አንዱን ባንዳ፣ ሌላውን ልዩ የሀገር ፍቅር ያለው አድርጐ ለማቅረብ መሞከር አደገኛ ነው፡፡ ሰው ያላሰበውን እንዲያስብ የሚያደርግ ነው፡፡ ይሄ አካሄድ ሀገሪቱን ዋጋ ያስከፈለባቸው ጊዜያት በርካታ ናቸው፡፡ አፄ ኃይለሥላሴ ለሀገር ፍቅር የነበረውን ሁሉ ባንዳ ማለታቸው፣ ሀገሪቷን በሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ወቅት ዋጋ አስከፍሏታል:: ሰውን ባንዳ እያሉ ለመፈረጅ መሞከር አደገኛ ነገር ነው፡፡ ይሄ መስተካከል አለበት፡፡    

Read 6508 times