Saturday, 29 August 2020 11:04

የታገል ሰይፉ “የእንቅልፍ ዳር ወጐች” የልጆች መጽሐፍ ለንባብ በቃ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(3 votes)

  በኦሮሚኛ ቋንቋ እየተተረጐመ ነው ተብሏል

                 የገጣሚና ደራሲ ታገል ሰይፉ “የእንቅልፍ ዳር ወጐች” `Be time Story` አዲስ የልጆች መጽሐፍ ለንባብ በቃ፡፡ መጽሐፉ ፈረንጆች `Be time Story` የሚሉት አይነት ሆኖ በኢትዮጵያ ልጆች ቴሌቪዥን ከሚተርካቸው 7ቱን የተመረጡ ተረቶች እና 21 ስዕሎችን በመጽሐፉ ማካታቱን ታገል ሰይፉ ለአዲስ አድማስ ተናግሯል፡፡ ስዕሎቹ ልጆች ታሪኮቹን አንብበው ሲጨርሱ ከለር እንዲቀቧቸው ታስቦ የተሰሩ መሆኑም ታውቋል፡፡ መጽሐፉ በዋናነት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ቤት ለተቀመጡ ልጆች ታስቦ የተዘጋጀ ሲሆን የመጽሐፉ ሽፋን በሳኒታይዘር ፀድቶ ልጆች ተዋውሰው እንዲያነቡት የሚያስችልም ነው ተብሏል፡፡
መጽሐፉ በአሁኑ ሰዓት በተክሉ ተሲሳ (ሞቲ) ወደ ኦሮሚኛ ቋንቋ እየተተረጐመ ሲሆን በቅርቡም ለኦሮሚኛ ተናጋሪ ልጆች ይደርሳል ተብሏል፡፡
በህትመት መወደድ ምክንያት በኢትዮጵያ ልጆች ቴሌቪዥን ከተተረኩት በርካታ ተረቶች መካከል ሰባቱ ወጥ ታሪኮች በመጽሐፉ የተካተቱ ቢሆንም ቀሪዎቹን በተከታታይ ለማሳተም ባለሀብት እየፈለገ እንደሆነም ታገል ጨምሮ ገልጿል፡፡ ለህትመት የበቃው ይሄው የልጆች መጽሐፍ አምስት ሺው ኮፒ በሙሉ አዲስ አበባ በሚገኙት 18 የሸዋ ሱፐር ማርኬት ሱቆች ብቻ እንደሚገኝ የተገለፀ ሲሆን በ52 ገፆች ተቀንብቦ በ60 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡ መታሰቢያነቱም በተረት መጽሐፍታቸው ላሳደጉትና የተረት መጽሐፍ እንዲጽፍ ምክንያት ለሆኑት ለክቡር ዶ/ር ሃዲስ ዓለማየሁና ለዶ/ር ከበደ ሚካኤል መደረጉንም ገጣሚና ደራሲ ታገል ሰይፉ ጨምሮ ገልጿል፡፡

Read 19636 times