Tuesday, 25 August 2020 06:31

ሰለሞን ጎሳዬ ገዳ

Written by 
Rate this item
(7 votes)

 ኧረ ጉድ ባየህ ወዳጄ ኧረ ጉድ ባየህ ጓዴ!


ጓዴ ባለህበት ፅና!
ስምንት አመት ሆነው ዝክርህ፤
ይህንን ጉድ ከማየት ያለህበት ነው እሚሻልህ!
ገበያው ተደበላልቋል፤ ተገዢው ጊዜውን ይቃኛል
ገዢው ግና ተሰናብቷል
ስምንት ዓመት ሆነህ ጓዴ፣ ካለፍክ ከዚህ ሀገር እክል
  ተበዳይ አርፎም ቢተኛ፣ በዳይ ዘራፍ ነው አመሉ
“ምሴን አምጡ ነው ጠበሉ”
“ግፍ አይጠግቤ ደም ነው ውሉ!
ሳይመሽ ጨለመበት ባህሉ፡፡
እንዲህ ሆነልህ ብሂሉ፡-
“ቀና ሰው ጫጩት ሲያረባ ጐረቤቱ አየና አሉ
ምቀኛ ሱሱን ሲወጣ፣ ሸለምጥማጥ አረባ አሉ”
የሞተ ፈረስ መጋለብ፣ የተበላ እቁብ ነው ስሙ
የሞተ ዛር ነው ትርጉሙ፤ ዛሬስ ጉድ ባየህ ወዳጄ፡፡
ኧረ ጉዱን ባየህ ጓዴ…
ተቀትሎ በዘር ጐራዴ
ደም በደም ሆኗል መንገዴ
አራሙቻ አብቅሏል ሀገር
ሲወርድ ሲዋረድ እንዲሉ የጐሳ የቡድን ውርዴ
የሀገር ማህፀን አምካኝ እንደ ሞት ጭንጋፍ እንግዴ!
እንኳን አላየህ ወዳጄ….
ሠልፍም እንደ ግብር - ውሃ፣ የትም ሲፈስ በየሜዳ
መንጋ ለሁከት ሲነሳ ሥርዓተ - አልበኛ ሠልጥኖ፣ “ሰይጥኖ” በሀገሩ ፍዳ
በኋላ ቀር ጥፋት ናዳ፣ ነውጥ እንደ ለውጥ ሲሰናዳ
በንብረት ቃጠሎ ውድሚያ፣ ጥሪት ሲፈስ እንደ ጭዳ
ደም እንደ ውሃ ሲቀዳ እንኳን አላየህ ወንድሜ፣ ይህንን የትውልድ እዳ!
አንዱ ለግድብ ሲተጋ፣ ሌላው ለሀገር ሞት ሲሰለፍ
አንዱ ውሃ ሲያጠራቅም፣ ሌላው ከጐርፍ ጋር ሲጐርፍ
እብድ እንደበላው በሶ ሰው ተበትኖ ሜዳ፤
ህንፃ እንደ አሻንጉሊት ሲወድቅ እንደ አላዋቂ ተራዳ፤
ላብና እድሜ እንዳልወጣበት፣ በአንድ ጀንበር ድንጋይ በልቶት
ስንት ንብረት ስንት ጥፋት!
ኧረ ጉድ አላየህ ጓዴ፣ ታሪክ በአንድ ቀን ሲጨልም
የንፁሀን ሞት ሲተምም
የአንተ ዘመን ከዚህ ዘመን ሊወዳደር፣ ምን እና ምን!
ደሞም “በእንቅርት ላይ እኮ፣ ጆሮ ደግፍ” ብሂል እንዲል፣
ተደራራቢ ጣርም ነው፤ የኮሮና እክል ላይ እክል!
ህይወት በቁም ሞት ሲፈተን፣ ማሰብ ሲያቅት ኑሮ ማፍረስ፣
ፍትህ ሲነጥፍ ህግ መጣስ፤ ዛሬ ሰው በራሱ ፈርዶ
የራስ ላይ ክተት አውጆ፤ በገዛ ቤቱ ከትሟል
   ክተት ለሽሽት ነው ቋንቋው፤ ከሞት መራቅ
   አስፈልጓል፡፡
ግን እሱ ነው የሚያዋጣው፤
“ሞት ሳይሞቱት ነው እሚለመድ”፣ ያለን ጋሽ ፀጋዬ ይሄን ነው፡፡
አለመውጣት ነው ቋንቋው፤ እስከ መፍትሔው ማየት ነው፡፡
እና ጓዴ…..
አለምም ዛሬ ጠባለች፤ የሁሉንም ሞት አስተናግዳ፣ በደዌ ተሸማቃለች፡፡
ራሷን በልታ እንደ አብዮት፣  ክፋቷን ገድላ
ቀብራለች፤
ከኛው ቤት እኩል ጠባብ፣ አንድ መንድር አክላለች፡፡
እና ሰሌ ይህን አልኩህ፤  የዓለምን ስቃይ እንዳታይ
እዛው ጽና፣ እዛው ጋ ቆይ
እዛው ባለህበት ጽና…
(ለሰለሞን ጐሣዬ 8ኛ ሙት አመትና ለሁላችንም)
ነቢይ መኮንን - ነሐሴ 2012

Read 2912 times