Tuesday, 25 August 2020 05:49

የትራንስፖርት ቢሮ ስራ፣... ትራንስፖርትን መቀነስ ነው? የዞረበት ዘመን!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

የትምህርት ሚኒስቴር ስራስ? እውቀትንና የመልመጃ ጥያቄዎችን መቀነስ፡፡ ለበርካታ ዓመታት እየባሰበት የመጣ ስካር ነው - የትምህርት ፍኖተ ካርታን ተመልከቱ፡፡  
የግብርናና የእንስሳት ሀብት ሚኒስቴር ስራስ? የከብቶችን ቁጥር ማሳነስ፡፡ “የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ” ውስጥ ተዘርዝሯል፡፡ በ2002 ዓ.ም የጀመረ በሽታ ነው፡፡
በታክሲና በአውቶቡስ እጥረት፣ ስንትና ስንት የአዲስ አበባ ነዋሪ እንደሚጉላላ ይታያችኋል? ታይቶ አያልቅም፡፡ ወረፋው፣ ታች ድረስ ተዘርግቶ፣ ወደ ጐን ታጥፎ፣ እንደ እባብ እየተጠማዘዘ፣ ከአይን ይሰወራል:: እንደአባይ ወንዝ ርዝመት፣ ለታክሲ የሚፈጠረው የወረፋ ርዝመት፣ ከዓለም አንደኛ አይሆንም?
እንደዚያም ሆኖ፤ “የሰዎችን እንቅስቃሴ በማስቀረትና የትራንስፖርት ፍላጐትን በመቀነስ”፣ ችግሩ ይወገዳል፣ የሚል ዜና በኢቲቪ ብትሰሙ ምን ትላላችሁ? ለዚያውም፣ ይህንን “የምስራች” የምትሰሙት፣ ከትራንስፖርት መስሪያ ቤት ኃላፊ አንበደት እንደሆነ አስቡት፡፡ ለማመን ብትቸገሩ፣ “አይሆንም፣ አይደረግም” ብላችሁ ብትቆጡ፣ የጤንነት ምልክት ነው:: ነገር ግን፣ ነገርዬው፣ እውነት ነው፡፡ አሳዛኝ ቢሆንም፣ እውነት ነው፡፡
እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ፣ “ከመኪና ነፃ” እየተባለ፤ “በየወሩ መንገድ የመዝጋት ዘመቻ” ሲታወጅ ታዝበናል - በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፡፡ ይሄ፣ “ጤና የማጣት” ችግር አይደለም እንዴ?
ብዙ መቶ ሚሊዮን ብር የወጣባቸው አስፋልት መንገዶች ናቸው ተዘግተው የሚውሉት፡፡ እናም ሃምሳ እና መቶ ሰዎች፣ ዱብዱብ ይላሉ፡፡ እንዲያው ስታስቡት፣ ትንሽ ሮጥሮጥ ዱብዱብ ለማለት፣ ቦታ ጠፍቶ ነው? አስፋልት መንገድ ለመዝጋት የተወሰነው፣ የመፈናፈኛ ቦታ ጠፍቶ ነው:: አልጠፋም፡፡ ግን፣ መንገድ የመዝጋት ሱስ፣ በየአይነቱ የበዛበት ዘመን ላይ ነን፡፡ ከየአቅጣጫው፣ በየሰበቡ መንገድ ለመዝጋት መሽቀዳደም ተለምዷል፡፡
በጐርፍ ሳቢያ ድልድዩ ሲሰበር፣ ወይም አስፋልቱ ሲጥለቀለቅ፣ አልያም፣ ኮረኮንቹ መንገድ ተሸርሽሮ ሲቦረቦር ነበር “መንገድ ተዘጋ”፣ የምንለው፡፡ አንዳንዴ ደግሞ፣ በስካር የጦዘ ሰው፤ መሃል መንገድ ላይ ሲወላገድ፣ ወይም በመኪና ግጭት ሳቢያ መንገድ ይዘጋል፡፡ ዛሬስ? ዛሬማ፣ ነገር ሁሉ ተሳክሯል፡፡ የአላዋቂዎችና የጋጠወጦች፣ የሁከት ፈጣሪዎችና የአመፀኞች መደበኛ ስራ፣ “መንገድ ቁርጥ፣” “አስፋልት ዝጋ” እያሉ መንጋጋት ሆኗል፡፡ ምን ይሄ ብቻ? እንደምታዩት፣ መንገድ የመዝጋትና ትራንስፖርት የማቋረጥ ስካር፣ የሌሎችም ፈሊጥ ሆኗል፡፡ ታዲያ፣ ዛሬ ወይም ዘንድሮ፣ ድንገት የተፈጠረ ስካር አይደለም፡፡
ለበርካታ አመታት እየተደራረበ የመጣ ስካር ነው፡፡ የዛሬ 10 ዓመት የተዘጋጀውንና “የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ” የተሰኘውን ሰነድ ማየት ይቻላል፡፡  
ያኔ፣ “በወረቀት ላይ ብቻ የሚቀር ስካር” የመሰላቸው ሰዎች ይኖራሉ፡፡ ከዓመት ዓመት፣ ከወረቀት አልፎ፣ ኑሮን እያሳከረ ሲመጣ፣ ድንገተኛ ዱብዳ ይሆንባቸዋል:: ነገር ግን ድንገተኛ አይደለም፡፡ ከወረቀት ወደ ተግባር ለመሸጋገር፣ የተሳከረ ሃሳብ፣ ኑሮን ማናጋት ይጀምራል፡፡
በወረቀት ላይ ብቻ አልቀረም፡፡ የአስፋልት መንገድ ለሁለት ተከፍሎ፤ ገሚሱ “ለአውቶቡስ ብቻ” ተብሎ፣ በከንቱ ስራ እንዲፈታ የተደረገው፣ እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ ነው፡፡ ታክሲዎች ወደ ዳር ተጠግተው ተሳፋሪዎችን መያዝና ማውረድ አይችሉም:: በትራንስፖርት እጥረት ላይ፣ ተጨማሪ ችግር ተደረበ ማለት ነው፡፡ ታክሲዎች እንዲሁም የቤትና የንግድ መኪኖች፣ በግማሽ መንገድ ላይ ተጨናንቀው፣ ስንዝር ስንዝር እያዘገሙ፣ ጊዜንና ነዳጅን ያቃጥላሉ:: ከጐን በኩል ያለው ግማሽ መንገድ ግን፣ ጭር ብሏል፡፡ በአምስት በአስር ደቂቃ አንድ አውቶቡስ ያልፋል፡፡ በቃ፡፡ ከዚህ ውጭ፣ “አስፋልቱ ከመኪና ነፃ” ነው፡፡
“ለምን? እንዴት ሊሆን ይችላል?” እያሉ ብዙ ሰዎች ግራ ይጋባሉ፡፡ ወደው ነው? ነገሩ ሁሉ፣ መላ ቅጥ ሲያጣ፣ ምን ያድርጉ! ግን ድንገተኛ ዱብዳ አይደለም፡፡ አብዛኞቹ ችግሮች፣ ከ10 ዓመት በላይ ያስቆጠሩና በላይ በላዩ እየተደራረቡ የመጡ ችግሮች ናቸው፡፡ ብዙ እዳዎች አሉብን፣ ሰዎች፡፡ አንዳንዶቹን ችግሮች ለመፍታት፣ የጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ መንግስት እየሞከረ መሆኑ ጥሩ ነው፡፡
ለምሳሌ፣ በየአመቱ ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ኪሳራ የሚያስከትል የጂኦተርማል ፕሮጀክትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ እርቃኑ የወጣ ኪሳራ ውስጥ አገሪቱን ለመዝፈቅ አፋፍ ላይ ተደርሶ ነበር፡፡ መንግስት፣ እዚህ አሳፋሪ ኪሳራ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ላለመግባት መወሰኑ መልካም ነው፡፡
ብዙ ኪሳራ ያስከተሉ የስኳር ፕሮጀክቶችን ለግል ኩባንያዎች ለመሸጥ፣ መንግስት እየጣረ መሆኑም ያስመሰግነዋል - ቀላል ስራ ባይሆንም፡፡
አሳዛኙ ነገር፤ ግራ የሚያጋቡ የተሳከሩ ነገሮች፣ ለአመታት ስር በመስደዳቸው፣ በየጊዜው እየተፈለፈሉና እየተራቡ መሆናቸው ነው፡፡
በየእለቱ እንደምናየው ነው፡፡ ከ10 አመት በፊት፣ ወረቀት ላይ የሰፈረው ስካር፣ ዛሬ በእውን ያንገዳግደናል፡፡ ይሄውና፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፣ በታክሲ እጦት ከኑሮና ከስራ ሲስተጓጐሉ፤ በግፊያና በወረፋ ሲጉላሉ ይውላሉ፣ ያመሻሉ:: የትራንስፖርት መስሪያ ቤት ደግሞ፣ መንገዶችን፣ በከንቱ ያለ አገልግሎት ስራ እንዲፈቱ ይዘጋል - “ለአውቶቡስ ብቻ” እያለ፡፡
በአምስት በአስር ደቂቃ ለሚመጣ አውቶቡስ? ብዙ መቶ ሚሊዮን ብር የወጣበት አስፋልት እንዲህ ያለ አገልግሎት? ሚሊዮን ሰዎች በትራንስፖርት እጦት እየተጉላሉ? ይሄ፣ በሰው ኑሮ ላይ መቀለድ፣ በድሀ አገር ሃብት ላይ መጫወት ነው፡፡ ቢሆንም፣ “ውሳኔው” አይቀየርም፡፡ ምንም ብትናገሩ፣ የቱንም ያህል ብትሰቃዩና ብትማረሩ፣ “የሚለወጥ ነገር አይኖርም” ተብሎ ተዘግቷል፡፡ ለምን?
አለማቀፍ የስምምነት ውል ተዘጋጅቶለት፤ “በፊርማና በማህተም የተዘጋ” ጉዳይ ነው - የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ፕሮጀክትና የብድር ስምምነት ነው፡፡
“ለአውቶቡስ ብቻ” እያሉ ረዣዥም መንገዶችን መዝጋት፣ የፕሮጀክቱ  አንድ እቅድ ነው፡፡ ብድር ደግሞ ሌላኛው እቅድ:: አንዱን ከሌላኛው ጋር ያቆራኘ ነው፣ የስምምነት ፊርማው፡፡ ለነገሩ፣ በብድር የሚገነባው አዲስ መንገድ፣ “ሙሉ ለሙሉ ለአውቶቡስ ብቻ” እንጂ፣ ለሌሎች መኪኖች የተዘጋ ይሆናል ተብሎ ተፈርሟል፡፡ እሱም፣ በአስር ደቂቃ አንድ አውቶቡስ የሚያልፍበት ይሆናል ማለት ነው፡፡ በአብዛኛው ያለ አገልግሎት በከንቱ ስራ ይፈታል፤ ይባክናል::
በቅንጣት አገልግሎት፣ ሙሉ የብድር እዳ መሸከም ማለት ይሄ ነው፡፡ ግራ ያጋባል? ይሄ ብቻ አይደለም፡፡
አንድ የትራንስፖርት መስሪያ ቤት ኃላፊ፣ የአዲስ አበባን የትራንስፖርት ችግር ሲያስረዱ፣ የራሳቸውን ጥያቄ በማንሳት ይጀምራሉ፡፡ “ሰዎች ለምንድነው ከቤት የሚወጡት? ለምንድነው ትራንስፖርት የሚጠቀሙት?” የሚል ነው የኃላፊው ጥያቄ፡፡
ለትምህርት፣ ለመዝናናት፣ ለስራና ለግብይት ነው ሰዎች ከቤት የሚወጡት፤ ትራንስፖርት የሚፈልጉት፡፡ ይሄ፣ የራሳቸው የትራንስፖርት ኃላፊው ምላሽ ነው:: “አሁን ትምህርትና መዝናናት የለም”…አሉ ኃላፊው:: ስለዚህ ለእነዚህ ጉዳዮች፣ ትራንስፖርት አያስፈልግም፡፡
ለስራና ለግብይትስ? ሰዎች ለኑሮ የሚያስፈልጋቸውን ነገር፣ ከአገጠባቸው ከቤት ሳይርቁ እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚቻል ገልፀዋል - ኃላፊው፡፡ ስለዚህ ትራንስፖርት አያስፈልጋቸውም፡፡ እናም የትራንስፖርት ፍላጐት ይቀንሳል፡፡
ይሄ የትራንስፖርት መስሪያ ቤት ኃላፊ ማብራሪያ ነው - በኢቲቪ የቀረበ፡፡
እንግዲህ፣ ቁርጣችሁን እወቁ፡፡ “የትራንስፖርት ቢሮ”፣ “የትራንስፖርት ባለስልጣን” ምን እንደሚሰሩ ከራሳቸው አንደበት መስማት ትችላላችሁ፡፡
“አዲስ አበባን፣ ከሚኒባስ ታክሲ ነፃ እናወጣለን” የሚል፣ አስገራሚ መፈክር ይሁን ዛቻ በተደጋጋሚ ሲሰነዘር የሰማነው፣ ከአዲስ አበባ የትራንስፖርት ቢሮ ነው - በአዲስ አድማስም ተዘግቧል፡፡
ከቫይረስ ነፃ፣ ከቆሻሻ ነፃ፣ በየጐዳናው ከሚንጋጋ የውሻ መንጋ ነፃ፣ ከወንጀልና ከስርዓት አልበኝነት ነፃ…እንዲህ አይነት አባባሎችን መስማት ነበረብን፡፡
አሁን ግን፣ “ከሚኒባስ ነፃ”፣ “ከተሽከርካሪ ነፃ” የሚል ሆኗል - የዘመኑ ፈሊጥ፡፡
የሆነ ጊዜ፣ “የከተማ ባቡር” እየተባለ፣ ሌላ ጊዜ፣ “አውቶቡስ”…እየተባለ ለስንት ዓመት እንደተወራ ታውቃላችሁ፡፡ በመንግስት ባቡርና በመንግስት አውቶቡስ፣…እንደልብ ሽርሽር ሽው እልም ስትሉ ይታያችኋል? እንዴት ብሎ ይታያችኋል? እና ምን ተሻለ? “ባቡርና አውቶቡስን ለማሻሻል፣ የታክሲ አገልግሎትን ለማስፋፋት፣ አስተማማኝ ዘዴዎችን መፍጠር” ነበር መፍትሔው፡፡ የምንሰማው ግን የዚህ ተቃራኒ ነው፡፡
“ሁሉም ሰው፣ ከየቤቱ አጠገብ ሳይርቅ፣ የሚፈልገውን ነገር እንዲያገኝ በማድረግ የሰውን እንቅስቃሴ መቀነስ!” ትራንስፖርት አያስፈልገውም ማለት ነው፡፡ “የትራንስፖርት እጥረትን ለማስወገድ፣ የትራንስፖርት ፍላጐትን መቀነስ!” ትራንስፖትን ማስፋፋት ሳይሆን መቀነስ!
ይሄ፣ በመቶ ዓመት ውስጥ አንዴ ብቻ የሚፈጠር፣ “ጉድ” የሚያሰኝ አስገራሚ ክስተት ይመስላል፡፡ ቢሆን ጥሩ ነበር፡፡ ግን አይደለም፡፡
“ከእውቀት ነፃ ማውጣት” …የዘመናችን ትምህርት ተቋማት ፈሊጥ ሆኗል፡፡
“እውቀትን በማስፋፋትና በማሰራጨት” ምትክ፣ በተቃራኒው፣ “እውቀትን መቀነስ” የሚል ፈሊጥ፣ ባለፉት ሃያ ዓመታት እየገነነ መጥቶ፣ ዛሬ የትምህርት ሚኒስቴር መፈክር ሆኗል - የትምህርት ፍኖተ ካርታውን መመልከት ትችላላችሁ፡፡
የከብቶችን ቁጥር በግማሽ መቀነስ ደግሞ፣ የግብርናና የእንስሳት ሃብት ሚኒስቴር ስራ ሆኗል - በ2002 ዓ.ም በተዘጋጀው የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ፡፡
እነዚህና ተመሳሳይ የአመታት ስህተቶችን ለማረም፣ የስካርና የጥፋት ሱሶችን ለመግታት፤ ለዓመታት የተከማቹ እዳዎችን ለማጽዳት መጣር፣ የማንኛውም ጤናማ ሰው ኃላፊነት ነው - ለመንግስት ደግሞ ግዴታ ነው፡፡

Read 4591 times