Monday, 24 August 2020 19:44

"የህግ የበላይነት የማስከበሩ ስራ ወደ ኋላ መንሸራተት የለበትም"

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ ከፖለቲከኛውና ምሁሩ ዶ/ር አለማየሁ አረዳ  ጋር ሰሞኑን በነበረው ቆይታ በለውጡ ትሩፋቶች፣ በህግ ማስከበር እርምጃዎች፣ በፖለቲካ አለመረጋጋቶች፣ በሸገር ፕሮጀክትና ባልተጠበቀው የሰሞኑ ሹም ሽረት ጉዳይ ላይ አነጋግሯቸዋል፡፡
መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስጠበቅ በሚል እርምጃዎችን መውሰድ ጀምሯል:: የመንግስትን እርምጃዎች እንዴት አገኙት? በቅርቡ በተከሰተው ሁከትና ግርግር የተጠረጠሩ ታዋቂ ፖለቲከኞች መታሠራቸውን ተከትሎም፣ "የፖለቲካ እስር አዙሪት ውስጥ ተመልሰን እየገባን ነው" የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
የህግ የበላይነትን በተመለከተ ገና ከጅምሩ አንድን አካል ኮሽ ባለ ቁጥር "ህግ አፍርሰሃልና ታሰር" እየተባለ ቢኬድ ኖሮ፣ ዛሬ ላይ አንደርስም ነበር፡፡ የሀገሪቱ ችግር እየተባባሰ ነበር የሚሄደው፡፡ ምክንያቱም ያ ሁኔታ ተፈጥሮ መንግስትም እርምጃ እየወሰደ፣ ትርምሱ እንዲባባስ የሚፈልጉ ሃይሎች ነበሩ፡፡ ዝም እየተባለ ለመቆየት የተመረጠው ትርምሱ እንዳይባባስ ነው፡፡ አሁን ግን ድንበሮቹ በግልጽ ተለይተዋል:: ችግሮቹም በደንብ ተቀምጠዋል፡፡ አሁን የተያዘው በትክክልም የህግ የበላይነት የማስከበር ስራ ነው፡፡ የህግ የበላይነት የማስከበሩ ስራ ወደ ኋላ መንሸራተት የለበትም፡፡ አሁን ህብረተሰቡም ችግሩ ገብቶታል፡፡ ስለዚህ መንግስት የህግ የበላይነቱን አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል:: ሌላው የፖለቲከኞች መታሠር ጉዳይ ነው፡፡ ለኔ ታዋቂ ፖለቲከኞች የሚባሉት አይገቡኝም፡፡ ማን ነው የሚያውቃቸው? አንተ የምታውቃቸውን እኔ ላላውቃቸው እችላለሁ፡፡ ታዋቂ ሰዎች ታሠሩ ሲባል የየትኛው ፖለቲካ ፖለቲከኛ ነው እሱ? ዛሬ ፖለቲከኛም ይሁን ሌላ ሁሉም በህግ ፊት እኩል መታየት አለበት፡፡ ትልቁ ነገር የፍትህ አካሄዱ ግልጽና ነፃ፤ ፍፁም ከአድልዎ የጸዳ መሆኑ ነው፡፡ በተረፈ ፖለቲከኞች ሲታሠሩ የበለጠ ወደ ብጥብጥ ውስጥ እንገባለን የሚል ስጋት የለኝም፡፡ እስቲ አሁን ፖለቲከኞች ከሚባሉት የትኛው ነው፣ የደረጀ የበጀ ሃሳብ ይዞ የቀረበው? እኔ እንደዚያ አይነት ፖለቲከኞችን ብዙም አላውቅም፡፡  
ሰሞኑን ጠ/ሚኒስትሩ ያደረጉትን ድንገተኛ የካቢኔ ሹም ሽር እንዴት ይገመግሙታል?
ከአንድ ከሁለቱ በስተቀር ብዙዎቹ ያን ያህል ወሳኝ ሚና ያላቸው ሹመቶች አይደሉም፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈጠሩ ካሉ ሁኔታዎች ጋር ተያይዞ የተደረገ ሹም ሽረት ነው እንዳይባል ያን ያህል ወሳኝ ሃላፊነቶች አይደሉም:: ምናልባት ከስራ አፈፃፀም ጋር በተያያዘ በተደረገ ግምገማ የተካሄደ ለውጥ ሊሆን ይችላል፡፡ የመከላከያ ሚኒስትሩን በተመለከተ ስራቸውን ከለቀቁ ቆይተዋል፡፡ ዘግይተው ተኳቸው እንጂ እሳቸው ስራውን አስቀድሞም ትተውታል:: እኔ ትንሽ ትኩረቴን የሳበው የአቶ ታከለ ኩማና የወ/ሮ አዳነች አበቤ ሹመት ነው፡፡ ወ/ሮ አዳነች ከጥቂት ወራት በፊት አቃቤ ህግ ሆኑ፡፡ አቃቤ ህግ የሆኑት ገቢዎች ላይ ጥሩ ሠርተዋል እየተባለ በሚነገርበት ወቅት ነበር:: ወደ አቃቤ ህግ ሲመጡ ምን ቆራጥ ነገር ሊያመጡ ይሆን የሚል ጥያቄ ተፈጥሮ ነበር፡፡ ነገር ግን 6 ወር ሳይሞላ ከአቃቤ ህግነት ወደ ከንቲባነት መጡ፡፡ ወደ ከንቲባነት የመጡበት መንገድም ለኔ ምንም አልገባኝም፡፡ አቶ ታከለ ደግሞ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከሞላ ጐደል ብዙም የሚጠላ ሰው አይደለም፡፡ እንደውም የሚከበር ሰው ነው፡፡ ሠራተኞቹም ሆኑ ሌሎች አካላት ሽልማት ሁሉ ሲያዘንቡለት ነበር፡፡ አቶ ታከለ አዲስ አበባ ላይ ያጐደለው ነገር ምንድን ነው? ወ/ሮ አዳነች መጥተው የሚያስተካክሉት ምንድን ነው? የሚለው ትንሽ ግር ያሰኛል፡፡ ምናልባት ከዚህ ከአዲስ አበባ ዙሪያ ግብርናዎች፣ ከኮንዶሚኒየም አጠቃቀም ወዘተ ጋር በተያያዘ ምን አዲስ ነገር ሊፈጠር ይሆን የሚል ጥያቄ ያጭርብኛል፡፡ ሌሎቹ ሹመቶች ግን ያን ያህል ወሳኝና ለፖለቲካ ትርጉም እድል የሚሠጡ አይደሉም፡፡ የጠ/ሚኒስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊው አቶ ንጉሡ ጥላሁን ቀደም ብሎም ሊነሱ እንደሚችሉ ሲነገር ነበር፡፡ አቶ ዮሐንስ ቧያለው ምናልባት በሚመጥናቸው አቅም ቦታ ተሰጥቷቸው ይሆናል ብሎ መገመት ይቻላል፡፡ በተረፈ ግን ፖለቲካዊ ትርጉም ያለው ሹም ሽረት አይደለም የተካሄደው፡፡
ምናልባት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራር ውስጥ አለመተማመን ተፈጥሮ እንዳይሆን የሚል ስጋት ያላቸው ወገኖች አሉ፡፡ ይሄን ስጋት እርስዎ ይጋሩታል ?
አይመስለኝም፡፡ የተደረገው ለውጥ ለዚህ አይነት ስጋት የሚያበቃ አይደለም፡፡ በጣም ወሳኝ የሆኑ ቦታዎች ላይ ሹም ሽረት አልተደረገም፡፡ በቀጣይ ይመጣ እንደሆነ አይታወቅም፡፡ ይልቅ እነዚህ ሹም ሹረቶች ሲደረጉ እነዚህ ሰዎች ምን ያህል ለቦታው የሚመጥን የትምህርት ዝግጅት አላቸው? የሚለው ጥያቄ ነው  ሁሌም የሚመጣብኝ፡፡  
ደቡብ በክልልነት ጥያቄ፣ ትግራይ በምርጫ ጉዳይ፣ ኦሮሚያ የታሠሩ እንዲፈቱ በሚጠይቅ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ናቸው:: እነዚህ ሁኔታዎች በሀገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ የሚፈጥሩት ተጽዕኖ ምን ያህል ነው?
በመጀመሪያ ደረጃ ወላይታ ላይ የሆነው ነገር ባይሆን ጥሩ ነበር፡፡ ሰዎች በዚህ አይነት ጥያቄ ፈጽሞ መሞት የለባቸውም:: ምክንያቱም መነጋገርና ጉዳዩን በውይይት መጨረስ ይቻል ነበር፡፡ የወላይታ ዞን አስተዳደር ራሱን ከደቡብ ክልል ም/ቤት ካገለለ በኋላ ህገ-ወጡን መስመር ወስዷል ማለት ነው፡፡ አንድ አካል ራሱን ከህጋዊ ም/ቤት ካገለለ በኋላ የኔን ጉዳይ ካልመለሰ ብሎ እንዴት ይጠይቃል? እየተበደለም ቢሆን በህጋዊ ማዕቀፍ ውስጥ ቆይቶ ጥያቄን ማቅረብ ነው የተሻለ የሚሆነው፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ፓርላማ ላይ ጉዳዩን ወደ ፌደሬሽን ም/ቤት መልሰነዋል ሲሉ፤ የፌደሬሽን ም/ቤቱ የጉዳዩን  አሳሳቢነት ተረድቶ ቶሎ እርምጃ መውሰድ ነበረበት፡፡ ሌላው በደቡብ ክልል የሚነሱ ጥያቄዎችን በተመለከተ ጠ/ሚኒስትሩ በጽ/ቤታቸው እየጠሩ የሚያናግሩት ነገር ግልጽ መሆን አለበት:: ለወደፊቱም ቢሆን ከክልሉ ጋር የተያያዘ ነገር ሌላ የፖለቲካ ጣጣ እንዳያስከትል ከተፈለገ በግልጽ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ ይሄ የህዝብ መብት ጉዳይ ነው:: ህዝብ ነው መጨረሻ ላይ በህዝበ ውሣኔ የሚወስነው:: የተወሰኑ ልሂቃንና የመንግስት ኃላፊዎች ለእነሱ ፖለቲካ እንዲመቻቸው ብለው ነገሩን ለመቆጣጠር ሲጥሩ መዋል የለባቸውም፡፡ የሚነሱ ጥያቄዎችና ፍላጐቶች ግልጽ መሆን አለባቸው፡፡
እኔ ከሁሉም የሚያሰጋኝ እዚያ አካባቢ ያለው አለመረጋጋት ነው፡፡ ከዚያ በተረፈ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት የፖለቲካ አለመረጋጋቶች አዲስ አይደሉም፡፡ የህግ ማስከበር እርምጃ ከተጀመረ በኋላ በመጠኑም ቢሆን እየቀነሱ ነው፡፡ ትግራይን በተመለከተ የሚያዋጣው ዝም ማለት ነው:: ሥልጣኑ የፌደሬሽን ም/ቤቱ ነው፤ እርምጃ ሊወስድ የሚገባውም ም/ቤቱ ነው፡፡ ከዚያ ባለፈ ግን የሚያዋጣው በዝምታ መመልከቱ ነው፡፡ የህወኃት ፖለቲካ የአትርሱኝ ጨዋታ ነው፡፡ የሆነ ንትርክ የመፍጠር ጉዳይ ነው አላማቸው፡፡ እነሱ ይህቺ ሀገር መረጋጋት የለባትም የሚል አቋም ነው ያላቸው፡፡ ይህቺ ሀገር ተረጋጋች ማለት፣ እነሱ የሞቱ ያህል የሚቆጥሩት ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ እነሱን በተመለከተ ፌዴሬሽን ም/ቤት ነው እርምጃ መውሰድ ያለበት፡፡  የፌደሬሽን ም/ቤቱ ፈጠን እያለ እርምጃዎችን መውሰድ ያለበት ይመስለኛል፡፡ በተለይ ከአከላለል ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ ፈጣን ውሣኔ ቢሰጥ መልካም ነው፡፡
የትግራይ ክልል ምርጫ መካሄድ በቀጣይ ለመገንጠል እንደ ህዝበ ውሣኔም ሊቆጠር ይችላል ወይም አጋዥ ይሆናል የሚል ሃሳብም ይነሳል፡፡ ምናልባት በዚህ በኩል በእንዲህ ያለ ሂደት በር ሊከፈት ይችል ይሆን?
አንደኛ ነገር ምርጫው ህጋዊ አይደለም:: ያለው አማራጭ ምርጫው እንዳይካሄድ በጦር ሠራዊት ነው ወይስ በህግ ነው ማድረግ የሚቻለው የሚለው ነው:: የፌደሬሽን ም/ቤቱ በሚወስዳቸው እርምጃዎች ነው ምርጫውን ማስቆም የሚቻለው፡፡ ምርጫውን ካካሄዱ በኋላ ወደ መገንጠል ጥያቄ ይሄዳሉ ማለት የማያስኬድ ነው፡፡ ምንም ትክክለኛ መንገድ አይደለም እየተከተሉ ያሉት፤ ወዴትም አይወስዳቸውም፡፡ የተወሰኑ መሣሪያዎችን የያዙ ወታደሮችን ከተማ ውስጥ በማንቀሳቀስ ለማስፈራራት በመሞከር የሚሆን ነገር የለም፡፡ እውነት ለመናገር ትግራይ ውስጥ ራሱን የቻለ እነሱ ከሚያስቡት ውጪ የሆነ የወጣት ሃይል አለ:: የቱ እንደሚያሸንፍ እንኳ አናውቅም፡፡ እንደ እኔ ከሆነ የትግራይን ጉዳይ በትዕግስት ማየት ነው የሚያስፈልገው፡፡ ይሄ ሲባል ግን መወሰድ ያለባቸው ጥንቃቄዎች የሉም ማለት አይደለም፡፡ እነዚያን ጥንቃቄዎች አሁን ተናገር ብትለኝ ልናገር አልችልም:: ምክንያቱም እኔ መንግስት አይደለሁም፡፡ ግን በጣም እጅ አስፈላጊ የሆኑ መንግስት ሊወስዳቸው የሚገቡ ጥንቃቄዎች አሉ፡፡ ምክንያቱም አሁን ያለው ትርምስ የማይሳካ ሲመስላቸው ወደ ድንበር አካባቢ ረብሻ ሊፈጥሩ እንደሚችሉ አልጠራጠርም፡፡ ስለዚህም ጉዳዩን በትዕግስትና በጥንቃቄ መያዝ ያስፈልጋል፡፡ እውነቱን ለመናገር የትግራይ ህዝብ ነው የራሱን ችግር በራሱ የሚፈታው፡፡ ይሄን ደግሞ ያደርጋል፡፡ የፌደራል መንግስቱ ህዝቡን ነው መርዳት ያለበት፡፡ መገንጠል የሚለው ለኔ ብዙም አይታየኝም፡፡ የትግራይ ህዝብ ሙሉ ለሙሉ በህዝበ ውሣኔ ልገንጠል ብሎ ከወሰነ እንኳን ህገ መንግስታዊ ነው የሚሆነው:: ጥያቄው ግን የትግራይ ህዝብ ልገንጠል ብሎ ይወስናል ወይ ነው? የትግራይ ህዝብ ከኢትዮጵያ ተገንጥሎ መኖርን እንደ ታሪክ እውነት ይቀበላል ብሎ ማመን አስቸጋሪ ነው፡፡ የትግራይ ህዝብ መቼም ቢሆን ይሄን እያስብም፡፡ በዚህ በኩል ምንም ስጋት የለኝም፡፡
የሀገሪቱ የፖለቲካ ችግሮች በዘላቂነት እንዲፈቱና የለውጥ ሂደቱ የታለመውን እንዲያሳካ ምን ማድረግ ይበጃል ይላሉ?
አንደኛው አሁን የተጀመረውን የህግ ማስከበር ስራ በግልጽና በተገቢው መንገድ እያካሄዱ መቆየት ያስፈልጋል:: ከዚህ ጋር ተያይዞ ሰዎች አፋጣኝ ፍትህ አግኝተው የታሠሩትም ታስረው፣ የተፈቱትም ተፈትተው ወደ መደበኛ ስራቸው እንዲመለሱና ህብረተሰቡ ውስጥ ሠላም እንዲሰፍን ውይይቶችን ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ሌላው ዋነኛ ነገር በምንም አይነት መንገድ ነገሮች ተሸፋፍነው መሄድ የለባቸውም፡፡ ሁሉም ነገር በግልጽ ነው መካሄድ ያለበት፡፡ በተለይ በደቡብ ውስጥ ያሉ የክልል ጥያቄዎች በጣም ግልጽ ሆነው ውይይት መካሄድ አለበት፡፡ በምንም አይነት ተሸፋፍኖ መሄድ የለበትም፡፡ አሁን ለምሣሌ ዋነኛ የሚባሉትን ሚዲያዎች ብንመለከት፣ በዚህ ጉዳይ ብዙም አይሠሩም፡፡ ኢሣት ነው አልፎ አልፎ ለመስራት የሚሞክረው:: ሚዲያዎች ብዙ ይጠበቅባቸዋል፡፡ አሁን ብዙም ግልጽ መረጃዎች እየቀረቡ አይደለም፡፡ በግልጽ ጉዳዩ ላይ መወያየት ያስፈልጋል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩም ብዙውን ስራ እሣቸው ናቸው የሚሠሩት፤ አሁን ትንሽ የስራ ክፍፍል ቢያደርጉ ጥሩ ነው፡፡
በሸገር ፕሮጀክት ምን ተሰማዎት?
እኔ በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሌሎች አንገብጋቢ ችግሮች እያሉ ለምን ለዚህ ጉዳይ ቅድሚያ ተሰጠው የምንል ሰዎች እንኖራለን፤ ይሄ ግን ተገቢ አይደለም:: ባለን ጊዜ ጥቅም የሚሰጥ ስራ ብንሰራ፤ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ነው የሸገር ፕሮጀክት ያሳየኝ፡፡ አዲስ አበባ እውነትም እንደ ስሟ አዲስ አበባ እንደምትሆን ነው ያመላከተኝ:: በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡ በዚህ ትርምስና ግራ የሚያጋባ ሁኔታ ውስጥ ለመንፈስ ምግብ እንዲሆን የሚያስችል አስደሳች ነገር ቀርቦልን ስናይ በጣም ነው ደስ የሚለው፡፡ ተስፋ ይፈጥራል:: ጠ/ሚኒስትሩ ደጋግመው እንደሚሉት፤ ትንሽ ጀምረን ካሳየን ትልቁን ለመስራት እንደምንችል መተማመን ይፈጥርልናል፡፡ የእንጦጦ ፕሮጀክት በጣም ድንቅ ነው፡፡ እኔ በአዲስ አበባ ከ50 ዓመት በላይ ኖሬያለሁ፤ አዲስ አበባ እንደዚህ አምራ በማየቴ በጣም ደስ ብሎኛል፤ስራዎቹ ደግሞ ቀጣይ መሆን አለባቸው፡፡ በየአካባቢያችን ጠቃሚ ስራ እንድንሰራ ያበረታታናል፤ መንፈሳችንንም ያጐለብትልናል፡፡        


Read 1652 times