Thursday, 27 August 2020 00:00

ኮሮና በፍጥነት መሰራጨቱን ቀጥሏል፤ በህንድ በ1 ቀን 69,672 ተጠቂዎች ተገኝተዋል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

አለማችንም ሆነ የአለም ጤና ድርጅት፣ ኮሮናን ያህል ፈታኝ የጤና ቀውስ ገጥሟቸው እንደማያውቅና ቫይረሱ በ188 የአለም አገራት በፍጥነት እየተሰራጨ የከፋ ጉዳት ማስከተሉን እንደቀጠለ የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ከሰሞኑ በሰጡት መግለጫ ያስታወቁ ሲሆን በህንድ ከትናንት በስቲያ ሃሙስ ብቻ 69,672 የኮሮና ተጠቂዎች መመዝገባቸው ተነግሯል::
ቫይረሱ እስካለፈው ሃሙስ አመሻሽ ድረስ በመላው አለም ከ22.6 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ማጥቃቱንና ከ792 ሺህ በላይ ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት መዳረጉን የጠቆመው የወርልዶ ሜትር ድረገጽ መረጃ፣ ያገገሙት ሰዎች ቁጥር በአንጻሩ 15.3 ሚሊዮን መድረሱን አመልክቷል፡፡
በኮሮና ቫይረስ ሟቾችና ተጠቂዎች ቁጥር አሁንም ከአለማችን አገራት በመጀመሪያው ደረጃ ላይ በምትገኘው አሜሪካ የተጠቂዎች ቁጥር ከ5.7 ሚሊዮን ሲያልፍ፣ የሟቾች ቁጥር ደግሞ ከ176 ሺህ በላይ መድረሱን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ ከሰሞኑ ባወጣው ትንበያ፤ በአሜሪካ የኮሮና ቫይረስ ሟቾች ቁጥር እስከ መጪው ታህሳስ ወር ከ295 ሺ በላይ ሊደርስ እንደሚችል ማስጠንቀቁን የዘገበው ቢቢሲ፣ ወረርሽኙ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከባድ ተጽእኖ ማሳደሩንና እስከ ሰኔ በነበሩት 3 ወራት  ብቻ አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት በ33 በመቶ መቀነሱንም አስታውሷል፡፡
ብራዚል በ3.5 ሚሊዮን ተጠቂዎችና በ111 ሺህ ሟቾች ከአለም አገራት በሁለተኛነት ስትከተል፣ ህንድ በ2.8 ሚሊዮን ተጠቂዎች ሶስተኛ ደረጃን ይዛለች፡፡ 58 ሺህ ያህል ሰዎች ለሞት የተዳረጉባት ሜክሲኮ በበኩሏ፤ በሟቾች ቁጥር በ3ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡
ኮሮና ቫይረስ በ55 የአፍሪካ አገራት እስካለፈው ሃሙስ አመሻሽ ድረስ በድምሩ ከ1.15 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ማጥቃቱን የዘገበው ኦል አፍሪካን ኒውስ፣ የሟቾች ቁጥር 27 ሺህ፣ ያገገሙት ሰዎች ቁጥር ደግሞ 870 ሺህ ያህል መድረሱን አመልክቷል፡፡ ደቡብ አፍሪካ በ596 ሺህ ተጠቂዎችና በ12 ሺህ በላይ ሟቾች ከአህጉሩ ቫይረሱ ከፍተኛ ጥፋት ያደረሰባት ቀዳሚዋ አገር ስትሆን፣ የተጠቂዎች ቁጥር በግብጽ ወደ 97 ሺህ፣ በናይጀሪያ ወደ 51 ሺህ፣ በአልጀሪያ ወደ 40 ሺህ፣ በጋና ደግሞ ወደ 43 ሺህ መጠጋቱ ተነግሯል፡፡
ባለፉት ቀናት በተለያዩ የአውሮፓ አገራት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ ዕለታዊ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች መመዝገባቸውን የዘገበው ሮይተርስ፣ በአውሮፓ በየዕለቱ በአማካይ 26 ሺህ አዳዲስ የቫይረሱ ተጠቂዎች እየተመዘገቡ እንደሆነ መነገሩን አመልክቷል፡፡ ባለፈው ረቡዕ ብቻ በጣሊያን 642፣ በስፔን 3 ሺህ 715 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ሃሙስ ዕለት ደግሞ በጀርመን 1 ሺህ 707 የቫይረሱ ተጠቂዎች መመዝገባቸውን አስታውቋል፡፡
በሕንድ ከትናንት በስቲያ ብቻ 69 ሺህ 672 ያህል ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን፣ ይህም በአገሪቱ በአንድ ቀን የተመዘገበ ከፍተኛው ቁጥር መሆኑን ሂንዱስታን ታይምስ የዘገበ ሲሆን፣ በአገሪቱ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ2.8  ሚሊዮን ማለፉና የሟቾች ቁጥር ደግሞ ወደ 54 ሺህ መጠጋቱ ተነግሯል፡፡
በተያያዘ ዜና፤ አገራት በኮሮና ቫይረስ ክትባትና መድሃኒቶች ላይ የጀመሯቸውን ምርምሮች አጠናክረው የቀጠሉ ሲሆን፣ ሲኖፋርም የተባለው የቻይና መድሃኒት አምራች ኩባንያ እስከ መጪዎቹ አራት ወራት የኮሮና ቫይረስ ክትባቱን ምርምር አጠናቅቆ በአገሪቱ የተለያዩ ከተሞች በአነስተኛ ዋጋ ለገበያ እንደሚያቀርብ ያስታወቀ ሲሆን፣ አውስትራሊያ በበኩሏ ወደ መጨረሻው የምርምር ምዕራፍ የተሸጋገረውን የኮሮና ቫይረስ ክትባቷን በስኬት ካጠናቀቀች 25 ሚሊየን ዜጎቿን በነጻ ለመከተብ ቃል መግባቷን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በበኩሉ፤ ከአራት ወራት በኋላ በመላው አለም 265 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ ለምግብ እጥረትና ረሃብ ሊጋለጡ እንደሚችሉ ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ ያስጠነቀቀ ሲሆን፣ በወረርሽኙ ሳቢያ ለኪሳራ የሚዳረጉ ኩባንያዎች ቁጥር መጨመሩም ተነግሯል፡፡
ግዙፉ የአውስትራሊያ አየር መንገድ ኳንታስ፣ ከኮሮና ወረርሽኝ መስፋፋት ጋር በተያያዘ በአመቱ ወደ 2 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ኪሳራ እንደደረሰበትና ይህም ኩባንያው ባለፉት 100 አመታት ታሪኩ ገጥሞት የማያውቅ አስከፊ ኪሳራ መባሉን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡



Read 4840 times