Print this page
Sunday, 23 August 2020 00:00

በኮሮና ቫይረስ ከተያዙት 90 በመቶ ያህሉ የተገኙት ማህበረሰቡ ውስጥ ነው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(3 votes)

         • ዘመቻው ከተጀመረ ወዲህ በቫይረሱ የሚያዙት በ80 በመቶ ጨምረዋል
          • በሁለት ሣምንት ዘመቻ ከ220ሺ በላይ ሰዎች ተመርምረዋል
              
            በኮሮና ቫይረስ ከሚያዙ ሰዎች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት በማህበረሰቡ ውስጥ በተደረገ ቅኝትና ዳሰሳ የተገኙ መሆናቸው የተገለፀ ሲሆን በለይቶ ማቆያ ከገቡት ውስጥ በሽታው እንዳለባቸው የተረጋገጡት ከ10 በመቶ በታች እንደሆኑ የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ አስታውቀዋል፡፡
ከነሐሴ 10 ጀምሮ በአምስት ቀናት ብቻ ለ105ሺ ሰዎች ምርመራ ተደርጐ 6942 የሚሆኑት ቫይረሱ እንዳለባቸው ተረጋግጧል፡፡ በበሽታው ሣቢያ የሚሞቱና ጽኑ ህሙማን ክፍል የሚገቡ ህሙማን ቁጥርም እያሻቀበ ነው ተብሏል፡፡
ባለፈው ነሐሴ 1 የተጀመረውና በሁለት ሣምንታት ውስጥ 200ሺ ሰዎችን የመመርመር ዕቅድ ተይዞለት የነበረው መርሃ ግብሩ በትናንትናው ዕለት የተጠናቀቀ ሲሆን እስከ ትናንት በስቲያ ሐሙስ ነሐሴ 14 ድረስ 225ሺ 279 ሰዎችን ለመመርመር ተችሏል:: ዘመቻው ከተጀመረ በኋላ የመመርመር አቅማችን በአማካይ በቀን 15ሺ ደርሷል ያሉት ጤና ሚኒስትሯ፤ በዘመቻው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በ80 በመቶ ማደጉን ሚኒስትሯ በፌስቡክ ገፃቸው ገልፀዋል፡፡
ዘመቻው ከመጀመሩ በፊት 8ሺ ቫይረሱ ያለባቸውን ሰዎች ለማግኘት 114 ቀናትን ወይንም አራት ወራትን መውሰዱን የገለፁት ሚኒስትሯ፤ ዘመቻው ከተጀመረ ወዲህ ግን 8ሺ ሰዎችን ለማግኘት 7 ቀናት ብቻ ወስዷል ብለዋል፡፡ በዘመቻው ቫይረሱ ከተገኘባቸው መካከል 90 በመቶው በማህበረሰብ ቅኝት የተመረመሩ ናቸው። ቀሪዎቹ 10 በመቶ ደግሞ በለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበሩ መሆናቸው ተገልጿል።
ኮሮና ቫይረስ ያለባቸውን ሰዎች ሁሉ ወደ ህክምና ማዕከላት ማስገባት አለመቻሉን የገለፁት ሚኒስትሯ፤ ወደ ህክምና ማዕከላት እንዲገቡ የተደረጉት 2760 ብቻ መሆናቸው ጠቁመው 2551 የሚሆኑት ደግሞ በለይቶ ማቆያ ስፍራዎች እንዲገቡ ተደርገዋል ብለዋል። ቀሪዎቹ ደግሞ በየቤታቸው ሆነው ራሳቸውን አግልለው እንዲቆዩና ራሳቸውን እንዲንከባከቡ መደረጉንም ሚኒስትሯ ተናግሯል፡፡

Read 7564 times