Tuesday, 18 August 2020 00:00

አዲስ ጥያቄ - ለግብጽና ለሱዳን!

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

 ግብጽና ሱዳን የናይል ተፋሰስ ልማት የምክክር መድረክ አባል አገሮች ነበሩ:: "በተፋሰሱ ውስጥ ያለውን የውኃ ሃብት ማልማት፣ ከወኃ ሃብት ተመጣጣኝ ጥቅም ማስገኘት፣ በሀገሮች መካከል ትብብርና የጋራ አሠራርን ማረጋገጥ፣ ድህነትን መቀነስ ወዘተ--" የትብብር መድረኩ ከያዛቸው ዓላማዎች ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ግብጽና ሱዳን እንተገብራቸዋለን  ብለው የያዟቸውን እነዚህን ዓላማዎች ወደ ጎን ገፍተው የትብብር መድረኩን ለቀው እንዲወጡ ያደረጋቸው ግን እ.ኤ.አ 2010 ላይ መድረኩ ያጸደቀው የናይል ትበብር ማዕቀፍ (CFA ) በ14ኛ አንቀጹ ላይ ስለ ፍትሐዊና ምክንያታዊ የውኃ አጠቃቀም መደንገጉ እንዲሁም እነሱ አለን የሚሉትን ታሪካዊ የውኃ ተጠቃሚነት መብት አለመቀበሉ ነበር፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ወደ ምክክር መድረኩ ብቅ ብለው አያውቁም:: በእነሱ ዘንድ እ.ኤ.አ በ1929 እና በ1959 የተደረጉ ውሎችን ውድቅ ማድረግ ‹‹አሁን ገና በዓይኔ መጣህ›› የሚያሰኝ መሆኑ  ድብቅ አይደለም፡፡
"አገራችን  በአረብ  አብዮት ባትጠመድ ኖሮ ኢትዮጵያዊያን ታላቁን የሕዳሴ ግድባቸውን አይጀምሩም ነበር" የሚሉት ግብጾች፤ መሠረቱ ከተጣለና  ግንባታው ከቀጠለ በኋላ መጮህና አብረዋቸው የሚጮሁትን ማሰለፍ የጀመሩት የግድቡ ቁመት እንዲቀንስና የሚይዘውም የውኃ መጠን አነስተኛ እንዲሆን ነበር፡፡ እሱን የሚሰማ ጆሮ ከኢትዮጵያዊያን ዘንድ  ሲያጡ፣ ግድቡ የሚሞላበት ጊዜ ወደ 21 ዓመት እንዲጎተት ፈለጉ፡፡ ይህን ለማስወሰን አቅም አላት ተብላ በግብጽ የተመረጠችው አሜሪካ ከታዛቢነት ወደ አደራዳሪነት፣ ከዚያም ወደ ውል አርቃቂነት ብትሸጋገርም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ራሱን ከሂደቱ አገለለ፡፡ እንኳን ባለ ጉዳዩዋ ኢትዮጵያ ቀርቶ ሱዳንም ፊቷን በሰነዱ ላይ አዞረች፡፡ ሰነዱም  በሶስቱ አገሮች የድርድር ታሪክ ውስጥ በግብጽ ብቻ በመፈረም ብቸኛ ታሪካዊ  ሰነድ ሆነና አረፈው፡፡
ግብጾች እጅግ ከፍተኛ የከርሰ ምድር ውኃ አላቸው፡፡ ሚዲትራኒያንና ቀይ ባሕር በጃቸው ነው፡፡ ሁልጊዜ የሚናገሩት ግን  ዘጠና ከመቶው የግብጻዊያን ሕይወት በዓባይ ላይ የተንጠለጠለ አድርገው ነው፡፡ እንኳን እራሳቸውን ዓለምንም አሳምነውበት ስለነበር  የውኃ ጉዳይ ሲነሳ ግብጽ እንደምትጠፋ አድርጎ የሚያስብ ተከታይም ፈጥረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ አስተሳሰብ በጊዜ ሂደት እየተሸረሸረ መጥቷል፡፡ እኔን ጨምሮ ብዙ ኢትዮጵያዊያን ከዚህ አስተሳሰብ እየወጡ ነው፡፡
ፕሬዚዳንት ጋማል አብድል ናስር በዓባይ ጉዳይ ምን እንዳሉ የማውቀው የለኝም:: እሳቸውን የተኩት ፕሬዚዳንት ሳዳት ግን ግብጽ በዓባይ ውኃ ያላትን ጥቅም ለማስጠበቅ የሀገሪቱን የጦር ኃይል እንደሚጠቀሙ ብዙ ጊዜ ተናግረዋል:: ሙባረክም የተለዩ ሰው አልነበሩም፡፡ የግብጽ ወንድማማችነት ፓርቲ ተመራጭ ፕሬዚዳንት ሞሐመድ ሙርሲ፣ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን ከጎናቸው አሰልፈው፣  በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት  "መጣሁላችሁ" ብለውን ነበር:: የአሁኑ የግብጽ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ የቀጠሉት በዚያው ነው:: እንዲያውም ከወር  በፊት ኢትዮጵያ ከአንድ አስገዳጅ ስምምነት ውስጥ ሳትገባ የሕዳሴውን ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውኃ ሙሌት የምታካሂድ ከሆነ የኃይል እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደዱ መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡ የአገሪቱ ጦር በተጠንቀቅ እንዲገባ ማድረጋቸው፣ ሃሳቡንም ግብጻዊያን ባለ ሃብቶች እንደተጋሩት መዘገቡም ይታወሳል፡፡
አሜሪካ ከወዲያ፣ ግብጽና ሱዳን ከወዲህ የሚችሉትን ያህል ቢያስፈራሩም፣ የሚፈራ ልብ ባለመኖሩ ኢትዮጵያ በራሷ እቅድ መሠረት ተራምዳ፣ የታላቁን የሕዳሴ ግድብ  የመጀመሪያ ዙር የውኃ ሙሊት አካሄደች:: ግብጽ ለዓመታት "ስታስፈራራበት" የነበረው ወታደራዊ እርምጃ እንደማይሠራ  አየችው:: ያዙኝ ልቀቁኝ ሲሉ የቆዩት ፕሬዚዳንቷ አብዱል ፈታህ አል ሲሲ፣ ሐምሌ 21 ቀን 2012 ዓ.ም በሰጡት መግለጫም በራሳቸው አንደበት፤ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ኃይል አማራጭ እንደማይሆን በይፋ አስታወቁ፡፡
የሕዳሴ ግድብ "በገዛ ውኃዬ ማንን፣ ምን አገባው" በሚል  ስሜት  ከስምምነት ውጪ በመሞላት ግብጽ "በኢትዮጵያ ላይ ወታደራዊ እርምጃ  እንወስዳለን" የሚለውን ፉከራዋን ወደ ኋላ እንድትስብ ብቻ በማድረግ አልቆመም፡፡ የውኃ አጠቃቀም ሥርዓቷን እንድትፈትሽም አስገድዷታል:: 62.5 ቢሊዮን ዶላር በመመደብ ሃያ ሺህ ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን የውኃ ቦይ በኮንክሪት ለመሸፈን መነሳቷን ይፋ አድርጋለች፡፡ ሱዳን ምን እያሰበች እንደሆን እስከ አሁን የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ በሁለቱ አገሮች ስምምነት መሠረት ካላት 18.5 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ ውስጥ እስከ አሁን የምትጠቀመው ከ12 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ስለማይበልጥ ለማሰቢያ በቂ ጊዜ አለኝ ብላም ሊሆን ይችላል፡፡
በኢትዮጵያ ላይ በሕዳሴው ግድብ ምክንያት ግብጽ ለማምጣት የሞከረችው ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ፍሬ አለመስጠቱ ከታወቀና ግድቡ ከተሞላ በኋላ የሶስቱ አገሮች ድርድር ቢጀመርም፣ ግብጽና ሱዳን የሚፈልጉትን አሳሪ ውል ሊያገኙ አልቻሉም፡፡ ኢትዮጵያ ለሁለቱ አገሮች ያቀረበችው አዲሱ "እጄን ሰጥቻለሁ" የማይለው የድርድር ሃሳብ፣ ሱዳንን "ኢትዮጵያ የሕዳሴውን ድርድር ወደ ውኃ ክፍፍል እየወሰደችው ነው" ብላ እንድትለፍ ከማድረጉ በላይ ከድርድሩ ለመውጣትም መዛቷ እንዳለ ሆኖ፣ የሶስቱ አገሮች የውኃ ሚኒስትሮች ድርድሩ በምን አጀንዳ ላይ እንደሚቀጥልና እነማን እንደሚወከሉ ለመወሰን ጊዜ ያስፈልጋል የሚል ጥያቄ በማቅረቧ፣ ግብጽም በመስማማቷ ድርድሩ ለአንድ ሳምንት እንዲዘገይ ተደርጓል፡፡ በመጪው ነሃሴ 11 ቀን 2012 ዓ.ም ይቀጥላል ተብሎም ይጠበቃል፡፡
ከግብጽና ከሱዳን ኢትዮጵያ የምትጠብቀውና የምታገኘው ነገር ስለሌለ ግዴታ የምትገባበትና የምትቀበልበት ምክንያት የለም፡፡ ሱዳንን ያስፈራው የውኃ ክፍፍል ጉዳይ ግብጽን አያሰጋትም አይባልም፡፡ ይህን ኢትዮጵያ አንድ የመጫወቻ ካርድ ማድረግ ብትችል መልካም ይሆናል፡፡
"አመል ስጠኝ እንጂ ሙያስ ከጎረቤቴ እማራለሁ" ይባላል፡፡ በ1889 ዓ.ም ጣና ላይ ግድብ ሠርቶ  የሱዳን መንግሥት በዓመት አስር ሺህ ፓውንድ የውኃ ኪራይ እንዲከፍል እንግሊዞች ለአፄ ምኒልክ በደብዳቤ ቢያሳውቁም፣ ምኒልክ ሃሳቡን ሳይቀበሉት ቀሩ፡፡ በ1912 ዓ.ም ነገሩ እንደገና ተነሳ:: ልዑል  አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ መኮንን  ግድቡን ኢትዮጵያ እንደምትሠራ፣ ሥራው በኩባንያ የሚሠራ ከሆነ ደግሞ ለእንግሊዞች አክስዮን እንደሚሸጥላቸው ገልጸው፤230 ሺ ፓውንድ እንግሊዝ እስካልከፈለች ድረስ ምንም ድርድር እንደማይደረግ ማስታወቃቸውን "የኢትዮጵያና የግብጽ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከጥንት እስከ አሁን ዘመን" የተሰኘውን የአምባሳደር ተፈራ ኃይለ ሥላሴ መጽሐፍ ጠቅሰው ግርማ ባልቻ ጽፈዋል፡፡ (አምባሳደር ተፈራ ኃይለ ሥላሴ "የታላቋ ብሪታኒያና የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ግንኙነት" መጽሐፍ ደራሲ መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡) በኛ ዘመንም ቢሆን ደቡብ አፍሪካ ለሌሴቶ በየዓመቱ 35 ሚሊዮን ዶላር የውኃ ኪራይ እንደምትከፍል መጠቆም  ግድ ይላል፡፡ ኢትዮጵያ በድርቅና በተከታታይ ድርቅ ከሕዳሴው ግድብ ውኃ ለመልቀቅ የምትስማማ ከሆነ፣ ሁለቱ አገራት ለሚያገኙት ውኃ ኪራይ መክፈል እንዳለባቸው መግለጽና ጥያቄውን በሁለቱ ጠረጴዛ ላይ ማስቀመጥ አለባት፡፡ ለግብጽና ለሱዳን የሚቀርብ አዲስ ጥያቄ!!  

Read 5501 times