Tuesday, 18 August 2020 00:00

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by  (ጌታሁን ሔራሞ)
Rate this item
(1 Vote)

 ለዎላይታ ጥያቄ፣ ከሲዳማው እንማር
                                 

            ከ20 ሰዓታት በፊት የብልፅግና ፓርቲ በፌስ ቡክ ገፁ ላይ ወቅታዊውን የዎላይታ ዞንን ሁኔታ በተመለከተ ካስቀመጣቸው አንቀፆች ውስጥ መግቢያው ላይ የሚከተለው ይገኝበታል፦
“በዎላይታ ዞን የህዝቡ ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ እንዳይመለስና በህዝብና በመንግስት መካከል መጠራጠር እንዲፈጠር ለውጡን ከማይደግፉ አካላት ጋር በጋራ እየሰሩ ነው ተብለው የተጠረጠሩ አመራሮች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ፡፡” በዚህ አንቀፅ ውስጥ “ለውጡን ከማይደግፉ አካላት ጋር በጋራ እየሰሩ ነው..; የሚለውን ዓ.ነገር አስምሩልኝ።
በእኔም እምነት የትኛውም ዓይነት የደቡብ ብሔሮች ጥያቄ ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት በክልሉ ብሔሮች ብቻ መቅረብ አለበት ብዬ አምናለሁ። ማንም ማዕከላዊ መንግስትን ለማዳከም የደቡብ ብሔሮችን ጥያቄ በመሳሪያነት ለግሉ አጀንዳ መጠቀም እንደሌለበት ስናስገነዝብም ወራት አልፈዋል። ሆኖም ግን መንግስት በተለይም የክልል ጥያቄዎችን በተመለከተ የያዘው ግትርና አዝጋሚ የመፍትሔ አሰጣጥ ሂደት በቆይታ የክልሉን ብሔሮች ፖለቲካዊ ዳይናሚክስ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዳይወስደውም በተደጋጋሚ እንደ አቅማችን ስንጮህ ነበር። ይህን በተመለከተ በቅርቡ ፖስት ያደረኩት ልጥፍ መልዕክት ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል፦
“በአሁኑ ወቅት በመንግስት አዝጋሚና ግትር የውሳኔ አሰጣጥ የተሰላቹ የደቡብ ብሔሮች ቀደም ሲል ለብልፅግና ፓርቲ የነበራቸውን ውግንና በማለዘብ ሌሎች አጋር ፓርቲዎችን በማፈላለግ ላይ ይገኛሉ፤ እናም ይህን ክፍተት የተገነዘቡ ፅንፈኛ ብሔርተኞችና ሌሎች ፓርቲዎችም ዓይናቸውን ወደ ደቡብ ብሔሮች እያማተሩ ይገኛሉ፣ የብልፅግና ፓርቲ ቀጣዩን የደቡብ ፖለቲካ ዳይናሚክስን ለመተንበይ አቅም ያጣ ይመስላል።”
እንግዲህ የብልፅግና ፓርቲ ዛሬ የዎላይታን አመራሮች፤ “ለውጡን ከማይደግፉ አካላት ጋር በጋራ እየሰሩ” ነው በማለት እየከሰሳቸው ይገኛል። እኛ ደግሞ ይህ ሊከሰት እንደሚችል ቀድመንም ያሳወቅነው ሐቅ ነው፣ የተቸገረ እርጉዝ እንዳያገባ ክፍተቶችን ከመፍጠራችን በፊት እንዳይቸገር ማድረጉ ጥሩ አማራጭ ነበር። አስቸግረነው እርጉዝ ካገባ በኋላ ግን “ስለ ምን እርጉዝ አገባህ?” ብሎ መክሰሱ አዋጪ መስሎ አይታያንም። ሲቀጥልም ዋናውን ምንጭ ትቶ “አባሪው” ላይ ጦር ማስዘመት ምን ያህል አመክንዮአዊ ነው? የዲፋክቶ መንግስት ከፍ ሲልም ክልልን ለመገንጠል ወደሚፎክሩት በመንግስት ዕውቅና ሽማግሌ እየተላከ በሕገ መንግስቱ መሠረት የክልል እንሁን ጥያቄ ወዳነሱት ዞኖች፣ የጦር ኃይል መላኩስ የቱን ያህል ፍትሐዊ ነው?
 እስካሁን ድረስ በዎላይታ ለተቀጠፈው የወጣቶች ሕይወት እንደ ክልሉ ተወላጅም እንደ ኢትዮጵያዊነቴም ሐዘኔን እገልፃለሁ። የዎላይታ ሕዝብ ከጅምሩም የለውጡ ደጋፊና በኢትዮጵያዊነቱም የማይደራደር ኩሩ ሕዝብ ስለመሆኑ የአደባባይ እውነት ነው። አሁን እየተፈጠረ ያለው ሁኔታ ግን ዎላይታነቱን ከኢትዮጵያዊ ማንነቱ ጋር እንዳያጋጭበት ስጋቱ አለኝ። አሁንም ቢሆን በክልል ጥያቄ ሰበብ በዎላይታም ይሁን በሌሎች የደቡብ ዞኖች የአንድ ሰው ሕይወት እንኳን መቀጠፍ የለበትም፣ የዎላይታ ወጣቶችን ጨምሮ የሌሎች የደቡብ ብሔሮች ወጣቶችም ሕገ መንግስታዊ ጥያቄን ሕጋዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ብቻ ማቅረብ እንዳለብን ለአፍታም መዘንጋት የለብንም። ሰላማዊ አካሄድ የኃይል እርምጃ አመክንዮችንና ሰበቦችን የማክሸፍያ አዋጪ ስልት ነው!


Read 621 times