Saturday, 15 August 2020 00:00

“ሁላችንም ወደ ቀልባችን መመለስ አለብን”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

           • ኦሮሚያ ውስጥ ሰላም ካልተፈጠረ፣ ኢትዮጵያ ሰላም አትሆንም
           • ሁሉም ያለውን ሃሳብ የሚዘረግፍበት የውይይት መድረክ ያስፈልገናል
           • ኢ-ዲሞክራሲያዊ መንገድ ዲሞክራሲን አያመጣም

              የፖለቲካ መሠረቱን ኦሮሚያ ላይ አድርጐ የሚንቀሳቀሰው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ም/ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ፤ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ፣ በክልሉ የተፈጠረውን ሁከትና ግርግር እንዲሁም የሰው ህይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት አስመልክቶ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ እንደሚከተለው አነጋግሯቸዋል፡፡ እነሆ፡-

              በየጊዜው በኦሮሚያ ክልል በሚፈጠሩ ነውጦች የበርካቶች ህይወት እየጠፋና ንብረት እየወደመ ነው፡፡ በክልሉ እንዲህ ያሉ ጥፋቶች በተደጋጋሚ የሚከሰቱት ለምን ይመስልዎታል?
ትልቁ ችግር በሀገሪቱ ብሔራዊ መግባባት አለመፈጠሩ ነው፡፡ ሌላው መንግስት መቼም ጠንካራ የደህንነት ተቋም እንዳለው ነው የሚነገረው፡፡ ይህ የደህንነት አካል ምን ያህል ስራውን እየሠራ ነው? ፀጥታ የሚነሱትን ሰዎች ለይተው አያውቁም ብለን አናምንም፡፡ ምክንያቱም ኢህአዴግ ውስጥ ነበሩ፡፡ ኢህአዴግ ደግሞ በ1 ለ5 ጥርነፋው እያንዳንዷን ነገር ነው የሚያውቀው:: ደህንነቱም ውስብስብና ጠንካራ ነው:: በዚህ አይነት ሁኔታ ሰው ሰውን ገድሎ ይጠፋል ብለን አናምንም፡፡ ነገር ግን ለውጡ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ሰዎች በኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎችም ይገደላሉ፡፡ ነገር ግን ማን ለምን ገደላቸው የሚለው ጉዳይ አይነገርም ወይም አይታወቅም፡፡ ይሄ በኢትዮጵያ ምድር ላይ በጣም አሳዛኝ ክስተት ነው፡፡ ከዚያ ባለፈ ግን ህዝብ ለህዝብ ይጋጫል የሚባለው ለኔ እንቆቅልሽ ነው፡፡ ህዝብ ከህዝብ ጋር ፈጽሞ አይጋጭም፡፡ አንዱ በአንዱ ላይ የሚነሳበት ምክንያት የለም፡፡
አሁን በኦሮሚያ የተከሰተውን ግድያና ውድመት እንዴት ይገመግሙታል?
አንዱ በአንዱ ላይ ይነሳል፤የጐሣ የእርስ በርስ ግጭት ይፈጠራል የሚባለው ነገር ሁኔታዎችን ለማባባስ ካልሆነ በስተቀር በተግባር መሬት ላይ የለም፡፡ በአጋጣሚ ሆኖ ሁለት ሰዎች ወይም አካላት ከተጣሉ በሚዲያው የሚቀርበበት ግነት ያዘለ ዘገባ ልዩነትን ለማስፋት እንጂ ችግሩን ለመፍታት የሚረዳ አይደለም፡፡ የጐሣ ነው የሃይማኖት ነው፤ የብሔር ነው እያሉ ክፍፍል ለመፍጠር ነው አላማ የሚደረገው:: ነገር ግን የተረፉትን ሰዎችስ ማን ነው ያዳናቸው? በእርግጥ ህዝቡ ነቅሎ ወጥቶ ነው ጥቃት የፈፀመው ወይስ ጥቂቶች ናቸው የፈፀሙት? የሚለውን መርምሮ እውነታውን ለህዝብ በማቅረብ የህዝቡን የቆየ ማህበራዊ መስተጋብር ለመጠገን ከመስራት ይልቅ ወደ አንድ ጽንፍ እየጐተቱ ነገሩን ለማባባስ ነው ጥረት የሚያደርጉት፡፡ የበለጠ ልዩነትን ለማስፋት ነው ጥረት የሚደረገው፡፡ ከዚህ ምን አይነት መልካም ውጤት እንደሚገኝ አላውቅም፡፡ ህዝባችን ግን ለብዙ ዘመን አብሮ የኖረ ነው፤ ዝም ብሎ በድንገት ተነስቶ የሚለያይ አይደለም፡፡ ይሄን የሚያስቡ ካሉም ተሳስተዋል፡፡ አሁን በየቦታው የሚፈፀመው መሠረት የሌለው አርቴፊሻል ነገር እንጂ የህዝቡን የቆየ ማህበራዊ ህይወት የታሰበውን ያህል የሚያናጋ  አይሆንም፡፡ የሚያለያይና ለሀገር ጠንቅ የሚሆን ጉዳይ አይደለም፡፡
ድርጊቱ ከተፈጸመ በኋላ ቢሆንም መንግስት ተጠርጣሪዎችን ለህግ ለማቅረብ ያሳየውን ቁርጠኝነት ብዙዎች እያደነቁት ነው፡፡ እናንተስ እንዴት አገኛችሁት?
በመንግስት በኩል አሁንም እስራቱ እንደቀጠለ ነው፡፡ እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ይሄ የፖለቲካ ልዩነት በእስራት የሚፈታ አይደለም፡፡ እስከ ዛሬም በእስራት የተፈታ ችግር የለም፡፡ እንዲህ ያለው ነገር የሚፈታው ቀርቦ በመነጋገር፣ በውይይት ነው፤ ችግሮችን አንጥሮ አውጥቶ ተወያይቶ መተማመን መፍጠር እንጂ ማሰር ብዙም ዋጋ የለውም፡፡ ከዚህ በፊትም እንዲህ ያለው እስር ሲፈፀም ነበር፤ ያመጣው ውጤት ግን የለም፡፡ #አንተ የዚህ ደጋፊ ነህ; በማለት የሚፈፀም እስርና ደባ ለመንግስትም ለታሳሪውም አይጠቅምም፡፡ ልዩነቶችን በዚህ መልኩ እያገዘፍን በሄድን ቁጥር ለሀገሪቱ ጠንቅ ነው የሚሆነው፡፡
መንግስት የህግ የበላይነትን ማስጠበቅ የለበትም እንዴ?
የህግ የበላይነት የግድ ማስጠበቅ ይገባል፡፡ የህግ የበላይነት ሲጠበቅ ግን በሸርና በተንኮል መሆን የለበትም፡፡ እጅግ በጣም ምክንያታዊ የሆነና ሰዎችን ማሳመን የሚችል መሆን አለበት፡፡ አሁን ግን እንደዚያ አይመስልም፡፡ የቀድሞ አይነት የፍ/ቤት ሂደትም እየተመለሰ ነው ያለው፡፡ ግማሹ በህግ በተቀመጠው መሠረት በ48 ሰዓት ውስጥ ፍ/ቤት አይቀርብም፡፡ ሌላው ዋስትና በፍ/ቤት ሲፈቀድለት ፖሊስ የፍ/ቤትን ትዕዛዝ ወደ ጐን ትቶ ግለሰቡን ያለ አግባብ አስሮ ያቆየዋል፡፡ እንዲህ ያሉ የህግ ክፍተቶች ካሉ የህግ የበላይነት ጉዳይ መተማመን አይፈጥርም፤ አስቸጋሪ ነው፡፡ የህግ የበላይነት በትክክል አጥፊዎችን በህግ የመጠየቅ ጉዳይ ነው፡፡ እንዲህ ያለው እስር ግን አላማው መንግስትን እንዲፈራ ማድረግ ነው፤ ይሄ ደግሞ ለማንም የሚጠቅም  አይሆንም፡፡
ብዙ ጊዜ ሰዎች ተገድለውና ንብረት ወድሞ እናንተ ድርጊቱን ከማውገዝ ይልቅ "የፖለቲካ አባሎቻችን ያለአግባብ ስለታሰሩ ይፈቱልን" ብቻ ነው የምትሉት የሚል ወቀሳ ይሰነዘርባችኋል፡፡ እውነት ለምንድን ነው እንዲህ ዓይነት ድርጊቶችን በግልጽና በይፋ ደጋግማችሁ የማታወግዙት?
በኛ በኩል ሁልጊዜ የምናምነው ሰውን መግደል ኢ-ሰብአዊነት ነው ብለን ነው፤ ንብረት ማውደምን እናወግዛለን፤ ደጋግመንም አውግዘናል፡፡ የሰዎች ህይወት በግፍ መጥፋቱ፣ የለፉበት ንብረት በአንድ ጀንበር መውደሙ በእጅጉ ያሳዝነናል፡፡ ከማቃጠልና ከማውደም የሚገኝ ቅንጣት ጥቅም የለም፤ ይሄን እኛ ሁሌም የምናወግዘው ነው፡፡ ሁሉም ትግል ሠላማዊ እንዲሆን ነው የምንሻው፡፡ ጦርነትና የሃይል እርምጃ ሁሉ ለዲሞክራሲ ጠቃሚ አይደለም፤ ኢ-ዲሞክራሲያዊ መንገድ ዲሞክራሲን አያመጣም፡፡ ከጦርነትና  ከግጭት የሚያተርፍ ማንም የለም፡፡ በመወያየት በመግባባትና የህዝባችንን እሴት በመጠበቅ ችግሮችን መፍታት አሁንም ቢሆን ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም፡፡ ህዝባችን ሁሉንም ነገር ያውቃል፡፡ በሆታና በጉልበት የሚደረጉ ነገሮችንም አይቀበላቸውም:: በመመካከር በመስማማት ነው ነገሮች እንዲፈቱ የሚፈልገው፡፡ መሆንም ያለበት ይሄ ነው፡፡
አንዳንዶች በክልሉ የተፈፀመው ድርጊት "ብሔርንና ሃይማኖትን መሰረት አድርጎ የተፈጸመ ጥቃት ነው" ሲሉ "የጅምላ ጭፍጨፋ ነው እውቅና ይሰጠው" የሚሉ ወገኖችም አሉ፡፡ በእናንተ በኩል የተፈፀመው ድርጊት ምንድነው ትላላችሁ?
ሁሉም ለራሱ በሚመቸው መንገድ "እገሌ አላጠፋም እገሌ አጥፍቷል፤ እኔ አላጠፋሁም እሱ አጥፍቷል" ነው የሚለው፡፡ ለራሱ በሚመቸው መንገድ ነው ነገሩን ማየት የሚፈልገው፡፡ ለዚህ መፍትሔው ገለልተኛ የሆነ አካል የተፈፀመውን ነገር እንዲያጣራ ማድረግ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈጸሙ መሠል ድርጊቶች በገለልተኛ አካል እንዲጣሩና እውነቱ እንዲታወቅ ነው የኛ አቋም፡፡ ስለዚህ ይሄንንም ገለልተኛ አካል አጣርቶ ነው ጉዳዩን ማቅረብ ያለበት፡፡ የህሊና ዳኝነት የሚሠጥና ነፃ ሆኖ የሚያጠና ገለልተኛ አካል ያስፈልጋል፡፡ የኛም ጥያቄ ይሄ በአፋጣኝ እንዲከናወን ነው፡፡      
ግን ለምንድን ነው ተመሳሳይ የጥፋት ድርጊቶች ተደጋግመው የሚፈጸሙት?
አንደኛ ህገ መንግስቱን ሙሉ በሙሉ ያለማክበር ችግር ነው፡፡ ለኛ ሲመቸን ብቻ ማክበር ካልተመቸን ደግሞ ወደ ጐን ማድረግ ይህቺን ሀገር ለተወሳሰበ ችግር ዳርጓታል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይሄ ህግን ሙሉ ለሙሉ ያለማክበርና ለህግ ያለመገዛት ጉዳይ ያመጣው ነው፡፡ ባለፉት 30 አመታት ባህል ሆኖብን ስር የሠደደና አሁን በኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለሚፈጠሩ #ከዚህ ውጣልኝ፣ ይሄ ያንተ ግዛት አይደለም; ለሚሉ ውዝግቦች የዳረገን ጉዳይ ነው፡፡  
እንደ አንጋፋ ፖለቲከኛ ለዚህ መፍትሔው ምንድን ነው ይላሉ?
ሁላችንም ወደ ቀልባችን መመለስ አለብን:: መፍትሔው የሚጀምረው ከዚህ ነው፡፡ አንዱ የአንዱን ሸክም ለማቃለል፣ እንዴት እንረዳዳ ብሎ መመካከር ያስፈልጋል:: የአማራ የፖለቲካ ልሂቃን ኦሮሞን ምንድን ነው ችግርህ? የኦሮሞ ልሂቃን አማራን ምንድን ነው ችግርህ? ሌላውም እንደዚሁ እየጠየቀ ቁጭ ብሎ የጋራ ውይይት ማድረግ ይገባዋል፡፡ ምንድን ነው ቅሬታችን? እንደዚህ የሚያናቁረን ምንድን ነው? በማለት የፖለቲካ ተዋንያኑ ወደ አንድ ጠረጴዛ መጥተው ጥልቅ ውይይት ማድረግ አለባቸው:: እንዴት ብናደርግ እና ምን ብንሆን ይሻላል የሚለውን መነጋገር ያስፈልጋል:: በሃይልና በጉልበት የምናተርፈው በጐ ነገር አይኖርም፡፡ ትርፉ መጠፋፋት ብቻ ነው:: እንዲህ ያለውን አካሄድ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ሞክረን አይተነዋል:: ጉልበተኛ ለጊዜው በጉልበቱ ፀጥ ለጥ አድርጐ ሊገዛ ይችላል፤ ግን ለትውልዱ የተቀበረ ቦንብ ነው የሚያስቀምጠው፡፡ ላለፉት 150 አመታት በዚህች ሀገር የሆነውም ይሄው ነው፡፡ በሃይል ይቀዘቅዛል እንጂ መቼውንም የሚጠፋ የህዝብ ጥያቄ የለም፡፡ ጊዜ ሲያገኝ የተዳፈነበትን አመድ አራግፎ የሚፈነዳ ነው የሚሆነው:: ስለዚህ መፍትሔው ይህቺ ሀገር አድርጋው የማታውቀውን አይነት ውይይት ማካሄድ ብቻ ነው፡፡ ሁሉም ያለውን ሃሳብ የሚዘረግፍበት፣ ጭነቱን የሚያራግፍበት ብሔራዊ የውይይት መድረክ ያስፈልገናል:: ብሔራዊ ውይይት ያደረጉ ሀገሮች ዛሬ በውጤታማነት ችግራቸውን ፈተው መሻገር ችለዋል፡፡ የጋራ ሀገር የምንገነባው በዚህ መንገድ ነው፡፡ አሁን ግን ሁላችንም የየራሳችንን መዝሙር እየዘመርን ነው:: ይሄ መዝሙር ደግሞ አስቸጋሪ ነው:: የአንዱ መዝሙር ለሌላው አይመቸውም፡፡ "ድንበሬን ገፋህ፣ ታሪካዊ መሬቴን ነጠቅከኝ፣ መሬቴን ለቀህ ውጣ" እየተባባልን በየራሳችን መንገድ እየዘመርን ከሄድን፣ መገፋፋቱን እያሰፋን ከመሄድ በቀር የሚኖረው በጐ ውጤት አይኖርም፡፡ በዚህ ሁኔታ እኮ ወደ ምርጫ ብንገባም ቁርሾ ተይዞ ስለሚሆን ወደ ኋላ ነው የምንመለሰው፡፡ የቀድሞውን የምርጫ ሂደትና ታሪክ ነው የምንደግመው:: ለውጡም ቢሆን ፍኖተ ካርታ ይኑረው፤ መሸጋገሪያ መርህ ይኑረው ብለን ነበር፤ ክቡር ጠ/ሚኒስትሩ ግን "እኔ አሸጋግራችኋለሁ" አሉ፡፡ ግን የብሔራዊ ውይይት መድረክ አልፈጠሩም፡፡   
ግን እኮ የፖለቲከኞች ዘር ተኮር ትርክት ነው ህዝብን እርስ በርሱ የሚያጋጨው? በፖለቲከኞች ያለፈ ትርክት ህዝብ እየተጎዳ እስከ መቼ  ይቀጥላል?
ህዝቡ አብሮ የኖረ ነው፡፡ በክፉም በደጉም አብሮ ሲረዳዳ የኖረና የቆየ ህዝብ ነው፡፡ አንዱ ህዝብ ሌላውን ተነስቶ ከዚህ ውጣልኝ አይልም:: ማንም ኢትዮጵያዊ የፈለገበት ቦታ መኖር እንደሚችል ደግሞ በህገ መንግስቱ ተደንግጓል:: ከዚህ በፊት በታጠቀ ሃይል ለፖለቲካ አላማ ከ1 ሚሊዮን በላይ ኦሮሞ ከሶማሌ ክልል ተፈናቅሏል፤ በተመሳሳይ ለሌላ የፖለቲካ አላማ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ከ2 መቶ ሺህ በላይ ኦሮሞ እንዲፈናቀል ተደርጓል፣ በጉጂም ተመሳሳይ ድርጊት ተፈጽሟል:: ሌላው ህዝብም እንዲሁ ለፖለቲካ አላማ እንዲፈናቀል ተደርጓል:: ይሄን ታዲያ ማስተካከል የማን ኃላፊነት ነው? መንግስት የሚያስፈልገው ለምንድን ነው? የዜጐችን የመኖር ዋስትና ለማስጠበቅ አይደለም እንዴ? እንዲህ ያሉ ችግሮችን እንዴት ቀድሞ መከላከል አይቻልም? መንግስት በእጁ ላይ በህግ የተሰጠ ስልጣን አለው፤ መሣሪያ አለው፤ ጉልበት አለው፡፡ ታዲያ ለምንድን ነው በተደጋጋሚ እንዲህ አይነት ችግር የሚፈጠረው? ይሄን መንግስት ራሱ ነው መመለስ ያለበት:: አብዛኛው መፈናቀል የሚፈፀመው በታጠቀ ሃይል ነው፡፡ ያ ታጣቂ ሃይል ማን ነው? እንዴት አይታወቅም? የቤተ እምነቶች መቃጠልም ተመሳሳይ ነው:: ለምሣሌ ሞጣ ላይ መስጊድ ተቃጠለ፡፡ መስጊዱን ያቃጠሉት እነማን ናቸው? ምን አላማ ነበራቸው? የሚለውን ማንም በግልጽ ያቀረበ የለም፡፡ ግን ገንዘብ ምናምን ተዋጥቶ እንደገና ተቋቋመ:: በተመሳሳይ ሻሸመኔ ቤተ ክርስቲያን ተቃጠለ ተባለ፡፡ አሁንስ ማን አቃጠለው?  ምን አላማ ነበራቸው? የሚለው በግልጽ እየቀረበ አይደለም፡፡
እነዚህን ተቋማት በተመለከተ ማን ለምን አላማ አቃጠላቸው የሚለው ጥያቄ ነው መመለስ ያለበት፡፡ ይሄን የመመለስ አቅም ያለው ደግሞ መንግስት ነው፡፡ እነዚህ ተቋማት ሲቃጠሉ፣ ሰዎች ሲገደሉ፣ ንብረት ሲወድም መንግስት በአካባቢው የለም እንዴ? የታጠቀ ፖሊስ ሃይል የለውም እንዴ? ለምን የዜጐችን ህይወት አስቀድሞ መታደግ አልቻለም? መንግስት እንዴት በህግ የተሰጠውን ዋነኛ ኃላፊነት ይዘነጋል? ይሄ መዘንጋቱስ ከተጠያቂነት ያድነዋል? አንዳንዱ የፀጥታ ሃይል እኮ "ለምን አልተከላከልክም?" ሲባል "ከመንግስት ትዕዛዝ አልተሰጠኝም" ሲል ነበር፡፡ ለዚህ አሁን ማነው ተጠያቂው? ጉልበተኛን ዘራፊን ማስቆም የማን ኃላፊነት ነው? ሁሌም ወደ አዕምሮዬ የሚመጣ  ጥያቄ ነው፡፡
የሀገሪቱ የፖለቲካ ችግር እንዴት ነው መፈታት የሚችለው?
አሁን በየቦታው የፖለቲካ መፈረካከስ አለ:: በትግራይ፣ በደቡብ፣ በኦሮሚያ፣ በሌላውም ደረጃው ይለያይ እንጂ አለ፡፡ ለዚህ ደግሞ በየቦታው ግርግር መፍጠርና ዝም ብሎ ሴራ ማሴር ሳይሆን ሁነኛ መፍትሔ ያስፈልጋል፡፡ ለምሣሌ ትግራይ ውስጥ የሚካሄደውና እዚህ ፌደራል ላይ የሚካሄደው እኮ ትግራይን ወደ ኢትዮጵያ ከመሳብ ይልቅ ወደ ማስገንጠል የሚገፋ ነው፡፡ አሁን ምርጫው ከተካሄደ በኋላ የኢትዮጵያ አካል ላለመሆንም ጥያቄ ሊቀርብ ይችላል ማለት ነው፡፡ መለስ ዜናዊ ኤርትራን አስገነጠለ፡፡ አሁንም ትግራይን ልናስገነጥል ነው? በትግራይና በአማራ መካከል በተለይ ወልቃይት አካባቢ ያለው ችግር በጣም ውስብስብና አስቸጋሪ ነው:: ኦሮሚያ ውስጥ የሚንተከተከተው ነገር ለኢትዮጵያ ሠላም አይሠጣትም፡፡ ኦሮሚያ ውስጥ ሰላም ካልተፈጠረ፣ ኢትዮጵያ መቼም ሰላም አትሆንም፡፡ በደቡብ የሚነሱ የክልልነት ጥያቄዎችን ሁሉ ማፈን ምን ያህል ሰላም ያመጣል? ይሄን ማድረግ ምንድን ነው ጥቅሙ? ጥያቄ የሚያቀርብን ማሰር ምን ውጤት ያመጣል? ለምሣሌ የሲዳማ ህዝበ ውሣኔ የተደረገው ስንት ሰው ከሞተና ካለቀ በኋላ ነው:: ታዲያ ለምንድን ነው መመለሱ ለማይቀር ጥያቄ አሁንም የህዝብ ህይወት  የሚጠፋው፡፡ ከዚህ አጣብቂኝ መውጫው መንገድ በአፋጣኝ ወደ ብሔራዊ ውይይት መግባት ነው፡፡ ሂደቱ መጀመሩ በራሱ የተፈጠረውን ውጥረት ያረግበዋል፡፡         

Read 1200 times