Sunday, 16 August 2020 00:00

“እባካችሁ፣ እባካችሁ፣ እባካችሁ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

 "እናማ… “እባካችሁ፣ እባካችሁ፣ እባካችሁ…” እየተባለ እስከ መቼ ሊዘልቅ ይችላል! ነገሮች ወደ ጎርፍነት፣ ነገሮች ወደ 8.5 የሪከተር መለኪያ መሬት መንቀጥቀጥነት፣ ነገሮች ወደ ናዳነት መለወጥ ሳያስፈልጋቸው ቀና ማለቱ፣ ቀበቶ ማጥበቁ ሳይሻል አይቀርም!--"
                  
           እንዴት ሰነበታችሁሳ!
“የዘንድሮ ብርድ ለብቻው ነው፡፡” ሰሞኑን በስልክም፣ በምንም የምንለዋወጣት አባባል ነች፡፡ እውነትም የዘንድሮው ከባድ ብርድ ነው፡፡ ተፈጥሮም ያዘነችለን አይመስልም፡፡ ይሄን ያህል ‘ሳስተናል’ እንዴ! እኛም በቆዳና በአጥንታችን መሀል ብዙም ‘ማቴሪያል’ የሌለን፣ እነኛም ልብሰ ሰፊውን… “ለመለካት እንዲህ እየተሽከረከረ ከሚሰቃይ መለኪያ ማሽን የማያስመጣሳ!” የሚባልላቸውም ‘እኩል’ እየተንዘፈዘፍን ነው፡፡ “እሰይ ስለቴ ሰመረ!” ብለን የምንጨፍርበት ‘እኩልነት’ አይደለም እንጂ!
“ስማ፣ ክረምቱን እንዴት ይዘኸዋል?”
“ይዞኛል እንጂ ምን እይዘዋለሁ!”
“አጅሬው እንደሁ መከላከያ ነገር አታጣም…”
“አንተ ምን አለብህ፣ አሹፍብኝ እንጂ…”
“ምነው… እነ ባሮንስ የቅንጦት መጠጥ ሆኑ እንዴ!”
“ከአንድ ስኒ በላይ  ቡና መጠጣት አቅቶናል አንተ ስለባሮንስ ታወራለህ፡፡”
የምር ኑሮ ከብዷል..ጤፉ በኩንታል አራት ሺህ ምናምን ብር፣ ያቺ ከአፋችን አልጠፋ ያለች ሲገዟት አቃጣይ፣ ሲልጧት አቃጣይ ሽንኩርት ኪሎ አርባ ብር፣ አንድ ሻይ ከቦምቦሊኖ ጋር በርካሽ ሲገኝ ሀያ አምስትና ሠላሳ ብር በሆነበት እንዴት ብሎ ነው ለባሮንስ የሚተርፈው! በሰሞኑ አይነት ብርድ ባሮንስ ከ‘አስፈላጊ’ ግብአቶች ጋር ልትደመር ትችላለቻ! ቂ…ቂ…ቂ…
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… የአዲስ አበባ መንገዶች ያው ‘የክረምት መደበኛ አገልግሎታቸውን’ እየሠጡ ነው:: ልክ ነዋ…ውሀ በማቆር አዲስ አበባን የሚስተካከል ትልቅ ከተማ እስቲ ፈልጉ! ነገርዬው እኮ ቱሪስትን ማባበያ የማይሆን ሆኖ ነው እንጂ ፓሪስና ዱባይ ጭር ይሉ ነበር፡፡ መከረኛው የአዲስ አበባ እግረኛም ፈገግ ያለ ነገር ለብሶ ከቤቱ ይወጣና ‘አስነክሮት’ ይመለሳል፡፡ ኸረ እባካችሁ… የቀበሌ አዳራሽ በሚያካክሉ መኪኖች እየከነፋችሁ በየአንዳንዱ ሊትር ሰባ ግራም አፈር የያዘ የሚመስለውን ውሀ አትርጩን! አንዳንዱ አሽከርካሪ እኮ ሆነ ብሎ ወደ እግረኛ መንገድ የሚጠጋ ነው የሚመስለው:: እንዲህ ‘ሞራል’… አለ አይደል… ‘የቅንጦት እቃ’ ነገር በመሰለበት ሁኔታ ሥራዬ  ብለው አግረኞችን በመርጨት የሚደሰቱ ቢኖሩ አይገርምም፡፡ (በአንድ ወቅት… “ዊርድ ሰው በዝቷል፣” ያልከው ወዳጃችን ዘግይተንም ቢሆን ትርጉሙን እያገኘነው ነው፡፡)
ስሙኝማ…የኮቪድ አስራ ዘጠኝን ወረርሽኝ ለመቋቋም ይኸው ወራትን ያስቆጠረ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አለ፡፡ በአዋጁም የተደነገጉ ህጎች አሉ፡፡ ህግ ደግሞ የሚወጣው ወደድንም ጠላንም እንዲከበር ነው፡፡ አሁን ወረርሽኙ ነገን በምንፈራበት ደረጃ እየተስፋፋ ያለው አንደኛውና ምናልባትም ዋነኛው ምክንያት አነኝህን ህጎች ሁሉ እንደሌሉ ስላደረግናቸው ነው:: በሚዲያ የ“እባካችሁ” ተማጽኖ እየሰማን ነው፡፡ እባካችሁ የፊት መሸፈኛ አድርጉ፣ እባካችሁ እርቀታችሁን ጠብቁ፣ እባካችሁ እጆቻችሁን ታጠቡ…እባካችሁ፣ እባካችሁ፣ እባካችሁ… “እባካችሁ፣” የሚለውን ጥሪ መስማት ካልቻልን ታዲያ ምን ይሻላል!
በዋና ከተማዋ ጭምብል የሚያደርገው ሰው ቢያንስ ሰማንያ በመቶዎቹ እንኳን አለመድረሱ ማስደንገጥ ይገባው ነበር፡፡ እርቀትን ያለመጠበቅ ብቻ ሳይሆን አሁን እኮ ሰዉ በየአውቶብስ ፌርማታ መጋፋት እየጀመረ ነው…እንደ ድሮው፡፡ ‘ህዝብ ማስተማር’ የምትባለዋ ነገር ሲሰሟት ደግ ነች፡፡ ግን እኮ ሀያ ዓመት አሽከርከሮ ቀይ መብራት የሚጥሰውን ሰው ስለ ትራፊከ መብራት አጠቃቀም ለማስተማር መሞከር ስታንድ አፕ ኮሜዲ ቢሆን ነው፡፡ በሁሉም ወገን ያለ ቸልተኝነት ሁላችንንም ነው ዋጋ የሚያስከፍለን፡፡ “ጭምልብህን አላደረግህም፣” ሲባል “አያገባህም!” ባይ በበዛበት ነገሮች በጣሙኑ ነው አስቸጋሪ የሚሆኑት፡፡
መሀል ከተማ ነው፡፡ አውቶብሶች መቆሚያ ስፍራ በፊት ከነበረበት መንገድ ተሻግሮ ወዳለ ስፍራ ተሸጋግሯል፡፡ ሰዉ በአምስት ረድፍ ሆኖ ይጠብቃል ሳይሆን እንደ ጉድ ላይ በላይ ተዛዝሏል፡፡ በእርግጥ አብዛኛው ሰው ማስክ አድርጓል፡፡ ግን እኮ የፊት መሸፈኛውም ቢሆን ሊከላከልበት የሚችልበት የሚሳሳበት የሆነ መስመር አለው እኮ! እንደዛ አፍ ለአፍ ገጥመን እየተጋፋን ማስካችን እንደ ካዛና መዝጊያ ግጥም ቢልም ዋጋ የለውም፡፡ (በነገራችን ላይ፣ በየበሮቻችሁ ‘ማክስ’ እያላችሁ የጻፋችሁ መደብሮች ወይ አስተካከሉ፣ ወይ የፈረንጅ አፍ ይቅርባችሁ!)
 አንድ አባት ፈንጠር ብለው ቆመው እጃቸውን አፋቸው ላይ አድርገው ትርኢቱን ትኩር ብለው እያዩ ነበር::  መናገር አላስፈለጋቸውም፡፡ ለሚያዩት ሁሉ ትርጉም እንዳጡለት ገጽታቸው ላይ ይነበባል፡፡ አስገራሚ የሚያደርገው ነገር በአንድ በኩል ሰልፍ ቢጤ እየሞከርንም፣ በሌላ በኩል እየተገፋፋንም እንዴት ይሆናል? አውቶብሶቹ ከተፈቀደላቸው በላይ አይጭኑም… ቢያንስ፣ ቢያንስ እስካሁን በዛ በኩል ይህን ያህል ከመስመር ውጪ የሆነ ተግባር ስለመፈጸሙ የሰማነው ነገር የለም፡፡ 
ከፈለገው የዓለም ክፍል ድንገት ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ ሰዎች በከተማችን ሁኔታ  ቢደናገጡ አይገርምም፡፡ “ምን የጉድ ሀገር ነው!” ቢሉን የሚገርም አይሆንም:: “እነኚህ ሰዎች ነገር አይግባችሁ የሚል እርግማን አለባቸው እንዴ!” ቢሉን አይገርምም፡፡ “ይህን ያህል ነገሮችን የመረዳት ችግር አለባቸው እንዴ!” ቢሉን “ድሮም የእኛ ጠላት ብዙ ነው ብለን መከላከያ አጥር የምናቆምበት አይደለም፡፡
አሁን አምስት መቶ ሰው ተያዘ ሲባል፣ ሰባት መቶ ሰው ተያዘ ሲባል ምናልባትም የሚታየን ከቁጥር ጀርባ ያሉት ዜሮዎች እየበዙ መሄዳቸውን አንጂ እነኛ ዜሮዎች መቶዎችና ሺዎችን የሚወክሉ መሆናቸውን አይደለም፡፡ እንደዛ ብናስብ ኖሮ ይህን ያህል ግዴለሽነት ባልታየም ነበር፡፡
የምር ግን ምን መሰላችሁ… መዘናጋት የሚለውን ቃል ሁላችንም እየተጠቀምንበት ነው፡፡ “ሰዉ እኮ ተዘናግቷል፣” እንላለን:: ከራሳችን አርቀን እንዳናስብ  እያደረገን ያለው ግዴለሽነት ሌላ፣  መዘናጋት ሌላ፡፡
እነኚህ ድርጊቶች ዳግም እየተለመዱና እየተስፋፉ ከመምጣታቸው የተነሳ ትክክለኞች እየመሰሉ ነው፡፡ መጀመሪያ ሰሞን መመሪያዎችና ህጎች ከሞላ ጎደል መከበር ጀምረው ነበር፡፡ አሁን ነገሮችን ‘ቢዝነስ አዝ ዩዥዋል’ አይነት ሲመስሉ… አለ አይደል… “ነገሮች ሁሉ ለይቶላቸው ሊበላሹ ነው እንዴ!” እያልን ብንሰጋ አይገርምም፡፡
እናላችሁ…  ከፍተኛ እጥረት ካሉብን ነገሮች መሀል አንዱ የመልካም ዜና እጥረት ነው፣ የበጎ ዜና እጥረት ነው፡፡ እናማ…አሁን ይሄን ሁሉ የትንሹንም፣ ትልቁንም ግዴለሽነት እያየን  እንዴት ነው ጠለቅ ብሎ ማሰቡ ያዳገተን ያሰኛል፡፡ “ይቺን ሳምንት እንኳን ደግ ነገር እየሰማን፣ ደግ ነገር እያየን ባሳለፍናት፣” ብለን ወጣ ስንል የአውቶብስ ግፊያና ደረቶችና ጀርባዎች የተለጣጠፉባቸው የታክሲ ተሳፋሪዎች ሰልፎች ስናይ ስጋት ቢገባን አይገርምም:: ችግሩ ብዙዎቻችን አንኳን ስጋት ሊገባን…ነገሮችን  ‘ቢዝነስ አዝ ዩዥዋል’ ብለን የተቀበልናቸው ነው የሚመስለው፡፡ አንድ ሰሞን ሳተላይት አመጠቅን ብለን ደረታችንን ነፋ አድርገን የነበርን ሰዎች እንዴት ነው ማገናዘብ ያቃተን ያስብላል፡፡
ይህንን ለእኛ ለማስረዳት መቼም የእንትን ሀገር ኮንሰልታቶች ጥናት አያስፈልገንም:: መልካም አስተሳሰብ ይበቃል፡፡ ለእኛም፣ ለሌላውም እኩል ማሰብ ይበቃል፡፡ ለሀገርና ለትውልድ ማሰብ ይበቃል፡፡
የምር በጣም አስቸጋሪ ጊዜ ነው…በአሁኑ ጊዜ የወረርሽኙ ነገር እንዳለ ሆኖ በአንድ ሺ አንድ ችግሮች የተዋሳሰብን ነን፡፡
አሁን ደግሞ አንድ ችግር እየሆነ የመጣው የሤራ ትርክት ነው፡፡ ምንም አይነት ማስረጃና ማሳመኛ የሌላቸው የሴራ ትርክቶች የሰዉን አመላካከት አያዛቡትም ማለት ትልቅ ስሀተት ነው፡፡ በሴራ ትርክት በተሞላች ዓለም አሁን እኮ ከምናየው ይልቅ የምንሰማውን የምናምን ሆነናል፡፡ በዓይናችን ከምናየውና በእጃችን ከምንዳስሰው ይልቅ በማህበራዊ ሚዲያ ፎቶሾፕን የምናምንበት ጊዜ ላይ ነን እኮ! ምን ላይ እንደምንነቃ፣ ምን ላይ “ይሄ ነገር እኮ እያሳሳቀ እንደሚወስደው ወንዝ እየሆነ ነው፣” እንደምንል ፈጣሪ ይወቀው!
እናማ… “እባካችሁ፣ እባካችሁ፣ እባካችሁ…” እየተባለ እስከ መቼ ሊዘልቅ ይችላል! ነገሮች ወደ ጎርፍነት፣ ነገሮች ወደ 8.5 የሪከተር መለኪያ መሬት መንቀጥቀጥነት፣ ነገሮች ወደ ናዳነት መለወጥ ሳያስፈልጋቸው ቀና ማለቱ፣ ቀበቶ ማጥበቁ ሳይሻል አይቀርም!
አንድዬ ደግ ነገሮችን የምንሰማበትን ጊዜ ያፍጥልንማ!  
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1611 times