Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 14 July 2012 12:06

ምርጫ ሲቃረብ የዋጋ ንረት ይረጋጋል ምርጫ ሲጠናቀቅ የዋጋ ንረት ይነሳበታል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

“የአለም አንደኛ” ለመባል የበቃው የአገራችን የዋጋ ንረት፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቀስ በቀስ እየተረጋጋ መሆኑን ሰምታችኋል? አለምክንያት አይደለም። ሚስጥሩ ምን ይሆን ብላችሁ አትጨነቁ። በመጪው አመት የሚካሄደው ምርጫ ነው፤ የሚስጥሩ ቁልፍ። ጥርጣሬ ሊያድርባችሁ አይገባም። እስከ ምርጫው ጊዜ ድረስ፤ የዋጋ ንረት እየረገበ እንደሚሄድ ማረጋገጫ ልሰጣችሁ እችላለሁ። የሁለት እና የሁለት ድምር አራት እንደሆነ ያጠራጥራል እንዴ? ኧረ በጭራሽ። የመላምትና የምኞት ጉዳይ አይደለማ፤ የሂሳብና የስሌት ጉዳይ ነው።

ልክ እንደዚያው፤ በፖለቲካ ምርጫና በዋጋ ንረት መካከልም፤ ጥብቅ ቁርኝት እንዳለ ጨርሶ አያጠራጥርም። የፖለቲካ ምርጫ ሲቃረብና ሲጋጋል፤ የኑሮ ውድነት ረገብ ይላል (ማለቴ እንዲረግብ ይደረጋል)። የፖለቲካ ምርጫ ሲጠናቀቅና ሲበርድለት ደግሞ፤ የዋጋ ንረት ይነሳበታል (ማለቴ... እንዲነሳበት ይደረጋል)።

“እንዴት እርግጠኛ ሆንክ?” ልትሉ ትችላላችሁ። መልሱ ቀላል ነው።

ነገርዬው... የግምት ወይም የመላምት፤ የፍላጎት ወይም የምኞት ጉዳይ ሳይሆን፤ የሂሳብና የስሌት ጉዳይ ነው። ማስረጃዎቼም፤ ባለፉት አስር አመታት የተሰበሰቡ የ127 ወራት አሃዛዊ መረጃዎች ናቸው - በቁጥር እና በመቶኛ ቁልጭ ብለው የሚታዩ መረጃዎች።

እመኑኝ ብዬ አላስቸግራችሁም። መረጃዎቹን ለመመልከት ፍቃደኛ ከሆናችሁ በቂ ነው። መረጃዎቹ ራሳቸው፤ እውነታውን ይናገራሉ። የፖለቲካ ምርጫ ከተጠናቀቀ በኋላ የዋጋ ንረት እንደሚነሳበት በግልፅ ታዩታላችሁ፤ ግን ብዙም መገረም የለባችሁም። መረጃዎቹን በደንብ ካስተዋላችሁ፤ የዋጋ ንረቱ መቼ እንደሚነሳበት ብቻ ሳይሆን መቼ እየተባባሰ መቼ  ጣሪያ እንደሚነካ ማወቅ ትችላላችሁ። የፖለቲካ ምርጫ 22 ወራት እስኪቀሩት ድረስ የዋጋ ንረት እየተባባሰ ይመጣና፤ በሁለት ወራት ውስጥ  ጣሪያ ላይ ይደርሳል። የሂሳብና የስሌት ጉዳይ ነው ያልኩትኮ ለማጋነን አይደለም።

ምርጫ 22 ወር እስኪቀረው፤ የዋጋ ንረት ይጦዛል

የ97ቱን ምርጫ እንደማመሳከሪያ ወስዳችሁ ሞክሩ። ከግንቦት 1997 ዓ.ም፣ ሃያ ሁለት ወራት ወደ ኋላ ተመልሳችሁ ስትመለከቱ፤ የዋጋ ንረት  ጣሪያ ላይ ደርሶ ታገኙታላችሁ። መቼ? ሰኔ 1995 ዓ.ም መሆኑ ነው። ከዚያ በኋላ ግን ምርጫው እየተቃረበ ስለሚመጣ የዋጋ ንረቱም ከወር ወር እየተሻለው ይሄዳል። ከ2002ቱ ምርጫ ተነስታችሁ ነገርዬውን ብትፈትሹትም ተመሳሳይ ውጤት ላይ ትደርሳላችሁ። ምርጫው ሃያ ሁለት ወራት እስኪቀሩት ድረስ የዋጋ ንረቱ እየጦዘ ቆይቶ፤ በመጨረሻ ከጣሪያ በላይ ይሆናል። መቼ? ሃምሌ 2000 ዓ.ም መሆኑ ነው። ከዚህ በኋላ፤ ያው... እንደተለመደው የዋጋ ንረቱ መርገብ ይጀመራል፤ ምርጫው የሚቃረብበት ጊዜ ነዋ።

በመጪው አመት በ2005 ዓ.ም የሚካሄደውንም ምርጫ ለማመሳከሪያነት መጠቀም ትችላላችሁ። በቃ፤ ... ምርጫው 22 ወራት እስኪቀሩት ድረስ የዋጋ ንረት እየተባባሰ ቆይቶ፤ በሁለት ወራት ውስጥ  ጣሪያ ሲነካ ታዩታላችሁ። መቼ? ነሃሴ 2003 ዓ.ም መሆኑ ነው። ይሄውና ከዚያን ጊዜ ወዲህ፤ ወደ መጪው ምርጫ እየተቃረብን በሄድን ቁጥር የዋጋ ንረቱ ቀስ በቀስ ሲረግብ እናያለን።

በሌላ አነጋገር፤ ምርጫ የሚካሄድበትን ወቅት ካወቃችሁ በቂ ነው... ቀሪው ነገር የስሌት ጉዳይ ነው። ምርጫው ገና ሩቅ ከሆነ፤ የዋጋ ንረት እየተባባሰ ይጦዛል (ምርጫው 22 ወራት እስኪቀሩት ድረስ)። ሲጦዝ የቆየው የዋጋ ንረት በሁለት ወር ውስጥ  ጣሪያ ይነካል። ከዚያ በኋላ ባሉት ወራት ግን የዋጋ ንረቱ ቀስ በቀስ ይረግባል (ምርጫውም ቀስ በቀስ ይቃረባላ)።  አሁንስ ተማመንን? የምታገኙት ውጤት ያው ተመሳሳይ ይሆናል ብያለሁኮ። ግን እኔ ስላልኩ አይደለም። የሂሳብና የስሌት ጉዳይ ስለሆነ ነው - ሁለትና ሁለት ሲደመሩ፤ ያው ተመሳሳይ ውጤት እናገኝ የለ!

እውነታውን ለማመን ከከበደን፤ ፕሮፓጋንዳ ጋርዶናል

የዋጋ ንረት መቼ ይነሳበታል? መቼ  ጣሪያ ይነካል? መቼ መርገብ ይጀምራል? መቼ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይደርሳል? ...ከባባድ ጥያቄዎች ሊመስሉ ይችላሉ። በእርግጥም ከባድ ናቸው። ነገር ግን፤ ከምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ጋር በማያያዝ፤ ለከባባዶቹ ጥያቄዎች በቀላሉ መልስ ተገኝቶላቸዋል እያልኩ ነው። “ለማመን ይከብዳል” ልትሉ እንደምትችሉ ይገባኛል። “የፖለቲካ ምርጫና የዋጋ ንረት ምን አገናኛቸው?” የሚል ጥያቄ እንደሚፈጠርባችሁም አውቃለሁ።

ለማመን ብትቸገሩና ብትጠራጠሩ አይገርምም። የዋጋ ንረት በተከሰተ ቁጥር፤ በነጋዴዎች ላይ እየተሳበበ ነጋዴዎች ላይ የውግዘት ፕሮፓጋንዳ የሚሰራጭበት አገር ውስጥ ነው የምንኖረው። ፕሮፓጋንዳውን እያመንን በጭፍን የምንደናበር ከሆነ፤ የዋጋ ንረት ከፖለቲካ ምርጫ ጋር ግንኙነት የሌለው ሊመስለን ይችላል። አለማቀፍ የኢኮኖሚ ቀውስ ሳይቀር፣ ለዋጋ ንረቱ እንደማመኻኛ ሲቀርብልን አልነበር?

የፕሮፓጋንዳው ናዳ፤ የማመኻኛና የሰበብ አይነቶችን እያግበሰበሰ እላያችን ላይ ሲዘረግፍብን፤ አይናችን ከተጋረደ ግራ መጋባታችን አይቀርም። ነገር ግን፤ ወዲህ ወዲያ በማያወላውሉ መረጃዎች አማካኝነት ግርዶሹን ማስወገድና እውነታውን ማየት እንችላለን። መረጃዎቹን መመልከትና ማገናዘብ ብቻ ነው የሚጠበቅብን!  ከዚያማ... የዋጋ ንረት የሚባባሰውና የሚረጋጋው፤ ከምርጫ መቃረብና መጠናቀቅ ጋር እንደሆነ፤ ፈፅሞ በማያጠራጥር ሁኔታ ታረጋግጣላችሁ።  ታዲያ ዛሬስ የመጪው አመት ምርጫ እየተቃረበ አይደል? አዎ፤ የዋጋ ንረትም እየተረጋጋ ነው።

በነገራችን ላይ... በሚቀጥሉት ወራትም... እስከ ምርጫው ድረስ፤ የዋጋ ንረት እየረገበ እንደሚሄድ የማበስራችሁ በደስታ ነው። በእርግጥ የምስራቹ ለተወሰነ ጊዜ ብቻ የሚያገለግል መሆኑን ልብ በሉ። ከምርጫ ዘመቻው ጋር ተያይዞ ለበርካታ ወራት፤ የዋጋ ንረት እየተረጋጋና እየረገበ ሲሄድ፤ ለዘላለሙ የተገላገልነው እንዳይመስላችሁ። አትሳሳቱ፤ ከምርጫው በኋላ የዋጋ ንረቱ እንደሚነሳበትና እንደሚባባስ አትርሱ። “እንዴት?” ለሚለው ጥያቄ፤ ምላሹ በሂሳብና በስሌት ይገኛል። “የዋጋ ንረቱ ኡደት” ምንም ሳይዛነፍ፤ “የፖለቲካ ምርጫ ኡደትን” የሚከተል ነውና።

“ለምን?” ለሚለው ጥያቄስ፤ ምላሽ እናገኝለታለን?

ጥያቄው ብዙም አይከብድም። መልሱም አጭር ነው - “ምርጫ በሚቃረብበት ወቅት፤ በዋጋ ንረት ዜጎችን ለማስመረርና ለማስቆጣት የሚፈልግ ሞኝ መንግስት አይኖርም፤ ከኖረም እድሜው አጭር ይሆናል”።

መንግስት ዜጎችን ይፈራል ማለት ነው? - “ትንሽ ትንሽ”

በእርግጥ፤ እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉ የአፍሪካ አገራት የሚካሄድ ምርጫ፤ የአውሮፓና የአሜሪካ አይነት ምርጫ አይደለም። አፍሪካ ውስጥ፤ ስልጣን የያዘ ገዢ ፓርቲ፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን አዋክቦ በማዳከም እንዲሁም ዜጎችን ተጭኖ በማስፈራራት ተከታታይ ምርጫዎችን ማሸነፍ ይችላል። እንዲህም ሆኖ፤ ገዢ ፓርቲዎች እንዳሰኛቸው መሆን ይችላሉ ማለት አይደለም። በወከባም ሆነ በአፈና፤ በማስፈራራትም ሆነ በማጭበርበር ሁሌም የምርጫ አሸናፊ እየሆኑ ስልጣን ላይ ለመቆየት ከፈለጉ፤ ጥቂት የጥንቃቄ ዘዴዎችን መጠቀም ይኖርባቸዋል። አለበለዚያ፤ ችግር ይፈጠራል። ከጥንቃቄዎቹ መካከል አንዱ፤ “ምርጫ ሲቃረብ ዜጎችን የሚያማርርና የሚያስቆጣ የዋጋ ንረት እንዳይኖር ማድረግ” ነው። አሜሪካና አውሮፓ ውስጥ፤ የምርጫ ጊዜ ቢቃረብም ባይቃረብም፤ የዋጋ ንረትን ሲፈጥር የቆየ መንግስት፣ በስልጣን ላይ የመቀጠል እድል አይኖረውም። ከ6 እና ከ7 በመቶ በሚበልጥ የዋጋ ንረት የዜጎችን ኑሮ የሚያናጋ ፓርቲ፤ በቀጣዩ ምርጫ ከስልጣን ለመውረድ መዘጋጀት አለበት፤ በአፈናና በወከባ ምርጫዎችን የማሸነፍ እድል ጨርሶ የለውማ።

እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉ አገራት ግን፤ በአፈናና በወከባ የማሸነፍ እድል አለ። አለቅጥ ገንዘብ እያሳተመ የዋጋ ንረት ሲፈጥር የቆየ መንግስት፤ ምርጫ ሲቃረብበት የዋጋ ንረቱን ማረጋጋት ከቻለ፤ ያን ያህልም ፈተና ላይገጥመው ይችላል።

የምርጫው ጊዜ ገና ሩቅ ከሆነማ፤ ስለ ዋጋ ንረት ጨርሶ አይጨነቅም። መረን በለቀቀ የገንዘብ ህትመት ሳቢያ የዋጋ ንረቱን ሲያባብስ የሚያድር መንግስት፤ “እኔ የለሁበትም” እያለ ሲያስተባብል፣ ሲያሳብብና ሲያላክክ ይውላል። የዋጋ ንረቱን በተለያዩ ማመካኛዎች ላይ እያሳበበ፤ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ያካሂዳል። በዋጋ ንረት ሳቢያ፣ ኑሮ የተናጋባቸው ዜጎች ክፉኛ ቢማረሩና ቢቆጡ እንኳ፤ ምንም ሊያደርጉ አይችሉም። ሌላው ይቅርና፤ እሮሯቸውን ለመግለፅም ይቸገራሉ። አብዛኞቹ የሚዲያ ተቋማት በመንግስት ስር የፕሮፓጋንዳ መሳሪያ ሆነዋልና። የምርጫ ጊዜ ሲቃረብ ግን፤ መንግስት ጥንቃቄ ለማድረግ ይገደዳል። በምርጫ ጊዜ፤ መንግስት ዜጎችን ትንሽ ትንሽ ይፈራቸዋል።

እና ምን ይሻለዋል? በዋጋ ንረት ለተማረሩ ዜጎች፤ ፕሮፓጋንዳ መፍትሄ እንደማይሆን ግልፅ ነው። እናም መንግስት ሞኝ ካልሆነ በቀር፤ ከወዲሁ ምርጫው ከመድረሱ በፊት፤ የዋጋ ንረቱን ከምር ማረጋጋትና ማርገብ እንደሚገባው ይገነዘባል። ነገሩ ቀላል ነው። በአለማቀፍ የኢኮኖሚ ቀውስ ላይ የማመካኘት ቀልዱን ይተዋል። በነጋዴዎች ላይ የማላከክና ነጋዴዎችን የማውገዝ ፕሮፓጋንዳውን ያቋርጣል። በአገራችን የንግድ አሰራር ኋላቀርነት ላይ የማሳበብ ጨዋታውን ያቆማል።

የምርጫ ጊዜ ሲቃረብ፤ ቀልድና ጨዋታ አያስፈልግም። የቁም ነገር ጊዜ ነው። የዋጋ ንረት የሚፈጠረው፤ መረን በለቀቀ የገንዘብ ህትመትና ስርጭት አይደል? የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋትም፤ ብቸኛው መንገድ፤  የገንዘብ ህትመትንና ስርጭትን አደብ ማስገዛት ነው።

እውነትም የዋጋ ንረት መረጋጋት ይጀምራል (ምርጫው ሲቃረብ)። ተረጋግቶም ይረግባል (የምርጫ ዘመቻ በሚካሄድበት ወቅት)። ከዚያ በኋላ የዋጋ ንረት እንደገና ይነሳበትና ይጦዛል (የምርጫ ጣጣ ሲያልፍ)።

የዋጋ ንረቱ ኡደት ይቀጥላል - መጦዝ፣ መረጋጋት፣ መርገብ፣ እንደገና መጦዝ...። የምርጫው ኡደቱ አልተቋረጠማ - የምርጫ ጣጣ ያልፋል፣ ምርጫ ይቃረባል፣ የምርጫ ዘመቻ ይካሄዳል፣ እንደገና የምርጫ ጣጣ ያልፋል...።

አያችሁ? የዋጋ ንረት ኡደት፤ በየጊዜው የምርጫ ኡደትን እየተከተለ የሚሾረው በአጋጣሚ ወይም በዘፈቀደ አይደለም። ሁለቱም የመንግስት ስራ ናቸው። ምርጫ የሚካሄደው በመንግስት ነው። በዘፈቀደ ሳይሆን እቅድ ተዘጋጅቶለት የጊዜ ሰሌዳ ወጥቶለት የሚካሄድ ነው - ምርጫ። የመራጭ ምዝገባ፣ የተወዳዳሪ ምዝገባ፤ የምርጫ ዘመቻ፤ የድምፅ መስጫ ቀን፤ የድምፅ ቆጠራ ቀን ተብሎ ይታቀዳል፣ ፕሮግራም ይዘጋጃል። የዋጋ ንረት መንስኤ የሆነው የብር ህትመትም በዘፈቀደ አይካሄድም፤ እቅድና የጊዜ ሰሌዳ ይወጣለታል። ከአታሚዎች ጋር ለመዋዋል ጨረታ ማውጣት፤ ስንት ቢሊዮን ብር እንደሚታተም መወሰን፤ የታተመው ብር የሚጓጓዝበትና ርክክብ የሚካሄድበትን ቅደም ተከል ማስተካከል... በአጠቃላይ የጊዜ ሰሌዳና እቅድ ይዘጋጅለታል። ሁለቱን ኡደቶች የሚያገናኛቸው ገመድ ምንድነው? “መንግስት፤ በሌላ ጊዜ ያሻውን ያህል ገንዘብ ማሳተምና ማሰራጨት ቢችልም፤ በምርጫ ወቅት ግን የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት ይገደዳል” ... ይሄ ነው ሁለቱን ኡደቶች የሚያገናኛቸው።አንደኛ፤ የምርጫ ወቅት ሲቃረብና ሲሟሟቅ፤ የዋጋ ንረት እየረገበ ይረጋጋል (በእርግጥም በምርጫ ወቅት፤ ዜጎችን በዋጋ ንረት የሚያስቆጣ መንግስት በጣም ሞኝ ነው)።

ሁለተኛ፤ የምርጫ  ጣጣ ሲጠናቀቅና ሲያልፍ፤ የዋጋ ንረት ይጋጋላል (የምርጫ ጊዜ ካለፈ በኋላ፤ በዋጋ ንረት የተጎዱ ዜጎች ያሰኛቸውን ያህል ቢቆጡ ምን ሊያመጡ ይችላሉ?)

የዋጋ ንረት ተረጋግቶ ወደ ምርጫ ዘመቻ

ምርጫው 22 ወራት እስኪቀረው ድረስ የዋጋ ንረት እየተባባሰ እንደሚቀጥል፤ ከዚያም በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ጣሪያ እንደሚነካ ጠቅሻለሁ።  ጣሪያ የነካው የዋጋ ንረት ቀስ በቀስ እየተረጋጋና እየረገበ ይመጣል። እናስ መቼ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይደርሳል? ይሄም ኡደትን የሚከተል ነው። መረጃዎቹ እንደሚያሳዩት፤ ጣሪያ ላይ ደርሶ የነበረው የዋጋ ንረት በ14 ወራት ውስጥ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይደርሳል (የምርጫ ዘመቻ የሚጀመርበት ወቅት ላይ ደርሰናል ማለት ነው)።

ለምሳሌ ያህል የ97ቱን ምርጫ እንውሰድ። ሰኔ 1995 ዓ.ም  ጣሪያ ላይ ደርሶ የነበረ የዋጋ ንረት፤ ቀስ በቀስ እየተረጋጋ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው ነሃሴ 1996 ዓ.ም ላይ ነው - 14 ወራት ፈጅቶበት። አያችሁ? የ97ቱ የምርጫ አመትና የምርጫ ዘመቻ የተጀመረው፤ የዋጋ ንረቱ ከተረጋጋ በኋላ ነው።

በ2002ቱ ምርጫም ተመሳሳይ ኡደት እንመለከታለን። በሃምሌ 2000 ዓ.ም ጣሪያ የነካው የዋጋ ንረት፤ ቀስ በቀስ ተረጋግቷል። በ14 ወራትም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል - በመስከረም 2002 ዓ.ም ላይ። እንዲህ የዋጋ ንረቱ ተረጋግቶ ነው የምርጫው አመትና የምርጫው ዘመቻ የተጀመረው።

በአጭሩ፤ የዋጋ ንረት ኡደት ከምርጫ ኡደት ጋር የተያያዘ ነው -  በሶስት ወቅቶች የተከፋፈለ ኡደት። አንደኛ፤ የምርጫ ጊዜና ጣጣ ካለቀ በኋላ የዋጋ ንረት ሽቅብ መመንጠቅ ይጀምራል - መጪው ምርጫ 22 ወራት እስኪቀሩት ድረስ። እየጦዘ የነበረው የዋጋ ንረት የተራራው አናት ላይ ደርሷል።

ሁለተኛ፤ ለመጪው ምርጫ መዘጋጀት ያስፈልጋል፤ ምርጫው እየተቃረበ ነው። ጣራ የነካው የዋጋ ንረት ቁልቁል መውረድ ይጀምራል። ከ14 ወራት ጉዞ በኋላ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይደርሳል። ሶስተኛ፤ የዋጋ ንረቱ ተረጋግቶ ረግቧል። እስከ ግንቦት ድረስ ለስምንት ወራት ያህል እንደተረጋጋ ይቆያል - የምርጫ ዘመቻ የሚካሄድበትና የምርጫ ጣጣ የሚጠናቀቅበት ጊዜ ነው።

ኡደቱ በዚህ አያቆምም። ምርጫው ካለቀ በኋላ እንደገና የዋጋ ንረት ይነሳበታል - ያኔ መንግስት ያለስጋት ከልክ በላይ ብር ማተምና ማሰራጨት ይችላላ።

 

 

Read 1922 times Last modified on Saturday, 14 July 2012 12:18