Print this page
Saturday, 15 August 2020 13:59

ኢትዮጵያና ኬንያ የረጅም ርቀት ሩጫን ማዳን አለባቸው ካለፈው የቀጠለ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

 የውድድር አይነቱ በኮሮና ወረርሽኝ ክፉኛ ተመቷል፡፡
የቡድን ልምምድ የቀረባቸው፤ ውድድር የተቋረጠባቸውና ቋሚ ገቢ የሌላቸው የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች አጣብቂኝ ውስጥ ናቸው፡፡ ከስፖርቱ እየራቁ ነው፡፡
ለምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች የበላይነት የፕሮፌሰር ያኒስ ፒስታሊደስ ማብራርያ በአጭሩ
በምንግዜም ምርጥ  ፈጣን ሰዓቶችና ወቅታዊ ደረጃዎች የኢትዮጵያና የኬንያ የበላይነት
የረጅም ርቀት ሩጫ ከዓለም አትሌቲክስ እየተመናመነ መጥቷል፡፡ 10ሺ ሜትር ከትራክ ወጥቶ በ10ኪሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ መለወጡ ያሳዝናል፡፡
የዓለም አትሌቲክስ ማህበር ባሳለፋቸው ውሳኔዎች  በ3ሺ ሜትር መሰናክልና በ5ሺ ሜትር ላይም ተመሳሳይ አደጋዎች ተረጋርጠዋል፡፡ ስፖርት አድማስ ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት የረጅም ርቀት ሩጫን ለማዳን የሚያስፈልገውን ትኩረት ለማመልከት ይህን ፅሁፍ አዘጋጅቷል፡፡
የኮሮና ወረርሽኝ በረጅም ርቀት ላይ ያሳደረው ተፅእኖ
አሁን ወቅቱ የኦሎምፒክ ነበር፡፡ በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ የጃፓኗ ቶኪዮ የምታስተናግደው 32ኛው ኦሎምፒያድ በ1 ዓመት መሸጋሸጉ በየአራት ዓመቱ የነበረው ሂደት ተስተጓጉሏል፡፡ የኦሎምፒክ መሸጋሸግ በርካታ ኦሎምፒያኖችን ለተለያዩ ቀውሶች ዳርጓቸዋል፡፡ በበሽታው የተጠቁ፤ ማህበራዊ ቀውስ ያጋጠማቸው፤ ለገቢ እጥረትና ለስነልቦና ቀውስ የተዳረጉ ኦሎምፒያኖች ጥቂት አይደሉም፡፡ ከኦሎምፒክ መድረክ እስከ 40 ሚሊዮን ዶላር የገቢ ድርሻ ያለው የአትሌቲክስ ማህበር ታላቁ የስፖርት መድረክ ወቅቱን ጠብቆ ባለመካሄዱ ውስብስብ ችግሮች አጋጥመውታል፡፡ በተለይ በረጅም ርቀት ውድድሮች ላይ የደረሰውን ጉዳት ለመታደግ የማይችልበት ደረጃ መድረሱን የተለያዩ ሁኔታዎች ያመለክታሉ፡፡ ዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ከ31ኛው ኦሎምፒያድ መሸጋሸግ ጋር በተገናኘ ለሚደርሱ ችግሮች እስከ 800 ሚሊዮን ዶላር በጀት አፅድቋል፡ ከዚሁ በጀት 650 ሚሊዮን ዶላሩን በኦሎምፒክ መሸጋሸግ የተፈጠረውን ኪሳራ ለመሸፈን እንዲሁም ከ150 ሚሊዮን ዶላር በላይ ከዓለም አቀፉ ኮሚቴ ጋር ለሚሰሩ ዓለም አቀፍ ፌደሬሽኖችና ብሄራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴዎች ማከፋፈሉን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የዓለምን ስፖርት በከፍተኛ ደረጃ ያናጋው የኮሮና ወረርሽኝ በተለይ በአትሌቲክስ ላይ የሚያደርሱ ጉዳቶች እየጨመሩ ሄደዋል:: በመላው ዓለም የሚካሄዱ ውድድሮች ከ6 ወራት በላይ በመቋረጣቸው፤ የኦሎምፒክ መሸጋሸግ፤ የልምምድና የዝግጅት መርሃ ግብሮች መዛባት በተለይም በምስራቅ አፍሪካና በሌሎች አገራት የረጅም ርቀት አትሌቶች ላይ የሚያደርሰው ተፅእኖ የሚብስ ሆኗል፡፡ የዓለም አትሌቲክስ ማህበር ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ Athlete Welfare fund በሚል የተቸገሩ አትሌቶችን በመደገፍ መስራቱ ይታወቃል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ለገቡት የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች የድጋፍ ማመልከቻ ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ማህበር ምንም ምላሽ ሳይሰጥ መቅረቱ ለምስራቅ አፍሪካ ትኩረት መንፈጉን ያመለክታል፡፡
የረጅም ርቀት አትሌቶች ለወራት ያለቡድን ልምምድ፤ ያለውድድር እና ገቢ በመቆየታቸው ከፍተኛ ችግር ውስጥ ገብተዋል፡፡ በኬንያ ሚዲያዎች የተሰሩ ልዩ ዘገባዎች እንዳመለከቱት በርካታ አትሌቶች የኑሮ ዋስትና በማጣታቸው ስፖርቱን በመተው ወደሌላ የሙያ መስክ መግባት ጀምረዋል፡፡ ከ30 በላይ የኬንያ አትሌቶችን በማናጀርነት የያዘው ሆላንዳዊው ማይክል ቦይቴግ  ሲናገር የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች ቋሚ ደሞዝተኞች ባለመሆናቸው ሩጫውን በመተው ላይ ናቸው፤ በንግድ እና በግብርና ስራዎች ላይ ለመሰማራት እየወሰኑ ይገኛሉ ነው ያለው፡፡  ኢትዮጵያዊው የአትሌቶች ማናጀር ጌታነህ ተሰማ በበኩሉ በኮሮና ወረርሽኝ ለአደጋ የተጋለጡትን የረጅም ርቀት አትሌቶች በ3 ከፍሏቸዋል፡፡ በትልልቅ ውድድሮች ከፍተኛ የገንዘብ ሽልማት አግኝተው ምንም ያልተቸገሩ ቢኖሩም፤ ዓለም አቀፍ ውድድሮች በመቋረጣቸው ብቃታቸውን ለመጠበቅ ፈተና ውስጥ ናቸው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የተለመዱት ዓለም አቀፍ ውድድሮች በመቋረጣቸው በቀጥታ የሚያገኙት ገቢ የቀነሰባቸው ፕሮፌሽናል አትሌቶች ናቸው፡፡ በመጨረሻም  እነሱን ለመተካት በየአገር ውስጥ ውድድሮች ያሉ አትሌቶች ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን አብራርቷል፡፡
የሰው ልጅ የፅናት መለኪያ እንጅ ለምስራቅ አፍሪካ ብቻ የተሰጠ ፀጋ አይደለም
በረጅም ርቀት ሩጫ የሚካሄዱ ውድድሮችን ከምድረ ገፅ እየጠፉ እንዲሄዱ ካደረጉ ምክንያቶች ተደጋግሞ የሚጠቀሰው በዓለም አቀፍ ውድድሮች የምስራቅ አፍሪካ የውጤት የበላይነት ማሳየታቸው ነው፡፡ በረጅም ርቀት ሩጫ ላይ በከፍተኛ ውጤት እና ፈጣን ሰዓት የዓለማችን  ምርጥ አትሌቶች በተለይ ከሁለቱ የምስራቅ አፍሪካ አገራት መውጣታቸው የሚደንቅ አይደለም፡፡ ከኢትዮጵያዋ በቆጂ እንዲሁም  ከኬንያዎቹ ኢቴን፤ ካፕታጋት እና ኤልዶሬት  ከተሞች የሚፈልቁ የረጅም ርቀት ሯጮችን በጥራትና ብዛት የሚስተካከል ሌላ የዓለም ክፍል የለም፡፡ ስለዚህም ባለፉት 20 እና 25 ዓመታት ከዚሁ የአፍሪካ ክልል የሚወጡ አትሌቶች በትልቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ከ80 በመቶ በላይ ድል አድራጊ ሆነው ቆይተዋል:: ከዓለማችን የስፖርት ኢንዱስትሪ የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች ልቀው የተገኙበት ነው የረጅም መርቀት ሩጫ፡፡   በብዙ ስፖርቶች ግን ከዚህ የዓለም ክፍል የሚወጡ አትሌቶች እንኳንስ ውጤት ሊኖራቸው ይቅርና ከሌላው ዓለም መፎካከር አለመቻላቸውን መታዘብ ያስፈልጋል፡፡
በረጅም ርቀት አትሌቲክስ ሩጫ ለምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች የውጤት የበላይነት በመላው ዓለም በርካታ ጥናቶችና ምርምሮች ተሰርተዋል:: በትልልቅ ዩኒቨርስቲ በሚያስተምሩ የስፖርት ባለሙያዎች እና ከፍተኛ ምሁራን የጥናት ሰነዶቹና መፅሃፍት ተዘጋጅተዋል፡፡ ከምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች የውጤት የበላይነት ጋር በተገናኘ ደግሞ የስኮትላንዳዊውን ፕሮፌሰር ያኒስ ፒስታሊደስ ያህል የሰራ የለም፡፡ በኢትዮጵያና ኬንያ አትሌቶች ባካሄዷቸው ምርምሮች  በብዙ ትንታኔዎች እና ዘገባዎች በተደጋጋሚ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ Kenyan and Ethiopian Distance Runners: What Makes Them So Good?  በሚለው ጥናታቸው የሰጡትን ማብራርያ በአጭሩ መመልከት ይቻላል፡፡   የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች ከኬንያ ካሌንጂን እንዲሁም ከኢትዮጵያ በቆጂ መገኘታቸው በዚያ ከተሞች ያለውን ልዩ  የዘር ግንድ በማመልከት የመጀመርያው ግንባር ቀደም ምክንያት ነው፡፡ ከሁለቱ አገራት ዝቅተኛ የኢኮኖሚ አቅም አንፃር ዜጎቻቸው በስፖርት ስኬታማ ሆነው ከድህነት ለመውጣት የሚያደርጉት መፍጨርጨርም ሌላው ነው፡፡ ከ2000 እስከ 2500 ሜትር ከባህር ወለለል በላይ በሆነ ከፍተኛ አልቲትዩድ በመኖራቸው ያጎናፀፋቸው ተፈጥሯዊ ብቃትም አለ፡፡ በኬንያ 86 በመቶ እንዲሁም በኢትዮጵያ 68 በመቶ የሚሆኑት ፕሮፌሽናል ሯጮች በልጅነታቸው 20 ኪሜትር እየሮጡ ትምህርት ቤት መመላለሳቸውም በጥናቱ ተጠቅሷል:: የሁለቱ ምስራቅ አፍሪካ አገራት አትሌቶች ተክለሰውነትም የተነሳ ሲሆን ኬንያውያን በቁመታቸው ዘለግ ያሉ እና ባለረጃጅም እግሮች ኢትዮጵያውያኑ ደግሞ አጭርና ፈርጣማ በመሆናቸው ከሌላው ዓለም የተለየ ብቃትን ሰጥቷቸዋል ነው:: በአመጋገባቸውም ከሌላው ዓለም በተለየ ለረጅም ርቀት ብቁ ሁኔታን እንደፈጠረላቸው የፕሮፌሰሩ ጥናት ያመለክታል፡፡ የረጅም ርቀት አትሌቶቹ በተለምዶ አመጋገባቸው በኬንያ  10 በመቶ ፕሮቲ፣ 13 በመቶ ስብ እና 72 በመቶ ካርቦ ሃይድሬት እንዲሁም በአትዮጵያ 13 በመቶ ፕሮቲ፣23  በመቶ ስብ እና 64 በመቶ ካርቦ ሃይድሬት ማግኘታቸው ፅናትን መሰረት ባደረገ ስፖርት እንዲሳካላቸው አድርጓል፡፡
በረጅም ርቀት የምንግዜም ምርጥ 25 ፈጣን ሰዓቶችና ወቅታዊ ደረጃ
በ10ሺ ሜትር ወንዶች የምንግዜም ፈጣን ሰዓቶች ዝርዝር ላይ የኢትዮጵያዊው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ የዓለም ሪከርድ መሪነቱን እንደያዘ ቢሆንም ሁለተኛ ደረጃ ይዞ የሚገኘው ከ22 ዓመታት በፊት ሌላው የኢትዮጵያ ኃይሌ ገብረስላሴ 26፡22.25 በሆነ ጊዜ ያስመዘገበው ነው፡፡ በወንዶች 10ሺ ሜትር የምንግዜም 25 ፈጣን ሰዓቶች የደረጃ ዝርዝር ላይ 11 አትሌቶችን በማስመዝገብ ኬንያ ግንባር ቀደም ስትሆን 7 ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም ይገኙበታል:: ከ27 ደቂቃ በታች ርቀቱን ለመሸፈን የቻሉ ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን አበበ ዲንቄሳ፤ ስለሺ ስህን፤ ኢማና መርጋ፤ ሃጎስ ገብረህይወትና ዮሚፍ ቀጀልቻ ናቸው፡፡ በምንግዜም ፈጣን ሰዓቶች ዝርዝር ውስጥ ከገቡት የሌሎች አገራት አትሌቶች መካከል እንግሊዛዊው ሞፋራህ እና አሜሪካዊው ጋለን ሩፕ የሚጠቀሱ ሲሆን የሞሮኮ፤ የኡጋንዳ፤ የኤርትራና ዜግነታቸውን ቀይረው ለኳታር የሚወዳደሩ አትሌቶም ይገኙበታል፡፡ በሴቶች 10ሺ ሜትር በውድድሩ ታሪክ ባስመዘገቧቸው ከፍተኛ ስኬቶች የምናውቃቸው የኢትዮጵያ አትሌቶች ናቸው፡፡
በምንግዜም 25 ፈጣን ሰዓቶች ዝርዝር 11 ለማስመዝገብ የቻሉ ሲሆን ከ30 ደቂቃ በታች የገቡት 4 ይሆናሉ፡፡ 10ሺ ሜትር በኦሎምፒክ መድረክ የገባው በወንዶች ምድብ በ1912 እኤአ ሲሆን በሴቶች ደግሞ በ1983 እኤአ ላይ ነው፡፡ ዛሬ በመላው ዓለም የሚካሄዱ የ10ሺ ሜትር ውድድሮች በጣት የሚቆጠሩ ቢሆንም በትልልቅ አለም አቀፍ ውድድሮች ላይ በወንዶች የኢትዮጵያና የኬንያ አትሌቶች በሴቶች ደግሞ ከሁለቱ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ባሻገር የቻይና አትሌቶች ተመራጭ ያደርጉታል:: የዓለም አትሌቲክስ ማህበር ለውድድር ዘመኑ በ10ሺ ሜትር፤ በአገር አቋራጭ ፤ በ5ሺ ሜትር የረጅም ርቀት ውድድሮች ላይ ባወጣው ደረጃ በሚያስገርም ሁኔታ ኡጋንዳዊው ጆሽዋ ጄፕቴጊ በ1407 ነጥብ ይመራል፡፡  ኬንያዊው ሮኔክስ ኪፕሮሮ በ1389 ነጥበ ሁለተኛ ሲሆን ኢትዮጰያዊው ዮሚፍ ቀጀልቻ በ1375 ነጥብ 3ኛ ነው፡፡ከ1 እስከ 10 ባለው ደረጃ 4 ኢትዮጵያውያን 2 ኬንያውያን ሲሆኑ ኡጋንዳ፤ አሜሪካ፤ ጣሊያንና ካናዳ እያንዳንዳቸው በአንድ አትሌት ተወክለዋል፡፡ ኢትዮጵያውያኑ አንዱአለም በሃይሉ በ1321 ነጥብ 6ኛ እንዲሁም ሃጎስ ገብረህይወት በ1298 ነጥብ እና ሰለሞን ባረጋ በ1272 ነጥብ 8ኛ እና 9ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
በ5ሺ ሜትር በምንግዜም ምርጥ 25 ፈጣን ሰዓቶች ዝርዝር ላይ አሁንም የኢትዮጵያና የኬንያ አትሌቶች ውክልና ከሌላው ዓለም የላቀ ሆኖ ተቀምጧል፡፡ በወንዶች 5ሺ ሜትር የምንግዜም 25 ፈጣን ሰዓቶች ዝርዝር 9 በኬንያ፤ 4 በኢትዮጵያ አትሌቶች የተመዘገቡ ሲሆን በሴቶች ደግሞ 9 በኢትዮጰያ 6 በኬንያ አትሌቶች ተሳክተዋል፡፡ በምንግዜም ፈጣን ሰዓቶች ዝርዝሩ ላይ በሁለቱም ፆታዎች ከምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች ባሻገር የቻይና፤ የኔዘርላንድ፤ የእንግሊዝ፤ የአሜሪካ፤ የጀርመን፤ የቱርክና የራሽያ አትሌቶች ተጠቅሰዋል፡፡በ5ሺ ሜትር ሴቶች ውጤታማዋዎቹ አትሌቶች ከኬንያ እና ከኢትዮጵያ ቢሆኑም ታንዛኒያ፤ ኡጋንዳ፤ አልጄርያና ሞሮኮ ምርጥ አትሌቶችን አፍርተዋል፡፡ የእንግሊዝ፤ ጀርመንና፤ ሆላንድ አትሌቶች ከአንድ እስከ 10 ባለው ደረጃ ገብተዋል፡፡
በዓለም አትሌቲክስ ማህበር የውድድር ዘመኑ የውጤት ደረጃ ላይ 5 ኬንያውያን ሁለት ኢትዮጵያውያን ፋንቱ ወርቁ እና ለተሰንበት ግደይ ተጠቅሰዋል፡፡ በወንዶች 5ሺ ሜትር ላይ የውድድር ዘመኑን የደረጃ ሰንጠረዠ የሚመራው ሰለሞን ባረገሃ ሲሆን ከአንድ እስከ 10 ባለው ደረጃ እሱን ጨምሮ አራት የኢትዮጵያ አትሌቶች ተመዝግበዋል፡፡ በደረጃ ሰንጠረዡ የኡጋንዳ፤ የአሜሪካና የእንግሊዝ አትሌቶች ይገኙበታል፡፡

Read 487 times