Wednesday, 12 August 2020 12:37

“40 ዓመት በህክምና ያገለገለችውን እናቴን ቀጥቅጠው ገደሉብኝ”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

 የማይሽር ቁስል ይዣለሁ፤ መንግስት ደሜን ይመልስልኝ
                              (ሀኪም ሰራዊት ተረፈ፤ የዓለም ማያ ከተማ ነዋሪ)


                ዓለም ማያ ከተማ ውስጥ ብዙ ዓመት ኖሬያለሁ፡፡ ልጆቼን ሁሉ እዚሁ ከተማ ውስጥ ነው ወልጄ ያሳደግሁት፡፡ እናቴ ከአዲስ አበባ ከመጣች ገና ሃያ ቀኗ ነበር:: ሰኔ 23 የተፈጠረው ችግር ብዙ ጠባሳ ጥሎብን ነው ያለፈው፡፡ የዚያን ቀን ከእንቅልፋችን ስንነሳ አብራኝ የኖረች ጐረቤቴ፤ “ሀጫሉን ቀብረን ስንመለስ ሌላ ሰው መቅበር የምንጀምረው ከዚህ ቤት ነው” እያለች ብሔርና ሃይማኖቴን እየጠቀሰች ስታስተባብርብኝ ነበር፡፡
ከዚያ በኋላ ልጆቼን ሰብስቤ በሬን ዘግቼ፣ ቤት ውስጥ ቁጭ አልኩኝ፡፡ ትንሽ ቆይተው እየጨፈሩ መጡ፡፡ የድንጋይ እሩምታ ቤታችን ላይ ያወርዱብን ጀመር፡፡ ባለቤቴ ተኝቶ ነበር፤ በዚህ ድንጋጤ ተነስቶ ወጣ:: በጣም ብዙ ድንጋይ ይወረውሩ ጀመር:: እኛ ግራ ተጋባን፡፡ የባለቤቴ የወንድሙ ባጃጅ በር ላይ ቆማ ነበር፡፡ መጀመሪያ እሷን ማንደድ ያዙ፡፡ ከዚያ በኋላ የመንግስት ሃይል እንዲደርስልን ብሎ ባለቤቴ ወደ ሰማይ መተኮስ ጀመረ፡፡ እሱ ሲተኩስ ትንሽ መለስ ይሉና እንደገና ግር ብለው ይመጣሉ፡፡ ከዚያ በኋላ የመካከለኛውን የውጭ በር ገንጥለው ገቡ፡፡ ባለቤቴን “አንተ ነፍጠኛ አማራ፤ ስምህም ቴዎድሮስ ነው፤ እንገድልሃለን፤ ና ውጣ” አሉት፡፡
ከዚያ እኔ ቤት አንዲት ልጅ ነበረች፡፡ “እሷ ኦሮሞ ነች እንዳትነኩ” ብለው ድንጋይ ውርወራውን አስቁመው፤ እሷ ከወጣች በኋላ እኛ ላይ ጥቃቱን ቀጠሉ፡፡ “እሷን አስወጥተህ እንዴት ደካማ እናቴን አታስወጣልኝም” ስለው “ፖሊስ እኮ ደጅ  አለ” አለኝ፡- ያ  እኔ ጋ የነበረችውን ሚስቱን ያስወጣው ሰውዬ፡፡ ፖሊስ ካለማ ብዬ፣ ባጃጁ እየነደደ የነበረበትን እሳት ዘልዬ ወጣሁና “እባካችሁ እናቴን አውጡልኝ፤ ልጆቼንም አውጡልኝ” አልኳቸው፡፡ ያኔ እኔን ይቀጠቅጡኝ ነበር፡፡ በዚህ መሃል እርዳታ ለመጥራት ወደ ሰማይ ሲተኩስ የነበረውን ባለቤቴን መሳሪያውን ነጥቀው ወደ ፖሊስ ጣቢያ ብቻውን ወሰዱት፡፡ ያኔ እኛ  ብቻችንን ቀረን፡፡ ከዚያ በኋላ የሆነውንማ ምኑን ከምኑ አድርጌ ልንገራችሁ… ወገኖቼ (ከፍተኛ ለቅሶ …) ልጄ እናቴን በእሳቱ ላይ እያንገዳገደ ይዟት ወጣና አሻግሮ አስቀመጣት፤ ምክንያቱም እናቴ የአስም በሽተኛ ስለሆነች ታፍና ልትሞትብን ሆነ፡፡ ከዚያም ልጄን ሰባት ቦታ ጭንቅላቱን ብትንትን አድርገው፣ በሜንጫ ጐኑን ወግተው ሲያበቁ፣ እናቴን ስታገለግል በኖረችበት አገር፣ ጭንቅላቷን በሜንጫም በድንጋይም ቀጥቅጠው፣ ልጄንም እናቴንም ራሳቸውን ስተው ሲወድቁ ሞተዋል ብለው ተዋቸው፡፡  ይኸው እኔን ያለ እናት አስቀሩኝ፡ (ለቅሶ)፡፡ ፖሊሶቹ ባለቤቴን ብቻ ይዘው ከሚሄዱ እኛንም ፖሊስ ጣቢያ ወስደው ሊያተርፉን ይችሉ ነበር፡፡ ባለቤቴን ይዘው ሄደው ልክ እጥፍ እንዳሉ ቀሪዎቹ እኔን ይሄ እግሬን በጥይት መትተውኝ ጥይቱ በአንድ በኩል ገብቶ በዚህ ወጣ (እግራቸውን እያሳዩ) ከዚያ እኔም አቃተኝ፡፡ እናቴና ልጆቼም እዛ ወድቀው የሚያነሳቸው አጥተው፣ ከአንድ ሰዓት በላይ ደማቸው ፈሰሰ፡፡ ልጄ ወድቆ “ውሃ ውሃ” ሲል ሰዎች ሊያነሱት ሲመጡ፣ ስታስተባብርብኝ የነበረችው የጐረቤቴ ልጅ “እስኪ ወንድ አንድ ሰው መጥቶ ያንሳው” በማለት ሁለት ጊዜ ከሰዎች እጅ ላይ ውሃውን ተቀብሎ ደፋው፡፡ እኔ ምን አይነት ጉድ እንደመጣብን አላውቅም፡፡ ሁለተኛውን ጉድ ልንገራችሁ፡፡ ይሄ ሁሉ ሆኖ ልጄንና እናቴን ሃኪም ቤት ለመውሰድ እንኳን ሌላ ፈተና ገጠመን፡፡ እኔ በጥይት መመታቴና ሽባ መሆኔ ሳያንስ፣ በሜንጫ አንገቴን ሊቆርጡኝ ሲሉ አንዷ እግዚአብሔር ይስጣት፣ ጐትታ ቤቷ አስገባችኝና በር ቆለፈች፡፡ ይመጣሉ በር ይደበድባሉ፤ “የለችም ሄዳለች” ትላቸዋለች፤ ተመልሰው ይመጡና በር ይመታሉ፡፡ በጣም ከፍተኛ መከራና ስቃይ ነው የደረሰብን፡፡
እኔ ተቆልፎብኝ እሰማለሁ፤ “ልጁም አሮጊቷም ሞተዋል” እያሉ በኦሮምኛ ሲያወሩ ነበር፡፡ መጨረሻ ላይ እነሱ ሞተው የኔ መትረፍ ዋጋ የለውም ብዬ ተጐትቼ በሩን ከፈትኩና ወጣሁ፡፡ ሁለቱም ወድቀው ደማቸው ይፈስሳል፡፡ “ኡኡ” አልኩ፤ ለፍልፌ ለፍልፌ “ኡኡ” ብዬ አንድ መኪና መጣ፡፡ ስንትና ስንት ቦታ ተደውሎ አንዲት ፀበል ላይ የነበረች ጓደኛዬ “እህቴ እየሞተች ነው” ብላ ቤተ - ክርስቲያኑን በጩኸት ስታናጋው፣ በስንት ሰው ጩኸት ተነስተን ሃኪም ቤት ከሄድን በኋላ፣ ልጄንና የባለቤቴን ወንድም እንደነገሩ ሰፋፏቸው:: እኔና እናቴን ግን ምንም አላደረጉልንም፡፡ ከሀረር ሆስፒታል ሪፈር ተጽፎልን ድሬደዋ ለመሄድ እዚህ አለማያ መጣን፤ አጃቢ እንዲሰጠን፡፡ ከግማሽ ሰዓት በላይ አጃቢ እንዲሰጠን ብንጠይቅም “መልሳችሁ ሀረር ሆስፒታል ውሰዷቸው፤ አጃቢ የለንም፤ መንገድም ዝግ ነው፤ ምንም ማድረግ አንችልም” አሉ፡፡ ሹፌሩ እግዚር ይስጠው “እኔ እስከ መጨረሻው እሞታለሁ እንጂ አልመልሳቸውም” ብሎ በሁለት አምቡላንስ ነው የሄድነው፡፡ ሹፌሮቹ ራሳቸው መንገድ የተዘጋበትን ድንጋይ እያነሱ ማታ 12፡00 ድሬደዋ ማሪያም ወርቅ ሆስፒታል ገባን፡፡ እዛ እየተረዳን ቆየን፡፡ ለእናቴ ከአዲስ አበባ ድረስ ኒዮሮሎጂስት  መጥቶ ህክምና ተደረገላት፤ ጭንቅላቷን በጣም ስለተመታች፤  ልትተርፍ አልቻለችም፡፡ በ6ኛው ቀን ሰኔ 29 አረፈች፡፡
እናቴ ካራሚሌ ሆስፒታል ከ40 አመት በላይ ያገለገለች ሀኪም ናት፡፡ ድሮም “ብሞት ካራሚሌ ወስደሽ እንድትቀብሪኝ አደራ” ትለኝ ነበር፡፡ ሆኖም ካራሚሌ ወስደን መቅበር አልቻልንም፤ ድሬደዋ ደብረመንክራት መድሃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን ተቀበረች፡፡ እኔም ሆስፒታል ነበርኩኝ፤ እናቴ በዚህ ዓይነት ወድቃ ቀረች፤ የደረሰብን መከራ አይነት ብዙ ነው፡፡
ይሄ ሁሉ አልበቃ ብሎ በነጋታው በሰኔ 24 መጥተው፣ ቤታችንን በድጋሚ አቃጠሉት:: ይህንን አቃጥለው ሲያበቁ ገጠር ውስጥ መልካ ገመቹ የሚባል ክሊኒክና ፋርማሲ ነበረን፡፡ እኔም ከ20 ዓመት በላይ አገርና ህዝብ ያገለገልኩ ሀኪም ነኝ:: እዚያ ገጠር  ድረስ ሄደው 7 ክፍል ቤት የሆነውን ፋርማሲና ክሊንክ አቃጥለው እንዳልነበረ አደረጉት:: ሁለት ሶስት ጊዜ ነው የገደሉን፡፡ በጥናት ስማችን ተለይቶ ተይዞ፣ ከከተማ ውጪ ያለ ንብረታችን ሳይቀር ነው የተቃጠለው፡፡ እናቴን ቀጥቅጠው የገደሉት፣ እኔን በጥይት መትተው ሽባ ያደረጉኝ፣ ልጄንና የባለቤቴን ወንድም ጭንቅላታቸውን መዓት ቦታ ፈነካክተው ደማቸውን ያፈሰሱት፤ እኔና እናቴ አዋልደን ከልጆቻችን ጋር ያሳደግናቸው የምናውቃቸው ልጆች ናቸው፡፡
እኔ ክሊኒኩን ልጄ ደግሞ ፋርማሲውን ይዘን በገጠር የምንሰራበትን ሁሉ ሲያጠፉት ሲያወድሙት፣ የከተማው መኖሪያ ቤታችን ሲቃጠል፣ ባጃጃችን በራችን ላይ ሲነድ፣ የቤተሰቤ ደም አስፋልት ላይ ሲፈስስ ፖሊስ ደጃፋችን ላይ ቆሞ ነበር፡፡ የቤታችንንም እሳት ማጥፋት፣ እኛንም ከሞትና ከጉዳት መታደግ ይችሉ ነበር፡፡ ከሁሉም ከሁሉም የእናቴ ነገር ነው የሚያንገበግበኝ፤ እዚህ ቦታ በዚህ ሁኔታ መሞት አልነበረባትም:: የእድሜ ልክ ፀፀት ነው የሆነብኝ፤ በሰላም ከተቀመጠችበት ከአዲስ አበባ አምጥቼ አስገደልኳት (ለቅሶ) የኢትዮጵያ ህዝብ፣ መንግስት፣ እናት ያለው፣ ልጅ የወለደ ሁሉ ይፍረደኝ፤ ባለቤቴ ታስሮ፣ ንብረታችን ወድሞ፤ እናቴን ቀብሬ እኔ ሽባ ሆኜ፣ ጭንቅላታቸው ወንፊት የሆኑ ልጄንና የባለቤቴን ወንድም ይዤ ሜዳ ላይ ወድቄያለሁ፡፡ መቼም ቢሆን የማይሽር ቁስል ይዣለሁ፤ ፍረዱኝ፤ መንግስት ደሜን ይመልስልኝ እላለሁ፡፡  


Read 9823 times