Wednesday, 12 August 2020 12:12

“17 የልጅ ልጅ ባየሁበት ከተማ ነው ይህ ሁሉ መከራ የደረሰብኝ”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 መጦሪያዬን፣ እምነቴን፣ ተስፋዬን ተነጥቄ ቁጭ ብያለሁ
                       (አቶ አበባው ከበደ፤ የአለማያ ከተማ ነዋሪ)


            እንድንተነፍስ ላበቃን አምላክ ምስጋና አቀርባለሁ፡፡ ድምፃችን እንደታፈነ እንሞታለን ብለን ተስፋ ቆርጠን ነበር፡፡ ተንፍሼ መከራዬን አገር ሰምቶት፣ ለምን አሁን አልሞትም፤ አይቆጨኝም፡፡ ጥቃቱ ከደረሰ ልክ ዛሬ አንድ ወር ከአንድ ቀን ሆነው:: በዚህ በአንድ ወር ውስጥ የደረሰችልን ይህቺው የምንሞትላት የምንደበደብላት ቤተ ክርስቲያን ብቻ ናት፡፡ መጠለያም የሆነችን፣ የምንበላውንም የምንለብሰውንም ያቀረበችልን ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ በዕለቱ ሥራ አድሬ ወደ ቤት በተመለስኩበት ሰዓት በግምት 3፡30 ይሆናል፡፡ ከ60 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ህፃናትን ከፊት አስቀድመው የውጭውን አጥር ገልብጠው ገቡ፡፡ እኔ በሰዓቱ እየታጠብኩኝ ነበር:: ቤንዚን በፕላስቲክ ጠርሙስ ሞልተው ይዘው እያርከፈከፉ፣ መስታወት እየሰባበሩ በመኝታ ቤት፣ በሳሎንና በተለያዩ ክፍሎች ያሉ ባለፉት 50 አመታት ያፈራሁት ንብረት ሲወድም፣ በእኔ ላይ ከባድ ድብደባ ተፈጽሞብኝ፣ በአዛውንትነቴ ላይ ይህ ጉዳት ሲጨመር ሰውነቴ በሙሉ ተሰባብሮ ደቅቋል:: በመጨረሻም ከፍተኛ መፍጨርጨር አድርጌ፣ ባለቤቴንና ልጄን ይዤ አንድ ክፍል ውስጥ ገብቼ በር ዘጋሁ:: በሩን ቀጠቀጡ ቀጠቀጡና አልሰበር ሲላቸው ትተው ሄዱ፡፡ እኛ ከሞት ተረፍን:: ከልጅነት እስከ እውቀት ሃብትና ንብረት ያፈራነው፣ ልጄ አረብ አገር ተሰቃይታ ያፈራችው ወርቅ፣ መዓት እቃ፣ ምን የቀረ አለ?! ውድም አለ፡፡
በጥቂት ሰዓት ውስጥ ቤታችን ወደ ፍርስራሽነት፣ ንብረታችን ወደ አመድነት ተቀየረ፡፡ በዚህ ውድመት ከ2.ሚ ብር በላይ አጥቻለሁ፡፡ ይህ የሆነው ከ50 ዓመት በላይ በኖርኩበት፣ 17 የልጅ ልጅ ባየሁበት፣  ከጐረቤቶቼና ከአካባቢው ጋር በደስታም በሀዘንም ተካፋይ ሆኜ በኖርኩበት ከተማ  ነው፡፡ ይሄ ሁሉ መከራና ውርደት የደረሰብኝ ይህን ሁሉ ህይወት ባሳለፍኩበት ዓለማያ ከተማ ነው፡፡ አሁን መጦሪያዬን፣ እምነቴን ተስፋዬን… ተነጥቄ ባዶ እጄን ቁጭ ብያለሁ:: የት ነው የምሄደው? ከአለም ማያ ከተማ ውጭ አገር የለኝም፤ አለምም የለኝም፤ ወገኖቼ እስኪ ፍረዱኝ (ሁሉም ተሰብሳቢ እንባ እየተራጨ፤)
“ከእገሌ ቤት ጀምረህ እገሌን ምታው” እየተባለ ስም ዝርዝራችን ተይዞ ነው ጥቃት የደረሰብን፡፡ ክርስቲያን መሆን ሀጢያት ነው እንዴ? ለማን ነው አቤት የምንለው?! “ልጆቻችን መጡብን ሊገድሉን ነው” እያሉ ሌሊቱን እየበረገጉ በስቃይ ላይ ነው ያለነው፡፡ ቆርቆሮ በንፋስ ኳ ባለ ቁጥር “መጡብን እንሽሽ” እያሉ ሌሊት ሌሊት እንቅልፍ የለንም፡፡ ቀጣይ እጣ ፈንታችን ምንድን ነው? ለቀጣይ ህይወታችን ምን ዋስትና አለን? እንግዲህ መንግስት ምንድን ነው የሚያደርገን? አሁንም ማስፈራሪያና ዛቻው ቀጥሏል፤ “እንደጀመርናችሁ እንጨርሳችኋለን” እየተባልን ነው፡፡ ዋስትና የለንም፤ የዛሬ አዳራችንንም አናውቅም፤ መከላከያ ከዚህ ከተማ እንዳይነሳብን፤ እንዲጠብቀን ለዓለምና ለኢትዮጵያ ህዝብ ንገሩልን፤ ጩኹሉን፤ ድምፃችን ይሰማ፤ መከራችን ይታይ፡፡ እናንተም ጋዜጠኞች ቃላችሁን ጠብቁ፤ የተናገርነውን ወስዳችሁ ለሁሉ አሰሙልን፡፡ እኔ ይህን ተንፍሼ እንባዬን በማፍሰሴ ከላዬ ላይ የሆነ ሸክም የወረደልኝ ያህል ቀለል ብሎኛል፤ ክብር ለመድሃኒዓለም ይሁን፡፡Read 990 times