Wednesday, 12 August 2020 12:04

በኢትዮጵያ መከሰቱን ለማመን የሚያዳግት የጭካኔ ተግባር

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

“ባለቤቴ በ200 ሰዎች ነው ተቀጥቅጦ የተገደለው”

     - ተጐጂዎች የደረሰባቸውን አሰቃቂ በደል በአንደበታቸው ይገልፃሉ
     - መንግስት ይድረስልን፤ ህዝብ መከራችንን ይስማ
     - መንግሥት አጥፊዎችን ይቅጣልን


        የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በተለይም በኦሮምያ አካባቢዎች በተከሰተው ሁከትና ግርግር ወደ 200 የሚደርሱ ሰዎች መገደላቸውንና በብዙ ቢሊዮን ብሮች የሚገመት የመንግስትና የግል ሃብትና ኢንቨስትመንት መውደማቸው ተዘግቧል፡፡
ይሄ ዓይነቱ ዘገባ ከቁጥር ባሻገር የጥፋቱን መጠንና ዕልቂት በቅጡ አይገልፀውም፡፡ እንዴት? ብትሉ የጉዳት ሰለባዎቹ የደረሰባቸውን ሲናገሩ ከአንደበታቸው መስማት እውነታውን ያሳያል፡፡ የተፈፀመው ድርጊት አሰቃቂ ነው፡፡ በኢትዮጵየ ምድር ላይ የተፈፀመ ነው ብሎ ለመቀበል ያዳግታል፡፡ የጭካኔና አረመኔነት ጥግ የሚታይበት አሰቃቂ ክስተት አገራችን እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰችው መቼ ነው የሚል ጥያቄም ያጭርብናል - የጭካኔና አረመኔነት ድርጊቱ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ሰሞኑን በምዕራብና ምስራቅ ሀረርጌ በጥሮ፣ አለምማያ፣ ባቲ፣ ሀረርና ኮምቦልቻ ከተሞች ተገኝታ ከብዙዎቹ ጥቂቶቹን አነጋግራለች፡፡ ያነጋገረቻቸው ሰዎች ብሶት እነሆ፡-


                   “ባለቤቴ በ200 ሰዎች ነው ተቀጥቅጦ የተገደለው”

                 ሙስሊም ጐረቤቴ ሁለቱን ልጆቼን ደብቃልኝ ነው የተረፉት
                       (ወይዘሮ ወይንሸት ገብሬ፤ የጭሮ ነዋሪ)


            በእኔም ሆነ በቤተሰቤ የደረሰብን ሰቆቃ በቃላት የሚገለጽ አይደለም፡፡ ሰኔ 23 ከባለቤቴ ከብርሃኑ ዝቅአርጋቸው ጋር የስራ ባልደረባችን ልጅ ሞቶ ቀብር ሄደን ነበር:: ከቀብር ስንመለስ ግርግር ተፈጠረና ገና ሀዘንተኞቹን ሳንሰናበት ነበር ቶሎ ብለን ወደ ቤት የመጣነው፡፡ አሰላ ብንወለድም እዚሁ ጭሮ ከተማ ውስጥ ነው የኖርነውም ሆነ ልጆች ወልደን ያሳደግነው፡፡ ባለቤቴ ቤት ከገባን በኋላ የጐረቤቶቻችን ፎቅ ሲመታ “ድረሱላቸው” እያለ ለህግ አካላት ሲደውል ነበር፡፡ “እኛን አይነኩንም፤ እኔን ሲያዩ ይመለሳሉ ተረጋጉ” ብሎን ነበር፡፡ ነገር ግን 200 የሚሆኑ ሰዎች የውጭውን በር ሰብረው ገብተው  (ወጣቶችም በእድሜም ጠና ያሉም) “በለው በለው” እየተባባሉ፤ የ5 ዓመት ልጄ አይኑ እያየ፣ እንደ እባብ ቀጥቅጠው ገደሉት፡፡ ልጄ ሌሊት ሌሊት አባቴ እያለ እየተወራጨ ጥርሱን እያፋጨ በቅዠት ሲሰቃይ ነው የሚያድረው፡፡ ልጄ አዕምሮው ተቀይሮብኛል፡፡ “ልጆቹን ይዘሽ ሽሺ ይገድሉሻል” እያለ መትረፋችንን እንኳን ሳያይ ነው የሞተው፡፡
እኔ ያንን የ5 ዓመት ልጄን ይዤ እሪ ስል፣ አትርፉልኝ እያልኩ ስጮህ ሙስሊም ጐረቤቴ፣ ሁለቱን ልጆቼን ደብቃልኝ ነው የተረፉት፡፡ ባለቤቴ ሁለት ጊዜ ነው የሞተው፤ ምክንያቱም ወደ ህክምና እንዳይሄድ እንኳን ሬሳውን ሰው ቤት ውስጥ ደብቀው ቆለፉበት:: “ኧረ ባለቤቴ የት ሄደ እባካችሁ አፋልጉኝ” ስል በቀይ መስቀል አምቡላንስ ወደ ህክምና ተወስዷል ብለውኝ ነበር፡፡ ሁሉም ካለፈ በኋላ ግን አስክሬኑ ሰው ቤት ውስጥ ተደብቆ ነው የተገኘው፡፡ እስካሁን ባለቤቴ ለምን እንደተገደለ የምናውቀው ነገር የለንም፡፡ ይህን ሁሉ በደልና ግፍ የተቀበልነው በምን ምክንያት እንደሆነ አናውቅም፡፡ ቤታችን ወድሟል፣ ንብረታችን የለም፤ አሁንም ዘመድ ቤት ተጠግተን በልመና ነው ከልጆቼ ጋር እየኖርን ያለነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ይፍረደኝ፤ ወላድ ይፍረደኝ (ለቅሶ…)
ባለቤቴ ከሁሉም ጋር ሰላም ነው፡፡ በኦዳ ቡልቱ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር ሰራተኛ ነበር:: ከበፊት ጀምሮ በዩኒቨርሲቲው ሲያገለግል ነው የቆየው፡፡ እኔም በዚሁ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ነው የምሰራው፡፡ ባለቤቴ ብርሃኑ በደግነቱ በተግባቢነቱ ነው የሚታወቀው:: “እኔን ሲያዩ ይመለሳሉ” ያለውም በዚሁ ቅንነቱ ነው፡፡ እኛ ሌላ ጠላት፣ ሌላ ገዳይ አልመጣብንም፤ እዚሁ እያየናቸው ያደጉ የዚሁ አካባቢ ሰዎች ናቸው ያጠቁን:: መንግስት የባለቤቴን ደም ያውጣልኝ፣ አስተማሪ የሆነ ቅጣት በገዳዮቻችን ላይ ይጣልልን፤ ያን ጊዜ ነው የምንጽናናው:: በእኛ የደረሰ በማንም አይድረስ በእኛ ይብቃ፡፡Read 1207 times